ባለፈው ሳምንት ግጭትን አለመፍራት በሚል ርዕስ አንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦችን በጥቅሉ አንስቼ እንደነበረ አንባቢያኑ ታስታውሳላችሁ። ዛሬም መጪውን የአዲስ ዘመን ምክንያት በማድረግ የማቀርበውን ጽሑፍ ከማስነበቤ በፊት በግጭት ርዕሰ ነገር ላይ መቆየትን መረጥኩ።
ግጭት በስርዓት ከተያዘ ለዕድገትና ብልጽግና ለመልካምነትም በር እንደሚከፍት አንስቼላችሁ ነበር። ግጭትን መሸሽም ሆነ መፍራት ለመፍትሔ እንደማያበቃም መዳሰሴን አስታውሳለሁ። ዛሬ ይህንን ጉዳይና ሌሎቹን ነጥቦች ማነሳሳት ፈለግሁ። ለመሆኑ ግጭትን መሸሽ ማርገቢያ ይሆናልን?
እስቲ የአንዳንድ ሰዎችን የግጭት መፍቻ መንገድ እንቃኝ ።
አንዳንዶቹ ሰዎች ግጭቱ ካለበት ሥፍራ መሸሽን (Withdrawal) አንዱ መንገድ አድርገው ያዩታል። ሌሎች ደግሞ ለቅቆ መውጣት ነገርን ያቀላል፤ ግጭትን ያረግባል፤ ብለው ያስባሉ። ግጭትንም በጣም ስለሚጠሉ ወይም ስለሚፈሩ ከግጭት ማምለጥን አንዱ ዘዴ ነው ፤ ይላሉ።
ስለዚህ መስሪያ ቤት ከሆነም ለቅቀው ይወጣሉ። መኖሪያ ቤትም ከሆነ “ይስፋሽ” እና “ይድላው” ብለው ይወጡና ይሄዳሉ።
ከትዳር አጋራቸው ጋርም ቢሆን ፍቺ ለመጠየቅ አያመነቱም። ከመጋቢው ጋር ሲጣሉ ቤተክርስቲያኑን ትተው ይሄዳሉ። ላልተስማሙበት ነገር መፍትሔ ነው፤ የሚሉት ከአካባቢው ለቅቀው መሄድን ነው። ባል ሚስቱን ጥሎ ሲሄድ፣ ሚስት ባሏን ትታ ስትሄድ እግሮቻቸው አያመነቱም። ፍቺ ሲጠይቁም አፋቸውን ያዝ አያደርጋቸውም። ምክንያቱም ቤት በግጭት አይቆምም ፤ ቤት በንትርክ “አይደምቅም” ብለው ነው፤ የሚያስቡት። ከግጭቱ የሚወለደውን ሰላም ሳይሆን ግጭቱ የሚወልደውን የአፍታ ጦርነት ነው፤ የሚፈሩት።
እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ያጣችሁት ነገር እኮ የከበረ ነው፤ ብላችሁ ብትሏቸው፤ “የመታሁት ደረቴን የነጨሁት ፊቴን” ነው፤ የሚሏችሁ። የቀረብኝ እኔ፤ አንተንና አንቺን በእኔ እጦትም ግኝትም ምን አገባችሁ ለማለት ፈልገው ነው። ይሁንናም ምንም እንኳን ቤት ማፍረስ ደቦ ባይጠይቅም መገንባትና የፈረሰን መጠገን ህብረትንና መተሳሰብን ይጠይቃል።
ለማንኛውም ጸብ ፈሪና ሽሹ ሰው፣ ሊነገር የሚገባው ነገር ትዳርና ሐገር በሽሽትና በስደት አይገነባም ፤ ስለዚህ በተቻለን መጠን የዘመመ ጎጆን ለማቃናት ሁላችንም አብረን ቀና ደፋ ማለት ይገባናል። ህይወት ደግሞ ይህንን አበክራ ከእኛ ትጠብቃለች። ስለዚህ ግጭትን በመሸሽ ወይም በማምለጥ ከቶውንም ለውጥ አናመጣም ። የተሻለ ቀንና ቤትም አንገነባም።
አንዳንድ ሰዎች በዝምታቸው የሚባረኩ፣ ባለመናገራቸው የሚሆንላቸው ስለሚመስላቸው ሊናገሩት በሚገባው ጉዳይ ላይ እንኳን ዝምታን ይመርጣሉ። ስለዚህም ውሎ አድሮ፣ ዝምታቸው የሚያስከፍላቸውን ዋጋ ሳይወዱ በግድ ይቀበሉታል። የሰፈር ሰዎች “ጨዋዎች” ናቸው፤ እንዲሏቸው በጎረቤት “ስማቸው እንዳይነሳ”ና በመሳሰሉት የእነርሱ ባልሆነ ምክንያት ዝምታን መርጠው ዝምታቸው ዋጋን አስከፍሏቸዋል።
እንዲህ መሰል ሰዎች ቤት ሲገቡ ሰላማቸው እንዳይደፈርስ ይጨነቃሉ እንጂ በሰላም አይኖሩም። አርፍዶ ገብቶ “ለምን” ላለማለት ወይም ቆይታ ደርሳ “ምነው” ላለማለት ዝም ይባባላሉ።
ይህ የተጠራቀመ ዝምታ የፈነዳ እለት እንደእሳተ ገሞራ ቤቱን ጠራርጎት ይሄድና መተንፈሻው መለያየት ይሆናል። በውጤቱም፣ ወንዱ “ ብዙ ጊዜ ቻልኳት -ቻልኳት አሁንስ በዛና ጠነዛ” ሲል፣ ሴቷም “ ቀዝቃዛ ሲዖል ውስጥ ከመቀመጥ የአውራጎዳናው ንፋስ ይሻላል” ትላለች። እውነቱ ግን በመቻል ውስጥ ዝምታው ጌታ ነበር በሲዖሉ ውስጥ ለአፍታ “አፍ ተካፍተውና ተነጋግረው” ስለማያውቁ ነው።
እንዲህ መሰል ሰዎች፣ ሰላም በሚመስሉበት ወቅት ሄዳችሁ ብታናግሯቸው፣ “ሁሉ መልካም ነው ፣ እርሷ እንደሆነ “አትሸት፣ አትገማ” ሲል፣ እሷም መልሳ እርሱ እንደሆነ፣ “ድምፁ አይሰማ፣ ገላው አይሰማ” እንዲሁ ነው ይሉህና ፤ ይመስገነውን ይጨምሩበታል።
ይሄኔ ያንን ቤተሰብ የምትወድ ከሆነ ዝምታቸውም ችግር እንደሆነ ከመናገር አትቦዝን፣ ፀጥታቸው አደጋ እንዳለው ከመጠቆምና መጋጨት ተፈጥሯዊ ሂደት እንደሆነ ሳትሸሽግ ንገራቸው እንጂ “በጨዋነታቸው” አድንቀህ ዝም አትበላቸው። በቤታቸው ውስጥ ቤት አፍራሽ የሆነ ዝምታ የሚባል መጋዝ እንዳለ አጠንክረህ ንገራቸው እንጂ ቸል አትበል። በእውነት የምትወዳቸው ከሆነ በዝምታቸው ወንዝ ውስጥ ሰምጠው ድንገት “ደራሽ ፈረሰኛ የፀብ ውሃ” ጋልቦ ትዳሩን ከመበተኑ በፊት መላ ፈጥረህ አውርተህ አነጋግራቸውና፣ አድናቸው።
ሰው በአዳማዊ ተፈጥሮውና በዙሪያው ባለው ኣለም ተጽዕኖ ሳቢያ ከግጭት ነፃ ሊሆን አይችልም፤ ከቶውንም። ስለሆነም ግጭትን አንፍራ።
የሰው ልጅ በራሱ ከራሱ ጋርም ይጋጫል። ሰው በህይወቱ የሚያጋጥመውን ነገር፣ በሥርዓት ማየት ሲያቅተው ከራሱ ጋር ይጋጫል። በአንድ ጊዜ ሁለት ሶስት ነገሮች ተደራርበው ሲገጥሙት ወይም አንዱን ችግር ተጋፍጦ ሳያበቃ ሌላኛው ሲጨመርበትና ለውሳኔ ሲቸገር ከመፍትሔው ይልቅ ችግሩ ላይ ሲያፈጥ በግለ ግጭት ውስጥ ገብቶ ይወጠራል። ማንኛችንም ችግሮችን ለመፍታት የምንከተላቸውን ዘዴዎች ሙሉ በሙሉ አናውቅም። ፍጽምና የለንም፤ ስለዚህ እንጨነቃለን።
