የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) በመጪው ዓመት ምርጫ መካሄድ ጉዳይ ቁርጠኛ አቋሙን ደጋግሞ አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንደሚከናወን ብቻ ሳይሆን ራሱም ዝግጅት ስለመጀመሩም ይፋ አድርጓል። የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ላይ ግልጽ አቋም ከወሰደበት ጉዳዮች አንዱ የመጪው ምርጫ ጉዳይ ነበር።
ሥራ አስፈጻሚው በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል። “ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫም ሕገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት 2012 ላይ የመካሄዱ አስፈላጊነት ላይ አቋም በመያዝ እንደ ድርጅትም እንደ መንግስትም ዝግጅት ይደረግ” ብሏል።
በአንጻሩ ቁጥራቸው ከ130 በላይ የዘለቁት የተቀናቃኝ ፓርቲዎች እስካሁን ስለምርጫው በተረጋጋ ሁኔታ እያሰቡ ስለመሆኑ ምንም የሚታይ ፍንጭ አለመኖሩ አነጋጋሪ ሆኗል። በተለመደው የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መጪውን ጊዜ እናስላው? ምን ያህል ጊዜ አለን?… ቢበዛ ስምንት ወር?
አዎ! የምርጫው የድምጽ መስጫ ዕለት በግንቦት ወር ይካሄዳል ቢባል የተወዳዳሪ ዕጩዎች ምዝገባ በታህሳስ ወር ቢበዛ በጥር ወር 2012 ዓ.ም መከናወኑ የግድ ነው። ይህ ጊዜ ደግሞ ከአሁን ጀምሮ ስናሰላው የቀረው ጊዜ ከአምስት ወራት የማይበልጥ ነው። በዚህ ስሌት መሠረት በመጪው ምርጫ የፓርቲዎች ተሳትፎ በትክክል የሚታወቀው እስከመጪው አራት እና አምስት ወራት ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
ስለመጪው ምርጫ ሲታሰብ ከፓርቲዎች በላይ የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ እና መንግሥት ዝግጅት ከቃል ያለፈ የቱን ያህል የተሳካና ተስፋ ሰጪ ነው ብሎ መጠየቅም ይገባል። ሰሞኑን የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ በደቡብ ኮርያ ጉብኝታቸው ወቅት ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ማለታቸው ተሰምቷል።
“ኢህአዴግ መጪውን ምርጫ የሚወዳደረው ተዋህዶ ነው።” የውህደት ውሳኔው አዲስ ነገር ባይሆንም በዚህ ፍጥነት ሊተገበር ስለመቃረቡ ሲነገር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በግሌ ይኸ የገዥው ፓርቲ ውሳኔ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሮብኛል። ኢህአዴግ ለመዋሃድ የሚያስችል ቁመና ላይ ነው ወይ የሚል ገራገር ጥያቄም በውስጤ ማጫሩን መደበቅ አልሻም።
ለምን እንዲህ ተሰማኝ?… ለዚህ ስሜቴ ገፊ ምክንያቶች አሉኝ።
አንዱና ዋናው የኢህአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች እንደ ቀድሞው ከአንድ መጽሐፍ የሚያነቡ አለመሆናቸው በሚታይ፣ በሚዳሰስ ደረጃ እየታየ መሆኑ አንድ ጉዳይ ነው። በውስጣቸው ያለው ልዩነት ወደመቃቃር ደረጃ ስለማደጉ አስረጂዎች አሉ። አንዱና ዋናው የኢህአዴግ መስራች አባል ድርጅት የሆነው ህወሓት አሁንም ከኩርፊያና ከቅሬታ ማጥ ውስጥ አለመውጣቱ ነው።
ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ሰሞኑን 38 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመቐለ ጉባኤ ጠርተው “ኢህአዴግ ከለውጥ ማግስት ጀምሮ የገጠመው ቀውስ የሕግ ጥሰት ነው” በማለት ራሳቸው በከፍተኛ አመራርነት የተወከሉበትን ድርጅት አብጠልጥለውታል። “… ባለፉት ጥቂት ዓመታት በታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የዜጎች መብቶች በአደባባይ ሲጣሱ የታየበት፣ ህዝቦች በነፃነት ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉበት፣ ሃብት ለማፍራት የተቸገሩበት፣ ለጥቃት የተጋለጡበትና የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ ወድቋል።
ይህም ለዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ጉስቁልናና የወደፊት ተስፋ ማጣት ምክንያት ሆኗል” ብለዋል። ዶክተር ደብረፅዮን ችግሩ በዚህ ከቀጠለ በአገሪቱ አንድነትና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ላይ የከፋ አደጋ እንደሚከተል ተንብየዋል። “ይህን ስጋትም ሁላችንም ተባብረን በመታገል ህዝቦቻችን የሚፈልጉትን ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማስፈን ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በብቃት መመከት አለብን” ማለታቸው ተዘግቧል።
ከዚህ ቀደምም ዶክተሩ የትግራይ ተወላጆችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሆን ተብሎ እየተፈጸመ ስለመሆኑ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረው ነበር።
“…ከለውጡ ችግሮች መካከል ለውጡ ኢሕአዴግን እንደ ፓርቲ ማግለሉ፣ የአመራሩ እውነታን መሸሽ፣ በየሥፍራው የታጠቁ ኃይሎች መበራከት፣ እንዲሁም ድሮም ጠንካራ ያልነበሩት ተቋማት ከለውጡ ወዲህ ይበልጥ መልፈስፈሳቸውን ፤ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ ለውጡ ፈተና ውስጥ የገባ ነው የሚል እምነት አለኝ።” ያሉት ደግሞ የህወሓት/ኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው።
የኢህአዴግ አመራሮች መሰል ቅሬታዎችና የሰሉ ትችቶች፤ አባል ፓርቲዎቹ በከፋ የእርስ በርስ አለመተማመን ወይም መጠራጠር ውስጥ እየቀዘፉ መሆኑን ጠቋሚዎች ናቸው። ኢህአዴግ በቅድሚያ በውስጡ የተፈጠረውን የእርስ በርስ መጠራጠር ማጥራት ሳይችል ስለውህደት ማሰቡ ከፈረሱ በፊት ጋሪውን የማስቀደም ያህል የሚሆነውም ለዚህ ነው። ምርጫው በቀሩት አጭር ጊዜያት እነዚህን የከባድ ሚዛን የልዩነት ሃሳቦች እልባት ሰጥቶ ወይንም አስታርቆ መቀጠል ይቻላል ወይ የሚለው ገና መልስ ያላገኘ ጉዳይ ነው። ወይንም አንዱ ሃሳብ አሸንፎ ለመውጣት ቀሪው ጊዜ በቂ ነው ወይ የሚለው እንዲሁ ተገማች አለመሆኑ ያሳስባል።
ይህም ሆኖ ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አሕመድ ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህን ጉዳይ ቀለል አድርገው ማየታቸው ያረጋጋቸው ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ነበር ያሉት። “የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ጋር ውህደትን በተመለከተ ጥናት ሲደረግበት እንደቆየ እና ወደፊትም ሰፋፊ ውይይቶች እንደሚካሄዱ፣ ከእህት ድርጅቶች ዘንድ ከውህደቱ በፊት መስተካከል አለባቸው በሚል የተነሱ ነጥቦች መኖራቸውን፤ ይህ ግን ውህደቱን መቀበል የማይፈልጉ ፓርቲዎች አሉ በሚል መውሰድ አይገባም።” የእሳቸው ንግግር በአጭሩ ከአንድ መጽሐፍ እያነበብን ነው የሚል ነው።
የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጉዳይ
በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 137 መድረሱ በቅርቡ በምርጫ ቦርድ በኩል ሲገለጽ ብዙዎች በመገረም አፋቸውን በመዳፋቸው ይዘዋል። ፓርቲዎቹ ቁጥራቸውን ለመቀነስ አንድ አስገዳጅ እና አንድ በፈቃደኝነት የሚተገበር ምርጫ ግን ከፊታቸው ተደቅኗል።
አንዱና ዋናው ጥቂት የማይባሉ ፓርቲዎች በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ሕግ ውስጥ የተካተተውና ከረቂቁ ጀምሮ ከፍተኛ ጩኸት ያሰሙበት ሕግ ሆኖ መጽደቁ ነው። እሱም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምስረታ ወቅት ለአገራዊ ፓርቲ 10 ሺህ የድጋፍ ፊርማ እና ለክልል ፓርቲ ምስረታ 4 ሺህ የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ በሕጉ ውስጥ በአስገዳጅነት መቀመጡ ነው።
ይህ ሕግ ለምን ተካተተ?
ምርጫ ቦርድ ስለሁኔታቸው ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። “የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው ከመፈለግ አንጻር፣ ከአገሪቷ ህዝብ ቁጥር አንጻር እንዲሁም የሚወክሉት ህዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማጥበቅ አንጻር 10 ሺህ እና 4 ሺ የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ ተደንግጓል። በአንዳንድ ፓርቲዎች የሚነሳው ቅሬታ አሁን ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር 10 ሺህ ሰው ማስፈረም አንችልም የሚለው ሃሳብ ይገኝበታል።
ሆኖም ይህ ሃሳቡ በቦርዱም ይሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በኩል ተቀባይነት አላገኘም። ቦርዱ ለዚህ ቅሬታ በሰጠው መልስ “ሃሳቡ ምንም እንኳን የሚያሳምን ቢመስልም መታወስ ያለበት ግን አንድ ሕግ ሲወጣ ለአንድ ዓመት ብቻ ተብሎ አለመሆኑን ነው። ሕግ የሚወጣው ለረጅም ጊዜ ከመሆኑ አንጻር የሕጉን መር በጊዜያዊ ሁኔታ ብቻ ማየት አይገባም” ብሏል።
ከምርጫ ቦርድ በተገኘ መረጃ መሠረት ቀደም ሲል በምስረታቸው ወቅት አሁን የቀረበውን መስፈርት አሟልተው የተመዘገቡ ፓርቲዎች ብዛት በሀገር አቀፍ ደረጃ 9፣ በክልል ደረጃ 16 ናቸው። እንግዲህ 112 ያህል ፓርቲዎች ይህን መስፈርት እንዳላሟሉ ይጠቁማል። በአዲሱ አዋጅ መሠረት ሁሉም ፓርቲዎች እንደገና መመዝገብ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው። ይህ ሒደት ለምርጫው ከቀሩት አጭር ጊዜያት አንጻር እንዴት እንደሚሳካ እስካሁን በውል የሚታወቅ ነገር የለም።
ሕዝቡስ?
የምገልጸው የግል ምልከታዬን ነው። ስለሕዝቡ ስሜት በድፍረት ለማውራት መጠነኛም ቢሆን ጥናት ማድረግ እንደሚገባ አልጠፋኝም። ግን እንደማንኛውም ሰው ቤተሰብ፣ ወዳጆች፣ ለመረጃ የቀረቡ የሙያ አጋሮች አሉኝ። ከምንም በላይ ሙያዬ በቀን ውስጥ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንድገናኝ፣ ሃሳብ እንድለዋወጥ ይረዳኛል። እናም ብዙ ሕዝብን ሊወክል የሚችል ሀሳብ እንዳለኝ ይሰማኛል።
ስለመጪው ምርጫ ጉዳይ ከጋዜጠኛ ጓደኞቼ ጋር በተደጋጋሚ አውርቻለሁ፤ ተከራክሬያለሁ። ብዙዎቹ ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ የሥነልቦና ዝግጅት በሕዝብ ውስጥ አለማየታቸው ሲበዛ ያሳስባቸዋል። ባለፉት ዓመታት ከተፈጠረው አገራዊ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ቀውሶች፣ አለመተማመኖች እንዲሁም በነጻነት ከክልል ክልል፣ ከከተማ ወደ ከተማ መዘዋወር ያልተቻለበትን አስቀያሚ የጸጥታ ችግር ምርጫውን ሊያደናቅፍ ይችላል ብለው ይሞግታሉ።
የጸጥታ ችግር በአስተማማኝ መልኩ ባልተቀረፈበት ሁኔታ እንደምን ምርጫ ማድረግ ይቻላል በሚል ብዙ አውግተናል። አንድ ወዳጄ አንድ ቀን የምርጫ ዓላማ ምንድነው ሲል ድንገተኛ ጥያቄ ወርወር አድርጎ ራሱ መልስ ወደመስጠት ገብቷል። የምርጫ ዓላማ ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ውክልና እና አመኔታ ያለው መሪዎችን/የሕዝብ ተወካዮችን ማስቀመጥ ነው። ሠላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ይህንን ታላቅ ዓላማ እንደምን ማሳካት ይቻላል የሚለው የጋራ ጥያቄያችን ሆኗል።
እናም የሕዝቡ ጥያቄ ከምርጫ ይልቅ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መሰራት እንዳለበት ጠቋሚ ነው። ጸጥታ በአስተማማኝ መልኩ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተአማኒ የሆነ ምርጫ ማሳካት እንደማይቻል ብዙ ወገኖች በሚገባ የተረዱት ይመስላል።
