አዲስ አበባ፡- ‹‹በእርቀ ሰላም ሥራው ድል ማስመዝገብ የሚቻለው ከራሳችን ጋር በምናደርገው ጦርነት ራሳችንን ማሸነፍ ስንችል ነው›› ሲሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ አስታወቁ፡፡ በየደረጃው ያሉ መሪዎች ኮከብ በመሆን ህዝቡን ሊመሩት እንደሚገባም ገለጹ፡፡
ምክትል ሰብሳቢዋ ሎሬት የትነበርሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የእርቀ ሰላም ሥራው የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ኩራቱንም ሆነ ‹‹እኔ ብቻ›› ማለትን መተው ይጠበቅበታል፤ራስን የመከላከል ሥራ በማቆም ከራስ ጋር በሚደረገው ጦርነት ውስጥ ራሱንም ማሸነፍ መቻል ይኖርበታል፡፡
‹‹ራስን በማሸነፍ እኔ ከአገሬ አንሳለሁ፤ የእኔ ኩራት ከአገሬ ኩራት አይበልጥም፤ ስለዚህ ለህዝቤና ለአገሬ ስል ዋጋ እክፍላለሁ፡፡›› ሊባል ይገባል ያሉት ምክትል ሰብሳቢዋ፣ራሱን ማሸነፍ የሚችል መሪ እንደሚያስፈልግ እና ከዚህ አኳያም በየደረጃው ያሉ መሪዎች ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም ደረጃ ላይ ያሉ መሪዎች እንደ መሪ በራሳቸው ላይ ያለውን ከፍ ያለ አመለካከት ‹‹አሸንፋለሁ›› ማለት እንዳለባቸው ተናግረው፣ ከዚህም አኳያ የኃይማኖት መሪዎች ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቃቸውም አመልክተዋል፡፡ ‹‹መሪ አሸንፌያለሁ እንጂ ተሸንፌያለሁ ሲል ሰምተን ስለማናውቅ ብዙም ስለማይጠበቅም ራሳቸውን አሸንፈውና ድል አድርገው በድያለሁ ከሚለው መስመር ለመቀላቀል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል::›› ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ሰብሳቢዋ ገለፃ፤ በይቅርታ ጠያቂነት ታላቅነቱን የሚያረጋግጥ መሪ ያስፈልጋል:: እንደነዚህ ዓይነት የአካባቢ፣ የጎሳ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ መሪዎች ሲኖሩ ህዝቡንም እየመሩ ማውጣት ይችላሉ:: ይህ ህዝብ መሪዎቹን ለመከተል ችግር የለበትም:: ኮከብ ግን ይፈልጋል፡፡ ህዝቡ ሰባሰገሎችን እንደ መራው ኮከብ ከፊት ሆኖ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚመራ ቁርጠኛ መሪ ይፈልጋል፤እሳቱንም ሆነ ውርጩን የሚጋፈጥለትንና ከእነርሱም የሚታደገውን መሪ ይፈልጋል፡፡
ምክትል ሰብሳቢዋ፣ ‹‹መሪዎቻችን አርዓያ ሊሆኑን ይገባል፤ እነሱ ተደማምጠው ችግሮችን ሲፈቱም ማየት ይኖርብናል፡፡ አንዳንዴ የሚነገር ውሳኔና የሚተገበር ውሳኔ ሲለያይ ህዝቡ ጥያቄ ያነሳልና የመሪዎች መልካምነት እዚህ ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ህዝቡ መሪውን ስለሚከተል ነው›› ብለዋል::
መሪ ሆኖ የተሾመው ሰው ለእርቅ የሚያበቁ ነገሮችን ማውራት ብቻ ሳይሆን ማድረግም ጭምር እንደሚጠበቅበት አስገንዝበው፣መሪው ለዚህም ዋጋም ጭምር በመክፈል መሥራት ሲጀምር ህዝቡ እንደሚከተለው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ አሻግሮ ማየት መቻል መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹የሚጠብቁን ውብ ገፀታዎች ብቻ አይደሉም፤የማናውቀውና ያላየነው የከፋ ነገርም ሊጠብቅን ይችላል፤ስለዚህ ከእይታችን አድማስ ባሻገር ማሰብ ያስፈልጋል፤ መሪነት ደግሞ ድፍረትን፣ ብስለትንና ብልሃትን ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነት መውሰድንም የግድ ይላል፡፡›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ምክትል ሰብሳቢዋ እንዳሉት፤የሰዎችን አመለካከት ለመቀየር በአንድ ጀምበር የሚሠራ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ተበዳይ ነኝ እንጂ እኔ በዳይ ነኝ አይልም፤እርቅ ውስጥ ለመግባት ተበድያለሁም በድያለሁም ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡በአንድ ፅንፍ ላይ ብቻ መቆም እርቅን አያመጣም፡፡ እርቅ የግል ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የጋራ ውሳኔ ነው፡፡ በጋራ እንደ አገር ወደፊት ለመሄድ እርቅ ያስፈልገናል ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡
‹‹መንግሥት እየሠራ ያለውና የሠራው ተቋማዊ አደረጃጀቱ ላይ ነው፡፡ አዋጅ አወጣ፤ በጀትም መደበ:: ይህ መንግሥት ማድረግ ከሚገባው አንዱ ነው፡፡ዜጎችን ይጠብቃል ተብሎም ስለሚታመን ደግሞ ከዚህም የበለጠ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሎሬቷ፣ እርቅ ካልተደረገ በጣም የከፋ ችግር ሊመጣ እንደሚችል ጠቅሰው፣ ‹‹እንደ አገር ለመቀጠል አይቻለንም ወደሚለው የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ መቻል አለብን፡፡›› በማለት ገልጸዋል፡፡ የሌሎችን ሐሳብ አለማዳመጥ ለእርቁ አለመሳካት የበኩሉን ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011
አስቴር ኤልያስ