ኢትዮጵያውያን የበርካታ ባህል ባለቤቶች ነን፡፡ ከእነዚህ ባህሎች መካከል በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በስፋት የሚታወቀው ከዕርገት ጋር ተያይዞ የሚከበረው የልጃገረዶች ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓል መካከል የአሸንዳ፣ማሪያ፣ ዓይኒ ዋሪ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል አንዱ ነው፡፡
ይሄ የልጃገረዶች በዓል እንደየአካባቢዎቹ በተለያዩ ስያሜዎች ቢጠራም ተመሳሳይ ነው። በደማቅ ሁኔታ የሚከበረውም ከነሐሴ 16 ጀምሮ ሲሆን ልጃገረዶች በተለያዩ ጌጣጌጦች አግጠው፣ በባህላዊ አልባሳት አምረውና በወገባቸው ሸብ በሚያደርጉት የአሸንዳ ቄጤማ ደምቀው በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ይሄ በዓል በተለይ የልጃገረዶች በዓል በመሆኑ ሴቶች ያለ ማንም ከልካይ በራሳቸው ላይ ነጻነት አውጀው፤ በፍቅር እና በአንድነት ያከብሩታል። በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ትርዒት ታጅቦ በርካታ ዘመናትን ያሳለፈ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ባህሉን እንዲያውቁት ለማድረግም ከትግራይ እና ከአማራ ክልሎች ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ እንዲከበር ተደርጓል፡፡
ይሄን ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን በዓል በቀጣይ እንደ መስቀል፣ ፊቼ ጨምበላላና የገዳ ሥርዓት ሁሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርስነት ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ እንደሚሆን ትልቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል። ዓላማውም ሠላምን፣ አንድነትን፣ መደጋገፍንና መከባበርን በመስበክ በዓለም ላይ መሠረት ያላቸው ህዝቦች ሆነን እንድንታይ የሚረዱ የኩራታችን ምንጮች ናቸው፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የአሸንዳ በዓል በተከበረበት ወቅት በስፍራው በመገኘት «በበዓሉ ወቅት ለአካባቢው ሴቶች የሚሰጠው ክብር ለሁሉም የኢትዮጵያ ሴቶች በ365ቱ ቀናት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ውብ የሆኑ እሴቶቻችን የመነሻ ቀለምና ለዛቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር ውስጣዊ አንድነታችንን ከማጠናከር ባለፈ ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸውን እምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ከባለቤቶቹ ባለፈ ሌላውም ዓለም እንዲያውቃቸው ለማድረግ ሠፊ ሥራ መስራት ያስፈልጋል» ብለዋል፡፡
በዓሉ በቱሪዝም መስህብነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑም ሃይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫውን ጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ሰው ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካል አስፈላጊውን ስራ መስራት ይኖርበታል፡፡ በዓሉ የሰላም እና የፍቅር መገለጫ በመሆን ልጃገረዶች ባህሉን ጠብቀው እና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፤ እንዲሁም ስለ ፍቅር፣ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ አንድነታቸውን ጠብቀው መቀጠል ያስፈልጋል።
የአሸንዳ፣ ማሪያ፣ ዓይኒ ዋሪ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በተለይ ከባህላዊና ሀይማኖታዊ ጠቃሜታው ባሻገር ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቃሜታ ያለው በመሆኑ ለየአካባቢው ትውፊታዊ ሃብት ነው፡፡ ስለሆነም እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል። የሴቶችን በራስ መተማመን ከፍ ማድረጉም የበዓሉ ትልቁ ትሩፋት ሲሆን በህዝቦች መካከል በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ከማጎልበት አንጻር ሚናው ጉልህ ነው፡፡ እንዲሁም በዓሉ በትውልድ መካከል የታሪክ ቅብብሎሽ ለማጠናከርና ጥላቻን ለማስወገድ ትልቅ ጠቃሜታ አለው፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ባህሎች ውስጥ አንዱ የሆነው ይሄ በዓል ባህሉን ጠብቀው ላቆዩት አባቶችና እናቶች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ያሉንን ባህሎች ጠብቀን በማቆየትም ተጠቃሚ መሆን ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም ከፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥቶ በዓሉ የሴት ልጆች የእኩልነትና የነጻነት ቀን መሆኑን በመገንዘብ ታሪክ አጥፊ ሳይሆን ታሪክ አሻጋሪ መሆን ይጠበቅበታል። ይሄን የሰሜኑን የኢትዮጵያውያን ታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ እና የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በሚሰራው ስራም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ይሆናል። በባህል ዘርፍ ለውጥ የሚመጣው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን ህዝቦች በእንዲህ ዓይነቶቹ ባህላዊ እሴቶች ላይ አብሮነታቸውን ሲያጎሉ በመሆኑ ሁሉም ሊተባበር ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19/2011