የስነ-አዕምሮ ሳይንስ በዓለም በተለይም በአፍሪካ ገና በማቆጥቆጥ ላይ እንዳለ በስነ- አዕምሮ ህክምና ዙሪያ የተፃፉ የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ። በሃገራችን ኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕመምን በተመለከተ በተለምዶ የሚሰነዘሩ የተለያዩ አባባሎች ያሉ ሲሆን በሕክምናው ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥርም በጣም ውስን ነው። ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ በሃገራችን ውስጥ በብቸኝነት የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኘው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዱ ነው። አንዳንድ የግል ተቋማት ቢከፈቱም አሁንም ግን ከሚፈለገው ቁጥር አንጻር ኢምንት ናቸው።
የአዕምሮ ሕመም
ከተለመደውና ትክክለኛ ከሚባለው ውጭ የአስተሳሰብ፤ የስሜት ወይም የባህሪ ለውጥ ሲኖር እና ከባድ የአዕምሮ ጭንቀት ሲያስከትል ለራሱ ጭንቀትን የሚፈጥር ከሆነ፤ በሕመም ምክንያት የሚፈጠረው የግለሰቡ ባህሪ ለውጥ በሰላማዊ ማህበራዊ ግንኙነት ወይም ከሰዎች ጋር በመግባባት አብሮ ለመኖር እንቅፋት ከሆነ፤ በተጨማሪም ከነባራዊ እውነታዎች መውጣትና ሌሎች ሊገሯቸው በማይችሉት የራስ አለም ውስጥ መገኘት፤ እንዲሁም ከህመም የተነሳ ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ሲዛቡ የአዕምሮ ሕመም ተከሰተ እንላለን።
የአዕምሮ ጤና ማለት ምን ማለት ነው?
የአዕምሮ ጤና ማለት እንደ የዓለም ጤና ድርጀት አገላለጽ ”የራስን ማንነት አውቆ ራስን መምራት መቻል፤ ሃላፊነትን ማወቅና መወጣት፤ ምክንያታዊ ካልሆነ ጭንቀት ነጻ የሆነ ህይወት መምራት መቻል እንዲሁም ካለበት ማህበረሰብ ጋር በመግባባት ተግባርን ማከናወንና በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤን የመከተልን ሁኔታ” ያመለክታል።
በተቃራኒው የአዕምሮ ሕመም ክስተቶች ዙሪያ ሳይንሳዊ የሆነና ተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትምህርት ያልተስፋፋ በመሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ አዕምሮ ህመም ያለው ግንዛቤ በጣም አነስተኛና በባህል ሲወርድ ሲዋረድ በመጡ አባባሎች ላይ የተመሰረተ ነው።
የአዕምሮ ህመም እንደሚባለው ልክፍት ወይም ቁጣ ሳይሆን ማንኛውም የሰው ልጅ አካል እንደሚታመም ሁሉ አዕምሯችንም ይታመማል፤ በተለያዩ ምክንያቶችም መረበሽ ይደርስበታል። ስለ አዕምሮ መረበሽ ሦስት ዋና ዋና እውነታዎች ይጠቀሳሉ።
1. የአዕምሮ ሕመም የርኩስ መንፈስ ውጤት ሳይሆን እንደ ማንኛውም የሰውነት ሕመም በተወሰነ የክፍሉ አካል (አንጎል) መታመም የተነሳ የሚፈጠር ነው፣
2. አብዛኛው የእርስ በእርስ ሰላም ማጣት ካለመከባበር እና ካለመተባበር ጋር ይያያዛል።
3. የአዕምሮሕመም እንደማንኛውም የአካል ሕመም በአብዛኛው በህክምና ሊድን ይችላል።
የአንድ ሰው አዕምሮ ጤነኛ አይደለም የሚባለው መቼ ነው?
