)
ዛሬ ሀገራችን ለምትገኝበት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፈተናዎች በተናጠል መልስ ለመስጠት ተሞክሯል። ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ ፣ለኢኮኖሚያዊ ፈተና ኢኮኖሚያዊ መልስ፣ ለማህበራዊ ቀውስ ማህበራዊ መላ ለማበጀት ተንቀሳቅሷል ። ሆኖም በሚፈልገው ልክ አልተሳካም ። አልሆነም ። ለችግር ፣ ለቀውስ ፣ ለፈተና በዳረገ አግባብ ከችግር ፣ ከቀውስ ፣ ከፈተና ለመውጣት ስለሚሞከር ከንቱ ድካም ሆኖ ቀርቷል።
በማንነት በዘውግ ላይ የተመሰረተ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ላስከተለው ፖለቲካዊ ቀውስ ተመልሶ በማንነት በዘውግ ላይ በተመሰረተ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መፍትሔ ለማግኘት ይባዘናል። ልማታዊ መንግስት እና የትልቅ መንግስት Big Government ፍልስፍና ያመጣውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መልሶ በልማታዊ መንግስትና በትልቅ መንግስት እሳቤ ለመፍታት ይጣራል። ለዛውም ልማታዊ መንግስት እና ደካማ ሀገራዊ አንድነት ሆድና ጀርባ እንደሆኑ እየታወቀ።
እነዚሁ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ያመጡትን ማህበራዊ ቀውሶች በእነዚሁ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ከቀውስ ለመውጣት ይማሰናል። ላለፉት በርካታ ዓመታት ግን ጠብ ያለ ነገር የለም ። ከተገባበት የቀውስ አዙሪት፣ ኡደት መውጣት አልተቻለም። ከሳጥኑ ወጣ ብሎ ማሰብ፣ ማሰላሰል አልተሞከረም። በየአስር ዓመቱ እያሰለሰ ከሚመታን የድርቅ ፣ የርሀብ ቀለበት ሰብሮ መውጣት እንኳን አልተቻለም። ድርቁ ፣ እርሀቡ እጅ ተጣጥፎ ሲጠበቅ በየአምስት፣ በየሶስት፣ በየዓመቱ ይጎበኘን ጀምሯል። ለዚህ ይመስላል አልበርት አነስታይን
“ተመሳሳይ ነገርን ደግሞ ደጋግሞ በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው።” ያለው። እውነት ለመናገር ጨርቃችንን ጥለን ባናብድም ስራችን ግን የአውቆ አበድ አይነት እየመሰለብን ነው። አነስታይን ለዚህ ይመስላል እንዲህ ሲል ዘወር አድርጎ በአናቱ የጨመረልን “ችግሩን በፈጠረው በዚያው እይታ፣ አስተሳሰብ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም።”
በአጠረ ጊዜ እና በዝቅተኛ ወጪ ከአዙሪት የምንወጣበትን ሌላ አማራጭ ፣ አቋራጭ መንገድ ማማተር አለብን። ከምቾት ዞን በመውጣት ለማያዳግም መፍትሔ ሁሉንም ድንጋይ በመፈንቀል ፣ ስር በመማስ መላ ማቀበል ፣ ሃሳብ ማዋጣት ይገባል። የኢኮኖሚ ባለሙያ ባልሆንም ሁለት አስርት ዓመት የተሻገረው ሁለገብ የጋዜጠኝነት ልምዴ በሰጠኝ ድፍረትና ሞኝነት ከታላቅ ይቅርታ ጋር ከተዘፈቅንበት አረንቋ ሊያወጣን ይችላል ያልሁትን መፍትሔ እንደሚከተለው አቀብላለሁ።” ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው።” ካላላችሁ!? የዘርፉ ልሒቃን በቀጣይ ሊተቹት፣ ሊሔሱት አልያም ሊያጎለብቱት ይችላሉ።
የሃሳቤ መነሻ ችግሮቻችንን ሊወክላቸው በሚችል ሌላ አንድ ችግር ለመፍታት መሞከር ነው። ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻችንን በሙሉ በኢኮኖሚያዊ መፍትሔዎች ለመፍታት መሞከር። ወይም ችግሮቻችንን እንደ ካርታ የመጫወቻ ካርድ በተለምዶ በጆከር ወክሎ ከማየት ይነሳል። ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮቻችንን በጆከርነት በመረጥሁት በኢኮኖሚ መወከልና መፍታት። ችግሮቻችን እንደ ካርታ መጫወቻ ካርዶች የተለያዩ ምስሎችንና ቁጥሮችን የያዙ ናቸው። ቁጥሮቹ ከአንድ ተነስተው እስከ አስር እንደሚደርሱት ሁሉ ምስሎቹም ከወለድ ተነስተው ኪው ፣ ኬን አስከትለው አንድን መልሰው የሚሾሙ ናቸው።
ችግሮቻችን ከቀላል ተነስተው እየተወሳሰቡ ፣ እየከበዱ የሚሄዱ ናቸው። እንደ የካርታው “ 1 “ ቁጥር ነጠላ የነበረው ችግር በጊዜ ባለመፈታቱ ተወሳስቧል። ተተባትቧል። ውሉን ማግኘት ቸግሯል። እንደ ካርዶች መልክ እንዲሁ ችግሮቻችን ዥጉርጉር እና የተለያዩ ሆነዋል ። የካርታ ጨዋታው በዚህ ልዩነት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ጨዋታውን ለማስዋብ እና በአጠረ ጊዜ ለመጨረስ ይመስላል ሁሉንም ተክቶ ፣ ወክሎ ለመጫወት የሚያስችል ጆከር JOKER / WILDCARD የሚባል ካርድ የተፈጠረው። ተጨዋቹ ይህን ካርድ ለማግኘት በተስፋ ይስባል። አንዳንዶች
“ ከሰጪው “ ያገኙታል ። ከካርታ ተጨዋቾች ይህ ካርድ የደረሰው እንደ እድለኛ ከመታየት አልፎ ከፍ ያለ የማሸነፍ እድል እንዳለው ይታመናል። ሆኖም ጆከር ለብቻው ያለ ችሎታ አሸናፊ ላያደርግ ይችላል ። ለሀገራችንም ኢኮኖሚው እንደ ጆከር ፖለቲካዊም ፣ ማህበራዊ ችግሮችን ወክሎ ለመፍታት ፣ ለመጫወት እምቅ አቅም ያለው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህን አቅም ግን በጥበብ ስራ ላይ ማዋል ይጠይቃል። አሁን ስራ ላይ የሚውሉትንም ሆነ በቀጣይ ማሻሻያ የሚደርግባቸውን የኢኮኖሚ ዘርፎች መረጣ ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይጠይቃል ።
ውጤታማ የሆነውን ለማስቀጠል አዋጭ ያልሆነውን ለመጣል ደፋር ውሳኔ ሰጪ መሆን ይገባል። ለአብነት ለጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉ የተሰጡ አጠቃላይ ድጋፎችን በተለይ የፋይናንስ አቅርቦቱን ስኬታማነት መለስ ብሎ መፈተሽ እንዲሁም በቀጣይ ወጣቶችን በመስኖ ስራ ለማሰማራት የተያዘውን ዕቅድ ከጠባቂነት አባዜ ጋር ያልተጣባ መሆኑን ማረጋገጥን ማንሳት ይቻላል። ይህን ማረጋገጥ ካልተቻለ ኢኮኖሚውን ( ጆከሩን ) ስቦም አሸናፊ መሆን አይቻልም።
የካርታ ጨዋታው “ኮንከር “ ነው ብለን እንውሰድ ። በዚህ የጨዋታ አይነት የምንጠብቀውን ፣ የምንይዘውን፣ የምንጥለውን ካርታ በጥንቃቄ በማስተዋል መወሰን እንዲሁም ትኩረታችንን ለአፍታ እንኳ ከጨዋታው ሒደት ማንሳት የለብንም ። ሀገራዊ ችግሮቻችንን በዚሁ እይታ ማንሰላሰል እንችላለን። ከጥናት መደርደሪያዎች ፣ ከልሒቃን ፣ ከፖሊሲ አመንጪዎች ፣ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ ከረጂ ሀገራት ፣ ወዘተ . ከቀረቡ የመፍትሔ ሃሳቦች የቱን ስበን የትኛውን እንደምንጥል፣ በየትኛው አሰካክ ለአሸናፊነት እንደምንበቃ በጥልቅ ማሰብ፣ መወሰን ግድ ይላል ።
የአገዛዞቻችን በትረ ሙሴ ከሰለሞን፣ ከሶቪየት ፣ ከአልባንያ በጭፍን ፣ በጨበጣ የተወሰደ ነው። ይሁንና ዛሬም በምንከተለው ፖለቲካዊ አይዶሎጂ መግባባት አልቻልንም ። የኢኮኖሚያችን ሌማት ከፊውዳል፣ ከዕዝ ፣ ከቅይጥ ፣ “ ከልማታዊ መንግስት “ ፣ ከነፃ ገበያ ፣ ወዘተ ቀላውጠናል። ሆኖም ከችጋር አዙሪት አልወጣንም። ሀገር በቀል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲን ማንበር ላይ ገና አልተቃረብንም። የኑሮ ውድነቱን ፣ ስራ አጥነቱን ፣ ግሽበቱን ፣ የተቆለለብንን የእዳ ጫና ፣ ወዘተ . ያጤኑአል። ከፍ ሲል ለመግለፅ እንደሞከርሁት ኢኮኖሚያዊ ችግር ፣ ቀውስ ባለበት ተገድቦ አይቆምም ። ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ከፍ ሲልም ወደ ደህንነትና ፀጥታ ችግርነት ፣ ቀውስነት ይባባሳል።
ወደ ለውጥ ኃይሉ ስንመጣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ከፍ ሲልም የፀጥታና የሕግ የበላይነት ችግሮችን በአንድ ላይ ለመፍታት መንቀሳቀሱ ትኩረቱን በታትኖታል። ጊዜውን ፣ ጉልበቱን ፣ ሀብቱን አባክኖታል። ስለሆነም በኢኮኖሚው (በጆከሩ ) ላይ ማተኮር ፣ መረባረብ አልቻለም። ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማለትም የኑሮ ውድነቱ፣ ስራ አጥነቱ ፣ ግሽበቱ ፣ ከትልቅ መንግስትነት ወደ ትንሽ መንግስትነት ማለትም መንግስት ኢኮኖሚውን ለገበያውና ለዜጋው ትቶ እሱ ድንበር ፣ የሕግ የበላይነት ፣ መልካም አስተዳደር ፣ ወዘተ . ሲያተኩር ዜጋው መሰረታዊ ፍላጎቱን አሟልቶ በሂደት ጥሪት ፣ ሀብት ሲያፈራ ፣ ተስፋ ሲሰንቅ ወዘተ . በሂደት ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ያቀለዋል ።
ተስፋ ከሰነቀ ፣ ስራ ካለው ፣ በኑሮ ውድነትና በዋጋ ግሽበት ከማይማረር ፣ በየሰዓቱ በሚያሻቅብ የሸቀጥ ዋጋ ከማይራቆት ፣ የትርፍ ህዳግ ከተቀመጠለት እንደ አሽዋ ከበዛ ቀማኛ ደላላ ከተላቀቀ ፣ ስለሚበላውም ሆነ ለልጆቹ ምሳ ስለመቋጠር ወዘተ . ሀሳብ ጭንቀት ከሌለበት እንዲሁም ከ5/11 ስሌት የተላቀቀ ሲቭል ሰረቫንት መፍጠር ከተቻለ ቁጭ ብሎ በተረጋጋ ሁኔታ ስለሰላም ፣ ስለፍቅር፣ ስለእርቅ ፣ ስለይቅርታ ፣ ስለዴሞክራሲ ፣ ስለፖለቲካ፣ ወዘተ . ቢወራ መደማመጥ መቀባበል ይቻላል። ከዚህ በላይ ኢኮኖሚው በማንነት ፣ በዘውግ ፖለቲካ ፣ በሴራ ተረክ ተከፋፍሎ የሚገኘውን ዜጋ ድልድይ ሆኖ የማቀራረብ፣ የመገናኘት አቅም አለው ። የሚፈጠር የስራ ዕድል ፣ የኑሮ ውድነት መቀነስ ፣ የፍላጎትና አቅርቦት መጣጣም ፣ ወዘተ . በሂደት የሚመጣ ፍትሐዊ ብልፅግና የሚፈጥረው ነፃ ምህዳር ስለፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች ቁጭ ብሎ በሰከነ አእምሮ ለመነጋገር እድል ይፈጥራል።
ኢኮኖሚው ብሔር ፣ ማንነት ፣ ዘውግ የለውም። የኦሮሞውም ፣ የአማራውም ፣ የወላይታውም ፣ ወዘተ የጋራ ወኪል ፣ የጋራ አካፋይ ነው። የጋራ ችግር ነው። ኢኮኖሚው እንደ ጆከር ዘር ፣ ማንነት ሳይለይ ሁሉንም ወክሎ ሊያጫውት ይችላል። የአንድነት ሆነ የንኡስ ብሔር ኃይላትን ሊወክል ይችላል። የሊበራል ዴሞክራቱንም ሆነ ሶሻል ዴሞክራቱን አልያም “ አብዮታዊ ዴሞክራቱን “ ያለ ልዩነት ይወክላል። ኦዴፓን ፣ አዴፓን ፣ ደኢህዴንን ፣ ህወሀትን ሆነ አዜማን ፣ ኦነግን ፣ አብንን ፣ ኦፌኮን ፣ ወዘተ ከፍ ሲልም ሀገርን ሕዝብን ያለ ልዩነት ይወክላል።
አዎ ! በዚህ ወሳኝ ሰዓት የሀገራችንን ዜጎች ለአንድነት ፣ ለእርቅ ፣ ለመነጋገር ፣ ለመቀባበል ፣ ለሰላም የሚያቀራርብ ለጊዜው (ታክቲካዊ) እና እጃችን ላይ የቀረን ካርድ ኢኮኖሚውና አኮኖሚው ብቻ ነው ። ምንከተለው ፖለቲካዊ ሥርዓት በማንነት ላይ የተመሰረተው ፌዴራሊዝም ይሁን በግለሰብ መብትና ነፃነት የተዋቀረው ሊበራል ዴሞክራሲ ወይስ ራሱን ሶስተኛ አማራጭ ብሎ የሚጠራ ይሁን ኢኮኖሚው ሁሉን ወክሎ ማጫወት፣ መጫወት ይችላል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደስልጣን ከመምጣቱ ኢኮኖሚውን ወደለየለት ቀውስ ከመግባት የታደገ የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል። ከመድሃኒት እና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ግዥ ውጭ ከሶስት ወር በላይ የማይዘለውን የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ በማሳደግ ኢኮኖሚውን ከኮማ ተላቆ እስትንፋስ እንዲዘራ ተደርጓል። እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ችግር በጥናት በመለየትም ከውድቀት መታደግ ተችሏል።
በማስከተልም በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግብረ ኃይልም ቀጣይ ስራዎችን እያጠና ይገኛል። ይሁንና የኢኮኖሚው ችግር ትናንት የተፈጠረ ሳይሆን የበርካታ ዓመታት የተዛባ የአመራርና የፖሊሲ ችግሮች ድምር ውጤት ስለሆነ ከተዘፈቀበት መዋቅራዊና ተቋማዊ አረንቋ በቀላሉ ይወጣል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም ሀገሪቱ በታሪኳ አይታው የማታውቅ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ ወድቃለች።
ይሄው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ብዛት ዕድገት፤ ከአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ፤ ከምርታማነት ባለበት መርገጥ ፤ ከንግድ ሥርዓቱ መረን የለሽነት ፤ ከገበያ ሥርዓቱ የተራዘመ ሰንሰለት ፤ ከሕገ ወጥ ድለላ ወዘተ . ጋር አብሮ፣ አድሞ ኢኮኖሚውን ፅኑ ታማሚ አድርጎታል። በዚህ የተነሳ የኑሮ ውድነቱ በሰዓታት ፣ በቀናት ልዩነት ጣራ እየነካ ነው። የብር የመግዛት አቅም በብርሃን ፍጥነት በሚባል ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው። የስራ አጡ ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል። የእነዚህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሁሉ ድምር ቅርሻት የሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ እንደ ሰኔ ዝናብ መጣሁ መጣሁ እያለ ሰማዩም እያጉረመረመ ነው።
እስካሁን እዚህም እዚያም ያስተዋልናቸው ግጭቶች ለዓመታት ሲቀነቀን ከኖረው የልዩነት ተረክ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን ተከትለው የተከሰቱ ማህበራዊ ቀውሶች ለመሆናቸው ሞራ ገላጭ መሆን አይጠይቅም። የተሳሳተው ፖለቲካዊ አመራር ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎናል። ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ማህበራዊ መፍረክረክን አስከትሏል። መላ ካልተበጀለት በዚህ ይቆማል ተብሎ አይጠበቅም። ወደለየለት የፀጥታ ፣ የደህንነት ስጋት ሊሸጋገር ይችላል። ይህ ከመሆኑ በፊት ከገጠመን ምስቅልቅል በጊዜ ለመውጣት መስራት አለብን ። ከዚህ ለመውጣት ደግሞ ዜጋው ፣ መንግስት ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ከፖለቲካው ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ በአንድነት ሊረባረቡ ይገባል።
እንደመላ
ዛሬ ለምንገኝበት ፖለቲካዊ ቀውስም ሆነ ማህበራዊ መፍረክረክ ትናንት ለነበርንበት አጠቃላይ አበሳ መንስኤው ፍትሐዊ ያልነበረው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ነው። የተወሰነ ቡድን ከነጭፍራው ብቻውን ዘግቶ የበላበት ስግብግብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ። በዚህ ላይ የኢኮኖሚ ምንጩን ሁሉ በመዳፉ ጠቅልሎ ከዘይት ፣ ከስኳር አቅርቦት እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መያዙ ዛሬ ድረስ ለምንገኝበት የገነገነ ሙስና ዳርጎናል ።
