መቼም የአንድን ቃል ትክክለኛ ፍቼ ሳያገኙ ተንደርድሮ ወደ ሥነ ጽሑፍ አራት ማዕዘን ተጉዞ የጉዳዩን ምንነት በባሕረ ገብ ለመጨበጥ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናልና የዚህን የዛሬውን ጽሑፍ ምንነት ለመረዳት የቃሉን ትርጓሜ በተገባ ሁናቴ መገንዘብ ያሻ ይመስለኛል። አልያ ግን ማንበብ ሳይሆን ማየት ብቻ ሆኖ የሚቀር ነውና!!
በመሠረቱ ‹‹ሰብዓዊ ባሕርይ›› ሲል ቃሉ ምን ሊያስተምር እንደፈለገ ለመረዳት ‹‹ሰብእ›› ከተሰኘው ሥርወ ቃል መነሣት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም።
‹‹ሰብእ›› የተሰኘው ስም ሰብአዊ የሚለውን ቅጽል ይወልዳል። ይኸውም ‹‹ሰው›› ማለት ሲሆን ‹‹ሰብአዊ›› ማለት ደግሞ ‹‹ሰው የሆነ›› የሚለውን ፍቺ ይሰጣል። እንግዲህ ‹‹ሰብአዊ ባሕርይ›› የሚለውም የ‹‹ባሕርይን›› የቁም ትርጉም ብንሄደው ‹‹የሰው አኳኋንን፣ መታወቂያን›› ሲገልጽ የተጠቃሹን ግለሰብ የማንነት መገለጫ ሊሆን የቻለውን ድርጊት፣ ተግባር፣ ጠባይ ያመለክታል።
ይህን መሰሉ ‹‹ድርጊት የማንነት መገለጫ ተግባር፣ ሙያና የመሳሰለው ሁናቴ እንግዲህ የዚያ፣ የዚያችን ሰው አዋዋል አስተዳደግና ጉዳዮች ለመመዘን መሠረት ይጥላል። እናም ይህንን በምናይበት ጊዜ የዛሬው ጽሑፍ እንዲያተኩርበት ምክንያት የሆነውን ተግባር ጠለቅ ዘለቅ ብለን እንድናይበት ያደርገናል።
በየጊዜው ተመራማሪዎች እየደጋገሙ እንደሚያመ ለክቱትና ታሪክም በየወቅቱ ምሳሌ እያደረገ እንደሚጠ ቅሰው የትኛው ወንድ የትኛዋን የሴት ዓይነት እንደሚያ ፈቅር ወይም የትኛዋ ሴት የትኛውን የወንድ ዓይነት እንደምታፈቅር ጠለቅ ብለው ሲያጤኑት በአግራሞት ከመሞላቱ በቀር ሰው ይናገረው ዘንድ የሚሻውን ቃል ያጣዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ‹‹ እገሌ ተእገሌ›› ሳይባል ሁሉም የሰው ዓይነት ጋብቻ ይፈጽማል። ሌላው ይቅርና የመዳን ተስፋ የሌላቸው የሚመስሉ ሕሙማን መጋባታቸውን እናውቃለን። የአካል ጉዳተኞችም ጋብቻ መፈጽማቸውን እናያለን። የአካል ጉዳተኛ ከመባልም አለፈው ጭርሱን የመሥራት አቅም እንዳይኖራቸው የተደረጉ ድኩማንም ያገባሉ።
ተጠባቢያዎች እንደሚነግሩን አካላዊ ቅልጥፍና በከፊል ብቻ ሳይሆን በአፈጣጠሩም ሳቢያ እጅግ የጎደለው፣ በእንቅስቃሴው እጅግ ዝግተኛ ይሆን ዘንድ የሚገደው፣ ለአደጋ የፈጥኖ ተጋላጭነት ዕድሉ የሰፋ፣ በአካልም ብቻ ሳይሆን በአእምሮም ጭምር ዘገምተኝነት ያለበት ወንድ ሚስት ያገኛል።
እጅግ በሚደንቅ አኳኋን ደግሞ የመልከ ጥፉዎች ውድድር ቢካሄድ አንደኝነቱን ማንም የማይቀማት ሴት የደም ግባቱና ውበቱ ‹‹ይህ ነው›› የማይባል ወንድ የትዳር ጓደኛ ይሆናት ዘንድ ለማግኘት የባል ደጅ ጥናት ሳያሻት እንደምትጣመር የታየበት ወቅት ሞልቷል።
