ዘንድሮ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ወርቅ የ34 ነጥብ 5 ቶን ብልጫ እንዳለው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ34 ነጥብ 5 ቶን ብልጫ እንዳለው የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ። በበጀት ዓመቱም 38 ነጥብ 8 ቶን ወርቅ ለውጭ ገበያ መቅረቡም ተገልጿል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት በኩባንያዎች እና በባሕላዊ መንገድ የተመረተ 38 ነጥብ 8 ቶን ወርቅ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።

በ2016 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 215 ቶን የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ 377 ነጥብ 97 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን አውስተው፤በ2017 በጀት ዓመት የተገኘው የወርቅ ምርትና ገቢ በ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የቀረበው ወርቅ በመጠን 34 ነጥብ 5 ቶን እና በውጭ ምንዛሪ ደግሞ 3 ነጥብ 122 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን አስረድተዋል።

በዘንድሮ ዓመት የተላከው እና የተገኘው ገቢ እጅግ በጣም ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለእዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አስረድተዋል።

አቶ ሚሊዮን እንደተናገሩት፤ በ2015 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 460 ቶን በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ 196 ነጥብ 79 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ተችሏል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማእድን ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖረው እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ የተቻለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ለማእድን ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት በመቻሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደጠቆሙት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማዕድናት ምርታማነትን በተለይ የወርቅ ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ነው። ማሻሻያው በአነስተኛ ደረጃ ይመረት የነበረውን የማዕድን ምርት በከፍተኛ መጠን እያሳደገው ነው፤ በተለይም የወርቅ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ መሆኑን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ማረጋገጫ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በተጨማሪም ማሻሻያው በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጣ የነበረውን የወርቅ ምርት ወደ ሕጋዊ ሂደት በማስገባት በኩል ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You