– የብድር መጠኑ ከአጠቃላይ የሀገሪቷ ሀብት ውስጥ 49 በመቶ ደርሷል
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ባሻገር ከ50 አገራት ብድር መውሰዷን እና መንግሥትም 830 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በ2011 ዓ.ም ኢትዮጵያ ካለባት ብድር መካከል መንግሥት 22 ቢሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም ደግሞ 25 ቢሊዮን ብር ብድር ለመክፈል አቅዷል። የገንዘብ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክ ተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያም ከፋይናንስ ተቋ ማት በተጨማሪ ከተለያዩ 50 ሀገራትም ብድር አለባት። ከአጠቃላዩ የመንግሥት ብድር 80 በመቶው በረጅም ጊዜ የሚከፈል እና አነስተኛ ወለድ የያዘ ነው።
በ2011 ዓ.ም አነስተኛ ወለድ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ያለው ብድር መንግሥት መውሰዱን የገለጹት አቶ ሃጂ፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለረጅም ዓመታት ከማዕከላዊ ባንክ እና ከውጭ አገራት የወሰደው ብድር 830 ቢሊዮን 641 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስረድተዋል። የተለያዩ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በበኩ ላቸው 729 ቢሊዮን 907 ሚሊዮን ብር ብድር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
እንደ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር መጠኑን ከአጠቃላይ የአገሪቷ ሀብት ውስጥ 49 በመቶ እንደሚደርስ እና በዓለም አቀፍ ምዘና እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር እስከ 55 በመቶ የሚደርስ ብድር ሊፈቀድ ይችላል። ኢትዮጵያም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ባትገኝም የብድር ጫናዋን ለመቀነስ የሚያስችል አካሄድ ላይ ትገኛለች። በዚህም መሰረት በ2010 እና 2011 ዓ.ም ብቻ 39 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለብድር ተከፍሏል። በቀጣይም 25 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ሊከፈል የታሰበው ገንዘብ የአንዳንድ ክልሎችን በጀት የሚያክል መሆኑ ሲታሰብ መንግሥት የብድር መጠኑን ለመቀነስ የያዘው አቋም ከፍተኛ መሆኑን መገመት ያስችላል።
አቶ ሃጂ እንደገለጹት፣ በሌላ ጎኑ ግን ብድር ለመቀነስ የሚያግዝ መመሪያ በመውጣቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ፕሮጀክት ልክ ማንም ባለስልጣን ብድር የሚወስድበት አሰራር የለም። በቂ ጥናት ተደርጎ ለወሳኝ ፕሮጀክቶች ብቻ በፓርላማው ሲጸድቅ ብድር ይወሰዳል። ለወሳኝ አገራዊ ፕሮጀክቶች ተብለው የሚወሰዱ ብድሮችም የረጅም ጊዜ እፎይታ እና አነስተኛ ወለድ የያዙ ናቸው። በተለይ ከጣልያን የሚወሰደው ብድር ምንም ወለድ የሌለው እና በ30 ዓመት የሚከፈል ነው። ከጃፓን፣ አፍሪካ ልማት ባንክ፣ አረብ ባንክ እና ኮርያ እንዲሁም ከሌሎች ዝቅተኛ የወለድ መጠን ከሚያቀርቡ አገራት የሚወሰደው ብድር ከ0 ነጥብ አንድ በመቶ ጀምሮ እስከ አንድ በመቶ ብቻ ወለድ የሚታሰብባቸው በመሆኑ ዋነኛ አማራጭ ተደርገው ይወሰዳሉ። እንደ ነዚህ አይነት <<ኮንሴሽናል>> የሚሰኙ ብድሮች የክፍያ ጊዜያቸው ከ38 ዓመት እስከ አርባ ዓመት የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገሪቷ የግብር መጠን እና ኤክስፖርት በሚፈለገው ልክ ያለማደግ ጋር ተያይዞ 110 ሚሊዮን ህዝብ ላላት አገር ሁሉንም በእራስ አቅም ለማሟላት አስቸጋሪ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሃጂ፣ አንዳንድ ክፍተቶችን ለመሙላት አነስ ተኛ ወለድ ያላቸው ብድሮች ብቻ እንደሚወሰዱ ገልጸዋል። በአጭር ጊዜ የሚከፈሉ እና ከፍተኛ ወለድ ያላቸው የንግድ ብድሮች ሙሉ በሙሉ ከቆሙ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው የገለጹት አቶ ሃጂ፤ ከዚህ ቀደም የነበረ ውንም 10 በመቶ እና በላይ ወለድ የሚከፈልባቸውን የቻይና ንግድ ብድሮ ችን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥረት ወደረጅም ጊዜ ክፍያ እና አነስተኛ ወለድ መቀየር መቻሉን አስታውሰዋል።
እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ፤ ኢትዮጵያ ካለባት የንግድ ብድር መካከል በአንድ ቢሊዮን ዶላር የተገዛው ቦንድ ከፍተኛ ወለድ ካላቸው ብድሮች መካከል ዋነኛው ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም አይነት ከፍተኛ ወለድ ያለው ብድር አልተወሰደም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
ጌትነት ተስፋማርያም