አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሰባት የአፍሪካ ሀገራት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ ።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የምርት ገበያው የዘረጋው ዘመናዊ አሰራር የበርካታ ሀገራትን ቀልብ በመሳቡ ልምዱንና ተሞክሮውን እንዲያካፍሉት ጥያቄ በቀረበለት መሰረት ለሰባት የአፍሪካ ሀገራት ስልጠናዎችን ሰጥቷል።
በስልጠናው የተሳተፉት ሀገራትም ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባ ብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ታንዛንያ ሲሆኑ በስልጠናውም የገበያ ተቆጣጣሪዎች፣ የአፍሪካ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ባንኮች፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ማህበራት፣ ተሳትፈዋል።
ለአፍሪካ ፋይናንስ ዘርፍ ላበረከተውም አስተዋጽኦ ከተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ማግኘቱን አቶ ነጻነት ነግረውናል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለብዙ ሀገራት የልህቀት ማዕከል መሆኑ በመታመኑ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲጎበኙት ቆይተዋል።እንደ አቶ ነጻነት ገለጻም ሀገራቱ ልምድና ተሞክሮን በመጋራታቸው የራሳቸውን የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት አስችሏቸዋል።
ይህን መነሻ በማድረግ በሀገራችን ሥርዓቱን ተቋማዊ ለማድረግ በተደረገው እንቅስቃሴም በአሁኑ ወቅት ደረጃውን የጠበቀ አካዳሚ ለመክፈት የሚያስችል ጥናት ተዘጋጅቶ ተጠናቋል። በማዕከሉ የምርምርና የልማት ሥራዎችን ጨምሮ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት የሚከወንበት አሰራር እንደሚዘረጋና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ሰልጣኞች የሚሆኑ ዘርፎችም እንደሚዘጋጁበት ተናግ ረዋል። አካዳሚው ዓለም አቀፍ ገበያውን እንዲወዳደር ሆኖ የሚገነባ ነው ያሉት አቶ ነጻነት ሰልጣኞች በሚያገኙት ዕውቀትም ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም የሚስ ችላቸውን አቅም እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
በ2012 የምርት ገበያው ያለውን አቅም አጠናክሮ በአካዳሚ ስም ሥራውን እንደ ሚጀምር ያስታወቁት አቶ ነጻነት በሥራውም ከፍተኛ ለውጥ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። ኃላፊው አያይዘውም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጣይ ዕቅዶቹ ለአርሶ አደሩ የምርት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚሰራ ሲሆን በዋነኛነትም ሃያ አራተኛ ቅርንጫፉን ቴፒ ላይ በመክፈት ሶስት ግዙፍ የምርት መቀበያ መጋዘኖችን ገንብቶ ጥጥን አስረኛው የገበያ ምርት ለማድረግ ማሰቡን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በ35 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር 788 ሺ 910 ቶን ምርት ለመገበያየት ዕቅድ መያዙን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በምርት መጋዘን ላይ የሚገኝ ምርትን መያዣ በማድረግ አርሶ አደሩ የአጭር ጊዜ ብድር የሚያገኝበት አሰራር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
የዓለም ገበያውን ለመቆጣጠር የምርት ጥራት ጉዳይ ወሳኝ ስለመሆኑ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ አርሶ አደሩ ይህን አውቆ በቴክኖሎጂ መረጃዎች ተጠቃሚ እንዲሆንና በዋጋ ረገድም በደላሎች ተጽዕኖ እንዳይበዘበዝ እንዲሁም ኮንትሮባንድ እንዳይስፋፋ የምርት ገበያው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኗል ብለዋል። ወቅታዊውን የማዕከላዊ ገበያ ዋጋ ለማሳወቅ እንግሊዝኛን ጨምሮ በኦሮምኛ፤በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተደራሽ መሆን ችሏል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
መልካምስራ አፈወርቅ