በክልሉ በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ

አዲስ አበባ፡- በሶማሌ ክልል ለ2017 ዓ.ም አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የክልሉ አካባቢ ጥበቃና የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ መሀመድ ቡሌ ሰመተር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ለዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 14 ሚሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል።

በመርሃ ግብሩ ለተከላ ከተዘጋጁ የችግኝ ዓይነቶች አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆኑት የደን ችግኝ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሁለት ነጥብ 94 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኝ ዓይነቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም 980 ሺህ ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞች፤ 490 ሺህ ለእንስሳት መኖ የሚውሉ እንዲሁም፤ 490 ሺህ ለዘርፈ ብዙ ግልጋሎት የሚውሉ ችግኞች እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

አቶ መሀመድ እንደተናገሩት፤ የሶማሌ ክልል መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ ትልቅ ስኬት እያስመዘገበ ነው። በእዚህም ባለፉት ዓመታት ክልሉ ከ40 ሚሊዮን በላይ የደን ዛፎች፣ የፍራፍሬ ዛፎች፣ የከተማ ውበት ችግኝ፣ የግጦሽ ዛፎች፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ጨምሮ የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶችን መትከል መቻሉን አመላክተዋል።

አቶ መሀመድ አያይዘው በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እና በበጋ ወራት አምስት ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ችግኝ በማዘጋጀት ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ያነሱት አስተባባሪው፤ የዝናብ እጥረት፣ ድርቅ፣ በጀት በቂ አለመሆን፣ የማጓጓዣ አገልግሎት ውስንነትን እንደ ተግዳሮት አንስተዋል።

በክልሉ ከችግኝ አዘገጃጀት ጋር ተያይዞ በተለይም የባለሙያ ውስን መሆን እንዲሁም ችግኝ በስፋት ከማምረት አንጻር የዘር እጥረት መኖሩን አክለው ገልጸዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You