አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ከኢዴፓ አፈን ግጠው በወጡ አራት አባላት የተሰጠውን የፓርቲው ንብረቶች ያለምንም ህጋዊ መሰረት እየተጠቀመ ስለሆነ ሊመልስልን ይገባል ሲል ኢዴፓ ጥሪ አቅርቧል፤ ኢዜማ በበኩሉ በህገወጥ መንገድ የያዝሁት ምንም ንብረት የለም ብሏል።
ከኢዴፓ አፈንግጠው የወጡ አራት ግለሰቦች በምርጫ ቦርድ ፍፁም ህገወጥ የሆነ ትብብር የፓርቲውን ፅህፈት ቤቶች፣ በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ፣ መዛግብትና ማህተም ያለአግባብ በህገወጥ መንገድ እንዲረከቡ ተደርጓል ያለው ኢዴፓ ግለሰቦቹ ኢዴፓ ከግንቦት 7 ጋር እንዲዋሀድ የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ እንደወሰነ አድርገው የሀሰት መረጃ በማቅረብ ንብረቶቹን በፓርቲዎች ውህደት ሳይሆን በግለሰቦች ስብስብ ለተቋቋመው ኢዜማ ማስረከባቸውን የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ጠቅሷል።
ኢዜማም ያለምንም ህጋዊ መሰ ረት እነዚህን የኢዴፓ ንብረቶች እየተጠ ቀመባቸው እንደሚገኝ የጠቀሰው ማእከላዊ ኮሚቴው በዚህ የተነሳ የእለት ከእለት ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን መቸገሩን ገልፆ ኢዜማ ግለሰቦቹ የፈፀሙትን የማጭበርበር ወንጀል ተረድቶ ንብረቶችን እንዲመልስ ጠይቋል።
‘‘ኢዴፓ ከመጀመሪያውም ቢሆን አ ልከሰመም’’ ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው ፓርቲው ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምንም አይነት እገዳ እንደሌለበትና ሥራውን መቀ ጠል እንደሚችል ከተገለፀለት በኋላ ልዩና አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዶ የሌላ ፓርቲ አባላት ሆነው በተገኙ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ አቶ አዳነ ታደሰን የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና ወይዘሪት ፅጌ ጥበቡን ደግሞ ም/ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾሙን አስታውቋል።
የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ፓርቲያቸው በህገወጥ መንገድ የያዘው ምንም ንብረት አለመኖሩን ገልፀው የኢዴፓን ቢሮ እየተጠቀመ ያለው ግን የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲውን ለማክሰም የያዘው ቃለ ጉባኤ ላይ ንብረቶቹን ለማን እንደሚያስረክብ ሲገልፅ አዲስ የሚመሰረተው ፓርቲ እንዲገለገልበት መወ ሰኑን ተከትሎ እንደሆነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልፀዋል።
በዚህ መሰረት የኢዴፓ አራት አባላት ኢዜማን ሲቀላቀሉ በቃለ ጉባኤው መሰረት ኢዜማ የኢዴፓን ቢሮ መጠቀሙ ህገወጥ ሊያስብለው የሚችል ምንም መሰረት የለም ያሉት አቶ ናትናኤል የኢዴፓን መክሰም በተመለከተ ኢዜማ የሚያውቀው ፓርቲው መክሰሙን ሲሆን የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ለምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥያቄ ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ / ኢሶዴፓ/ ስያሜ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማ ህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መወሰዱን የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መግለ ፃቸውን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል። በተመሳሳይ ዜና ኢዴፓ መጪው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ግፊት የሚያደርጉ ጥቂት ፓርቲዎች ግፊት በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም ያለ ሲሆን ለዚህም ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሊከናወኑ የሚገባቸው ሥራዎች አልተሰሩም ብሏል።
ሀገሪቱ በአስተማማኝ ሰላምና አለመ ረጋጋት ላይ አለመገኘቷ፣ መንግሥት ህግና ሥርዓትን ማስከበር አለመቻሉ፣ የህገ መንግሥትና የወሰን አከላለል ችግሮች ብሎም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚያስችል ዝግጁነት ላይ አለመገኘቱ ምርጫው እንዲራዘም ምክንያት እንደሚሆኑ ፓርቲው ገልፆ አን ዳንድ ፓርቲዎች ምርጫው እንዲካሄድ ግፊት የሚያደርጉት የቡድንና የስልጣን ጥቅማቸውን በማስቀደም ነው ብሏል።
ነገር ግን አገራዊ ኃላፊነት የማይሰማቸው የኮንፌዴሬሽን ኃይሎች አሸናፊ ሆነው ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ኢዴፓ በመላ ሀገሪቱ በቂ የምርጫ ተሳትፎ ሊያደርግ ስለማይችል አዲስ አበባ ከተማ ላይ በትኩረት ለመወዳደር ያቀደ ሲሆን እንደ ምርጫ 1997 የአዲስ አበባ ምክር ቤትን በድጋሚ አሸንፎ ለመረከብ የሚስችለውን ዝግጅት እንደሚያደርግ አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
ድልነሳ ምንውየለት