የአንድ ጎረቤታችንን ታሪክ በምሳሌነት ላውጋችሁ። ባካባቢው በተፈጠረ ድንገተኛ ትርምስ፣ የሚስቲቱ የግል ኩባንያ ይቃጠላል ፤ ፋብሪካውም የዚያን ወር ደመወዝ ብቻ በመክፈል እንደሌሎቹ ሰራተኞች ያሰናብታታል፤ ትኖርባቸው የነበሩት የወላጆቿ አንድ ክፍል ቤት ድንገት በህመም በወደቁት አባቷ ማስታመሚያነት ትውላለች፤ እሳቸውም ከሥራ ይባረራሉ። ልጅም ከከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና፣ ይወድቃል፤ ትንሹ ልጅ ሰው ደብድቦ ይታሰራል። ለነገ ብላ ያጠራቀመችው አንዳች ነገር በሌለበት የፋሲካ በዓልም ይደርሳል….የቀረችው የባል እዚህ ግባ የማትባል ደመወዝ ብቻ ትሆናለች።
ከሥራ መሰናበት፣ የአባት ህመም፣ የልጅ በፈተና መውደቅ፣ የሌላኛው ጎረምሳ መታሰርና ተስፋ ማጣት ሲደራረቡ፣ ድንገት ማንንም ሳታማክር ቤቷንና ትዳሯ ጥላ እብስ ስትል ሁላቸውም ግራ ይጋባሉ። ስልኳን ዘጋች፤ አድራሻዋን ቀየረች፣ ደምፁዋን አጠፋች። ይህ ግን ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ አባባሰው። ወጣቱ ልጅ በሱስ ተያዘ፤ ባሏ መጠጥ ጀመረ፤ ሽማግሌው አያት የልብ ድካም ተጨመረባቸው….
ሚስትም፣ ከሶስት ወር በኋላ ገዳም ገብታ ተገኘች። የሰው ልጅ ችግሩን ለማስቸገር ወኔውን ተቆጣጥሮ ሊዋጋ ይገባል እንጂ ችግሩን በመሸሽ ችግሩን ማስወገድ አይችልም፤ ያባብሰዋል እንጂ።
ሌላው ግጭት በሰዎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ነው። ይህን መሰል ግጭት ከላይ እንዳነሳነው በባልና ሚስት በወንድምና ወንድም፣ በእህትማማቾች፣ በሥራ ባልደረቦች፣ በጎረቤት ሰዎችና አለፍም ሲል ድንበርተኛ በሆኑ ጎረቤት ሀገራት መካከል ነው።
ይህንን መሰል ግጭት ለምን ተነሳ አይባልም ። ጉርብትና በራሱ፣ አብሮ መኖር በራሱ፣ የሚያማዝዘው ቅራኔ አይጠፋምና። ጉዳዩ የሚፈጠርን ግጭት ቀደም ብሎ አይቶ ግጭቱ እንዳይመጣ ለማድረግ የሚያስችል መላ በመፍጠርና ምናልባትም ከተፈጠረ በኋላ ችግሩን ለመፍታት የምንከተላቸው ዘዴዎች ናቸው፤ ወሳኞቹ ነገሮች። ግጭት በመካከላችን ለምን ተነሳ ብሎ መፍትሔውን መፈለግና እንዴትነቱን ማጤን ከአስተዋይ ልብ ይጠበቃል ።
አለበለዚያ በችግራችን ትብታብ ተይዘን “ሰላም የለም -ጦርነትም የለም” በሚለው የጋለ የነገር ውጥረት በርሜል ላይ ተቀምጠን ቁና ቁና መተንፈስ ነው። በስሜት ባህር ውስጥ ከገባን ቀላሉ ውስብስብ ፣ ለስላሳው ጠጣር ይሆንብናል።
ገጣሚው ሃይሉ ገብረዮሓንስ እንዳለው፡-(ገሞራው)
«ለስሜት ከሆነ የመኖርህ ጉዳይ ፤
ችግርን ተደሰት፤ ደስታን ተሰቃይ»።
እንዳለው መሆናችን አይቀርም።
ስለዚህ የችግሮቻንን እምብርት ጉዳይ በማጤን ለግጭቱ መፍትሔ በማምጣት ብልህነታችንን ማሳየት ይገባናል። ብዙ ጊዜ ግጭትና ግፊት የሚመጣው አለቅጥ ምቾት ከመፈለግና በተቃራኒው በጎረቤታችን ያለው ልዩ ምቾት በሚፈጥርብን ቅንዓት ነው።
አንደኛው በተፈጠረብን ምቾት ሳቢያ የበለጠና የተሻለ ምቾት ፍለጋ የጎረቤት ድንበር እንገፋለን ፤የጎረቤት ሰው እንጋፋለን፤ ግጭትም ይፈጠራል። በሌላ ወገን ደግሞ፣ ለፍቶ ጥሮ ግሮ ያገኘው ሃብት ዓይኖቻችንን ሲያቀላብን የሌላውን መልካም ቤት ፣ መኪና፣ ሰው እንደፍራለን፣ እናንጓጥጣለን። በሁሉም ረገድ ግን ግጭታችን የፍላጎቶቻችን እስረኞች ከመሆን የሚመነጭ የሰብዕና ግድፈት የሚመነጭ ዋልጌነት ነው።
ሌላው የግጭት ዓይነት ደግሞ ማህበረሰባዊ ግጭት ነው። ሰው፣ ለማህበራዊው ወግ፣ ልማድና እምነት እንዲሁም የተፃፉና ያልተፃፉ ህጎች ራሱን ማስገዛት ሲያቅተው ከማህበሩ ጋር ይጋጫል። አንዳንዴ እነዚህ ግጭቶች ተቋማዊ መልክ ሊይዙ ይችላሉ፣ ማህበር በማህበር ላይ፣ ተቋም በተቋም ላይ ሊነሳ ይችላል።
ግጭቱ ከግለሰብ የተነሳ ሲሆን ግለሰቡን ለማህበረሰቡ ወግና ልማድ እንዲገዛ በማድረግ በመሸምገል ማርገብ ይቻላል ። እንዲሁም በሲዳማ ብሔረሰብ ውስጥ፣ “ሽማግሌ አፈር ያስበላል” የሚል ነባር አባባል አለ። ሰው የማህበረሰብ ወግና ልማድን ሲጥስ ተጠርቶ አልሰማ ሲል ቤቱንና ቤተሰቡን ከማንኛውም ማህበራዊ ትስስሮሽ በማግለል ይቀጣል። ሚስቱ እንኳን እሳት ከጎረቤት እንዳትጭር ትደረጋለች። ይህ ሰው ፣ ጥፋቱ ተሰምቶት፣ “አማልዱኝ ባጠፋሁ እክሳለሁ” ብሎ እስኪል ድረስ ፣ ይቀጣና ምህረት ይደረግለታል ። ያኔም ቢያጠፋ ይክሳል። ጠፍቶበት ከሆነም ይካሳል ፤ ጥሪውን በመናቁ ግን ይወቀሳል፤ የሚገርመው ነገር ሽማግሌዎቹ ከስንብታቸው በፊት ግን ሽምግልናችን ቅር አሰኝቶህ ከሆነ ለእኛም ይቅርታ አድርግልን ብለው ይቅርታ ሰጥቶ ነው፤ የሚለያየው።
ስለዚህ ግጭት በህልው የመኖራችን ምስጢርና የመቀጠላችን ኃይል መሆኑን ማጤን ይገባል። እንዲያውም ፣ “ነፍስያው” ያለችው የሚንቀሳቀስ ሰው ያለግጭት ህልውና የለውም ‹። ሃሳብ በግጭት ይኳላል ፤ እውነት በግጭት ይዋባል፤ ፍትህ በግጭት ትሞቃለች፣ ርትዕ በግጭት ትሰርቃለች( ከፍ ትላለች) እንጂ አትከስምም ። ሐሰት ተበዳይን ያስለቀሰ ይመስለዋል እንጂ በቤቱ የሚያለቅሰው እርሱ ሐሰተኛው ነው። ክፉ ከሳሾች በፍርድ አደባባይ ያሸነፉ ይመስል ይንጎማለሉ ይሆናል እንጂ የተሸነፉት ገና ለክስ ሲነሱ ነው። ስለዚህ በግጭት መሐል እውነት የዘገየባችሁ ተሸናፊዎች ሳትሆኑ አሸናፊዎች ናችሁና ደስ ይበላችሁ። ይህንን እውነት ህይወት አሳምራ አሳይታናለች።
