
አዲስ አበባ፡- በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ ሚሮ ዶራ በተባለ አካባቢ ከሉሲ(ድንቅነሽ) እና ዝርያዋ ከሆነው አውስትራሎፒቴክስ አፋረንሲስ መካከል ያለውን ግንኙነት ከመላምት ባለፈ በበቂ ደረጃ ያረጋገጠ የሰው ቅሬተ አካል መገኘቱን ተመራማሪዎች አስታወቁ።
የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቱ መሪ ዶክተር ዮሐንስ ኃይለ ሥላሴ እንደተናገሩት፤ ይህ ግኝት አውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ በሚባል ከሚታወ ቀው የቀድሞ ሰው ዝርያ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ ሥለ ዝርያው ያልታወቁትን የፊትና የጭንቅላት ቅርጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየ ነው ብለዋል።
አውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ የሚባለው የቅድመ ሰው ዝርያ ይታወቅ የነበረው ከ4.2 ሚሊዮን እስከ 3.9 ሚሊዮን ዓመት ድረስ ሲሆን ይህ አምአርዲ (MRD) በመባል የሚታወቀው የራስ ቅል ዝርያው እስከ 3.8 ሚሊዮን ዓመት ድረስ እንደሆነ ያሳያል ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ እስከ አሁን ድረስ ከ3.9 እስከ 3.6 ሚሊዮን ዓመት ድረስ ምንም አይነት የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካል አልተገኘም የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ግኝት እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም፤ በመላምት ደረጃ እስከአሁን የነበረውን የአውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ ሉሲ(ድንቅነሽ) እና ዝርያዋ በሆነው አውስትራሎፒቴክስ አፋረንሲስ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በቂ በሚባል ደረጃ መልስ ያስገኘ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
የተገኘው የራስ ቅል እድሜ ሌላኛው የጥናቱ የትኩረት አካል መሆኑን የገለጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሙሉጌታ አለነ ናቸው። የቅሪተ አካሉ እድሜ እንዴት እንደተለካ ሲያብራሩም፤ ቅሪተ አካሉ ከተገኘበት የአለት አነባበሮዎች መካከል የተሰበሰቡት ናሙናዎች ዘመኑ ያፈራውን የእድሜ መለኪያ መሳሪያ በመጠቀምና ከሌሎች የሥነ-ምድራዊ መረጃዎች ጋር ተዳምሮ የቅሪተ አካሉ አስተማማኝ እድሜ 3.8 ሚሊዮን ዓመት እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ለሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ቅሪተ አካላት የተገኙባት በመሆኗ የሰው ዘር ምንጭ አስብሏታል፤” የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ በአፋር ክልልና በሌሎች የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ባሉት መካነ ቅርሶች የሚገኙ እስከ ስድስት ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያስቆጠሩ የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካላት ኢትዮጵያ በእርግጥም የሰው ዘር ምንጭነቷን በተደጋጋሚ ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በዓለም ላይ እስከአሁን ድረስ ከሚታወቁት ከሃያ የማያንሱ የቅድመ ሰው ዝርያ የምርምር ግኝቶች መካከል 13ቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙ የቅርስ እሴቶች መሆናቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
ሙሐመድ ሁሴን