
ዜና ሐተታ
በግብርናው ዘርፍ እየተሠራ ባለው ሥራ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የዳቦ ቅርጫት የምትሆንበት እድል እየተፈጠረ ይገኛል። በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ እና በሌማት ትሩፋት የተገኘው ስኬት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በቱሪዝም ዘርፉም የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብትና ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠቀም መንግሥት “ገበታ ለሸገር” እና “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፤ ገቢም እያስገኙ ናቸው። የ“ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች ደግሞ በጥሩ የአፈጻጸም ግንባታ ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪዶር ልማቶችም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እያደረጓት ነው።
“በመላ ኢትዮጵያ መንደሮችን እና ከተሞችን የሚያገናኙ አዳዲስ መንገዶች እየተገነቡ ነው። እነዚህ መንገዶች ሰዎች በቀላሉ እንዲጓዙ፣ እቃ እንዲሸጡ እና ንግድ እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። የአዳዲስ ድልድዮች እና ፋብሪካዎች ቁጥር እየጨመረ ነው” ይላሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉዋለ ፍስሐ።
ተገንብተው ከተጠናቀቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የዓባይ ግድብ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ግልጽ አድርገው የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኤሌክትሪክ ለሁሉም ነገር አስፈላጊ ነው። በመጠናቀቅ ላይ ያለው የዓባይ ግድብ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርብ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ብዙ ኤሌክትሪክ ምርት ሲኖር እናቶች ጤንነታቸው ተጠብቆ ምግብ ማብሰል ይችላሉ። በገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችም በምሽት ማጥናት እንዲችሉ ያደርጋል ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከአዳዲስ መንገዶች እስከ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ ከትምህርት ማሻሻያ እስከ ዲጂታል አስተዳደር ድረስ ዘላቂ ሀገራዊ እድገትን የሚደግፉ ምሰሶዎችን በማጠናከር ላይ ትገኛለች ያሉት ወይዘሮ ሙሉዋለ፤ የእዚህ ሥራ ውጤት ወዲያውኑ ላይታይ ይችላል ነገር ግን ለሁሉም የተሻለ ነገን እየቀረጸ ይገኛል ነው ያሉት።
በተማሪዎች ምገባ እየተከናወነ ያለው ሥራም ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸው፤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከናወነው ማዕድ ማጋራትም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የመረዳዳት እሴት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። እነዚህ ሥራዎች ለሀገር ግንባታ መሠረት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ስዩም መንግስቱ በበኩላቸው፤ ትምህርት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አንዱ መሣሪያ ነው። መንግሥትም ትምህርት ቤቶችን እያሻሻለ፣ መምህራንን በመጨመር እና የሥራ ማሠልጠኛ ማዕከላትን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
እነዚህ ፕሮግራሞች ወጣቶች የራሳቸውን ንግድ ለመጀመር ወይም ጥሩ ሥራዎችን ለማግኘት የሚጠቀሙባቸውን ክህሎቶች እንዲማሩ ያግዛቸዋል ያሉት አቶ ስዩም፤ ብዙ አገልግሎቶች አሁን ወደ ዲጂታል እየሄዱ ነው። ይህ ማለት ሰዎች ነገሮችን በፍጥነት ማከናወን እንዲችሉ ያደርጋል። ይህም ሀገር ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ አሁንም ብዙ ፈተናዎች አሏት። ነገር ግን በጠንካራ መሠረት ላይ ማተኮር ተስፋን ይሰጣል። ሰዎች ለእውነተኛ ለውጥ ጊዜ ይወስዳል። በዝግታ የሚገነባውም ረጅም ጊዜ እንዲቆይ በማሰብ እንደሆነም መዘንጋት አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት እና በተቋማዊ ማሻሻያ ሥራዎች ደረጃ በደረጃ ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት እየሠራች ነው። ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ላይ ትኩረት አድርጋለች። እነዚህ ሥራዎች ኢትዮጵያ መሠረቷን በአሸዋ ላይ ሳይሆን በአለት ላይ እየገነባች መሆኑን ያሳያሉ ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በኮሪዶር ልማትና በሌሎች ዘርፎች የሚጨበጡና የሚታዩ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል። ይህ የሚያሳየውም ኢትዮጵያ የብልፅግና መሠረቷን እየጣለች እንደሆነ ነው።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም