አዲስ አበባ፦ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ አንድ አገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን አዘጋጅቶ ሁሉም መሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት በዚህ መሰረት እንዲመሩ ማድረግ ይጠበቅበት እንደነበር ተገለፀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አልማው መንግሥቴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው አንድ አገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን አዘጋጅቶ የመሰረተ ልማት አቅራቢዎች በሙሉ በእርሱ እንዲመሩ ማድረግ ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ይህንን ማድረግ አልቻለም ብለዋል፡፡
ማስተር ፕላኑን ማዘጋጀት ያልቻለበት ዋናው ምክንያት ኤጀንሲ መሆኑ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ መሠረተ ልማት አቅራቢዎች ማስተር ፕላን እንዲያዘጋጁ ለማስገደድ እንደማያስችል ጠቁመዋል።
ባቡር የራሱ ማስተር ፕላን አለው። መንገዶች ባለሥልጣንም ማስተር ፕላን ለመባል የሚያበቃ ባይሆንም አለው፤ ሌሎቹ ግን በዚህ ደረጃ የሚጠቀስ የላቸውም፤ ወደፊት ሁሉም የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ መሠራት እንዳለበት አመልክተዋል።
ማስተር ፕላን የለም ብለን ዝም ብለን አልተቀመጥንም ያሉት ዳይሬክተሩ ‹‹በ2011 በጀት ዓመት ተቋማቱን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የጋራ ዕቅድ እንዲኖራቸው ተደርጓል። በዚህም የተቀናጀ ሥራ መሥራት ተችሏል። ግን አሁንም ማስተር ፕላኑ መዘጋጀት አለበት›› ብለዋል።
ዳይሬክተሩ “እንደ ዜጋ ካየነው ተቋማቱ ደንቡን በቀላሉ ሊያዘጋጁት አይችሉም፤ ምክንያቱም ማስተር ፕላኑ የተሟላ መረጃ ይፈልጋል፤ አሁን ላይ ደግሞ በየትኛውም ተቋም ያለ አመራርም ሆነ ባለሙያ የተሟላ መረጃ የለውም፤ ለምሳሌ ድሮ የቴሌ የመሬት ውስጥ መስመር የቱ ጋ እንዳለ የሚያውቅ የለም፤ ሌላውም እንደዚሁ ነው። በመሆኑም ሥራውን ለመሥራት የተደራጀ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል ።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
እፀገነት አክሊሉ