ማህበረሰብ ከማህበረሰብ ሲጋጭ ግን መልኩ ለየት ያለ ነው። ይህንንም ለምን ሆነ፤ ብለን አንስተን መቆላጨት አይገባንም። የሞላለት በጎደለበት ላይ ወይም የጎደለበት በሞላለት ላይ መብከንከኑ አለዚያም አክብሮ አለመያያዙ ጥንትም ያለና ወደፊትም የሚኖር እውነት ነው። የዚህኛው አያያዝ ከዚያኛው ለየት ይላል ያልኩበት ጭብጥ፣ ሁሉን በወጉና በደንቡ ለመያዝ የተዘጋጀ ያያያዝ ስልት ፣መፈጠርና ማህበረሰብ ለማህበረሰብ የመፍትሔ አካል ሊሆንበት ከልቡ መዘጋጀት ስለሚገባውና ወጋችንም ይህንን ግድ ስለሚለን ነው።
የማህበረሰብ ልምዶቻችን በግጭት አፈታት ዙሪያ የራሳቸው ወግና ልማድ እንዳላቸው ማጤንና መፍቻውንም ከህግና ደንብ ይልቅ በዚያው አግባብ ለመፍታት መሞከር ብልህነት ነው።
በሩዋንዳ በቱትሲዎች ላይ የደረሰው ዕልቂት እንደተጠበቀ ሆኖ ግጭቱን ለመፍታት የተሄደበት ስልት ግን እጅግ አስተማሪና ህግና የጦር ኃይል ብቻውን የልብን ቁስል የመሻር ኃይል የሌለው መሆኑን መገንዘብ ያስችላል ።
“ሁቱትሲ” ተብሎ የተተረጎመውን የኢማኪሌ (ሩዋንዳዊት ደራሲና የታሪክ ማስታወሻ ፀሐፊ Left to tell ባለችው ) መጽሐፍ ላይ እንዳለችው ፣ የበደሉኝን ለመበደል ከተነሳሁ እኔ ከእነርሱ አልተሻልኩም ማለት ነው፤ ግን ታሪካችን እንዳይደገም ስል ነው የፃፍኩት፤ እንዲውም ከእኔና ከቤተሰቦቼ ከሞቱት ጓደኞቼ ስም በስተቀር ለጥንቃቄ ስል በህይወት ያሉትን ሰዎች ሥም ሁሉ ለውጫቸዋለሁ ፤ ብላለች።
የዚህች ሴት ታሪክ የሩዋንዳውያን የ1994 ታሪክ ነው። ይህ የእርሷ ታሪክ፣ ወገን በወገኑ ላይ ጨክኖ የወጣበት ታሪክ ማሳያ ነው ፤ ይህ የእርሷ ታሪክ ፣ በዓለም ዙሪያ የሆነና፣ ሰው ባልመረጠውና ፈልጎ ባልተፈጠረበት ዘር ወይም ቤተሰብ ውስጥ ልጅ ሆኖ መገኘት ፣ ብቻ “ጥፋት ነው” ተብሎ ያስገደለበት ክፉ ዘመን ታሪክ ማሳያ ነው። ግጭቱ እንዴት ተነሳና እንዴት ተከናወነ ሳይሆን ግጭቱ እንዴት ተፈታ የሚለው ጉዳይ ነው፤ ለእኛ የሚረባን።
ከላይ፤ እንዳያችሁት ማንኛውም ግጭት መነሳቱ ደግ ነው ፤ ግን መፍቻው መንገዳችን ደግሞ የበለጠ ደግ ነው። ደግ ጦርነት የሌለውን ያህል መጥፎ የሚባልም ሰላም የለምና እስከ ሳምንት ሰላም ክረሙልኝ።
ፎቶ፡- በገባቦ ገብሬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 25/2011
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