አዕምሮን ጤነኛ ወይም ሕመምተኛ ብሎ ለመፈረጅ የሚያስችል መስፈርት ወይም መመዘኛ ግልፅ በሆነና ሁሉም ሰው ሊስማማበት በሚችል መልኩ የተቀመጠ አይደለም። የአንድ ሰው አዕምሮ ጤነኛ ወይም ሕመምተኛ ለማለትና ለመገምገም እንደ የህብረተሰቡና እንደየአካባቢው ባህልና ግንዛቤ እንደሚወሰን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በዚህም የአንድ ሰው አዕምሮ ጤነኛ አይደለም ለማለት ከሚያስችሉ አጠቃላይ መስፈርቶች ከሚከተሉት አንዱ ወይም ከአንድ በላይ ሲኖረው እንደሆነ አብዛኞች ምሁራን ይስማማሉ።
ሀ/ የግለሰቡ አዕምሮ ለራሱ ጭንቀትን የሚፈጥር ከሆነ፤
ለ/ የግለሰቡ አዕምሮ ለሠላማዊ ማህበራዊ ግንኙነት ወይም ከሰዎች ጋር በመግባባት ለመኖር እንቅፋት የሚሆን ከሆነ፤
ሐ/ በራሱ በግለሰቡ ወይም በሌሎች ላይ የአካል፤ የመንፈስ ወይም ማህበራዊ ቀውስን የሚያስከትል ከሆነ፤
መ/ ግለሰቡ የሚጠበቅበትን ቤተሰቡን፤ የመንግስት ስራን፤ ትምህርትን ወይም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ ባህሪው እንቅፋት ከሆነውና የመሳሰሉት ሲከሰቱ/ሲታዩ የግለሰቡ አዕምሮ ጤነኛ አይደለም ለማለት ያስችላል።
የአዕምሮ ሕመም መንስኤ
ለአዕምሮ ሕመም መከሰት ምክንያት የሚሆኑት ወይም መንስኤዎች የሰበቦች ጥርቅም ውጤት እንደመሆኑ መጠን ለሕመሙ አንድ የተወሰነ መንስኤ ማስቀመጥ አዳጋች ነው። በመሆኑም ለአዕምሮ ሕመም መከሰት በዋናነት የሚጠቀሱት ዝርዝር መንስኤዎች ግን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይፈረጃሉ። እነሱም Biological ወይም ስነ-ፍጥረታዊ (አካላዊ)፤ Psychological ወይም ስነ- ልቦናዊ እና Social factors ወይም ማህበራዊ መንስኤዎች ናቸው።
Biological ወይም ስነ- ፍጥረታዊ(አካላዊ) መንስኤዎች፡- ስነ- ፍጥረታዊ(አካላዊ) መንስኤ በአንጎል ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳት የሚያመጡ አደጋዎችና አካላዊ ሕመሞች እንዲሁም ተለያዩ የአንጎል ንጥረ ነገሮች መዛባት መሆናቸው ይጠቀሳል። እነዚህ ችግሮች አንጎል የዘወትር ተግባሩን በትክክል እንዳያከናውን በማድረግ ለአዕምሮ መታወክ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ኢንፌክሽን መፈጠር፤ የተለያዩ የሰውነት ንጥረ ነገሮች ማነስ ወይም መብዛት፤ በራስ ቅል (ጭንቅላት) ላይ የሚደርስ አደጋ፤ የደም ብዛትና የአንጎል መሳሳት ለዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
Psychological ወይም ስነ-ልቦናዊ መንስኤዎች፡- ይህ ማለት በራስና በሌሎች ምንነት ላይ፣ የተለያየ ማህበራዊ ክስተቶችን፣ የተለያዩ እምነቶችና ፍልስፍናዎችን ወይም ድርጊቶችን በተመለከተ የሚጋጩ ሃሳቦች በሰዎች አዕምሮ ውስጥ በየጊዜው ይፈጠራሉ። የሃሳብ መጋጨቱ የሚፈጠረውም በግለሰቡ መመራመር፣በአዕምሮ መታዎክ ወይም በሌሎች ሰዎች ተፅንኦ ሊሆን ይችላል። በዚህም በአዕምሮ ውስጥ የሚጋጩ ሃሳቦች ሲፈጠሩና አቋምን መለየት ሲቸግር ከፍተኛ መረበሽና የአዕምሮ ሕመም ሊከሰት ይችላል።
Social factors ወይም ማህበራዊ መንስኤዎች፡- ይህ ችግር በብዛት የሚስተዋልባቸው ምክንያቶች አደንዛዥ ዕጾችን የመጠቀም (substance abuse) እና የህይወት ውጣ ውረዶች (life stressors) ተጠቃሾች ናቸው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በሰዎች አብሮ የመኖር ሁኔታ ውስጥ፣ በእርስበርስ ግንኙነቶችና በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ወቅት አለመግባባቶችና ግጭቶች በየጊዜው ይፈጠራሉ። በዚህም አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠሩ ግጭቶችና አመለካከቶችን በግልፅና በተለመዱ ማህበራዊ ዘዴዎች ተጠቅሞ መፍታት ይቻላል። በዚህም የተነሳ ሰዎች የግድ አብረው መኖር ካለባቸው ሰው ወይም ማህበረሰብ ክፍል ጋር በዚህ ዓይነት ቋሚ ግጭት ወይም አለመግባባት ውስጥ ሲገቡ ልዩነቱን ተቀብለው ተቻችለውና ግንኙነቱን አስተካክለው ለመኖር ሳይችሉ ሲቀር እና የአዕምሮ መረበሽ ሲከሰት በጊዜ ሂደት ተባብሶ የአዕምሮ ህመም ሊከሰት ይችላል ።
የአዕምሮ ሕመም ምልክቶች
የአዕምሮ ሕመም ምልክቶች በጣም የተለያዩ ሲሆኑ ልዩነቶቹ ደግሞ እንደ ሕመሙ ዓይነትና ደረጃ ይወሰናሉ። እንዲሁም የግለሰቡ ዕድሜ፣ የትምህርት ወይም የዕውቀት ደረጃ ዓይነት፣ ባህልና ዕምነቱ በምልክቶቹ ላይ ጉልህ ተፅንኦ አላቸው። በዚህ ፅሁፍ ላይ የተጠቀሱት በብዛት የሚታዩና ሰዎች በቀላሉ ሊረዷቸው ይችላሉ ተብለው በተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች የተጠቀሱትን ብቻ ነው። እነርሱም የስሜት ችግሮች (ካለምክንያት የስሜት መቀያየሮች)፤የአካል ችግር (የእንቅልፍ፣ የወሲብ፣ የምግብ ፍላጎቶች መብዛት ወይም ማነስ)፤ የባህሪ ችግሮች (ከዚህም በፊት በግለሰቡ ላይ የማይታዩና እንግዳ የሆኑ ባህሪያት መታየት)፤ ማህበራዊ ችግሮች (በማህበራዊ ግንኙነት ላይ ያለምክንያት የተለያዩ ጠባዮችን ማንፀባረቅ)፤ በስራ ላይ ችግር መፍጠር (የስራ ምርታማነትና የፈጠራ ችሎታ መቀነስ፣ ፍላጎት ማጣትና የማስታወስ ችግር)። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የአዕምሮ ህመምተኛ ላይ የሚታዩ ምልክቶችን የስሜት፤ የአካል፤ የባህሪ፤ የማህበራዊ እና የስራ ብለን ልንከፍለው እንችላለን ።
የአዕምሮ ሕመም ሊድን ይችላል?