ይሁንና ከሁሉም በላይ ነጥብ ይያዝባቸው ዘንድ የሚሹ ሌሎች ዓበይት ጉዳዮቹ አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ጽዱነት፣ ንጹሕና፣ ራስን በሥርዓት ጠብቆ የመያዝ ‹‹ዋና›› ተብለው ሊቆጠሩ ሲበቁ ‹‹ሰብእና›› የተሰኘው ደግሞ ከሁሉም በላይ ተቀምጦ በመመጠኛ መስፈርትነት ሚዛኑን የሚቆጣጠር ነው።
ይሁን እንጂ ገና ከጅምሩ አንሥቶ ‹‹ሰብእ›› በፆታ ግንኙነትም ሆነ በፍቅር ጉዳይ ላይ እንዲህ የከበረ ቦታ ይዞ መገኘቱን አምነው ለመቀበል የሚችሉ በጣት ከመቆጠር የሚያልፉ አይደሉም። የሰብዓዊ ባሕርይ ምንነት ቢሰሙ እንኳ መረዳት የማይሹም ሞልተዋል። ዋል አደር ብለው ግን ሰብእና ባለመኖሩ ወይም በመጉደሉ ሳቢያ የመጣውን ችግር ሲገነዘቡ ኃዘናቸው የበዛ ይሆናል።
በዛሬ ዘመን በቴክኖሎጂ በገፉት ሀገሮች የሚገኙ ሴቶች ከልብም ይሁን ወይም አይሁን ሰብዓዊ ባሕርይን ይዘው ለመገኘት ወይም መስሎ ለመታየት ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ይገኛሉ። ይህም ከእነርሱ እየተወራረሰ ወደ ሦስተኛውም ዓለም ቀስ በቀስ እየተዳረሰ ሲሄድ ማየታችን አልቀረም።
ይሁንና የወርቅ ሰዓት አስረው፣ እጅግ ከከበረ ማዕድን የሚሠራ የጣት ቀለበት አድርገው፣ በእጅ አምባርም ተጊጠው በአንገት ሐብል አሸብርቀው የሚታዩ በአመዛኙ የቤት እመቤቶች ወይም የቢሮ ጸሐፊዎች አይደሉም። ብዙውን ጊዜ በአሳዛኝ መልኩ እንዲያ አጊጠው፣ እንዲያ አምረው የሚገኙት ዝሙት አደሮ ች የተባሉት ናቸው።
እዚህ ላይ ብዙውን ጊዜ በሀገራችን ከድሮ ጀምሮ ‹‹ሴተኛ አዳሪ›› የሚለውን ቋንቋ ሲጠቀሙ በምሰማበት ወቅት ከማዝንባቸው አጠራሮች አንዱ ስለሆነ እኔም ይህ አባባል ‹‹ክቡራት›› ሊባሉ የሚበቁትን እናቶች፣ እህቶች፣ ሴት ልጆች፣ ምራቶች፣ የሴት አያቶችንም ሳይቀር በጥቅሉ የሚያጎድፍ በመሆኑ በተለያየ ወቅት ተሟግቼበታለሁና ዛሬም አነሣው ዘንድ ግድ ብሎኛል። ለገንዘብ ሲሉ፣ ለጥቅም ሲሉ ዝሙትን መተዳደሪያ ያደረጉ ሴቶች ‹‹ዝሙት አደሮች›› እንጂ ‹‹እንደ ሴት የሚያድሩ አይደሉም። ይህንን ልብ ማለት ያሻል። ‹‹ሴተኛ አዳሪ ›› ማለት እንደ ሴት የምታድር ማለት እንጂ ሌላ አይደለም። ይህ አባባል ሊሻር የተገባው ነው።
ወደ ጉዳዩ ስንመለስ ‹‹እጅግ አሳዛኝ›› ሲባል በሚበቃ መልኩ ዝሙት አደርነት ‹‹አንቱ›› ሊባሉ በበቁ ታላላቅ ሰዎች ዘንድ ታላቅ ከበሬታ ያገኘ ‹‹ልዩ ሙያ›› ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል። በባሕር ማዶው አህጉር የታየው የአኗኗር ሁኔታ እዚህም በኢትዮጵያችን ይሁንታን ያገኘ መተዳደሪያ ሆኗል። ‹‹አለ›› የሚባል የአውቶሞቢል ዓይነት የሚሽከረከረው፣ ‹‹እኔ ነኝ› ያለ የከተማችን ቪላ ይኖርበት ዘንድ የተከበረው በዝሙት አደሮች ከሆነ ቆይቷል። ይህ ቀደም ሲል በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ፣ ጥቂትም በዘመነ ደርግ እየተንገዳገደ ሄዶ በኋላም አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ በዘመነ ኢህአዲግ ዓይን ባወጣ ሁናቴ ረጅም ጉዞውን ተያይዞታል።
ሌላው ቀርቶ ቀን ቀን በቢሮ ጸሐፊነት ሲሠሩ፣ በየግዙፋን ተቋማት ሲሰማሩ ውለው በተለይ እንደጉዞ ድርጅት፣ እንደ አየር መንገድ፣ እንደ ሆቴል ባለው እየሠሩ ወደ አመሻሹ ላይ ተኳኩለው የሚወጡ ንዑሳት ዝሙት አደሮች፣ ‹‹የጥሪ መንገደኞች›› የሚለብሱትም ሆነ የሚያጌጡበት፣ የሚያሽከረክሩትም ሆነ በቀጠሮ የሚሽከረከሩበት አውቶሞቢል ‹‹የጉድ›› ሊያሰኝ ይበቃል።
በአንድ በኩል ደግሞ የማንክደው ጥሬ ሐቅ አለ። ይኸውም እንዲህ ያሉ ዝሙት አደሮች ወይም ንዑሳት ዝሙት አደሮች ለማስመሰልም ቢሆን ትሕትናቸው፣ አቀራረባቸው፣ ፈገግታቸውና፣ የመስሕብ ገጽታቸው ከሩቅ የሚጠራ ነው። እንዲህም በመሆኑ ለሁሉም ዓይነት ወሲባዊ ተራክቦ ያለ አንዳች ማቅማማት ወይም ማመንታት አዎንታ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው። ጨዋ ናቸው ተብለው በሚሞገሱት የቤት እመቤቶችም ሆነ ሌሎች ወይዛዝርት ዘንድ ‹‹ እንደ ነውር›› የሚቆጠረውን የወሲባዊ ግንኙነት የድርጊት ዓይነት እነርሱ እንደ ጸያፍ አይተው አያጥላሉትም። ይበልጡን እንዲያውም ወንድየው ዓይቶም፣ ሰምቶም የማያውቀውን ነገር አሳይተው ያሳብዱታል። የሚሆነውን ያሳጡታል።
በዚህም ምክንያት በቁጥር ያላነሱ ባሎች ቤታቸውን እየጠሉ፣ ሚስቶቻቸውንም እየጠሉ እስከ መሄድ ደርሰዋል። በኢትዮጵያችን የተደረገ ጥናት ስለመኖሩ ርግጠኛ ሆኜ መናገር አልቻልኩም እንጂ ሥልጣኔ ባዘመነው አህጉር ባሉ ባለትዳር ሴቶች ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያስረዳው ዝሙት አደሮች ወይም ንዑሳት ዝሙት አደሮች በእሽታ የሚቀበሉትን የወሲባዊ ግንኙት ድርጊት ዓይነት ደስ ብሏቸው የሚያደርጉ እማወራዎች እጅግ በጣም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። እዚህ በሀገራችንም ከዚህ የተለየ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። በዚህም ሳቢያ ተላላው ወንድ ለጊዜያዊ ርካታ የዘመናትን ቤተሰባዊ ደስታ ያጣል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ያ ‹‹ሰብዕና›. የተሰኘ ታላቅ ጉዳይ ብቅ ይላል። የዝሙት አደሮችም ሆነ የጥሪ መንገደኞች ‹‹ማንነት›› እየጎላ መታየት ይጀምራል። አዎን! ዝሙት አደሮችና ንዑሳት ዝሙት አደሮች፣ የጥሪ መንገደኞች ዓላማቸው ገንዘብ ብቻ እንጂ ሌላ አለመሆኑ ይታወቃል። እነርሱ እንደ ኪራይ ወታደር ለከፈላቸው ሰው ለመሞት ቆርጠው የተነሡ፣ የራሳቸውን ማንነት የረሱ የሰውን ሰውነትም የሚያስረሱ የጥቅም ተገዥዎች ናቸው። ይህ ግን ከቀን ወደ ቀን በቁጥር እየቀነሰ ሳይሆን የዚህን መሰል ቁርኝትና ጉድኝት በአኃዝ እየዳጎሰ ሲሄድ ይታያል።
በዚያም አለ በዚህ ግን ዘለቄታው የሚያምር፣ መጨረሻው የሚሠምር አለመሆኑን ተመራማሪዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ያስረዳሉ። ምክንያት? ቢባል በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በገንዘብ ላይ የተንተራሰ ነው!! ‹‹ፍቅር የሌለው ወዳጅነትና ሥር የሌለው እንጨት አንድ ነው›› የሚለውን ምሳሌ በዚህ ረገድ ማስታወስ ያሻል።
የዓለም ተመራማሪዎች እንዲያውም በዚህ በኩል በአንድ ታላቅ ብለው በሚያነሡት ጥያቄ ላይ ዘወትር ውይይት ሲያካሂዱ እና በቅርቡም እያካሄዱ መሰነባበታቸው ይታያል። ጥያቄውም ‹‹ለመሆኑ ሴቶች በጥቅሉም ባይሆን በአመዛኙ ስለ ወንድ ሰብዕና ወይም ሰብዓዊ ባሕርይ ግንዛቤ አላቸውን?›› የሚለው ነው።
ብዙዎች ተሳታፊዎች መሠረት የሚያደርጉት ጥንታዊው ተጠባቢ ኦወን ብሎህ ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ነው። እሳቸው ያሉትም እንዲህ ይነበባል ።
‹‹ዓለም በሠለጠነ፣ ጊዜ በቴክኖሎጂ በዘመነ ቁጥር የታየ አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ። ወንዶች ስለ ወንዶች ሰብእና ወይም ሰብአዊ ባሕርይ ከሴቶች ይልቅ በጣም የተሻለ ግንዛቤ አላቸው። የሴቶች ግንዛቤ ግን እምብዛም ነው›› ካሉ በኋላ ካሮሊን ሽሌገል ለዊዘ ጎተር የጻፈቸውን ደብዳቤ እማኝ ያደርጋሉ እንዲህም ይነበባል።
‹‹ሶፊ የእርሱን ሰብእና ወይም ሰብዓዊ ባሕርይ ወይም ደም ግባቱን እንኳ ከቁም ነገር ሳትቆጥር አፍቅራዋለች። ምክንያቱም ሴቶች እንደምናውቀው በወንድ ላይ የሚያዩት ሰብዓዊ ባሕርይውን ወይም ሰብእናውን አልያም ደም ግባቱን አይደለምና! ይላሉ።
እናስ የሚያዩት ምኑን ነው? በርግጥ ሴቶች ብሎ በጥቅሉ መፈረጅ ይቸግራል። በአመዛኙ ግን እንዲያ ናቸው። የሚያዩት ኪሱን፣ አውቶሞቢሉን፣ ቤቱንና ንብረቱን እንጂ ሰብእናውን ሰብአዊ ባሕርይውን ወይም ሌላው ቢቀር፣ ከምንም እንኳ ባይቆጠር ደም ግባቱን እንኳ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ራሱ አንድ ምስክር ሊሆን ይበቃል።
በዚህ ረገድ ግን በሀገራችን በኢትዮጵያ የሚገኙት መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎችም ተመሳሳይ ተቋማት፣ ቤተ እምነቶች ጭምር በአንድነት ሊዘምቱበት፣ ባገኙትም መድረክ ሊያስተምሩበት የተገባ ዓቢይ ተግባር ሊሆን ይገባል። በተለይም ቤተ እምነቶች በአብያተ ክርስቲያናትና በመስጅዶችም ሳያሰልሱ ሊያስተምሩበት ይገባል። በብርቱም ሊጸለይበትና ማናቸውም የአምልኮ ሁናቴ ሊደረግበት ይገባል። ሰብዓዊ ባሕርይ እና ሥነ ምግባር ከቀን ወደ ቀን እየጎደፈ መሄዱን ከማየት አልታገድንምና!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
አሸናፊ ዘደቡብ