አዲስ አበባ ከተማ 100ኛ እና 125 ዓመት የልደት ሻማዋን ስትለኩስ ዕድል አግኝቼ እንደ ዶሮ ጫጩት ሰብስባ ስላቀፈቻቸው ጥንታዊና ዘመናዊያን ዥንጉርጉር ሰፈሮቿ አሰያየም ጥናት ብጤ ለማቅረብ ዕድል ማግኘቴን እንደታላቅ መታደል እቆጥረዋለሁ።በተለይም ለ125ኛ ዓመት ክብረ በዓሏ ከትምህርት ቤት ጓደኛዬ፣ ከማከብረው ወንድሜና ዛሬ በአፀደ ሥጋ ከተለየን ከዶ/ር ብቃለ ስዩም ጋር “የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ አመሠራረትና የአካባቢዎቿና የሠፈሮቿ አሰያየም” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የልደቷን መዘከሪያ ጥናት ስንሰራ ብዙ ተምሬያለሁ፤ ከብዙ ታሪካዊ እውነታዎች ጋርም ለመጋፈጥ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡
“የእኔ የግሌ ብቻ ካልሆንሽ!” ባይ “ጎረምሳ ትውልድ” በስተእርጅና ሊናጠቃት ስለሚሞክረው ስለዚህች ግራ ስለተጋባችውና ግራ እያጋባችን ስላለችው ስለአሳረኛዋና ስለአማላይዋ ባልቴት መዲናችን የሚሰማው፣ የሚወራውና የሚታማው ሁሉ እንደ ተጎለጎለ የሰነፍ ሴት ልቃቂት ውል አልባ ሆኖ ግራ የሚያጋባ ሆኖብናል።
የአህጉራችን የፖለቲካ መዲና፣ የዓለም ታላላቅ ጉዳዮች ከሚከወንባቸው፣ ከሚሰለቅባቸውና ከሚጋገርባቸው ከዓለማችን ሁለቱ ታላላቅ ከተሞች (ኒውዮርክና ጄኔቫ) ቀጥሎ ሦስተኛ ረድፍ ላይ የተሰነቀረችው ይህቺው የእኛይቱ ጉደኛ መዲና የውስጥ አሳሯ በዝቶ የውጭ ስሟ የገዘፈ ይመስላል።በተለይም ዛሬ በአሥራ ሶስተኛው ዓሠርት ዕድሜዋ ላይ፡፡
ስሟንና ክብሯን ቀጥፈንና ጠልፈን “በጓዳችን ውስጥ ካልሸሸግንሽ” እያልን እንደ ልጅነታችን በታሪክ ጢቢጢብ ልናቄላት የምንሞክረው የዛሬዎቹ “እኛዎች” ዕድሜውን ቢያድለንና የዚያ ሰው ቢለን ከአንድ ሁለት አሠርት ዓመታት በኋላ በሚከበረው የ150ኛ ዓመት ክብረ በዓሏና ስለ አቆራቆሯ ማን በድፍረት ወይ በእውነት አሊያም በስክነት ምን ይዘት ያለው የታሪክ ማስረጃ እያቀረበ ለሙግትና ለክርክር አለያም ለሰላምና ለፍቅር አደባባይ እንደሚወጣ መመልከቱ ያስናፍቃል።ያድርሰና!
እስከዚያው ድረስ ግን የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች የሰከነና የተፈተሸ የታሪክ ማስረጃ እያቀረቡ ድፍርሱ እንዲጠል ከመወያየትና ከመደማመጥ ይልቅ ለምን በጋሻ ጦር እንደሚማማሉ ለሰሚው ግራ ሆኗል።“ ያልታደልሽ እንደምን አደርሽ ” እያልን ነጋ ጠባ “በጠብ ያለሽ በዳቦ” ከመጯጯህና ከመንጫጫት ይልቅ በሰከነና ማስተዋል በታከለበት ውይይትና ንግግር ከታሪካዊ እውነታ መድረሱ በእጅጉ የተሻለ ይሆናል።
ለማንኛውም በጠነነ ጥናት የጋዜጣ ዓምዶችን ማጨናነቅ የሙያው ሥነ ምግባር ስለማይፈቅድ ብቻ ቀደም ሲል ከጓደኛዬ ከዶ/ር ብቃለ ስዩም ጋር ካጠናነው ጥናት ላይ ቆንጥሬ ለመንደርደሪያና ለማሰላሰያ እንዲረዳ ገር ገር ሃሳቦችንና አጠቃላይ ዳሰሳዎችን ለመፈነጣጠቅ እሞክራለሁ።
በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሰበብ ሕዝብ ተሰባስቦ እርስ በርሱ በሚያካሂደው መስተጋብር ሰፊ የሕዝብ ክምችት ስለሚፈጠር በትንሽ ሰፈርነት የተቆረቆሩ ቦታዎች በጊዜ ሂደት ወደቅድመ ከተማነት (Town) ከዚያም ቀስ በቀስ ወደከተማነትና (City) ብሎም ወደዘመናዊ ልዕለ ከተማነት (Metropolis) ያድጋሉ።እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች የሚመሰረቱ ከተሞች እያደር ሰፊ የሕዝብ ክምችት በመያዝ አንዳንዶቹ የንግድ፣ አንዳንዶቹ የጥበብ፣ አንዳንዶች ደግሞ የፖለቲካ ወዘተ… ማዕከላት ወደ መሆን ይሸጋገራሉ።ንባብዎትን ቆም ያደረጉና ባለ መቶ ሰላሳ ዕድሜዋ አዲስ አበባ ከሦስቱ የዕድገት ደረጃዎች ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ከራስዎ ውሳኔ ጋር ይሟገቱ፡፡
“አለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣
የለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፤” በማለት አምላኩን በአያዎ እንደሞገተው ባለሀገር አዲስ አበባንም በዚሁ ሥነ ቃል ተመሳስሎ፤
“ቅድመ ከተማዬ ብዬ እንዳልጠራሽ፣
ኒዮርክን ያስንቃል ሌሊትሽ ሲጫጫስ፡፡
ልዕለ ከተማ ብዬ እንዳላደንቅሽ፣
ጨርቆስና ቦሌ ዥንጉርጉር ነው መልክሽ፡፡” ይህን መሰሉ ስሜት ባጠላበት ግጥም ግራ መጋባታችንን ሳንሸማቀቅ ልናስረዳ ብንሞክር ስህተተኛ አንባልም፡፡
እንቀጥል ጎበዝ! አንዳንድ ከተሞች በትንሽ ሰፈርነት ተቆርቁረው በውስጣቸው በሚካሄድ ፈጣን እንቅስቃሴ ምክንያት በዘፈቀደ ሲያድጉና ሲስፋፉም ይስተዋላል።አንዳንዶችም ውስጣዊ እንቅስቃሴያቸው እየተዳከመ በመሄዱ እየከሰሙና እየፈረሱ መሄዳቸውን ከታሪክ መገንዘብ ይቻላል።አንዳንድ ከተሞች ደግሞ ከምንም በመነሳት በፈጣን ሁኔታ የማደግ ዕድል ይገጥማቸዋል።በዘመናዊ እቅድ የሚመሩና እድገታቸው በተገቢው አካሄድና ፍጥነት በመመራቱ ምክንያትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ ያለ እመርታ ያሳዩ የአለማችን ከተሞችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