የአዕምሮ ሕመም መዳን የሚችል ሲሆን ሙሉ ለሙሉ መዳን የማይችሉ ጥቂት ዓይነት የአዕምሮ ሕመም ዓይነት መኖራቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በ1993 ዓ.ም <<የአዕምሮ ደህንነት>> በሚል ባሳተመው መፅሐፉ ላይ ያትታል። ነገር ግን እነዚህን ሕመሞችንም ቢሆን በአብዛኛው ለታማሚውና ለቤተሰብ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይፈጥሩ በህክምና መቆጣጠር እንደሚቻልና ለአዕምሮ ሕመም ችግሮች እንደ ሕመሙና ታማሚው ልዩ ስብዕና የተለያዩ የህክምና ማስተካከያ ዘዴዎችና መድኃኒቶች እንደሚገኙ ያስቀምጣል።
ከአዕምሮ ሕመም ዓይነቶች ጥቂቶቹ፡-
ስኪዞፍሬኒያ (Schizophrenia/Psychosis)
ድባቴ (Depression)፣የሁለት ተቃራኒ ጫፍ ተለዋዋጭ ስሜት (Dipolar Disorder)፣ በአደንዛዥ እጽ ሱስ ሳቢያ የሚመጣ የአእምሮ ህመም (Mental illness due to substance use disorder)፣አንድን ነገር ለማድረግ ከውስጥ የሚወጣ አስገዳጅ ነገር ግን ተገቢ ያልሆነ ከፍተኛ ፍላጎት(Obsessive Compulsive Disorder)፣ የጭንቀት ህመም (Anxiety Disorder)፣ ከእርጅና ጋር ተዛማጅ የሆኑ የመርሳትና የማገናዘብ ችግሮች(Old age related cognitive disorder) የሚጠቀሱ ሲሆን የአዕምሮ ህመም ምልክቶች በጣም የተለያዩ ሲሆኑ ልዩነቶቹ እንደየሕመሙ ዓይነትና ደረጃ የሚወሰኑ እና የግለሰቡ እድሜ፤ የትምህርት ደረጃ፤ ባህል እንዲሁም እምነት በምልክቶቹ ምንነት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ አላቸው።
ነገር ግን በብዛት የሚታዩትና በቀላሉ ሰዎች ከሚረዷቸው ምልክቶች ውስጥ የስሜት ችግሮች ማለትም አብዛኞቹ የአዕምሮ ህመሞች በታማሚው ስሜት ውስጥ የተለያዩ ለውጦችን የሚያስከትሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ዝምታ፤ ብስጭት፤ ደስተኛ አለመሆን፤ ካለምክንያት መደሰት፤ የመንፈስ አለመረጋጋት፤ ካለምክንያት ጭንቅ- ጭንቅ ማለት፤ ማልቀስ ወዘተ ይገኙበታል። ሌላው የስሜት ህዋሳት ስራ መዛባት ሲሆን የሚታዩት ምልክቶችም በእውኑ ዓለም ሌሎች የማይጋሩትን የሌለን ድምጽ መስማት፤ የሌለን ነገር ማየት፤ የሌለን ነገር ማሽተትና የመሳሰሉትን ምልክቶች ሲያሳይ የእንቅልፍ መብዛት ወይም ማጣት፤ የሚካተቱ ናቸው።
በሌላ በኩል የአዕምሮ ሕመም ምልክቶች ከሆኑት መካከል የባህሪ ችግር ወይም የባህሪ መቀየር የሚስተዋል ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ቅብጥብጥነት፤ ቀሰስተኝነት፤ ራስን መጣል፤ ግዴለሽነት፤ አጉል ድፍረት፤ እና ሌሎች እንግዳ የሆኑ ባህሪያት ይንጸባረቃሉ። የማህበራዊ ችግሮችን በተመለከተ በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ማህበራዊ ግንኙነቶች ችግር ላይ ይወድቃሉ። የማህበራዊ ችግሮች በአዕምሮ ሕመም ስለመጠቃት የሚያመላክት ሌላው ምልክት ሲሆን በዚህ ስር የሚስተዋሉ ምልክቶች ግለሰቡ የሚጠበቅበትን ቤተሰቡን የመንከባከብ ስራ፤ ትምህርቱን፤ ስራውን ወይም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣት፤ ተነጫናጭነት፤ ወይም ምክንያት በሌለው ጉዳይ ላይ ተጨቃጫቂነት ያጠቃዋል።
በአጠቃላይ ሁሉም ሰው ያለ አዕምሮ ጤና ጤና ያለመኖሩን ተገንዝቦ የአዕምሮውን ጤና መጠበቅና መንከባከብ የሚኖርበት ሲሆን የአዕምሮ ጤና ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነውና ለአዕምሮ ሕሙማን ተገቢውን እንክብካቤ ልናደርግ ይገባናል።
ምንጭ፤ ገዛኸኝ ጋሞ- ከኢትዮሃኪምቤት ዶት ኮም
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 25/2011