የገዲቾ ብሄረሰብ በሰሜን ኦሞ ዞን ውስጥ ይኖራሉ ።ብሔረሰቡ አብዛኛውን ጊዜ ጋብቻ የሚመሠርተው በሽማግሌዎች አማካይነት በሚፈጸም ስምምነት ነው ።ከዚያ በፊት የገዲቾ ወጣቶችን በበለጠ ለጋብቻ የሚያስተዋውቃቸው “ዎንኖ” በመባል በሚታወቀው ባህላዊ መሪ በር ላይ የሚያደርጉት የምሽት ጨረቃ ጨዋታ ነው ።ልጃገረዶች ቀን እንጨት ሲለቅሙ ወንዶች ደግሞ ለከብቶቻቸው ሣር ሲያጭዱ ይውሉና ማታ ይሰበሰባሉ ።በተለይ ልጃገረዶች ወደ ጨዋታው የሚሄዱት የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን አበቦች በፀጉራቸው ላይ ሰክተውና አጋጊጠው ነው ።በገዲቾ ብሔረሰብ ሴት ልጅ በምትዳርበት ወቅት ጓደኞቿ የሚያወድሷትም በልጃገረድነቷ የተዋበችባቸውን የአበባ ቀለማት ዓይነቶች እየቆጠሩና እያነሱ ነው።
በምሽቱ ጨዋታ ወንዶቹ ትከሻ ለትከሻ ተያይዘው ሴቶቹ ደግሞ ከወንዶቹ መደዳና ፊት ለፊታቸው በመቆም እርስበርስ እየተሞጋገሱ ይጫወታሉ∷ ወንዶች በቀኝ እግራቸው መሬቱን እየረገጡ ልጃገረዶችን ያሞግሳሉ ።ሴቶችም ግጥም በመግጠም እያጨበጨቡ ይዘፍናሉ ።በዚህ ጊዜ ወንዱ ወደሚፈልጋት ሴት ፊት ለፊት ቆሞ ልቡን ወደ ደረቷ ያስጠጋና ይዘፍናል ።ልጅቱም የምትወድደው ከሆነ ዝም ትለዋለች ።ወንዱም ለፍቅረኛው “ፋፎ” የተባለና አራት ጥርስ ያለው የፀጉር ማበጠሪያ ይሰጣታል ።ሴቷ ደግሞ የጥርስ መፋቂያ በመስጠት ፍቅራቸውን ይገልጣሉ ።የማትወድደው ከሆነ ደግሞ በቡጢ ትነርተዋለች።
በጨዋታው ማሳረጊያ ልጃገረዶቹ የወንዶችን እግር ያጥባሉ ።ወጣቱ እግሩን ያጠበችውን ልጃገረድ ከወደዳትና ለጋብቻ መስማማቷን ካረጋገጠ ለቤተሰቡ ነግሮ ሽማግሌ ይልካል ።ሽማግሌዎች ወደ ሴቷ ቤተሰብ የሚመላለሱት ከ3-4 ጊዜ ያህል ነው ።በዚህ ምልልስ ወቅት የሴቷ ቤተሰብ ስለልጁ የጐሣ አቻነት፣ ስለጉብዝናውና ቁመናው ያጠናሉ ።ከዘመድ አዝማድ ጋር ተመካክረውም የጋብቻውን ጥያቄ በመጨረሻ ላይ ይቀበላሉ ።የሠርጉን ቀነ ቀጠሮ ከሽማግሌዎች ጋር በመመካከርም ይወስናሉ ።በብሔረሰቡ ሠርግ በማታና በቀን የሚፈጸም ተብሎ በሁለት ይከፈላል ።በማታ የሚፈጸመውን ሠርግ የሚመርጡት የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው ወገኖች ናቸው፤ የሁለቱ ሙሽሮች ቤተሰቦች በመጠነኛ ዝግጅት ዘመዶቻቸውን ይጋብዛሉ ።ሙሽራውም ከጓደኞቹ ጋር በጨለማ ወጥቶ ያለምንም ጭፈራ ሙሽሪትን ሹልክ አድርጐ በመውሰድ ትዳሩን ይመሠርታል ።ቀን ላይ በሚከናወነው በሁለተኛው የጋብቻ ዓይነት ከፍተኛ ዝግጅት ይደረጋል ።የልጁ ቤተሰብ ለሠርጉ የሚሆን እህል፣ ማር፣ ቅቤ፣ ከብት ያዘጋጃል ።የሴቷ ቤተሰብም ልጅቷ ይዛ የምትሄደውን ሰጦታ (ቅቤ፣ ገብስ ዱቄት) ያሰናዳሉ ።ሁለቱም ሙሽሮች በእኩያቸው አንዳንድ ሚዜ ይመርጣሉ ።የወንዱ ሚዜ ሠርጉ እስኪፈጸም ድረስ አቅሙ በፈቀደው መጠን የማስተባበርና የማስተናገድ ተግባሩን ይፈጽማል ።የሴቷ ሚዜም ሙሽራዋ አልባብ – አልባብ እንድትሸት ጥሩ መዓዛ ያለውን ዕጣንና እንጨት ታመጣና ከቅቤ ጋር ቀላቅላ ትቀባታለች ።
በሠርጉ ዕለት ማለዳ ላይ የልጁ አባትና ሽማግሌዎች የልጅቷን ጥሎሽ ይዘው ወደ ሙሽራዋ ቤት ይሄዱና ለአባቷ ያስረክባሉ ።በብሔረሰቡ ሦስት ዓይነት የጥሎሽ አሰጣጥ አለ∷ ይኸውም በደረጃ የተከፈለ ነው ።የመጀመሪያ ደረጃ ጥሎሽ በጥንቱ ባህል መሠረት 14 ጠገራ ብር ወይም ትልቅ ጊደር ነው ።ሁለተኛው ደግሞ 13 ጠገራ ብር ወይም መካከለኛ ጊደር ሲሆን፤ ሦስተኛው ጥሎሽ ደግሞ ሦስት ጠገራ ብር ወይም ትንሽ ጥጃ ነበር ።በአሁኑ ጊዜ ግን አሠራሩ ተለውጦ በደረጃ 140፣ 120 እና 60 ብር ሆኗል ።ሽማግሌዎች ጥሎሹን ሰጥተው ከተመለሱ በኋላ በእኩለ ቀን ላይ ሠርገኞች ወደ ሙሽራዋ ቤት ይሄዳሉ ።በዕለቱ የሠርገኞቹን ጉዞ የሚመራው የሙሽራው ቤተሰብ የሆነ ሽማግሌ ነው፤ የሚይዘው ዱላም (በትር) “ጫርፈራ” ተብሎ ይታወቃል ።ሽማግሌው ሲመራ ሙሽራውና ሚዜዎቹ እንደዚሁም ሠርገኞቹ እንደቅደም ተከተላቸው ይከተላሉ ።ሙሽራው በዕለቱ ከወገቡ በላይ ትልቅ ቡልኮ ይለብስና ከወገቡ በታች ደግሞ “ጐንፋ” የተባለ ባህላዊ የሸማ ሥራ ቁምጣ ይለብሳል ።ፀጉሩ እንዳይታይ ተደርጎ ብዙ ቅቤ ይቀባና ከግንባሩ ላይ “ከለቻ” የሚባል ባህላዊ የብረት ጌጥ ያደርጋል።
ከለቻው በጋሞ߹በኮንሶና በወላይታ ባህል እንደዘውድ የሚታይ ሲሆን፤ ሙሽራውና ሚዜው ተመሳሳይ በትር ይይዛሉ ።ሠርገኞችም በመንገድ ላይ ሙሽራዋን የሚያሞግስ ዘፈን እየዘፈኑ ከሙሽራዋ ቤት ሲደርሱ በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል ።ቦርዴም ይቀርብላቸዋል ።የልጅቱ አባት ወንድ ፍየል ይዞ ይቀርባል ።ሙሽራውም ተነሥቶ ፍየሉ አጠገብ ቁጢጥ ብሎ ከተቀመጠ በኋላ የፍየሉን እግሮች ይይዛል ።የሴቷ አባት ፍየሉን ይባርክና ደሙን በሸክላ በመያዝ በጣቱ ከደሙ ጠቅሶ የሙሽራውን ግንባር ይቀባል ።“በዚህ ደም ተዋድዳችሁና ተዋልዳችሁ ።ሀብት ንብረትም አፍርታችሁ በፍቅርና በደስታ ኑሩ” ብሎ ከመረቀ በኋላ ቀሪውን ደም ይዞ ወደ ቤት በመግባት ይህንኑ የምርቃት ቃላት እያነበነበና ከደሙ በጣቱ እየጠለቀ የሙሽራይቱን አንገት ሥር ይቀባል ።ይህም ደም የብሔረሰቡ የቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓት ነው ።ከዚህ በኋላ ሙሽራውና ሚዜው በመነሣትና ፊታቸውንም በነጠላ በመሸፈን እየዞሩ የሙሽራዋን ቤተሰቦች እግር ይሰማሉ ።የሙሽራዋ ቤተሰቦችም በተራቸው የሙሽራውንና የሚዜውን ጉንጮች ይስማሉ ።ይህ ከሙሽሪት ቤተሰቦች ጋር ለመዛመድና ለመቀላቀል ዓይነተኛ መግለጫ ነው።
ሙሽራዋን ለመውሰድ የመጡ ሠርገኞች ቦርዴ ከመጠጣት በስተቀር ምግብ አይቀርብላቸውም ።ቤትም አይገቡም ።የሚሸኙት ከውጪ ነው ።በዕለቱ ሙሽራዋ ከወገቧ በላይ ነጠላ ወይም ገቢ ትለብስና ከወገቧ በታች ደግሞ ከሸማ የሚሠራና “ቆሎ” የተባለ ባህላዊ ጨርቅ ታገለድማለች ።ጋቢው ወይም ነጠላው ፊቷን እንዲሸፍን በግንባሯ አቅጣጫ በክር ይያዛል ።የሴት ሚዜዎቿም ስሟን እያነሣሱ ይዘፍኑላታል ።ከቆይታ በኋላ ከልጅቱ ቤተሰብ ታላቅ የሆነ ሰው “ሙሽራዋን አውጧት” የሚል ትእዛዝ ሲሰጥ የተመረጡ ሁለት ጐረምሶች ተሸክመው ያወጧታል ።ሙሽራይቱ ከእናትና አባቷ ቤት ወጥታ ስትሄድ ከቆዳ ተሰፍቶ የተዘጋጀና “ኢቴ” የተባለ ባህላዊ ልብስ የሚሰጣት ሲሆን፤ የሚተኙበት ቁርበትና ዙሪያው በጌጣጌጥ ያሸበረቀ ትልቅ ቅልም ከእናቷ በስጦታ መልክ ይሰጣታል ።ታላቅ አሸኛኘትም ይደረግላታል ።
ሙሽራዋ በሚዜዎች ታዝላና በሠርገኞቹ ታጅባ በመጓዝ ከሙሽራው ቤት ሲደርሱ ዘመድ አዝማድ በጭፈራ ይቀበላቸውና ሙሽሮቹ “ጐሊ” ተብሎ ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ገብተው ይቀመጣሉ ።ከዚያም ከሙሽራው ወገን የሆኑ ሴቶች ልብሷን ያወልቁና ያስተኟታል ።ሠርገኞችም ከተጋበዙ በኋላ ወደየቤታቸው ይሄዳሉ ።በሁለተኛው ቀን የልጅቱ እናትና ሴት ቤተሰቦች ቅቤ፣ ወተትና ዱቄት ይዘው ወደሙሽራዋ ቤት ሲመጡ የሙሽራው ሴት ወገኖች ይቀበሏቸውና በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ ያስቀምጧቸዋል ።የሙሽራው አባት አቅሙ የፈቀደውን ያህል ዝግጅት አድርጐ ይጠብቃቸዋል ።የሙሽራው ሴት ወገኖችም የሙሽራዋን እናትና ተከታዮችዋን እግር ያጥባሉ ።ከዚያ በፊት “ከመታው ነገር ሙሉውን እንዳትቀምሺ” ብሎ ባሏ ካስጠነቀቃት የሙሽራዋ እናት እግርሽን ታጠቢ ስትባል “እምቢ አልታጠብም” ልትል ትችላለች ።ይህንንም እናት የምታደርገው ጥሎሽ ለልጅቱ በተሰጠ ጊዜ ያልተሟላ ነገር ካለ መሟላት እንዳለበትና ከዚህም ባሻገር በሁለቱ ተጋቢ ወገኖች መኻከል የቆየ ቂምና ቅሬታ ካለ በደንብ ይቅርታ መደረግ እንደሚያስፈልግ ለማመልከት ነው ።
የቀረው ጥሎሽ ከተሰጠና የቆየ ጠብ ካለ ይቅርታ ከተደራረጉ በኋላ እግሯን ትታጠባለች ።አብረዋት ከመጡ እንግዶች ጋርም ስትጋበዝ ታድራለች ።በነጋታው የሙሽራው ቤተሰቦች ብዙ ቂጣ ይጋግሩና እየቆረሱ ለሙሽራዋ እናትና ቤተሰቦች ይሰጣሉ ።የሙሽራዋ እናት ከተቆረሰው ቂጣ ለቀሩትና አብረዋት ላልመጡት ሴት ወገኖችዋ “የልጄን ሠርግ ቂጣ ቅመሱ” እያለች ትልካለች ።በሠርጉ ሦስተኛ ቀን የሚካሄደው ሥርዓት “አይን-ካይን” ይባላል ።ይህ ሙሽራው ከሙሽራዋ ቤተሰቦች ጋር የሚተዋወቅበት ዕለት ማለት ነው ።በዚህ ዕለት የሙሽራዋ ወገኖች ይዘው የመጡት ዱቄት፣ ቅቤና ወተት ተዘጋጅቶ ይበላል ።