ስለምርጫ ቦርድ ዝግጅት ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
የምርጫ ዝግጅት ከበጀትና ከሎጀስቲክ አኳያ ብቻ የሚታይ አይደለም። በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የምርጫ ቦርድ ሁለንተናዊ ለውጥ የማድረግ ህልምን የሰነቀ ነው። ቦርዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በቅርቡ አቅርቦት የነበረው የ2012 ምርጫ ማስፈጸሚያ የሚውል የ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ነበር። ሆኖም በፓርላማው በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተቀባይነት ያገኘው 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብሩ ብቻ ነው።
ይህ በጀት ከእስከዛሬው ጋር ሲነጻጸር በአምስት እጥፍ ገደማ ሊያድግ የቻለው ቦርዱ የሕግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል፣ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ለግል ተወዳዳሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ነው። አምስቱ የቦርዱ አባላት ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች የመሆናቸው ጉዳይም ሌላው ምክንያት ነው።
በተጨማሪም የቀድሞዎቹን የምርጫ ኮሮጆዎች በግልጽ በሚያሳዩ ኮሮጆዎች ለመቀየርና በአንድ የምርጫ ጣቢያ አንድ የነበረውን የምርጫ ኮሮጆ ሁለት ለማድረግ በመታቀዱ፣ እያንዳንዱ የድምፅ መስጫ ወረቀት የደኅንነት መለያ ቁጥርና የተወዳዳሪ ምስልን የያዘ ሆኖ እንዲሠራ በመታቀዱ፣ የመራጮች ቁጥር በሕዝብ ቁጥር መሠረት በመሰላቱ፣ እንዲሁም ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመልና ለማሠልጠን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ እንደሆነ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።
የምርጫ በጀቱ ሲዘጋጅ የመራጮች ቁጥር 53 ነጥብ 9 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ መገመቱን ቦርዱ የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል 45 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕዝብ ለመራጭነት ይመዘገባል ተብሎ ይታሰባል።
በዚህም መሠረት በአንድ የምርጫ ጣቢያ በአማካይ 1 ሺ 500 መራጮች ይመዘገባሉ የሚል ግምት የተወሰደ ሲሆን፣ በጀቱ 41 ሺ 600 የምርጫ ጣቢያዎችን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱም ታውቋል።
ይህ ሰፊ ሥራ ግን በቦርዱ በኩል ከምርጫው አስቀድሞ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ቀሪው ጊዜ ይበቃል ወይ የሚለው ጥያቄ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖችን ሁሉ የሚያሳስብ ሆኗል።
አገራዊ ሠላምና አለመረጋጋቱ አሁን ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ወይንም እዚህም እዚያም ሞቅ በረድ የሚሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ባሉበት ሁኔታ የምርጫ ሒደቱን እንዴት መምራት ይቻላል የሚለው በቅጡ መታየት ያለበት ነው። ሌላው ቀርቶ የምርጫ ቁሳቀሶችን በሁሉም የገጠርና የከተማ አካባቢዎች በኮንቮይ አጅቦ ምርጫውን ማሳካት አዳጋች መሆኑን በተለይ የአሁኑ ቦርድ በሚገባ እንደሚረዳው አምናለሁ።
ተጨባጩ ሁኔታ ምንን ያሳያል?
