– ህብረተሰቡ የተተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከብ ጥሪ ቀርቧል
አዲስ አበባ፡- የ2011 ዓ.ም የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ማሳረጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል፣ ህብረተሰቡም የተተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከብ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ ችግኞችን በመትከል በተካሄደው በዚህ የማሳረጊያ ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒስ ትር ዶክተር ዓቢይ አህመድን ጨምሮ የችግኝ ተከላ ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ተሳትፈዋል፡፡
አቶ ኡመር ሁሴን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ በሁለት ምዕራፎች ማለትም በሀገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊዮን እና በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታስቦ የተሰራው ሥራ ግቡን መቷል፡፡እስከ ሐምሌ 22 ድረስ ብቻ 3 ነጥብ 72 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን የተናገሩት ሚኒስትሩ ምንም እንኳን የሚጣራ መረጃ ቢኖርም የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላው ግቡን እንደመታ ጠቁመው፣ መረጃው ተጣርቶ ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
መረጃዎችን አጣርቶ የሚያጠናቅር ባለሙያ መመደቡን የተናገሩት አቶ ኡመር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና በ2012 ዓ.ም ለሚከናወን የተከላ ሥራ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። ከተተከሉት ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆነው ለምግብነት ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ ዝርያዎችን ያቀፈ ሲሆን ቀሪው 40 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለደን ጥቅም የሚውሉ ዓይነቶችን የያዘ እንደሆነም አቶ ኡመር ገልፀዋል፡፡
የውሃ መስኖ ኤሌክትሪከ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው በዘመቻው ከ23 ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብ እንደተሳተፈ ገልጸው፣ በየትኛው ክልል ምን አይነትና ምን ያህል ችግኝ፣ በየትኛው የቦታ አይነት የሚሉና መሰል መረጃዎችን የማጠናቀር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸ ዋል።
በሁለቱ ፕሮግራሞች የተገኘው ስኬት ኢትዮጵያውያን ሥራዎችን በአንድነት መንፈስ እየሰሩ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችሉ አመላካች ነው ያሉት ሚኒስትሩ በ2012 ለሚካሄደው ዘመቻ መልካም ተሞክሮ የተቀሰመበት ነበርም ብለዋል። መላው ኢትዮጵያውያን በዘመቻው ላሳዩት አንድነት እና ላስመዘገቡት ውጤት ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ እና ሶስቱ ሚኒስት ሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተከናወኑ ያሉ የግንባታና የግቢ ማስዋብ ሥራዎች ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን ግቢውን ማራኪ በማድረግ በመጪው አዲስ ዓመት ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ውጥን ተይዟል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
ድልነሳ ምንውየለት