የእውነታው መዥጎርጎር ይህንን ይምሰል እንጂ በየትኛውም መንገድ ተቆርቁሮና አድጎ የሚታይ ከተማ በውስጡ ያሉትን ነዋሪዎች ከተለያየ ብሔርና ቋንቋ አሰባስቦና በልዩ ልዩ አሰፋፈር አደራጅቶ ማኖሩ ግን የተለመደ ነው።አካባቢዎች በመንደሮች፣ በጎዳናዎች፣ በአደባባዮች፣ በውስጥ ለውስጥ መገናኛና መተላለፊያ መንገዶች ወዘተ. ተከፋፍለው የነዋሪዎቹን ግንኙነትና አኗኗር ያስተሳስራሉ።የሰዎችን የእርስበርስ መስተጋብር፣ የሕዝቡን ማህበራዊ አደረጃጀት፣ የነዋሪዎች ልዩ ልዩ አገልግሎቶችም በእነዚሁ አሰፋፈሮቻቸው አማካኝነት ይሟላሉ።
መንደሮች፣ ጎዳናዎችና አደባባዮች በነዋሪው ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳቢያም የተለያዩ ስያሜዎች ይሰጣቸዋል።ነዋሪዎቻቸው በተለያየ መንገድ ስያሜአቸውን ያፀደቁላቸው እነዚህ አካባቢዎች በበኩላቸው ስለነዋሪዎቻቸው አያሌ መረጃዎችን ይሰጣሉ።ከእነዚህን መሰል የአካባቢ ስያሜዎች በመነሳትም ስብጥሩ የተዥጎረጎረው የማኅበረሰብ አባላት የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ፣ የእርስበርስ መስተጋብሩን፣ ታሪኩን፣ ሥነ ልቦናውን ወዘተ. ለመረዳት አይከብድም።
ስለዚህም የአካባቢ ስያሜዎች የነዋሪዎቻቸውን አድራሻ ከመጠቆም ባሻገር ላቅ ያለ ፋይዳ አላቸው የሚባለውም ስለዚሁ ነው።ልብ ይባልልኝ! አዲስ አበባን በታሪክ ጥፊ ወዲያና ወዲህ እያላጋን የምናስለቅሳት ይህንን መሠረታዊ እውነታ ጨፍልቀን ይሆን እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡
የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ሊቃውንት የአካባቢ ስያሜዎች ላይ የጥናትና የምርምር ትኩረት የሚያደርጉት አለምክንያት አይደለም።የአካባቢዎቹ ስያሜዎች በውስጣቸው ሰፊ መረጃ ስላላቸውና የማኅበረሰቡን መሰባሰብና ነባር የእውቀት ክምችቶች የመያዝ አቅማቸው ከፍ ያለ ስለሆነ በጥንቃቄ የሚታይ ነው።
በመሆኑም በልዩ ልዩ የምርምር ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሊቃውንት ከየጥናታቸው ዘርፍ አኳያ የአካባቢዎችን ስያሜዎች በመሰብሰብ በውስጣቸው አምቀው ስለያዙት የመረጃ ሀብት ይመራመራሉ፤ አያሌ ቁምነገሮችን እየመዘዙ በማውጣትም የነዋሪዎቻቸውን እውነተኛ ገጽታ፣ በሰፊም ሆነ በጠባብ ጂኦግራፊያዊ ክልል ከሌሎች ጋር የነበሯቸውን ግንኙነቶች፣ በራሳቸውም ውስጥ የሚታዩትን ማኅበራዊ ትስስር፣ ታሪካቸውንና ሥነ ልቦናዊ አቋማቸውን ወዘተ. ይተነትናሉ፤ የደረሱበትንም ግንዛቤና ግኝት ለሌላው ያካፍላሉ፡፡
ወደ ተነሳንበት የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ እንመለስና በውስጧ የሚገኙትን የተለያዩ አካባቢዎችና ሠፈሮች እንዴት አደራጅታ ለመያዝ እንደቻለችና አካባቢዎቹም ስያሜዎቻቸውን እንዴት ሊያገኙ እንደቻሉ ቅንነት በታከለበት ምልከታ በማስተዋል ማጤን ቢቻል ብዙ እውነታ ሊፈነጥቅ ይችላል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ ዛሬ ዛሬ “አሮጊቷ አዲስ አበባን” እንደ ጨቅላ ሕጻን የጉዲፈቻ ማደጎ “የእኔና የኔዎች ብቻ” ካልሆነች ብሎ መሟገትና ዱላ መማዘዝ የደረስንበትን የንቃተ ህሊና ደረጃ ዝቅታ የሚያመለክት ካልሆነ በስተቀር ምንም ማለት አይቻልም።
እውነታውን ጫን ብለን ብናጤን በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በአብዛኞቹ የሀገራችን ክፍሎች ቀደምት ነገሥታት ዋና ማዕከሎቻቸውንና መናገሻ ከተማቸውን ይመሠርቱ የነበረው ወታደራዊ ኃይላቸውን ባሰፈሩበት አካባቢ አለያም አንዳች ዘመቻ ካካሄዱና ካሸነፉ በኋላ ከነሠራዊታቸውና ከነጓዛቸው የሚያርፉበትን ሥፍራ ከወታደራዊ ስትራቴጂ አኳያ ቅድሚያ በመስጠት ነበር፡፡
ገዥ ቦታዎችን በመለየትም ግራ ቀኙን፣ ዙሪያ ገባውን ለመቆጣጠር በሚያመች ተራራማ ወይም ኮረብታማ ሥፍራ ላይ ይሰፍራሉ።ይህንን ወታደራዊ ሰፈር ቀስ በቀስ የፖለቲካ ማዕከል በማድረግም መላ ግዛታቸውን መቆጣጠር የተለመደ አሠራራቸው ነበር።ብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች በከፍታ ቦታዎች ላይ ሊቆረቆሩ የቻሉበት ምክንያትም በዋነኛነት ይኸው ነበር።
ተራራማዎቹን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ከተሞች ለምሳሌ፤ ጎንደርን፣ አድዋን፣ እንጦጦን፣ መንቆረርን (ደብረ ማርቆስ)፣ ጎሬን ወዘተ… ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።ይህም የሚያመለክተው ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅድመ ከተሞች አመሠራረት ምክንያቱ በዋናነት የወታደራዊና የፖለቲካ ማዕከል መፍጠር ላይ ማተኮሩን ነው።የአዲስ አበባ ከተማም በአብዛኛው በአመሰራረቷ ይህንንው እውነታ መጋራቷ እውነት ነው።
የአሰፋፈር ድልድሉን በተመለከተም፤ በነገሥታቱ ቤቶችና አዳራሾች ዙሪያ ወታደራዊ መሪዎቻቸው ከነጭፍሮቻቸው ይሰፍራሉ።አስተዳደራዊና የዳኝነት ሥራዎች የሚከናወኑትም በእነዚሁ አካባቢዎች ነው።ተከትለውም ለሰፋሪው ሠራዊትና ነዋሪ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ ካህናትና ለወታደሮቹ አስፈላጊ የሆኑትን የጦር መሣሪያዎች የሚያመርቱ ባለሙያዎች እንዲሰፍሩ ይደረጋል።
ለልዩ ልዩ እለታዊ አገልግሎቶች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የሚያመርቱ የእጅ ባለሙያዎችም ይሰፍራሉ።ከእነዚህም መካከል፤ አናጺዎች፣ ሸማኔዎች፣ ለመጓጓዣ ዘዴዎቻቸው አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳቁሶች (ኮርቻ፣ እርካብ፣ ግላስ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን የፈረስና የበቅሎ እቃዎች) ያዘጋጁ የነበሩትን ባለሙያዎች መጥቀስ ይቻላል።
ቀስ በቀስም ለመኳንንቱ አልባሳት ሙካሽና ለወይዛዝርቱ ጌጣጌጥ የሚሠሩ የእደጥበብ ባለሙያዎች በአካባቢው መኖር ይጀምራሉ።ይህንን አሰፋፈር ተከትሎም በአካባቢው የሙያዎች መለያየት እየጎላ መሄድ ይጀምራል።ሰፈሮቹም የጥበብ፣ የባህል፣ የትምህርት፣ እንዲሁም የልዩ ልዩ ጉዳዮች ማዕከላት ወደመሆን ደረጃ ይደርሳሉ።
በተለይም ሃይማኖታዊ ተቋማት የተተከሉባቸው አካባቢዎች ፀጥታቸው የሚጠበቅ የሰላም ማዕከላት እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚደረግ እነዚህን መሰል አካባቢዎች አምልኮታዊ ሥርዓቶችን ለመፈጸምና ሰላም ፈላጊ ሕዝብም ማዕከላቱን ለመጠለያነት ለመገልገል መሰባሰብ ይጀምራል።ይህ በራሱ ለአካባቢዎቹ ወደ ቅድመ ከተማነት መለወጥ አንድ ዐቢይ ሚና ይጫወታል።እነዚህን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ትስስሮችና ተራክቦዎች የተነሳ የሕዝቡና የነዋሪው ብዛት ቁጥሩና ስብጥሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሄድ ይጀምራል።የአዲስ አበባም እውነታ ከዚህን መሰሉ ማሳያ የሚዛነፍ አይደልም፡፡
በኢትዮጵያ የከተሞች ምስረታ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካና ወታደራዊው ምክንያት ዋነኛው ባህርይ ይሁን እንጂ ኢኮኖሚያዊው ጉዳይም ምንም ሚና አልነበረውም ማለት አይደለም።ከተዘረዘሩት ታሪካዊ ሂደቶች ጎን ለጎን ሰፋሪው ኅብረተሰብ ምርቱን የሚለዋወጥበትና በዙሪያው ነዋሪ የሆኑ የገጠሩ ማኅበረሰብ አባላት ያመረቱትን ምርት የሚያቀርቡበት የመገበያያ ማዕከል መፈጠር ይጀምራል።በሀገራችን የንግድ ማዕከላት ሆነው የተመሠረቱ ጥቂት ቅድመ ከተሞች እንደነበሩም በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል።
እኒህን መሰል ቅድመ ከተሞች የልዩ ልዩ ምርቶች ልውውጥ ማዕከል ሆነው ከጀመሩ በኋላም መሸታና መዝናኛ ቤቶች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ።ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ ቁጥር እየተበራከተ መሄድ ይጀምራል።የሀብት መከማቸት ባህርይም በመጠኑ መታየትና እንደሁኔታውም የሰፈሮች ማደግና መስፋፋት ይከተላል።ሰፈሮቹ በዙሪያቸው ያሉትን ገጠሮች ማማከልና የተለያዩትን የገጠር አካባቢዎችም ማስተሳሰሩን ይቀጥላሉ።እንዲህ እንዲህ እያለ ነው የአዲስ አበባ ከተማነትም ጎልቶ የወጣው፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች በተጨማሪነት አንዳንድ አካባቢዎችና ሠፈሮች ዛሬም ድረስ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች የባዕድ ሀገሮችን ስሞች እንደያዙ ይገኛሉ።ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይ፣ ሩዋንዳ፣ አሜሪካን ግቢ፣ ጣሊያን ምሽግ፣ ጣሊያን ኤምባሲ፣ እንግሊዝ በር፣ ኮሪያ ሠፈር፣ ታይዋን፣ ዱባይ ተራ ወዘተ. እነዚህ ስሞች በአንድ አህጉር ውስጥ የሚገኙትን ሀገሮች ስሞች ብቻ ሳይሆን የዓለማችንን አህጉራት ማለትም፤ አፍሪካዊ፣ አውሮፓዊ፣ አሜሪካዊ፣ እስያዊ፣ አረባዊ ወዘተ. ስሞችን ይወክላሉ።ከዚህ ሁኔታ በመነሳት የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ከተማነት መፎከሪያ ማድረግም ይቻላል።
አዲስ አበባ ከተማ ግራና ቀኝ የውጥር ተይዛ “ካልነጠቅሁሽ” ባይ ሊበዛባት የቻለው ምክንያቱ ምናባልትም የምዕራቡ ዓለም የከተሞች አመሠራረትና እድገት ታሪክ የእርሷም ታሪክ ሆኖ ስለተደገመ ሳይሆን አይቀርም።እንዴታውን ላፍታታው።በብዙ ሀገራት ከተሞች በፍጥነትና ለሁሉም ተደራሽ በሆነ መልኩ በፍጥነት እንዲያድጉ ያስቻላቸው በዋናነት በገዥዎች እጅ የሀብት ክምችት፣ ማለትም ከፍተኛ ወረት (ካፒታል) ለመፈጠር በመቻሉና ሀብታቸውንም ለዕድገታቸው ማዋል በመቻላቸው እንደሆነ በርካታ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ የአገዛዝ ባህል ግን በየሥርዓተ መንግሥታቱ በትረ ስልጣን የጨበጡ መሪዎቻችን ዓውዳቸው በሚፈቅደው መሠረት የተገኘውን ሀብት ለራስ መቀራመት እንጂ ሀብትን በመቆጠብ የወረት ክምችት የመፍጠር ልምድ አልነበረም።ነገሥታት፣ ገዥዎች፣ ባለባቶች፣ መሣፍንት፣ መኳንንቶችም ሆኑ ዘመናዊ ነን የሚሉ መሪዎች ጭፍሮቻቸውን፣ አሽከሮቻቸውንና ወታደሮቻቸውን በየወቅቱ ግብር ማብላት፣ ለዝናና ለክብር ሲሉ መሸለምና መለገስ ወይንም የካድሬዎቻቸውንና የዘር ማንዘራቸውን ሕይወት መለወጥ እንጂ ለምዕራባውያን ከተሞች እድገት ዋናውን ሚና እንደተጫወተው ዓይነት ሀገራዊ የሀብት ክምችት የመፍጠር ጥረት ሲደረግ አይስተዋልም።እስከ ትናንት ያለው የመሪዎቻችን ታሪክ ገጽታም ይሄው ነው፡፡
በዚህም መንስዔነት ክብር፣ ዝናና ታይታ በመሻት በሚደረግ የሀብት ቅርምት ገዥዎች የህብረተሰቡን መደባዊ ክፍፍል ከማጠናከርና ወታደራዊ ኃይልን ከማጎልበት ውጭ ለከተማውና ለከተሜው እድገት መነሻ መሆን የነበረበትን የሀብት ክምችት የመፍጠር፤ የተፈጠረውንም ለሀገራዊ ጥቅም የማዋል ፍላጎቱ አልነበረም።በመሆኑም ኢኮኖሚ በዋና ሰበብነት በሚጠቀስበት በዚህን መሰሉ ጦስ የተነሳ ሕዝብ ስለሚማረርና የእኔ ከተማና ከተሜነት ምን ፋይዳ አለው ብሎ ስለሚያምጽ አብዮት መሰል አመጽ በመቀስቀስ በአደባባይና ውስጥ ለውስጥ አድማዎችን ማቀናበር ይጀምራል።
በውይይት ጠልሎ የሚወጣውን ታሪካዊ እውነታ ላለመቀበልም ጆሮውን ደፍኖ “ይዋጣልንና ከተማችንን ያሸነፈ ይውሰድ” ወደሚል ግትርነት ማምራት ይጀምራል።አዲስ አበባ ከተማችን ሆይ! በእውነት ይህ እውነታ እውነታሽም አይደል? ይበልጥ ሃሳቡ ይጎልብት ከተባለም ጸሐፊው በይደር ያቆያቸውን ዝርዝር የጥናቱን ክፍሎች በተከታታይ ከማስነበብ ወደ ኋላ አይልም። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25/ 2011