ከሲዳማ እና ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የክልል ይገባናል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የደቡብ ክልል አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የጸጥታና ሠላም የማስከበር ሥራ በኮማንድ ፖስት እዝ ሥር ከዋለ ሰንበት ብሏል።
በጥር ወር 2011 በቤንሻንጉል እና በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭትና የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ዘረፋ በቁጥጥር ስር ያዋለው ይኸው ኮማንድ ፖስት ነው።
በኦሮሚያና በአማራ… በአንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁ ያለኮማንድ ፖስት እገዛ ወጥቶ መግባት የማይታሰብ ሆኗል። ከምንም በላይ በአሁኑ ወቅት እዚህም እዚያም በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በሚያሳዝን ደረጃ የህዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ የመውደቁን ጉዳይ ማስተባበል የሚቻል አልሆነም። በአንዳንድ ክልሎችን በአመራሮች ደረጃ ከእነሱ ፍላጎት ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ክልላቸው ድርስ እንዳይሉ ግልጽ ዛቻና ማስፈራሪያ በሚራመድበት በዚህ ወቅት፣ አራቱ የኢህአዴግ ፓርቲዎች በማዕከላዊነት መርህ ተገዥ ሆነው፣ ተባብረው አብረው መቆም በተሳናቸው በዚህ ወቅት፤ ስለመጪው ምርጫ ማሰብ ይቻላል ወይ የሚለው በጥልቀት የታየ አይመስልም።
ሌላው ቀርቶ በወታደራዊ ኃይል ወይንም እገዛ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ የሚለው በአግባቡ የመለሰ አካል ስለመኖሩ የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ መረጃ የለውም።
እነዚህ የሠላምና የጸጥታ መደፍረሶች ባሉበት ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አንቀሳቅሰው፣ ያለምንም ችግር በምርጫው መሳተፍ ይችላሉ ወይ የሚለውም እንዲሁ መልስ የሚሻ፤ ግን እስካሁን ከየትኛውም አካል ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።
እንደማጠቃለያ- ምን ይሻላል?
በገዥው ፖርቲ በኩል በሕገመንግሥቱ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ግልጽ አቋም መያዙ ትክክለኛ እና መሆንም የነበረበት ነው። ይህም ሆኖ በቀሪው ከአምስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በሁሉም የምርጫ ተዋንያኖች በኩል ያሉ ዝግጅቶች ተጠናቅቀው የምርጫውን መርሃግብር ማስኬድ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይቻላል ወይ የሚለው አሁንም በቅጡ ሊታይና ሊመረመር የሚገባው ወቅታዊ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ።
በተለይ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ሊከናወኑ ከታቀዱ ትላልቅ ሥራዎች መካከል ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችን የመመልመል፣ የማሰልጠን እንዲሁም የማሰማራት ሥራ ብቻውን በቀሪው ጊዜ ሊከናወን ይችላል ወይ የሚለው እንዲሁ ማጤኑ ካልተፈለገ የሐብት ብክነት እንዲሁም ከጥድፊያ ጋር ተያይዞ በሒደቱ ላይ ከሚነሳ የተአማኒነት ጥያቄ ያድናል።
በአጭሩ የምርጫውን ሒደት ከቀሪው ጊዜ አንጻር መርምሮና ገምግሞ፣ ባለድርሻ አካላት ተወያይተውበት ወቅታዊ ውሳኔ እንዲሰጡበት በማድረግ ረገድ በዋንኛነት ከገዥው ፓርቲ ሲቀጥልም ከሁሉም ያገባኛል ባይ አካላት የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል። (የጸሐፊው ማስታወሻ፡-ለዚህ ጹሑፍ ጥንቅር የፋና፣ የኢዜአ፣ የሪፖርተር እንዲሁም የምርጫ ቦርድ፣የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዜናና ዘገባዎችን በግብአትነት መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልጻለሁ።)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25/ 2011