ዋግኽምራ (ኢቢሲ)፡- አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ቀድሞ በዳስ ትምህርት ሲሰጥበት የነበረውን ትምህርት ቤት አሰርቶ በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
አትሌት ኃይሌ በዋግ ኽምራ ፃግብጂ ወረዳ ላይ ያስገነባው ደረጃውን ጠብቆ የተሰራው የገልኩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ሦስት ወራት ብቻ ፈጅቷል ተብሏል። ደረጃቸውን የጠበቁ ስምንት የመማሪያ ክፍሎችን የያዘው ትምህርት ቤቱ፣ ለግንባታው አራት ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አትሌት ኃይሌ በምረቃው ላይ ተናግሯል ።
በአሁኑ ወቅት በዋግ ኽምራ ዞን 876 የዳስ ትምህርት የመማሪያ ክፍሎች እንደሚገኙም ኢቢሲ ዘግቧል። ሌሎች ባለሃብቶችና መንግስት ትብብር በማድረግ እነዚህን የዳስ የመማሪያ ክፍሎች ለመቀየር መስራት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፏል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው፤ በክልሉ 84 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ተናግረው፤ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የክልሉ መንግስት ከግሉ ባለሃብት ጋር በመሆን በትብብር ይሰራል።
139 ተማሪዎችን ያስተናግድ የነበረው ይኸው የቀድሞው የዳስ ትምህርት ቤት አሁን ላይ 350 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋልም ተብሏል። አዲስ ከዳስ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤትነት የተሸጋገረው ትምህርት ቤት “ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011