( Cities of Refuge )
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com
በሀገራችን ከመጣው ለውጥ ማግስት ጀምሮ እንደ ኦሪት ዘመኗ እስራኤል የሰው ነፍስ በስህተት ላጠፉ ሳይሆን ሆን ብለው፣ አቅደው ፖለቲካዊ አላማቸውን ኢኮኖሚያዊ አሻጥራቸውን ለማሳካት ሲሉ ለገደሉ፣ ዜጎች ላይ አካላዊም ስነ ልቦናዊም ስቃይ torture ለፈፀሙ፣ የሕዝብን የሀገርን ሀብት ለዘረፉ ከለላ፣ ሽፋን የሚሰጡ
“ የመማፀኛ “ ከተሞች እና ክልሎች እየተፈጠሩ ነው ።
በእነዚያ በአፄዎቹ አገዛዝ እንኳ ያልተከተሙ የመማፀኛ ከተሞችን አሁን አሁን እየተመለከትን ነው። በወንጀል የሚጠረጠሩ ባለስልጣናትን ፣ ታጣቂዎችን ፣ ግለሰቦችን ፣ ወዘተ ይዞ ለሕግ ማቅረብ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ መጥቷል። ሲጀመር በአንድ ክልልና ከተማ ጎልቶ ይታይ የነበረው ቀስ በቀስ የብሔር፣ የማንነትን መልክ እየያዘና በሀገሪቱ እየተስፋፋ ይገኛል። በዚህ የተነሳ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሕን ፣ ሰላምን ማክበር ፈታኝ ከመሆኑ ባሻገር ለውጡን በመገዳደር ላይ ነው። ከተሞቻችን ክልሎቻችን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ባህል መሣሪያነት የተጠርጣሪ ወንጀለኞች መሸሸጊያ ፣ መደበቂያ እየሆኑ ነው። ለመሆኑ “ የመማፀኛ ከተሞች “ ስረወ ሀረግ etymology ከወዴት ይመዘዛል ?
የኢትዮጵያ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ባሰናዳው የመፅሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የመማፀኛ ከተሞችን እንዲህ ይበይናል ፦ በእስራኤል በዘመነ ብሉይ ከቤተሰብ ከቤተዘመድ ሰው በዕለታዊ ግጭት ወይም በሌላ ምክንያት ከተገደለ ገዳዩን አሳዶ የመበቀል ደም የመመለስ የጥቁር ደም ልማድ ነበር ። በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች ደም የመመለስ ፣ የመበቀል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መነሻው ከወዴት እንደሆነ እዚህ ላይ ልብ ይሏል። ወደ የዛን ዘመንዋ እስራኤል ስንመለስ በስህተት በአደጋ የሰው ህይወት በእጁ ያለፈበት ሰው ግን ሆን ብሎ ነፍስ ካጠፋው በተለየ መንገድ የሚዳኝበት የሕግ ስርዓት ነበር። የሟች ቤተሰቦች እንዳይበቀሉት ደም መመለሻ እንዳያደርጉት የሙሴ ፣ የመጀመሪያው ፣ የብሉይ ሕግ ( ትