አጋሮ፡- አርሶና አርብቶ አደሮች በኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው በመሥራታቸው ምርታማነታቸው እየጨመረ፤ ገቢያቸውም እያደገ በመምጣቱ የኑሮ ደረጃቸው እየተሻሻለ መሆኑ ተገለፀ፡፡
በጎማ ወረዳ የድሮሚና ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበር አባልና የጎማ ወረዳ የኅብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሁሴን አባሜጫ እንደተናገሩት፣ በማኅበራት የተደራጁት ቡና አምራች ገበሬዎች ከነጋዴዎች ብዝበዛ ተላቀው ቡናቸውን በቀጥታ ለማዕከላዊ ገበያ እና ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡበት ዕድል በመፈጠሩ ገቢያቸው ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ገበሬዎቹ እንደሚያቀርቡት የቡና መጠን በትርፍ ክፍፍል አማካኝነት አባላት ከ300 ብር እስከ 73ሺ ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ይህም በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣላቸው ይገኛል፡፡ በመጋቢት 2002 ዓ.ም በ114 አባላትና በ268ሺ 760 ብር ካፒታል የተመሰረተው ማኅበሩ፣ በአሁኑ ወቅት የአባላቱን ብዛት 327 አጠቃላይ ካፒታሉንም 42 ሚሊዮን 38ሺ 149 ብር ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የማኅበሩ አባል አርሶ አደር ስንታየሁ አቡሲማል ‹‹ከዚህ ቀደም ይህ ማህበር ከመቋቋሙ በፊት ተጠቃሚው እኛ ሳንሆን ነጋዴው ነበር፡፡ አሁን ግን በማኅበራችን አማካኝነት ቡናችንን ከበፊቱ በእጥፍ እየሸጥን ነው፡፡ ገቢያችን አድጓል፡፡ የተሻለ ኑሮ መኖር ጀምረናል፡፡ ከአባላቱ አልፈን ለአካባቢው ነዋሪም መንገድና ትምህርት ቤት አስገንብተናል›› ብለዋል፡፡
ማኅበራቱ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለነዋሪው ህይወት መሻሻል አስፈላጊ ለሆኑ መሰረተ ልማቶችና ማህበራዊ አገልግሎቶች መሟላትም ድጋፍ እያደረጉ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ከዚህ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የጎማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቶፊቅ ራያ በበኩላቸው፤ ወረዳዋ በቡና አብቃይነቷ የምትታወቅ ብትሆንም የገበያ ችግር በመኖሩ ቡና አምራች ገበሬው ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ጠቁመው፣ ‹‹ኅብረት ሥራ ማህበራት ከተቋቋሙ በኋላ ግን ችግሩ በመቀረፉ አርሶ አደሩ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል›› ብለዋል፡፡ ማኅበራቱ አርሶ አደሩን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረጋቸው ባሻገር የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና የመንገድ አገልግሎቶች ለአካባቢው ኅብረተሰብ እንዲዳረስ በማድረግ የመሰረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
በ36 የገጠር፣ በአምስት የከተማ እንዲሁም በ41 ቀበሌዎች የተዋቀረችውና 300 ሺ የሚጠጋ ነዋሪ እንዳላት የምትገመተው የጎማ ወረዳ 93ሺ ሄክታር ከሚደርሰው አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 42ሺ ሄክታር የሚሆነው በቡና የተሸፈነ ነው፡፡
በወረዳዋ 20 መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በቡና ማጠብና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፤ በዓመት እስከ 19ሺ 500 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ ይዘው የሚሠሩ ናቸው፡፡ በዚህም ወረዳዋ በተገባደደው የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት 17ሺ 500 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርባለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
ይበል ካሳ