
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን መቻሏ ለግዥ ታወጣ የነበረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት መቻሉንና ሥርዓተ ምግብ እንዲሻሻል ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ እና የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ዋና አስተባባሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ከምግብ ሽግግር ሥርዓቱ ትግበራ በፊት በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለስንዴ ግዥ ታወጣ ነበር። አሁን ላይ በተፈጠረው የምግብ ሽግግር ሥርዓት በስንዴ ምርት ራሷን በመቻሏ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ሥርዓተ ምግብን አሻሽሏል ብለዋል።
በስንዴ ውጤት ማምጣት የተቻለው ስንዴን ለማምረት የሚያስፈልጉ ሥራዎች በመሠራታቸው ነው ያሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ የመስኖ አቅምን የመጨመር ሥራ ተሠርቷል። እንዲሁም የኩታ ገጠም አሠራርን በመተግበርና የስንዴ ዘርን በምርምር በማሻሻል ለውጤት መብቃት መቻሉን ገልጸዋል።
ይህም እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለስንዴ ግዥ ይወጣ የነበረውን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት የቻለና የሥርዓተ ምግብን በማሻሻል በኩልም የራሱ ድርሻ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አማካሪው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ እምቅ ኃይል አለ። ሰፊ የእርሻ መሬት እና ውሃ አለ። በባሕላዊ መንገድ በበሬ ከማረስ ወጥቶ መካናይዝድ የሆነ የግብርና ሥርዓትን መተግበር የሚቻል ከሆነ እና የገበሬውን የማዳበሪያ አጠቃቀም ማሻሻል ከተቻለ አሁን ከምናመርተው ዓመታዊ ጥቅል ምርት በ10 እጥፍ ማሻሻል ይቻላል።
የምግብ ሥርዓት ሽግግር ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያካትት መሆኑን የተናገሩት አማካሪው፤ መንግሥት፣ ነጋዴ፣ ተመራማሪ ጨምሮ በርካታ አካላት እየተሳተፉበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
16 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን በማሳተፍ ከ30 በላይ የሆኑ የልማት አጋሮች ፣ በርካታ የምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከክልል እና ከፌዴራል የተውጣጡ ተቋማት የተሳተፉበት በመሆኑ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የዘርፉን ችግር ለመፍታት የአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሥራ ድርሻ ብቻ ተደርጎ አለመወሰዱ በርካታ የፖሊሲ ክፍተቶችን በፍጥነት ለማረም እና ለሕግ አውጪው እንዲቀርብ ማስቻሉንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለዘርፉ ማደግ ያሳየችው ቁርጠኝነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለተኛው የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድባት ሀገር እንድትሆን አስችሏታልም ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት በዓለም ላይ ከፍተኛ አደጋዎችን እያስከተለና እየደቀነ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ያንን ለመቋቋም የሚያስችላትን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመተግበር ቀዳሚዋ ናት። ይኼውም ለሚዘጋጀው ጉባኤ ተመራጭ እንድትሆን እንዳስቻላትም ጠቁመዋል።
ጉባኤው የሦስት ቀን ቆይታ እንደሚኖረው የሚናገሩት አማካሪው፤ የምንለውን በተግባር የምንገልጽ መሆናችን በመጀመሪያው ቀን የመስክ ምልከታ መረጋገጡን ጠቁመው፤ በመድረኩም ላይ ተግባራዊ ጉዳዮች በስፋት የሚነሱ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ መስክ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የሚዲያ አካላት ኅብረተሰቡን በማንቃት እና ባሕላዊ እሳቤዎችን በመቀየር ረገድ የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆኑ የተነደፈውን ሃሳብ ከኅብረተሰቡ ጋር ለማድረስ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም