
አዲስ አበባ፡- የሠላም እንከንኖችን አስተውሎና አመዛዝኖ ማጥራትና ማራቅ እንደሚገባ የሠላም ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄርሜላ ሰለሞን በመጪው ጳጉሜ 2 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን የሠላም ቀን አስመልክቶ ትላንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት ከስድስቱ አገራዊ የመደመር ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የሠላም ቀን፤ ችግኝ መትከል ሠላምን የመትከል ተምሳሌት በመሆኑ “ሠላምን እንትከል” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ጠቅሰዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የችግኝ ተከላ መከናወኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤ አንድ ችግኝ በአንድ ጀንበር ወደ ዛፍነት እንደማይለወጥ ሁሉ በሀገር ደረጃ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የሰላም ናፍቆታችንን አፈር አስይዘን በየዕለቱ ልንከባከበው ይገባል ብለዋል፡፡
ሠላማችንን ለመመገብ የማይጠቅሙ እንከንና ጠጠሮችን አስተውሎና አመዛዝኖ ማጥራትና ማራቅ ይገባል ያሉት ወይዘሮ ሄርሜላ፤ የሰላም ቀኑ በመጪው መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከሚውለው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን አከባበር ጋር እንዲያያዝ ተደርጎ መቃኘቱን ተናግረዋል፡፡
መልከ ብዙ የሆነውን ሰላም በሀገር ደረጃ ማስጠበቅን ያሳስባል የተባለለት የሰላምን እንትከል መርሃ ግብር፤ ለልጆች፣ ለእኔ፣ ለቤተሰብ ሰላምን እተክላለሁ በሚሉ ሦስት ፕሮግራሞች የሚከበር ሲሆን ሁነቶቹ በቅደም ተከተል ነሐሴ 26፣ 30 እና ጳጉሜ 2 እንደሚከናወኑ ገልፀዋል፡፡
በተመረጡ ትምህርት ቤቶች፣ የጋራ መኖሪያዎች፣ የጤና ተቋማትና የዕፅዋት ማዕከላት የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ፕሮግራሞች በሦስቱም ዝግጅቶች እንደሚኖሩ የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ በዚህም ህፃናት፣ ቤተሰቦች እና መላው ሠላም ወዳድ ማህበረሰብ ተሳታፊ ይሆናል ብለዋል፡፡
የሠላም ውይይቶች፣ የእግር ጉዞ፣ ትርኢቶች፣ ጥናታዊ ፊልምና የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ፕሮግራሞች የዝግጅቶቹ አካል እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡
ክልሎች አውዱን በጠበቀ መልኩ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ የተገለፀ ሲሆን በውስጥ መፈናቀል ከቀያቸው ርቀው የነበሩና ተመልሰው ለተቋቋሙ ዜጎች የሰላም ደሴት በመከለል የሰላምን እንትከል አካል በመሆን ጥላ የሚሆኑ፣ የሚወያዩባቸውና የሚተጫጩባቸው ችግኞችን እንደሚተክሉም በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
የተመረጡ የመገናኛ ብዙሃን ተመልሰው የተቋቋሙ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉበትን ሁኔታ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዲያሳዩ የሚደረግ ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙሃን ሰላምን በማሰብና ስለ ሰላም በማውራት የሰላም ቃላትን ዘርቶ የማብቀል ሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ሠላምን ስለመትከል ያላቸውን ሐሳብና የሚያከናውኗቸውን ድርጊቶች “ሀሽታግ ሠላምን እንትከል” በማለት ለሠላም ያላቸውን ዋጋ እንዲያሳዩ፤ መላው ኢትዮጵያውያን በሁሉም የሠላም ቀን ክንውኖች በመሳተፍና ሠላምን በመጠበቅ አገራችንን እንድናስጠብቅ ሲል የሠላም ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
ድልነሳ ምንውየለት