የአማቾች የስም ትውውቅም ይደረጋል ።ሙሽራው ከዚህ ዕለት ጀምሮ አማቾችን በስማቸው እንዳይጠራቸውም ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል ።ከዚህ ሥርዓት በኋላ የሙሽራዋ ቤተሰቦች ይሸኙና ሙሽራዋ በበኩሏ ከሙሽራው ቤተሰቦች ጋር ትተዋወቃለች ።ሁለቱ ሙሽሮች ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽሙት በዚሁ በሦስተኛው ቀን ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ሙሽራዋ ገላዋን ታጥባ ቅቤ ትቀባለች፣ መኝታም ተዘጋጅቶ ውኃ በገበቴ ይቀርባል፤ አለንጋም በሚታይ ቦታ ላይ ይቀመጣል።
ከተቀመጠው የገበቴ ውኃ እየጠለቀች እግሩን እንድታጥበው ሙሽራው ሙሽራዋን ይጠይቃል ።እምቢ ካለች በአለንጋ ትገረፋለች ።ከዚያም ሙሽራው ወደተዘጋጀላቸው መኝታ ላይ ይሆንና “ተነሽና ነይ እንተኛ” ብሎ ሙሽራዋን ይጠይቃል ።እምቢ ካለች አስገድዶና በአለንጋ ገርፎ ያስተኛታል ።ሙሽራዋ ክብረ ንጽሕና ከሌላት በአለንጋ እየገረፈ አስቀድሞ የደፈራትን ሰው ስም እንድትናገር ያደርጋል ።በነጋታውም ወደ ቤተሰቦችዋ ይልካታል ።አባቷም ልጁን የደፈራትን ሰው ይጠይቅና የሚያገባት ከሆነ የተበዳዩን ጥሎሽ ሰጥቶ እንዲወስዳት ያደርጋል ።የማያገባት ከሆነ ደግሞ የሙሽራው ፍላጐት ተጠይቆ ታናሽ እኅቷ ትሰጠዋለች ።ይህ ካልሆነ አባት የተቀበለውን ጥሎሽ በሽማግሌ ተጠይቆ እንዲመልስ ይደረጋል ።ክብረ ንጽሕና ካላት ደግሞ ሙሽራው ከመደሰቱ የተነሣ የደም ሸማ ለሚዜው ያሳያል፤ ይዘፈናል ።የሙሽራው የጫጉላ ጊዜም ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት ብቻ ሲሆን፤ የሴቷ ግን ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሊሆን ይችላል ።በጫጉላዋጊዜ ሙሽራዋ ገንፎ በቅቤ እየተሠራ ትመገባለች ።ልጃገረዶችም ለሙሽሮቹ የጥርስ መፋቂያ ስጦታ ያበረክቱላቸዋል ።ወንድ ወጣቶች ደግሞ በየምሽቱ ወደ ሙሽሮች ቤት በመምጣት በባህላዊ ዘፈን ይጨፍሩላቸዋል።
ሙሽራዋ የጫጉላ ጊዜዋን ጨርሳ ከኅብረተሰቡ ጋር ከመቀላቀሏ በፊት “ሆሌ ቢሲን” የሚባል የመቀላቀያ ሥርዓት ይደረግላታል ።ይኸውም ፍየል ታርዶ ቆዳው ከተገፈፈ በኋላ ከወደጭንቅላቱ በኩል ቁራጭ ቆዳ ተቆርጦ ከተተለተለ በኋላ ትልታዩ በሙሽራዋ አንገት ላይ ይጠለቃል ።ሙሽራዋም ትልታዩን በአንገቷ ላይ አድርጋና የሠርግ ጊዜ ልብሷን ለብሳ ወደ ቤተዘመዶችዋ በመሄድ ናፍቆቷን ስትገልጥ ውላ ሲመሽ ወደ ቤቷ ትመለሳለች ።በገዲቾ ባህል የሚስት ቤተሰቦች ደግሰው የልጃቸውን ባል ወይም አማች መልስ የመጥራት ልማድ የላቸውም።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር