በአንድ የሚዲያ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት በምሰራበት ወቅት ለሪፖርተርነት የሥራ መደብ አመልካቾችን አወዳድሮ ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣን ። የተጠየቀው በዘርፉ ዲግሪ እና ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ስለነበር እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች አመለከቱ ።
አመልካቾቹ ብዛት ስለነበራቸው ለፈተና የሚቀርቡትን ለመለየት የግድ አጠቃላይ የትምህርት ውጤታቸውን ማየት ነበረብን ። በዚሁ መሠረት ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን መርጠን ለፈተና እንዲቀርቡ አደረግን። ለፈተና ከቀረቡት ከ20 በላይ ወጣቶች መካከል ፈተናውን አመርቂ በሚባል ሁኔታ የሰሩ ግን አልነበሩም። የአንዳንዶቹ ውጤት ትንሽ አስደንጋጭ ቢጤም ነበረ ።
በመጠኑ ለመመለስ የሞከሩትን ዕድል ለመስጠትና እግረመንገድም የሥራ ላይ ሥልጠና ሰጥቶ ለመደገፍ መ/ቤቴ በመወሰኑ ሶስት የሚደርሱ ወጣቶችን መቅጠራችንን አስታውሳለሁ ። ይህን ለምን ትዝ አለኝ? ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲዎች ይዘውት የሚወጡት ዕውቀት ከንድፈሀሳብ የዘለለ ተግባርን ያልተመረኮዘ መሆን የቱን ያህል ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ ለመጠቆም ያህል ነው። ችግሩ የአጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱ እንጂ የወጣቶቻችን ብቻም እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው ።
ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ባስመረቁት የትምህርት መስክ ተወዳዳሪ መሆን የማይችል ዜጋ ሲያመርቱ መቆየታቸው እንደውድቀትም ሊታይ የሚገባው ነበር እላለሁ።
ዛሬስ? በለውጥ ተስፋ እና ሥጋት መካከል ነን። ተስፋው ምንድ ነው?
እንደ ዕቅዱ ከሆነ በቀጣይ ዓመት ሊተገበር የታሰበው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓተ ትምህርት (ፍኖተ ካርታ) ብዙ ቁልል ችግሮችን ሊቀርፍ የሚችል አቅም እንዳለው ከወዲሁ ተስፋ ያደረጉ ብዙዎች ናቸው ።
በዕቅዱ መሠረት በቀጣይ 2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) የመጀመሪያ ዓመት (ፍሬሽማን) መርሃ-ግብር ይጀምራሉ ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች የሰጠው መግለጫ ስለመርሃግብሩ በበቂ ሁኔታ ያብራራ ነበር ።
በተያዘው ዕቅድ መሠረት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ 3 ዓመት የነበረው የዩኒቨርሲቲ የዲግሪ መርሀ ግብር ቆይታ ወደ 4 አመት ከፍ ይላል ። በዚህ የፍሬሽማን ጊዜ ውስጥ ወደ 15 የሚደርሱ ኮርሶች ሁሉም ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች እንዲወስዱ ይደረጋል ።
በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሰረት የሚከተሉት ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይጠበቃል፣
– አንድ አዲስ ዩኒቨርሲቲ የሚገባ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ከመሄዱ በፊት በአከባቢው ካለው ወረዳ ተወያይቶና ትምህርት እስከሚጨርስ ድረስ በምንም አይነት ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ አልሳተፍም የሚል ደብዳቤ ከወረዳው ያመጣል፣
– ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ እንደገቡ አንድ ህንፃ ለ100 ተማሪዎች ለመጠበቅና ኃላፊነት ለመውሰድ ፈርመው ይረከባሉ፣
– ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማር ተማሪ ሆነ መምህር ትኩረቱን በትምህርት ሥራው እንጂ በየትኛውም ፖለቲካ ውስጥ መግባት አይችልም፣ ይሄንን ተላልፈው የተገኘ ቀጥታ ለፖለቲካው ብሎ የትምህርት ሥራውን በማዋሉ የህግ ተጠያቂነት ያርፍበታል፣
እነኚህ የተጠቀሱ ሦስት ቁልፍ ነገሮች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታ በማረጋጋት ለትምህርት ዘርፍ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ በጥናት የተለዩ እርምጃዎች መሆናቸውን የደረሰኝ መረጃ ይጠቁማል ።
ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይ የፍኖተ ካርታ ይዘት በተመለከተ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአገራችን የመጀመሪያውን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከሶስት ዓመታት በላይ ከፈጀ የዝግጅት ምዕራፍ በኋላ ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል ።
ይህ ፍኖተ ካርታ አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ የትምህርትና ስልጠና ስርዓቱ ያለበትን ሁኔታ ከፈተሸ ወዲያ የደረሰባቸውን ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የተካተቱበት ነው።
ፍኖተ ካርታው እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር ሲሆን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የትግበራ ዓመት ይሆናል።
ፍኖተ ካርታው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ችግሮችን ለይቶ መፍትሔዎችን አስቀምጧል ።
በፍኖተ ካርታ ዝግጅት ወቅት ከተለዩ ችግሮች መካከል የሥርዓተ ትምህርት አዘገጃጀት ይዘትና ትግበራ ችግር፣ የዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮ አለመለየት፣ የትምህርት፣ አደረጃጀት ችግር፣ የህጎች፣ የአሠራሮችና ስታንዳርዶች አለመኖርና አለመናበብ፣ በቂና ብቁ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ግብዓቶች ከትምህርት መስፋፋቱ ጋር አለመጣጣም፣ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዝቅተኛ መሆን/አለመኖር፣ የሲቪል ሰርቪሱ አለመዘመን- ሥልጠና መስክና የሥራ ገበያ አለመጣጠም የሚሉት ይጠቀሳሉ ።
በዚህ ምክንያት የመጡ ችግሮች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው የስነምግባር እና የሞራል ውድቀት፣ ስርዓት አልበኝነትና ምክንያታዊ ያለመሆን፣ የስራ ጠባቂነትና ጥገኝነት፣ የወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያለማወቅና ያለመረዳት፣ የተግባቦትና የመረዳዳት ችግር፣ ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ይዞ አለመገኘት
በፍኖተ ካርታው እነዚህን ችግሮች ከስር መሰረታቸው ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሄ ምክረ-ሃሳቦች ተቀምጠዋል። ዋና ዋናዎቹም ፡-
• የአንደኛ አመት ተማሪዎችን የታሪክ፣ የጂኦግራፊና አንትሮፖሎጂ፣የኮምፒዩቲሽናል ክህሎት፣ የስነምግባር፣ የቋንቋ፣ የስነተግባቦት፣ ምክንያታዊነት፣ የቴክኖሊጂ እና ዓለም ዓቀፋዊ ዕውቀት ሊያስጨብጡ የሚችሉ ኮርሶችን መስጠት
•ዩኒቨርሲቲዎች እንደተልኳቸው ትኩረት ማደራጀት፤ የምርምር፣ የአኘላይድ ሳይንስ፣ የቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ሆነው እንዲደራጁ ማድረግ፣
• የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቆይታ 4 አመት እንዲሆን (ለኢንጂነሪንግ 5፤ ለሜዲሲን 6)፣ 2 አመት Masters, 4 ዓመት Ph.D.,
በዚሁ ግኝት መሰረት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ለሁሉም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት የሚሰጡ 15 የትምህርት አይነቶች የተለዩ ሲሆን እነዚህም ፡-
1. Critical Thinking
2. General Psychology
3. Global Trends
4. Economics
5. Communicative English Language Skills I
6. Geography of Ethiopia and The Horn
7. Mathematics (For Natural Science/ For Social Sciences)
8. Introduction To Emerging Technology
9. Anthropology
10. Entrepreneurship
11. History Of Ethiopia and The Horn
12. Communicative English Language II
13. Moral and Civics Education
14. Inclusiveness
15. Physical Fitness የሚሰጡ ይሆናል ።
ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮ የመለየት ስራዎችም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ። ተልዕኮ መለየት ሲባል ለምሳሌ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ኢንጂነሪንግ ትምህርቶች የሚሰጡ ከሆነ በቀጣይ የተሻለ ልምድና የማስተማሪያ ግብዓቶች ያሟላው ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንዲያስተምረው ይሆናል ማለ ት ነው ።
ይሄ ስራ ጊዜ የሚፈልግ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ሊገባበት ባይችልም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን ደረጃ በመፈተሽ የትኛው ተልዕኮ እንደሚሰጣቸው የማሳወቅ ስራዎች ይሰራሉ። በሂደት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ወደተሰጣቸው ተልዕኮ ብቻ አተኩረው ይሰራሉ። ይህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አንዱ መፍትሔ ይሆናል ።
ጥቂት ነጥቦች ስለፍኖተ ካርታው አመጣጥ
በ1986 ዓ.ም ተቀርጾ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ ውሎ ለ24 ዓመታት በስራ ላይ ውሎ የነበረው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲን አፈፃፀም በተመለከተ የተደረገ ጥናትን መሰረት በማድረግ ለቀጣይ ፖሊሲ ማሻሻያ የሚሆኑ ፅንሰ ሃሳቦች የተካተቱበት የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል ።
ፍኖተ ካርታው በአሁኑ ወቅት ያለው ስርዓተ ትምህርት በዘመናዊ መልኩ መሻሻል እንዳለበት፣ የመማር ማስተማር አካባቢና ስነ ዘዴው እንዲሁም የምዘናና የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ በተሻለ ሁኔታ መሰጠት እንደሚገባው ያስቀምጣል።
በተጨማሪም የዕጩ መምህራን ምልመላ ስርዓት መሻሻል እንደሚገባው እና የመምህራን ምደባና ዝውውር ፍትሃዊ መሆን እንደሚገባው፣ ከዚህ ባለፈም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን የመቅረፍ አቅም እንዳለው ይታመናል።
በኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በትምህርትና ስልጠና ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ሂደት አስመልክቶ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተካሂደዋል ።
በአጠቃላይ ትምህርትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወደፊት አደረጃጀትን አስመልክቶ በቀረበው ሰነድ ላይ ህብረተሰቡ በስፋት ተወያይቶ ጠቃሚ ሃሳቦችና አስተያየቶች ተሰብስበው ግብዓት ሆነዋል።
ሴክረታሪያት ጽ/ቤቱ በዝርዝር ተመልክቶ ለቀጣይ መስተካከል የሚገባቸውን የህብረተሰቡንና የምሁራንን አስተያየቶች አካቶ ረቂቅ ፍኖተ ካርታው ወደ ትግበራ ምዕራፍ መዳረሻ ላይ መሆኑን ተነግሯል ።
ባለፈው አንድ ዓመት የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ እስካሁን ከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዲወያይበት ተደርጎ ጠቃሚ ግብዓት የመሠብሠብ ሥራ ተከናውኗል ።
በፍኖተ -ካርታው ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማወያያቱ ተግባር እንደሚቀጥልና እስካሁን በተደረጉ ውይይቶችም በሚቀጥሉት 15 ዓመታት እንዲተገበር የሚጠበቀውን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ- ካርታ በእጅጉ ማዳበር ያስቻሉ በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች፣ ምክረ ሐሳቦችና አስተያየቶች መገኘታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
እንደ ማሳረጊያ
የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በዘርፉ ባለሙያዎች ተገቢውን ጥናት ተደርጎበት፣ በየደረጃው ውይይት ተካሂዶበት ለትግበራ እንዲዘጋጅ በማድረግ ረገድ የተጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ማድነቅ ተገቢ ይሆናል ። የአዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ተከትሎ በቀጣይ ዓመት በተለይም በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማሩ ሒደት ጤናማ ይሆናል የሚል በጎ ተስፋ በብዙዎች ዘንድ እንዲጸንስ ምክንያት መሆኑም እንዲሁ በአዎንታ ማየት የሚገባ እርምጃ ነው ።
ይህም ሆኖ በተደጋጋሚ በባለሙያዎች የሚነሳው አካዳሚ ነጻነት መከበር ጉዳይ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት መወገድ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው አይሆንም። በመምህራን ቅጥርና ዝውውር እንዲሁም ዕድገት ላይ የሚታየው የዘውጌ አካሄድ ለትምህርት ጥራት መጓደል ትልቁ መንስኤ መሆኑ ተጢኖ በዚህ ረገድ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻነት ማረጋገጥ ይገባል። በተጨማሪም ተቋማቱም ተልዕኳቸው በግልጽ ተለይቶ መታወቅ አለበት።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የህልውና ምክንያት በግልጽ መታወቅ አለበት ። ተቋሙ የቆመለት ዓላማ የሙያ ትምህርት ለመስጠት ነው ወይንስ የአካዳሚክ ትምህርት ለመስጠት ወይንስ ሁለቱን ተልዕኮዎች አጣምሮ ለመያዝ? ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ የማንኛውም ዩኒቨርሲቲ “ተልዕኮ” ግልጽ መደረግ አለበት የሚባለው ። ይህ በግልጽ ካልታወቀ የኮርሶች መምታታትና መዘበራረቅ ይፈጠራል።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የሀገሪትዋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸው አንድ ዓይነት መሆኑ ነው ። ሁሉም ተልዕኮ ማስተማር፣ ምርምር እና አገልግሎት መስጠት የሚሉ ናቸው ። እነዚህ ሶስቱ ተግባራት እንጂ ተልዕኮ አይደሉም ። ከተጠቀሱት ሶስት ተግባራት ውስጥ የትኛው ዋናው ተልዕኳቸው እንደሆነ ለይቶ ማወቅና ማሳወቅ አስፈላጊ ነው ። ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተግባራት የሁሉም ተቋማት ተልዕኮ ሊሆኑ አይገባም ።
ምንም እንኳን ከፍተኛ ትምህርትን በማስፋፋት ረገድ ባለፉት ዓመታት መጠነ ሰፊ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም በጥራቱ ላይ አሁንም ቢሆን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ሽፋን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ዓላማውን እንዲሳካ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ተገቢ ነው ።
የዓለም አቀፍ አሰራር በጎ ልምዶች እንደሚያስገነዝቡት የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ማስጠበቂያ ሥርዓት ስኬታማ እንዲሆን የጥራት ቁጥጥር (Quality control) እና የጥራት ማጎልበት (Quality Enhacement) ሊኖሩት ይገባል። በሌላ በኩል ጥራትን ለማረጋገጥና ዕውቅናን ለማግኘት የሚገመገሙት የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥትም ጭምር ሊሆኑ ይገባል። ይህም በጥራት ማስጠበቅ ሥርዓት ውስጥ የግሉም ሆነ የመንግሥት ተቋም በእኩል እንዲዳኙና በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት መመዘኛዎች (Double standard) ያሉት አሠራር እንዳይኖር ያደርጋል ።
በሀገራችን የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ውጤታቸው የሚፈለገውንና መሆን የሚገባውን ያህል ነው ለማለት አይቻልም ።… የሚታዩትን የጥራት ችግሮች አጢኖ ተገቢውን የማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ካልተጠበቀ ምንም ያህል ስርጭቱ ቢስፋፋ፣ የቱንም ያህል ቅዱስ የማሻሻያ ዕቅድ ቢዘረጋ የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል መቼም ሊዘነጋ አይገባም ።
(የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጹሑፍ ጥንቅር፡ – የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ አማረ አስገዶም -የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት አግባብነትና የመማሪያ ግብአቶች ይዞታ፤ ጥናታዊ ጹሑፍ፣ ዮሐንስ ወልደትንሳኤ- የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ሥርዓትና የተቋማት ዕውቅና ጥናታዊ ጹሁፍ፣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ…የተገኙ ዜናና መረጃዎችን በግብዐትነት መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልጻለሁ ።)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
ፍሬው አበበ