• 569 ሺ ተሽከርካሪዎች ብቻ የሦስተኛ መድን ሽፋን ተግባራዊ አድርገዋል
አዲስ አበባ፡- በመላ አገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች የፊተኛው ገጽ ላይ የሚለጠፈውና በከፍተኛ ምስጢራዊ ህትመት የሚዘጋጀው የሶስተኛ ወገን መድን ማረጋገጫ ምልክት ሙሉ ለሙሉ በአዲስ መልክ ሊቀየር መሆኑ ተገለፀ።በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ውስጥ 569 ሺ ብቻ የሦስተኛ መድን ሽፋን እንዳላቸው ተገልጿል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በተለይም ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለፁት፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ያለው የሶስተኛ ወገን መድን ማረጋገጫ ምልክት ለመቀየር ታቅዷል።
በአሁኑ ወቅት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚለጠፈው ምልክት ቅርጹ ክብ ሲሆን ከሌሎች ምልክቶች ጋር ስለሚቀራረብ ወደ ሦስት ጎን ቅርጽ ይቀየራል።በተጨማሪም ቀለሙና ዲዛይኑ በሌላ የሚተካ ይሆናል። ከዚህም ባሻገር ምስጢራዊ ህትመቱ በእጅጉ በረቀቀ መንገድ የሚከናወንና ከሀሰተኛ መረጃዎች ለመለየት ደግሞ በአመቺ ሁኔታ የሚታተም ነው።ምልክቱ ሐሰተኛ ቢሆን እንኳን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚሰሩ የትራፊክ ፖሊሶች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በሚገጠም አፕሊኬሽን መለየት ያስችላቸዋል።ቀደም ሲል የነበረው የሶስተኛ ወገን መድን ማረጋገጫ ምልክት ሐሰተኛ
ወይንም እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚችለው ምስጢራዊ ህትመቱን ያከናወ ነው ማተሚያ ቤት ብቻ እንደነበር አስታ ውሰው፤ አዲሱ አሠራር ተግባራዊ ሲሆን ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ማቃለል እንደ ሚችል ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
እንደ ወይዘሮ ወርቅነሽ ገለፃ፤ ምንም እንኳን የሦስተኛ ወገን መድን የተሽከርካሪ ባለቤቶች አረቦን ለመግዛት በዓመት ከ300 እስከ 1000 ብር የሚከፍሉ ቢሆንም በርካ ቶች ይህን ተግባራዊ ባለመድረጋቸው የህግ ጥሰት እየፈፀሙ ነው።ለአብነትም በ2011 በጀት ዓመት በአገሪቱ ካሉ 1 ነጥብ 38 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ውስጥ 569 ሺ ተሽከርካሪዎች ብቻ አረቦን መግዛታቸውን ጠቁመዋል። ይህም አፈፃፀሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ከሐምሌ 10 ጀምሮ የዘመቻ ሥራ በመጀመሩ እስካሁን 780 ሺ ተሽከርካሪዎች መስፈርቱን ማሟላታቸውን አስረድተዋል። የተቀሩትም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ህጋዊ መስፈርቱን ማሟላት አለባቸው።ይህንን ተግባራዊ ያላደረገ ተሽከርካሪ በጎዳና ላይ መገኘት እንደሌለበት አሳስበዋል።
ወይዘሮ ወርቅነሽ እንዳሉት፤ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን መፈፀም ጉዳት በሚደርስበት ወቅት በፍጥነት የመፍትሄ አካል ለመሆን የሚያግዝ ከመሆኑም በተጨማሪ ተጎጂዎች በተገቢው መንገድ እገዛ እንዲያገኙ ይረዳል።በመሆኑም ከሞ ተር ሳይክል ጀምሮ ማንኛውም ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ መግዛት ግዴ
ታው መሆኑን ገልፀዋል።ሆኖም በአሁኑ ወቅት ይህን ተግባራዊ ያላደረጉ አካላት መኖራቸውንና ምናልባት በህገ ወጥ መንገድ የተሰሩ የሶስተኛ ወገን መድን ማረጋገጫ ምልክቶች እየተጠቀሙ ሊሆን እንደሚችል አሊያም ደግሞ ከግንዛቤ እጥረት የሚመነጭ መሆኑን አብራርተዋል።
ኤጀንሲው በተሽከርካሪ አደጋ ምክን ያት ጉዳት የሚደርስባቸው ሁሉም ወገ ኖች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የሞትና የአካል መጉደል ጉዳት የሚደርስባቸው የሦስተኛ ወገን ተጎጂዎች በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚካሱትን ጨምሮ በጉዳታ ቸው መጠን ተገቢ ካሳ እንዲያገኙ በማድ ረግና በማስተባበር የሚደርስባቸውን ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ችግሮች እንዲቃለሉ በስፋት እየሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይሁንና ይህ ጥረት በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ በታቀደው መጠን ውጤታማ አለመሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ለሞትና ለአካል ጉዳት ለሚደርስባቸው ካሳ መክፈሉ እና ማህበራዊ ሕይወት እንዳይበላሽ ታስቦ የሚከፈል ቢሆንም የህግ ክፍተት መኖሩን ገልፀዋል።ለአብነትም ለሞት ከ5000 እስከ 40 ሺ ብር ካሳ የሚከፈል ሲሆን፤ ይህም አሁን ባለው የምጣኔ ሃብት ዕድገትና ከሚደርሰው ጉዳት አኳያ በቂ ባለመሆኑ መሻሻል ያለባቸው የህግ ክፍተቶች መኖራ ቸውን አብራርተዋል።ለአካል ጉዳት የተቀ መጠው የካሳ ግምትም ከ40 ሺ የማይበልጥና አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማነጻፀር አስቸጋሪ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ብሎም በህግ ላይ ያለውን ክፍተትና የተቋሙን አደረጃጀት ማስተካከል ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።
የመድን ፈንድ ኤጀንሲ በአዋጅ 799/2005 የወጣውን የተሽከርካሪ አደጋ ሦስተኛ ወገን መድን ለማስፈፀም በሚኒ ስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 300/2006 መሠረት ተጠሪነቱ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር