አቶ ግርማ በቀለ ወልደዮሐንስ የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ የቆዩና የኢትዮጵያን ፖለቲካም በቅርበት ለመረዳት ዕድል ያገኙ ናቸው፡፡ አቶ ግርማ በአሁኑ ወቅት ከለውጡ ወዲህ የተቋቋመውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በምክትል ሰብሳቢነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከእኒህ ፖለቲከኛ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መቼ እና በእነማን ተቋቋመ?
አቶ ግርማ፡- ምክር ቤቱ የተቋቋመው በ2011 ዓ.ም ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ሳምንት ሲሆን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ጨምሮ ፈቃደኝነታቸውን በገለፁ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰረተ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጋራ ምክር ቤቱ ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?
አቶ ግርማ፡- ዓላማዎቹ በቃልኪዳን ሰነዱ ላይ በዝርዝር ተቀምጠዋል። በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎች ኃላፊነት በተሞላ መልኩ እንዲሆን፣ በፓርቲዎች መካከል ችግሮች ሲፈጠሩም ወደ ክስ ከማምራታቸው በፊት በውስጣቸው ያለውን ችግር በውይይት እንዲፈቱ ለማስቻል ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑና ገዥው ፓርቲን ጨምሮ እነዚህ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የጋራ አቋም ለመያዝ ነው።
የጋራ ምክር ቤቱ ለየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ሳይወግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ ነው። የትኛውም ፓርቲ ቢሆን እወክለዋለሁ የሚለው ሕዝብና የሚቆምለት ዓላማ አለው። ይህን ዓላማ ሰላማዊ በሆነ የሕዝብን እና ሀገርን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ፓርቲዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ እንደ ዓላማ ይዞ ይንቀሳቀሳል። በአጠቃላይ የፓርቲዎች ህልውና የሚረጋገጠውና ነገም መንግሥት ሆነው ሕዝብን መምራት የሚችሉት ሕዝብና ሀገር ሲኖር በመሆኑ በሕዝብና በሀገር ላይ እንደዚህ ቀደሙ ግፎችና በደሎች እንዳይፈጸሙ የጋራ ምክር ቤቱ ይታገላል።
አዲስ ዘመን፡-የጋራ ምክር ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት የነበሩ ችግሮች ምንድን ነበሩ?
አቶ ግርማ፡- በአገራችን ባለፉት 27 ዓመታትና አሁንም የለውጥ ሂደት ተብሎ ከመጣ በኋላም ያለው አንድ ገዥ ፓርቲ ነው። በአጠቃላይ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በዚህ ገዢ ወይንም አውራ ፓርቲ የተመሰረተ ነበር። ሁሉንም አድራጊ ፈጣሪ ይኸው ፓርቲ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገሪቱን በሰብዓዊ መብትም ሆነ በልማት ወደ ኋላ እንድትቀር በማድረግ ውስብስብ የፖለቲካ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድጓታል። በርካታ የፖለቲካ ተዋናዮችን ባገለለ መልኩ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል ሕዝብና ሀገር የሚጎዱ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል። የሀገሪቱ ሀብት በስፋት ከመመዝበሩም ባሻገር በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።
በበርካታ መመዘኛዎች ሀገሪቱ ወደ ኋላ እንድትቀር ያደርጋት የነበረው የፖለቲካ ዕይታ ነው። ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ አንድ ፓርቲ እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ የሚል አባዜ ውስጥ ገብቶ ሀገራችን ውስብስብ ችግር ውስጥ እንድትገባ ምክንያት ሆኗል። ይህ ሁኔታ መቀጠል ስለሌለበትና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መስተካከል አለበት ከሚል እሳቤ ከአውራ ፓርቲ አስተሳሰብ ወጥተን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያገባቸዋል በሚል እሳቤ አዲስ የጋራ ምክር ቤት እንዲቋቋም ፓርቲዎች በጋራ ወስነዋል። በአጭሩ ቀድሞ ከነበረው የአፈና ሥርዓት ለመውጣት ታስቦ የተመሰረተ የጋራ ምክር ቤት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጋራ ምክር ቤቱ መቋቋም ባለፉት 27 ዓመታት ነበሩ የሚሏቸውን ችግሮች ይፈቷቸዋል?
አቶ ግርማ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ ችግሮች መደገም እንደሌለባቸው መተማመን ለመፍጠር በር የሚከፍት በቃልኪዳን ሰነዱ ላይ የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ቀርበው ፈርመዋል። ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ ውስጣዊ ሪፎርም ከማድረጉ አኳያ ለውጡን ለማስቀጠል ጽኑ እምነት ከተያዘና በተግባርም ማረጋገጥ ከተቻለ በጋራ ምክርቤቱ የሚነሱ ሃሳቦች መፍትሄ እያገኙ ይሄዳሉ ብለን እናስባለን። የችግሩንም አሳሳቢነት በመረዳትም በቃል ኪዳን ሰነዱ መግቢያ ላይም በግልፅ አስቀምጠናል። መንግሥትና ፓርቲ መለያየት አለባቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናም አይተኬና ከመንግሥት የማይተናነስ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ፓርቲ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሳተፍ የተፈጠረ አካል ነው። ይህንንም ተቋማዊ ማድረግ ከቻልንና ኢህአዴግ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ካለው ለውጥ ይመጣል ብለንም እናስባለን።
ያለበለዚያ ለይምሰል የሚደረጉ ነገሮች ካሉና ዛሬም እንደ ትናንቱ እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ የሚለው እሳቤ ካለ ከትናንቱ የከፋ ነገር ማጋጠሙ አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምክር ቤቱ የተቋቋመው ኢህአዴግን ከመጠራጠር ነው ወይስ ሁሉም ፓርቲዎች ለአገሪቱ በጋራ እንዲሰሩ ታስቦ ነው?
አቶ ግርማ፡- መንግሥትን ወይንም የኢህአዴግ ፓርቲን ከመጠራጠር ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ለማስገባት ተብሎ አይደለም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተቋቋመው። በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት አለ። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚያደርጓቸው ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች አሉ። ሁሉም ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን፤ እንቅስቃሴው ሕገ መንግሥቱን እንዲያከብር ሕግን የተከተለ እንዲሆን ለማስቻል ነው። በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እንጂ ኢህአዴግን ከመጠራጠር ሌሎቹን ከማመን የመነጨ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም ወዲህ ያስገኛቸው ተጨባጭ ለውጦችስ ምንድን ናቸው?
አቶ ግርማ፡- በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ይከብድ ይሆናል። ነገር ግን ገዢው ፓርቲና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ከጥርጣሬ ወጥተው በውይይትና መግባባት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሂደት እንዲገነቡ ጅምር ጥረቶች እየተደረጉ ነው። አገራችን ውስጥ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት መታየት አለባቸው። እነዚህ ተቋማት በትክክል ነፃነታቸውን አውጀው በተቋም ደረጃ ሙሉ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለውን በሂደት እየፈተሽን እንሄዳለን። ከነበርንበት እርስ በእርስ የመወነጃጀልና የመጠላለፍ ፖለቲካ አስተሳሰብ ተላቀናል ወይ የሚለውም ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
አሁን በቅርበት አብረን የምንሠራው ከምርጫ ቦርድ ጋር ነው። ለዚህ ምክር ቤት ቢሮ የሚሰጠንና የፋይናንስ ድጋፍ የሚደያርግልን ይህ ተቋም ነው። ይህንን በተመለከተ የተሟላ ባይሆንም አንድ ክፍል ቢሮ ሰጥቶናል። በሌላም በኩል በተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የመዳኘት ሥራ እየሰራን ነው። አንዱ ፓርቲ በሌላው ላይ ያቀረበውን ቅሬታ ተቀብለን መርምረን የውሳኔ ሃሳብ ለመስጠት አምስት አጣሪ ቡድን አቋቁመን ወደ ሥራ ገብተናል።
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲዎች ከጋራ ምክር ቤቱ ቢያፈነግጡ እርስ በእርስ ተግባብተው እንዲቀጥሉ የሚያስገድድ አሠራር አላችሁ?
አቶ ግርማ፡- ምክር ቤቱ በፓርቲዎች መልካም ፈቃድና እውቀት የተመሰረተ ነው። ስለዚህ ምክር ቤቱ የሚወስደው የተለየ እርምጃ የለም። ነገር ግን ፓርቲው በምክር ቤቱ የቀረበለትን ውሳኔ ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ በምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት ለሕዝብ ይፋ ይደርጋል። ስለዚህም ለራሱ ህልውና ሲል ፓርቲው በሕዝብ ዘንድ ስሙ እንዲጠፋ አይፈልግም። ከዚህ በተለየ ሁኔታ የሚያፈነግጥ ከሆነ ከደጋፊዎቹና ከሕዝብ ጋር መጋጨቱ አይቀሬ ነው። ሁኔታውን ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ውጪ የጋራ ምክር ቤቱ ሊወስድ የሚችለው እርምጃ የለም።
ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም በላይ የፓርቲ ጥቅም ያስቀድማሉ ይባላል። ይህንን ሁኔታ የጋራ ምክር ቤቱ እንዴት ያየዋል?
አቶ ግርማ፡- እንግዲህ ወደዚህ ድምዳሜ ለመድረስ ዝርዝር ጥናት ያስፈልጋል። ነገር ግን በአገራችን ያለውን የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ ይሄንን ሊያስብል የሚያስችል ጥርጣሬ ቢኖር የሚገርም አይደለም። ገዥው ፓርቲ እና መንግሥት ባልተለዩበት፤ ካለፈው ለውጥ ከ1983 ዓ.ም እስከ አሁን ዴሞክራሲ ከይስሙላ ባላለፈበት በተለይም ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ጸድቆ አምስት ምርጫዎች ተደርገው ሁሉም ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ነበሩ የሚሉ ቀልዶች ሲነገሩ በቆዩበት ሁኔታ ውስጥ ሁሉም በአንድ መንፈስ መተማመን ላይ ደርሶ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ይቆማል ቢባል ከእውነታው መራቅ ነው። ፓርቲዎች የሕዝብንና የአገርን ጉዳይ ከፓርቲ ጥቅም አንጻር እየቃኙ፤ ሕገ መንግሥቱንም በሚመቻቸው መንገድ እየተረጎሙ ወይም ደግሞ በአንድ ቀን ሕግ እያወጡ ሕዝብ ያፈኑበት ሁኔታ ነው ያለው።
እውን ዴሞክራሲን ለመገንባት ቁርጠኝነት ነበራቸው ወይ ከተባለ፤ ከገዥው ፓርቲ አንጻር ያየነውም ሆነ በዚህ አንድ ዓመት ተኩል በፓርቲዎች ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ካየን ሁሉንም ባይመለከትም የአገርና ሕዝብን ጉዳይ ከማስቀደም ይልቅ የፓርቲ ፕሮግራምን እና የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት የማጉላት አዝማሚያ ይስተዋላል። ይህንና መሰል አዝማሚያዎችን በተቻለ መጠን በውይይትና በምክክር ለማስተካከል እንሞክራለን።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። በአዋጁ ላይ የእናንተ ድርሻ ምን ነበር?
አቶ ግርማ፡- እንደጋራ ምክር ቤት በስተመጨረሻ ነው በዚህ ጉዳይ ላይ የተንቀሳቀስነው። ነገር ግን እንደጋራ ምክር ቤት ወይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሕይወት ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ፓርቲ ተስፋ ተጥሎብን አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል የመጀመሪያው ረቂቅ ቀርቦልን ተወያይተናል። የመጀመሪያው ረቂቅ ቀርቦልን በተወያየንበት ወቅት ያነሳናቸው ጉዳዮች ተካተው በሁለተኛው ረቂቅ ላይ እናገኛቸዋለን ብለን ስናስብ በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ያነሳናቸውን ጉዳዮች በከፊል አካቶ ያልተወያየንባቸው ጉዳዮችም ተካተው አጋጠሙን። ሁለተኛውን ውይይት ለመመልከት በተሰበሰብንበት ጊዜ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። በተለይም ደግሞ የሀገሪቱን መጪ የፖለቲካ ሁኔታን የሚወስን ይህንን ትልቅ አዋጅ በአንድ ቀን እይታ ልንወስን አንችልም የሚል ቅሬታ በማቅረባችን ቀጠሮው ለሌላ ቀን ተላለፈ። ለሌላ ቀን ተቀጥሮም መነጋገር ጀመርን። ይሁን እንጂ በሁለተኛው ዙር ውይይት ወቅት የማናውቃቸው ሀሳቦች ስለተካተቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመጽደቁ በፊት ሊታረሙ ይገባቸዋል ያላቸውን 15 አንቀፆችን፣ ንዑስ አንቀጾችንና የተብራሩ ጥያቄዎችን ከሥራቸው በ25 ንዑስ አንቀፆች ያሉትን ረቂቅ ሀሳብ አቅርበናል። ይሁን እንጂ ያቀረብናቸው ሀሳቦች ሳይካተቱ አዋጁ እንዲጸድቅ ተደርጓል።
ይህ ማለት በጋራ ምክር ቤቱ በኩል የተነሱት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በአካልም በደብዳቤም ጥረት ብናደርግም ምላሽ አላገኘንም። ኢህአዴግን ጨምሮ 107 ፓርቲዎችን ወክሎ ያለው የጋራ ምክር ቤት ቅድም የገለጽኳቸውን 15 ነጥቦች በዝርዝር በብዙ ንዑስ አንቀጽ የተያዙትን አጠቃለን ያቀረብንበት ዝርዝር ሁኔታ፤ በ25 አንቀጾች ስር ባሉ በርካታ ንዑስ አንቀጾች ያቀረብነውን አቤቱታ፣ ማመልከቻ ወይም የማሳሰቢያ ደብዳቤ ላይ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን አጽድቆታል። ይህ መሆኑ እንግዲህ ከመጀመሪያው ጀምሮ በዋና ተዋናይነት የተካፈለውን ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ነፃነትና ገለልተኝነት እንድንጠይቅ አድርጎናል።
አዲስ ዘመን፡- አከራካሪ የነበሩት አንቀጾች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ግርማ፡- ቅድም እንዳልኩት ከ40 በላይ አንቀጾች ከእነዚህ ስር ደግሞ በርካታ ንዑስ አንቀጾች አሉ። አዋጁ 66 አንቀጾች አሉት ከዚያ ውስጥ 40ዎቹ ላይ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ጥያቄዎች ቀርበዋል። አሁን ጎልቶ ወጥቶ እንደጸደቀ የምናውቀው አንዱ የፓርቲዎች ከመደራጀታቸው በፊት የሚያሰባስቡት የድጋፍ ፊርማ ነው። ቀደም ሲል ለክልል ፓርቲነት የሚሰበሰበው የድጋፍ ፊርማ 750 ነበረ፤ አሁን ግን ያለምንም አሳማኝ ሁኔታ ወደ 1500 አድጓል። ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ 10 ሺ የድጋፍ ፊርማ አሰባስብ የሚለው በምንም መልኩ የሚያስኬድ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አንድን ሀገር ለመምራት የሚወዳደር ፓርቲ እንዴት 10ሺ የድጋፍ ፊርማ ያሳስበዋል?
አቶ ግርማ፡- ዋናው ነገር የቁጥሩ ጉዳይ አይደለም። ጥያቄውም ፓርቲ ከቁጥር ይልቅ በሃሳብ ላይ መስራት አለበት የሚለው ነው። ዋናው ነገር የሃሳብ የበላይነት እንጂ የቁጥር የበላይነት አይደለም። አንድ ፖለቲካ ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው በሚያቀርበው ሃሳብ እንጂ በሚያሰባስበው ፊርማ አይደለም። የሚገርመው እኮ አንዳንድ አካባቢዎች 4 ሺ የማይሞላ ነዋሪ ያለባቸው አሉ። ከዚህ ውስጥ ለመምረጥ የደረሰውን ከ18 ዓመት በላይ የሆነውን ብታስብ ምርጫ ቦርድ ለክልል ፓርቲነት ያስቀመጠውን የ1500 የድጋፍ ድምጽ ለመሙላት የሚያስችል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን እያቀረቡት ያለው ቅሬታ በምክር ቤቱ የታቀፉት ፓርቲዎች የመከሩበት ነው ወይስ እንደ ግል ነው እየነገሩኝ ነው ያሉት?
አቶ ግርማ፡- እስከ አሁን እየመለስኩልህ ያለሁት የምክር ቤቱን ሃሳብ ወክዬ ነው። እንዴት የግሌ ሊሆን ይችላል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ ሰጥተዋል። ሌሎች ፓርቲዎችም ቅሬታቸውን በተለያየ መልኩ እያቀረቡ ነው። በቅርቡም የጋራ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፡- ጥሩ ሌሎችስ ከዚህ ከፊርማ ቁጥር በተጨማሪ አወዛጋቢ የነበሩ ህጸፆች አሉ?
አቶ ግርማ፡- አዎ አሉ። ለአብነት አዋጁ መንግሥት ሠራተኞች ያለምንም ክፍያ በምርጫ ሂደቱ በሚቆዩባቸው ጊዜያት ያለደመወዝ እንዲቆዩ የሚያስገድደው አንቀጽ ተገቢ ነው ብለን አናምንም። የመንግሥት ሠራተኛው እንኳን ለወራት ቀርቶ ለቀናት እንኳን የሚያቆይ ጥሪት እንደሌለው እየታወቀ ይህ አንቀጽ መካተቱ ተገቢ አይደለም። የሚገርመው ደግሞ ቀደም ሲል ኮሮጆ በመስረቅና የሕዝብ ድምጽ በማጭበርበር አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ የነበሩትን በመንግሥት ሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎችን በተመሳሳይ መልኩ አዋጁ ሊያግድ ሲገባው ምንም ገደብ ሳያስቀምጥ ማለፉ ተገቢ ነው ብሎ የጋራ ምክር ቤቱ አያምንም።
አዲስ ዘመን፡- እንደአጠቃላይ አዋጁን ምን ያህል ፓርቲዎች ደግፈውታል ምን ያህሉስ ተቃውመውታል?
አቶ ግርማ፡- እኛ እንደምንለው ይህንን በመደገፍ ሊሰለፉ የሚችሉ ብለን የምናምናቸው ኢህአዴግ እና ጠቅላላም ባይሆኑ እህት ድርጅቶቹ እና አጋር ድርጅቶቹ እንዲሁም ከኢህአዴግ ጋር ቁርኝት አለን ብለው ሕጉን ያረቀቅን እኛ ነን ለአገሪቷ ሪፎርሙ «ሮድ ማፕ» የሰራን እኛ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ናቸው። ከነዚህ ውጪ ያሉት ይደግፉታል ብለን አናስብም። ቀደም ሲል እንደገለጽኩልህም እስካሁን ከ58 ፓርቲዎች በላይ ቅሬታቸውን ለጋራ ምክር ቤቱ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎች ተሰባስበው መክረውበታል?
አቶ ግርማ፡- በጉዳዩ ላይ ስለተመካከ ርንበት ነው በቀጣይ መግለጫ እንሰጣለን እያልኩህ ያለሁት
አዲስ ዘመን፡- መጪው ምርጫ 2012 ዓ.ም በተመለከተ የጋራ ምክር ቤቱ ያለው አቋም ምንድን ነው?
አቶ ግርማ፡- የጋራ ምክር ቤቱ ሰባት አጀንዳዎችን አውጥቶ ምክር ሊያደርግ ተዘጋጅቷል። ከእነዚህ አጀንዳዎች ውስጥ አሁን በስፋት የተወያየንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅን የተመለከተው ጉዳይ የመጀመሪያው የውይይታችን አጀንዳ ነው። በሁለተኝነት ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ ሰፊ ውይይት የምናደርግበት ይሆናል። ስለዚህም አሁን ላይ ሆኜ ምክር ቤቱ አቋም የያዘበት ሁኔታ ስለሌለ ምርጫውን በተመለከተ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ግርማ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 25/2011