አዲስ አበባ፡- የክረምቱ ዝናብ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎችና ለግብርና እንቅስቃሴ ብሎም ለውሃ ክምችት ምቹ መሆኑ ተገለፀ።
የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ለዝግ ጅት ክፍሉ የላከው መረጃ እንደሚያመ ለክተው፤ በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበረው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና እንቅስቃሴና ለውሃ ክምችት ምቹ ነበር።
ከነሐሴ 15 ቀን እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም የሚኖረው የአየር ሁኔታ ባለፉት 10 ቀናት ከነበረው ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እንደሚሆንም መረጃው ያመለክታል። ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት የሚኖራቸው ሲሆን ቀስ በቀስ ግን በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች እየቀነሰ ይመጣል። በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ሆኖ ይቀጥላል።
እንደ መረጃው ከሆነ፣ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦርና ሁሉም የሸዋ ዞኖች ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይኖራቸዋል። በአዲስ አበባም ተመሳሳይ የዝናብ ሁኔታ ይኖራል። በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች፣ በትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ አርሲና ባሌ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ አፋርና ጅግጅጋ የዝናብ ሥርጭት ይኖራል። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ለቅጽበታዊ ጎርፍ መንስኤ የሚሆን ዝናብ እንደሚከሰትም ኤጀንሲው አስታውቋል።
የአየር ሁኔታው ለመኸር የሰብል ምርት ተጠቃሚዎች እና ለአርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሣር ምቹ ይሆናል። በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል የደረሱ ሰብሎች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤጀንሲው አሳስቧል። በእርጥበትና ሙቀት መፈራረቅ አረምና ተባይ ስለሚፈጠር አርሶ አደሩ የሰብል ጉብኝት ማድረግ አለበት ብሏል። በወንዞች አካባቢ የውሃ ሙላትና የመሬት መንሸራተት ሊያግጥም ስለሚችል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
ከነሐሴ 5 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም በነበረው የአየር ሁኔታ በሰሜን የአገሪቱ አጋማሽ፣ በመካከለኛውና ደቡብ ምዕራብ አጋማሽ፣ በመጠንና በሥርጭት የተጠናከረ ዝናብ ነበር። የአፈርን እርጥበት በማሻሻልና ለረጅም ጊዜ ሰብሎች በቂ የውሃ ክምትች እንዳስገኘ ኤጀንሲው የሰበሰበው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
ዋለልኝ አየለ