በርካታ ላይቤሪያውያን «ንጉስ ጆርጅ» በሚል ቅፅል ስም ይጠሩታል። የአፍሪካው የነፃነት አባት የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ «የአፍሪካ ኩራት ሲሉ አሞካሽተውታል። በሞናኮ፤ በፓሪሴን ጄርሜን እንዲሁም በኤሲሚላን ከለቦች እግር ኳስ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ዓለምን አሳምኗል። አስጨብጭቧል።
በእግር ኳሱ መንደር ችሎታውም ‹‹አንተ ምርጡ ነህ›› ተብሎ እ ኤ አ በ1995 ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ባሎንዶር ክብርን ተቀዳጅቷል። ይህን ክብርም ከእርሱ ውጪ ማግኘት የቻለ አንድም አፍሪካዊ ተጫዋች የለም። ይህ ታላቅ ሰው ላይቤሪያዊው ጆርጅ ዊሃ ነው።
ከትውልድ መንደሩ ሞኖሮቪያ ካላራ ከተማ ተነስቶ በታላላቅ የአውሮፓ ሊጎችና በአህጉራዊ መድረኮች በእግር ኳስ ሜዳ ሀገሩን በበጎነት ያስጠራውና ህዝቡን ጮቤ ያስረገጠው ዊሃ፣ ይህን ተግባሩን በሌላ ሃላፊነት ለመድገም ወደ ፖለቲካው መንደር ከገባ ቆየት ብሏል።
ከዓመት በፊት በላይቤሪያ በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫም በአፍሪካ የመሪዎች ታሪክ ቀዳሚ ሴት ፕሬዚዳንት የሆኑትንና የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን በመተካት የአገሪቱ ፕሬዚደንት መሆን ችሏል።
ጆርጅ ዊሃ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ለመምራት ፕሬዚዳንት ሆኖ ቃለ መሃላውን በፈፀመበት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረገው ንግግር ሀገሪቱ ላሉባት ችግሮች ‹‹ፈጣን መፍትሄ›› አመጣለሁ ፣ላይቤሪያውያንን ወደሚያልሟቸው ግቦች ለማድረስ ፈጣን እርምጃዎችን እወስዳለሁ›› ሲል አስታውቋል።
በመንበረ ስልጣን ቆይታው ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ትልልቅ ጉዳዮች መካከልም ሙስናን መዋጋት፣ የመንግስት ሰራተኞች ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም ላይቤሪያ ለግሉ ዘርፍ በሯን ክፍት እንድታደርግ መስራት የሚሉት ይገኙበታል።
ባሳለፍነው አንድ ዓመትም ይህን ቃሉን ለመፈጸም ብዙ ጥሯል። ይሁንና ጥረቶቹ በሙሉ ፍሬያማ ሊሆኑለት አልቻሉም። ቀደም ሲል በእግር ኳስ ሜዳ የኩራት ምልክታቸውና ጮቤ አስረጋጫቸው ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት የመሰክሩ ላይቤሪውንም በፖለቲካ ሚናው እንደቀድሞው አልተደሰቱበትም።
ሙስና እና የኢኮኖሚ ድቀት የአገሪቱን ህዝብ ክፉኛ ከማማረር አልፎ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዲያሰማ አስገድዶታል። ‹‹ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከውድቀት መታደግ አልቻሉም፤ በአግባቡ ይምሩ ወይ ስልጣን ይልቀቁ ›› ሲሉም ተደምጠዋል።
በእርግጥም በዊሃ የፕሬዚዳንትነት ዘመን በላይቤሪያ ሙስና እና የኢኮኖሚ ድቀት ሊቀንስ አልቻለም። እንደ የዓለም ባንክ መረጃ ከላይቤሪያ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፤ አማካዩ የመንግስት ሰራተኛ ወርሃዊ ደመወዝም 125 የአሜሪካ ዶላር ብቻ ነው። የአገሪቱ እድገት ምጣኔ ከመሻሻል ይልቅ እያሽቆለቆለ ነው፤ የዋጋ ግሽበቱም ከ28 በመቶ በላይ ስለመድረሱ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ ያመላክታል።
በመጀመሪያ ዓመት የፕሬዚዳንትነት ቆይታው ከኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተዛመደ እንደ ወደቀ ዛፍ መጥረቢያ የበዛበት ዊሃም፣ ቀውሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት የወርሃዊ ደሞዝና ጥቅማጥቅሙን 25 በመቶ ለመቀነስ በማሳወቅ መስዋእትነት መክፈል ጀምሯል።
አብርሃም ዳርዮስ ዲሎን የመሳሰሉ የአገሪቱ የህግ ባለሙያዎችም ይከፈላቸው ከነበረው ወርሃዊ 15 ሺ የአሜሪካ ዶላር ደሞዝ 5 ሺ ብቻ እንዲከፈላቸው እና ቀሪው 10 ሺ ዶላር ለተመረጡበት ክልል ማህበረሰብ እድገት እንዲውል በመጠየቅ አገሪቱን ከኢኮኖሚ ቀውስ ለመታደግ የበኩላቸውን እርምጃ እስከ መውሰድ ደርሰዋል።
ዊሃ ደሞዙን በመቀነስ ብቻ ሳይወሰን ቢጨንቀው ቢጠበው አገሪቷ ካለችበት ውስብስብ ኢኖሚያዊ ቀውስ እንድትወጣ ዜጎች በእያንዳንዱ ቀን ለሁለት ሰዓታት ያህል ፈጣሪያቸውን እንዲማፀኑ እስከ መጠየቅ ደርሷል። ላይቤሪያውያን ምዕመናን ከዚህ በተጨማሪም በየወሩ አርብ ለአገራቸው መንግስትና ህዝብ ሙሉ ሌሊት ተግተው እንዲጸልዩ መልዕክት አስተላልፏል።
ፕሬዚዳንቱ ይህን መሰል አርአያነት ያለው ተግባር መፈፀሙ በአብዛኞች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል። ይሁንና ይህ አይነቱ ተግባር ብቻውን ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር ከቀውስ ሊታደጋት አልቻለም።
በርካቶችም አሜሪካ፣ ቻይናና ጃፓንን የመሳሰሉት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገራት ወደ እድገት ማማ የወጡት ጠንክረው በመስራትና ብዙ መስዋዕትነት በመክፈል ነው፣ እናም ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲሻሻል በትጋት መስራት ላይ ቢያተኩሩ ይሻላቸዋል እያሉ ናቸው። በተለይ ክፉኛ እየተንሰራፋ በመምጣት የአገሪቱ እድገት ዋና ነቀርሳ እንዲሁም የህዝቡም ምሬት መነሻ የሆነውን ሙስና እንዲታገሉ እየጠየቁ ናቸው።
በእርግጥም አገሪቱ በኢኮኖሚ ድቀት ክፉኛ ለመጎዳቷና ይህን ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ ለተቀሰቀሰው ምሬት፣ ለግል ጥቅማቸው የቆሙ፣ ስልጣንን ተገን በማድረግ በሀገር ሀብት ምዝበራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብና ባለስልጣናት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ከዓመት በፊት አገሪቱ በውጭ አገር ካሳተመቻቸው ገንዘቦች በአንድ ኮንቴነር ውስጥ የነበረ አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገባበት አለመታወቁም ለዚህ አንድ ማሳያ ሆኖ ይቀርባል። ይህን መሰል ዝርፊያ በሚፈፀምባት አገር ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረቡ ተግባር በጣም ደካማ መሆኑ ደግሞ ለአገሪቱ ህዝብ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኗል።
ምንም እንኳን ወደ አገሪቱ ማእከላዊ ባንክ መግባት ሲኖርበት በዚያው ጠፋ በተባለው ገንዘብ የተጠረጠሩ የአገሪቱ ባለስልጣናትና የባንክ ገዥዎች ከአገር እንዳይወጡ እገዳ ቢጣልባቸውም፣ ጠንካራ ምርመራ በማድረግ ተጠርጣሪዎቹን ለህግ የማቅረቡ ተግባር ደካማ በመሆኑ ገንዘቡን የበላው ጅብ ከአንድ ዓመት በኋላም አልጮኸም።
ሕዝቡም ይህን ያህል ገንዘብ መሰወሩን በማስረጃነት በመንተራስ ‹‹አገሪቱ ለህግ ተገዥ ባልሆኑ ወንበዴዎች ሀብቷ እየተዘረፈ፣ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ጥቅም የሚሰጡ መሰረተ ልማትና ተቋማት በሌላ በኩል አስታዋሽ አጥተዋል›› ሲሉም ያማርራሉ። መንግስታቸውም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከህዝብ ጉሮሮ የሚነጥቁ ቀበኞችን እንዲያድን እየጠየቁ ናቸው።
ይህን የአገሪቱን ህዝብ ተደጋጋሚ እሮሮ ያደመጠው የዊሃ መንግስትም ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አገሪቱ ማእከላዊ ባንክ መግባት ሲኖርበት በዚያው ጠፋ በተባለው ገንዘብ ተጠያቂ ናቸው ተብለው ከተጠረጠሩ መካከል አንዱ ስለመሆኑ የተነገረውና ከአገር እንዳይወጣ እግድ ተጥሎበት የነበረው የቀድሞዋ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ልጅ ቻርልስ ሰርሊፍን በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ቀደም ሲል የአገሪቱ ማእከላዊ ባንክ ምክትል ገዥ የነበረው ቻርልስ ሰርሊፍ እምጥ ይግባ ስምጥ በማይታወቀው ገንዘብ ዙሪያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ቢውልም ዋነኛ የተጠረጠረበት ወንጀል ግን በሕገ ወጥ መንገድ 16 ሚሊዮን ዶላር አትሟል የሚለው መሆኑ ታውቋል።
ግለሰቡ የአገሪቱን ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ በማተም ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም የተገለፀ ሲሆን፣ የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ሃላፊ ሳያማ ሲሬኒየስ ሴፈስ ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ቢውልም በጤና ችግር ምክንያት ተለቅቆ እንደነበር አመልክተዋል።
አሁን በግለሰቡ ላይ በድጋሚ የቀረበው ክስ በዋናነትም ቀደም ሲል ከወደብ ላይ የጠፋውን የአገሪቱን ገንዘብ ያተመው ኩባንያ ተጨማሪ 16 ሚሊዮን ዶላር እንዲያትም ጥያቄ በማቅረብ ውስጥ ተሳትፎ አድርጓል ከሚለው በተጓዳኝ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ የወንጀል ሴራና ማጭበርበር መፈጸም የሚሉ ክሶች እንደሚጠብቁት ታውቋል።
ይህን ተከትሎም አንዳንድ ላይቤሪያውያንም በመንግስታቸው ተግባር ደስተኛ መሆናቸውን ቢገለጹም ፣በርካታ ወገኖች ግን አሁንም ቢሆን በርካታ ወንጀለኛ ባለስልጣናት በመንግስት ተቋማት ውስጥ መሰግሰጋቸውን መጠቆማቸውን ቀጥለዋል። አገሪቱን ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማውጣት ሁነኛ የማሻሻያ ትግበራ ከማድረግ በተጓዳኝ የሕዝቡን አመኔታ ለመመለስ መዝባሪዎችን ለፍርድ ማቅረብ ለነገ የሚባል ስራ መሆን እንደሌለበት እየወተወቱ ይገኛሉ።
ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከመፈተን ባለፈ የመንግስትን የአመራር ብቃት ሳይቀር ለቅሬታ የዳረገውና የህዝብ አመኔታን ያሳጣው በመንግስት ባለስልጣናት የሚፈጸመው ሙስና መሆኑ ታውቋል። ለእዚህም የአገሪቱ ማእከላዊ ባንክ አሰራርና ቁጥጥር ደካማ መሆኑ ይጠቀሳል።
መንግስት በማእከላዊ ባንክ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተቋሙን አመራሮች ለማንሳት፣ አንዳንዶቹንም ከሶስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጡረታ ለማሰናበት መወሰኑን ኒውስ 24 ዘግቧል። ይህ እና ሌሎች እርምጃዎችም የላይቤሪያ መንግስትና የገንዘብ ቀበኞቿም ፊት ለፊት እየተፋጠጡነ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 21/2011
ታምራት ተስፋዬ