አዲስ አበባ፡- አገሪቱ ለጀመረችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግቦች እንዳይሳካ እንቅፋት የሆኑ ከደንና ከደን ልማት ጋር የተያያዙ ቁልፍ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዝ ዘላቂ የደን ልማት አመራር ጥናት ውጤት ለውይይት ቀረበ፡፡
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የአካባቢና አየር ንብረት ምርምር ማዕከል ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ከወንዶ ገነት ደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ዘላቂ የደን ልማት አመራር የጥናት ውጤት አገሪቱ ለጀመረችው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እንቅፋት የሆኑ ከደንና ከደን ልማት ጋር የተያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብተው ተናግረዋል፡፡
አቶ አህመድ የደን ልማቱ ዘርፍ ለማህበረሰቡና አጠቃላይ ለአገሪቱ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ታስቦ የተካሄደ ጥናት መሆኑን ገልፀው ጥናቱ ከደን ጥበቃና ልማት፣ የደን ውጤቶችን ለገበያ ከማቅረብ፣ ከፖሊሲና የተቋማት አሠራር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዝ ዝርዝር ምክረ ሃሳቦች የተካተቱበት ሲሆን በጥናቱ ውጤት ላይ ከባለ ድርሻ አካላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የሚደረገው ውይይት የበለጠ ዳብሮ ለፖሊሲ አውጭዎች የሚቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በሚደረገው የልማት ጉዞ ከአካባቢና የአየር ንብረት ደህንነት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የአረንጓዴ ልማት የኢኮኖሚ ፖሊሲን ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗን አመላክተዋል፡፡
አቶ ከበደ የተቀመጠው ግብ ዕውን እንዲሆን ከመሬትና መሬት ነክ ከሆኑ የልማት ዘርፎች ጋር የተቆራኙ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መቅረፍና መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ በተለይም በደን ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የሚሠራው ሥራ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሚገባው የጠቆሙት አቶ ከበደ “በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በተጨባጭ መረጃ ተንተርሶ ለመፍታት የምርምር ተቋማት የሚሠሩት የጥናትና የምርምር ሥራ ፋይዳው የላቀ ነው” ብለዋል፡፡
የፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩትና ሌሎች አቻ የምርምር ተቋማት በመተባበር ያቀረቡት የጥናት ውጤት ከደን ልማትና አመራር ጋር የተያያዙ ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በአግባቡ ለመለየትና መፍትሔ ለማበጀት መንግሥትና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ድርሻቸውን አውቀው በኃላፊነት እንዲሠሩ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡
የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ተጠሪ ሚስ አኒካ ጃያዋርድና ድርጅታቸው በደኑ ዘርፍ ረጅም ጊዜ የካበተ ልምድ ያለው መሆኑን አስታውሰው፤ በኢትዮጵያም ከ1950ቹ ጀምሮ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ለዘርፉ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ የደን ልማት ዘርፉ አሳታፊ እንዲሆንና በተለይም የንግድ ደን ልማት እንዲያድግና ማህበረሰቡ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በዘርፉ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን በገንዘብ ከመደገፍ ባለፈ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ መሆኑንም ተጠሪዋ ተናግረዋል፡፡
ስዊድንና የስዊድን ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ደጋፊ መሆናቸውንና ሐምሌ 22 ቀን በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቀንም የስዊድን ኤምባሲ መቶ ችግኞችን አዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ መትከሉን ሚስ አኒካ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
ይበል ካሳ