ሕዝቡ በማያባራ ድህነት ፣ ችጋር ፣ እርዛት ፣ ወዘተ . ፍዳውን እየከፈለ ቢሊዮኖችን እያፈሰሰ ለእስያና ምዕራባውያን ባለጠጋዎች የኢንዱስትሪ ፓርክ ይገነባል። ቢሊዮኖችን እያዘረፈ ፣ ቢሊዮን ዶላሮችን ከሀገር እያሸሸ ሕዝቡን በችጋር እየጠበሰ ሀገሪቱ ደመወዝ ለመጨመር አቅም የላትም እያለ ያፌዛል። በተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ወላጅ ለልጁ ምሳ እንዳይቋጥር ፣ ደብተር እንዳይገዛ ፣ ዩኒፎርም እንዳያሰፋ አድርጎ ሲያበቃ የትምህርት ቤት የምገባ ሥርዓት ዘርጊ ፣ ዩኒፎርም አሰፊ ፣ ደብተር ገዥ ሆኖ ብቅ በማለት ያላግጣል ። ሁሉን አውቅልሀለሁ ይላል። መሬት በካሬ ሜትር እስከ 300 ሺህ ብር እየቸበቸበ የመሬት ዋጋ እንዳይቀመስ አድርጎ በዚህ በኩል ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤት ይገነባል።
በአንድ በኩል ሀገራችን አቅም እንደሌላት ከዜጎቿ የምትፈልግበት እንጂ ለዜጎች የምትሰጥበት ጊዜ አይደለም እያሉ እንደሜቴክ ፣ ስኳር ኮረርፖሬሽን ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፣ ወዘተ . ባሉ ተቋማት በመቶ ቢሊዮኖችን ለብክነት መዳረግ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ከመሆኑ ባሻገር ሀገሪቱ አቅም የላትም የሚለውን ወለፈንዲ አባባል ውሃ እንዳያነሳ ያደርገዋል። በአጠቃላይ ባለፉት 27 አመታት የተከተልነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሕዝብን ለከፋ ድህነት የዳረገ ጥቂቶችን ሚሊየነር ፣ ቢሊዮነር ያደረገ ስለመሆኑ ብዙ የሚያከራክር አይደለም ።
የለውጥ ኃይሉ ከዚህ የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስር ነቀል ሊባል በሚችል ደረጃ የሚለይ አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊስን ስለመንደፍ ማሰብ ያስፈልገዋል። ላለፉት በርካታ ዓመታት ተመዘገበ የተባለው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ እድገት የዜጎችን ሕይወት ካልለወጠ ፋይዳው፣ ትርጉሙ ምንድን ነው!? እውነት ለመናገር የለውጥ ኃይሉ ኢኮኖሚው ላይ እየተከተለ ያለው ከቀደመው ብዙ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም ። መንግስት ዛሬም ስኳር ፣ ዘይት ፣ ስንዴ ፣ ጤፍ ፣ ዘይት ፣ ስራ ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ፣ ወዘተ . ብቸኛ በሚባል ደረጃ አቅራቢነቱን ቀጥሏል ። በቀደሙት ዓመታት ይህ እንዳልተሳካ ዛሬም እንደማይሳካ ልብ ያለ አይመስልም።
ስለሆነም ኢኮኖሚው የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ የመሆን አቅም እንዳለው ተገንዝቦ ከአዙሪት መውጣት ያስፈልጋል። ኢኮኖሚውን ጠቅልሎ መያዝ ሙስናን ከማባባሱ ባሻገር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ከኪራይ ሰብሳቢነት ከአየር በአየር ንግድ እንዳይላቀቅ አድርጎታል ። መንግስት በሂደት ከጠቅላይነት ስለመውጣት በማሰብ መንገዱን አበክሮ ሊተልም ይገባል ። ክልሎች መዋቅራዊ የሆነውን ኢኮኖሚያዊ ችግር በተናጠል ለመፍታት የሚያደርጉት ያልተቀናጀ ጥረትንም ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለዜጋው ለገበያው ስለመተው ማሰብ ያስፈልጋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ሕገ ወጥ የንግድ አሰራሮችን ሥርዓት ማስያዝ ግድ ይላል። ከሁሉም በላይ ግን የቀጣዩ ምርጫ ቀዳሚ አጀንዳ ኢኮኖሚው ሊሆን ይገባል። ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ከተቀረፉ ፖለቲካዊ ቀውሶችንም ሆነ ማህበራዊ መፍረክረኮችን በቀጣይ ማስወገድ ስለሚቻል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25/ 2011