
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበትን ቀን ይፋ ማድረጉን የፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፕሬት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለብሮድካስቲንግ ኮርፕሬቱ በላከው መግለጫ፤ ቀደም ብሎ ቦርዱ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የክልል ምክር ቤት በፃፈለት ደብዳቤ ያቀረበላቸውን ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቱን አረጋግጦ፤ የህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ቀን ህዳር 03 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚሆን አስታውቋል።
ቦርዱ ህዝበ ውሳኔው ያለበትን ሂደት አስመልክቶ ያወጣው ዝርዝር መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽምለት ጠይቋል።
በዚህም መሰረት የቦርዱ አመራሮች ከተሟሉለት በኋላ ባደረገው ውይይት የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፤ በሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ቦርዱን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማድረግ የሚገባቸውን ዝግጅቶች በዝርዝር አሳውቋል።።
በዚህም መሰረት ቦርዱ ለምክር ቤቱ በላከው ደብዳቤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሃዋሳ ከተማን አስመልክቶ የህዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልላዊ መንግስት መቋቋም የሚያረጋግጥ ቢሆንም ከተማዋን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብቶችና ግንኙነቶች፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎች የሚያስተናግዱበትን አሰራር ዘርግቶ ለቦርዱ በጽሁፍ እንዲያሳውቅ ጠይቋል።
የህዝበ ውሳኔው ጸጥታና ደህንነት ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌዴራል የክልል እና የዞኑ ፓሊስ በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች የስራ እቅድ አዘጋጅቶ ለቦርዱ እንዲያሳውቅ፤ በተጨማሪ የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ከህዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃን በተመለከተ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅ መጠየቁ እንደሚታወስም በመግለጫው ተመልክቷል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የክልል ምክር ቤት በበኩሉ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ምላሹን ለቦርዱ አቅርቧል።በምላሹም ክልሉ ካለበት ሁኔታና የስራ ጫና አንጻር የሲዳማ ዞን ክልላዊ መንግስት ሆኖ ቢቋቋም ከሃዋሳ ከተማ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ህጋዊ ማዕቀፍና እና በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች የብሔር ብሔረሰብ አባላት ስለሚኖራቸው የመብት ጥበቃ ጊዜ ወስዶ መወያየት እንደሚገባው፤ ህግ ማውጣት ድረስ የሚደርስ ስራ መሆኑን ህግ ማውጣት፣ ማርቀቅ፣ የህዝብ አስተያየት መሰብሰብ እንዲሁም ማጽደቅን የሚጨምር ስራ በመሆኑ፤ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ክልሉ በኮማንድ ፓስት ስር የሚተዳደር በመሆኑ የተጠቀሱት የአሰራርና የህግማዕቀፎችን የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለማቅረብ ተለዋጭ ጊዜ እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡንም መግለጫው አስታውሷል።
እንደመግለጫው፤ ቦርዱ የተለያዩ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ ምክር ቤቱ ምላሹን እስከ ነሃሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቅ በሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቋል።። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በነሃሴ 16 ቀን 2011 አ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ህዝበ ውሳኔው የሲዳማን ክልል መሆን ቢያረጋግጥ የሃዋሳ ከተማን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት ስለሚኖራቸው ግንኙነትና የሃብት ክፍፍል ህግ ለማውጣትና ህጋዊ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እንዲሁም በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰብ አባላትን ስለሚኖራቸው መብትና ጥበቃ ከህገ መንግስቱ በተጨማሪ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚያስፈልግ አሁን ማቅረብ እንደማይችል ገልጾ፤ ነገር ግን ከህዝበ ውሳኔው አስቀድሞ የህግ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎቹን በማጽደቅ እንደሚያቀርብ አረጋግጧል።
ቦርዱ ባደረገው ውይይትም አምስት ዋና ዋና ውሳኔዎች አስተላልፎ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁ ተጠቁሟል።። በዚሁ መሰረት፤ ቦርዱ ከነሃሴ 20 ቀን 2011 አ.ም እስከ ህዳር 10 ቀን 2012 ድረስ የሚቆይ የህዝበ ውሳኔውን የድርጊት መርሃ ግብር እና በጀት አዘጋጅቶ ለደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና ለሚመለከታቸው አካላት የላከ ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት የህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ቀን ህዳር 03 ቀን 2012 ዓ.ም ይሆናል ብሏል።
ቦርዱም በድርጊት መርሃ ግብሩ መሰረት፣ የባለድርሻ አካላትን ማስተባበር እና የአፈጻጸም ውይይት የማድረግ ስራውን ከነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ የሚያከናውን ሲሆን፤ ስምንት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ምርጫ አስፈጻሚዎችን በመልመል አንድ ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሁለት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን የማደራጀት፣ የህዝበ ውሳኔ መመሪያዎች የማውጣትና የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት የመሳሰሉትን ስራዎች የማከናወን ሥራውን እንደሚሰራ መግለጫው አመልክቷል።
ከመስከረም 07 ቀን 2012 አ.ም ጀምሮ የህዝበ ውሳኔውን ጸጥታና ደህንነት ጥበቃ የእቅድ ዝግጅት ለማከናወን ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከዞን የጸጥታ አካላት ጋር የጋራ እቅድ የማውጣት ውይይቶችን ያደርጋል የሚለው ይኸው መግለጫ፤ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሀዋሳን ከተማ የወደፊት ሁኔታ ፤የሀብት ክፍፍል እና የሌሎች ብሄረሰብ አባላትን የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ማዕቀፎችን የማውጣት ስራ እስከ መስከረም 22 ድረስ ማጠናቀቅ እንዳለበት ተጠቁሟል።
ባለድርሻ አካላትም በተሰናዳው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ሕዝበ ውሳኔው በታቀደለት ጊዜ እንዲከናወን የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ቦርዱ አሳስቧል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
ምህረት ሞገስ