እስካሁን ለመስመር ዝርጋታው ክፍያ አልተፈፀመም፤ ቢፈፀምም 18 ወራት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዋሽ – ኮምቦልቻ የባቡር
መስመር ግንባታን ማጠናቀቁን፤ ኤሌክትሪክ ከቀረበለትም ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ፤ ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ክፍያ እንዳልተፈፀመለት፤ አገልግሎቱን ለማቅረብም 18 ወራት እንደሚፈጅበት ገልጿል።
በኮርፖሬሽኑ የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም መሐመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የአዋሽ – ኮምቦልቻ
ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ከ99 በመቶ በላይ ተጠናቋል። በአሁኑ ወቅትም የኤሌክትሪክ አቅርቦት በመጠባበቅ ላይናቸው፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ለባቡር መስመሩ የሚያስፈልገውን የኤልክትሪክ ኃይል ካቀረበላቸው አገልግሎቱን ወዲያውኑ ማስጀመር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የቀረውን የፕሮጀክቱን የአንድ በመቶ ሥራ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ሲለቀቅ ሙከራ እየተደረገ የሚከናወን ነው ።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በሰጡት ምላሽ፤ ለአዋሽ – ኮምቦልቻ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ክፍያ እንዳልተፈፀመ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በዃላም ክፍያው ቢፈፀም አገልግሎቱን ለማቅረብም በአማካይ እስከ 18 ወራት ጊዜ ያስፈልገናል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚፈልጉ ተቋማት ቅድሚያ ክፍያ መፈፀም አለባቸው ያሉት አቶ ሞገስ፤ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ክፍያ እንዳልፈፀመና ተቋማቸውም ካለበት የብድር ጫና የተነሳ በራሱ ፋይናንስ ለኮርፖሬሽኑ መሰረተ ልማት ሊዘረጋ እንደማይችል አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ሞገስ ማብራሪያም፤ ለባቡር መስመር ዝርጋታው የሚያገለግሉ ሰባት የሃይል ማሰራጫ ቦታዎች ጥናት ተጠናቋል። መስመሮችንና የሃይል ማሰራጫ ገንብቶ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ በአማካይ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ይፈጃል። ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ክፍያ ከፈፀመ ግንባታው ይጀመራል፡፡
አቶ ሞገስ፤ ከዚህ ቀደም ተቋማቸው ለኮርፖሬሽኑ የመስመር ዝርጋታ ያወጣውን ፋይናንስ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ወደ ኮርፖሬሽኑ እያዞርን ነው። ለባቡር መሰረተ ልማት ፋይናንስ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት አይዘረጋም ብለዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ቻይናን በጎበኙበት ወቅት ከቻይናው ኤስ ጂ ሲ ሲ ኩባንያ ጋር ለኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ መሥመር ዝርጋታ የአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት መፈፀማቸው ይታወሳል። የአዋሽ፣ ኮምቦልቻ- ሐራ ገበያ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የዚህ ስምምንት አካል መሆኑ ተነግሯል፡፡
በተመሳሳይ የፕሮጀክቱ አካል የሆነውና 120 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የኮምቦልቻ – ሐራ ገበያ ግንባታ አፈፃፀም 70 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