‹‹እኔ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነኝ። ሁለት አክስቶች አሉኝ። አንደኛዋ የኦርቶዶክስ ሃይማት ተከታይ ስትሆን፤ ሁለተኛዋ ደግሞ ሙስሊም ናት። ሁላችንም በምንከተለው እምነቶች ሳቢያ ቤተሰባዊ ግንኙነታችን ሻክሮ አያውቅም። የገጠመን ችግር የለም። በየሃይማኖት በዓላቱ ሁላችንም የምንሰባሰብበት በመሆኑ ዝምድናችን የበለጠ ጠንክሯል፤›› የምትለው በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ የተወለደችው ወይዘሮ ወርቅነሽ ገብሬ ናት።
ወርቅነሽ አሁን የምትኖረው አዲስ አበባ ዓለም ባንክ አካባቢ ነው። እርሷ እንደምትገልጸው ጎረቤቶቿ እንደ አክስቶቿ የተለያየ እምነት የሚከተሉ ናቸው። በመሆኑም ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት መስተጋብር በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ ነው ትላለች።
በዓላት በመጡ ቁጥር የትኛውንም እምነት ተከታይ ጎረቤቶቿ በአንድ የማክበር የተለመደ አብሮነት እንዳላቸውም ትናገራለች። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ሃይማኖቶች ቢሆኑም ሁሉም እምነቶች በጎነትንና በፍቅር አብሮ መኖርን ስለሚሰብኩ ከልዩነቱ ይልቅ የጠነከረ አብሮ የመኖር ባህላችን ይጎላል ስትል ገልጻለች።
የወሎዋ መርሳ ከተማ ነዋሪው አርሶ አደር አህመድ አሊም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። ማህበረሰቡ ተዋድዶ በፍቅር ስለመኖር፣ ስለአብሮነትና አንድነት አስተማሪ አያስፈልገውም። አንድ ሰው ተወልዶ ባደገበት ቀዬ ይህን ባህሪ ተላብሶ ማደግ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም። ለጥያቄም አይቀርብም። ምክንያቱ በፍቅር አብሮ መኖር ደግሞ ማህበረሰባዊ ግዴታ ሆኖ ለረጅም ጊዜ የኖረና የተዋሃደ ባህል ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አስፍረዋል።
‹‹እኔ 57 ዓመት ሆኖኛል። ተወልጄ ባደግኩበትም ሆነ በየትኛውም አካባቢ ሰው ሙስሊም፣ ክርስቲያን ወይም የሌላ እምነት ተከታይ በመሆኑ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ወይም ሌላ ሆኖ በመፈጠሩ ለግጭት ሲዳረግ አይቼም ሰምቼም አላውቅም። የራሴ እህት ወንድሞች ሁለቱ ክርስቲያን ሦስቱ ደግሞ ሙስሊም ነን። አንድ ቀን በመካከላችን የሃይማኖት ልዩነቱ የችግር መነሻ ሆኖና አጨቃጭቆን አያውቅም›› ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
ይሄ በአንድ ቤት ብቻ የሆነና የተገደበ አይደለም። በእያንዳንዱ ሰው ቤት የዚህ ዓይነት ሞልቷል የሚሉት አርሶ አደሩ በኀዘን፣በደስታ፣በእድር፣በለቅሶ ተለያይቶ የሚውልና የሚያሳልፍ የለም። ‹‹ሠርግ ተጠርተህ ሂደህ አታውቅም? ሁለት ዳስ ነው የሚሠራው፤የክርስቲያን እና የሙስሊም። (ለእህትና ለወንድምህ እንደማለት ነው) ለየራሳቸው ለፍሪዳ ሰንጋ በሬ ይሰጣቸዋል። ከበሉና ከጠጡ በኋላ ጭፈራውን የሚያቀልጡት አብረው ነው። ይሄን ሕዝብ እንዴት አድርገህ ልትለየው ትችላለህ?›› ሲሉ ሃሳባቸውን በጥያቄ አዋዝተው ይናገራሉ።
‹‹እኔ በበኩሌ አሁን የምናየው እና የምንሰማው ግጭትም ሆነ መፈናቀል በተለያዩ እምነቶች መካከል እና በተለያዩ ብሔሮች መካከል አይመስለኝም። ያልተጋባና ያልተዋለደ ማን አለ? እንዴት ብሎ ነው እየተቧደነ ወንድም ወንድሙን በቢላ ሊወጋ የሚችለው? የዚህ ዓይነት ባህሪ ካለው ዕድሜ ልኩን ሰው ተዋድዶና ተከባብሮ እንዴት ሊኖር ቻለ?›› በማለት አርሶ አደሩ ተግባሩ በዚህ መልክ በሚያውቁት ማህበረሰብ የተከናወነ አለመሆኑን አፅንኦት ይሰጣሉ።
በወሎ ኩታበር ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ ለይላ ሁሴን እና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ካስዬ ሁሴን እህትና ወንድም ናቸው። ወይዘሮ ለይላ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ናቸው። መምህር ካስዬ ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነትን ይከተላሉ። ወይዘሮ ለይላ እንደሚሉት ‹‹የተለያየ እምነት እንደምንከተል ተሰምቶን አሊያም አስበነውና ተከራክረንበትም አናውቅም። ምን ያደርግልናል። እኔም ሙስሊም በመሆኔ የሚጠበቅብኝን ሃይማኖታዊ ተግባርና ግዴታዬን ያለማንም ከልካይ እተገብራለሁ። እንደውም የሰላት-የስግደት ሰዓት መድረሱን ብዙ ጊዜ ወንድሜ ያስታውሰኛል።›› ስትል ገልጻለች።
‹‹እሱም(ካስዬም) እምነቱ በሚያዘው መሰረት ሃይማኖታዊ ተግባሩን በነፃነት ይፈጽማል። መጥፎ ተግባርን የሚመክርና የሚያስተምር እምነት የለም።
የመሰለውን ሊከተልና ሊያመልክ ይችላል። ከብዙ ብሔር ዘመድ የሌለው እና ከብዙ ሃይማኖት እህት፣ወንድም አለያም ዘመድ የሌለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አታገኝም።›› የምትለው ወይዘሮ ለይላ በሀገራችን እነዚህን ልዩነቶች በምንም ታዓምር ተከባብሮ አብሮ ለመኖር ጠንቅ ሆነው አያውቁም። ወደፊትም አይሆኑም ብላለች።
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ካሳዬ ሁሴን በበኩላቸው ‹‹ከለይላም ሆነ ከሌሎች ቤተሰቦቼ ጋር በሃይማኖታችን ምክንያት እንዴት አንድ እንዳልሆን ልናስብ እንዴት እንችላለን? ማንም ሰው ሊያደርገው አይችልም።›› ሲሉ ይሞግታሉ። አክለውም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ልምዱ የሚያሳየው የራሱን እምነት አክብሮ እንደሚጠብቅ ሁሉ የሌላውንም እኩል ይጠብቃል። የተለያዩ ሰዎች ከተለያየ ብሔር መፈጠራቸውንም ያውቃል። እኔ ይሄ እንደኩነኔ ሲቆጠር አይቼ አላውቅም። እንደውም እምነቶችና እነዚህ መለያየቶች የመከባበርና የአንድነታችን ምንጮች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል።
‹‹ማህበረሰቡ በሃይማኖቱና በተፈጥሯዊ ማንነቱ ላይ የመጣን ነገር ፊት ለፊት ለመመከት ጽኑ እምነት እንዳለው ስለሚያውቁ በዚህ ሽፋን የተጎነጎነ ሴራ እየሸረቡ ማህበረሰቡ እንደተጋጨ በማስመሰል ዓላማቸውን የሚያስፈጽሙ አካላት ተበራክተዋል። የዚህ ዓይነት ለኔ ብቻ የሚል የተንኮል አስተሳሰብ መክሰም አለበት›› የሚሉት መምህር ካሳዬ ሕብረተሰቡ እነዚህን ግለሰቦች ነጥሎ ማጋለጥ አለበት ባይ ናቸው።
እንደ መምህር ካሳዬ ገለጻ መከባበርን፣አንድነትን እና በፍቅር አብሮ መኖርን የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተምረኝ አይልም። ይልቅስ ተምረናል የምንል አካላት እነዚህን የሞራል ልዕልና ማሳያዎች ከማህበረሰባችን ልንማር ይገባል። ሌላው አካልም በዚህ ውስጥ ገብቶ የነበሩና ተፈጥሯዊ የሆኑ ልዩነቶችን እንደ አዲስ በማንሳትና በማቀንቀን በፓርቲ፣በማህበር፣በቡድን ወዘተ ሰበብ እየተሰባሰበና እየተደራጀ መርዝ እንዲረጭና አገር እንዲያፈርስ መፍቀድ አይገባም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር፣ቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህር ወይዘሮ ሕይወት አበሩ እንዲገልጹት በሀገራችን የአብሮነት እሴቶቻችን እየቀነሱ ለመምጣታቸው ምንም ማስተባበያ አያስፈልግም። ምክንያቱ ደግሞ የምንከተለው አዳዲስ የአኗኗር ዘይቤዎች የቆየውን አብሮነት ሊሸረሽር ይችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ስንባል የራሳችን የሆነ ለየት ያለና አንድነትን የሚያጠናክር ባህልና ታሪክ ያለን ሰዎች ነን። እነዚህ መለያ ዓርማዎቻችን በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሱ መጥተዋል። ዘመን አመጣሹንና የውጪዎችን ባህል ከማድነቅም አልፎ በአኗኗራችን እየተከተልን መጥተናል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳመለከቱት የሃይማኖት ብዝሐነት ከታሪክም ቢሆን መልካም ተሞክሮ ይዞ የመጣ እንጂ ስጋት ሆኖ አያውቅም። ብዝሐነቱ ለአብሮነታችን መጠናከር የራሱን በጎ ነገር አበርክቶ አሁን ላለንበት ጊዜ አድርሶናል። ትልቁ ስጋት ግን ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ይህን እሴት ለአደጋ ማጋለጥ እንዳይኖር መከላከል ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2011
መሐመድ ሁሴን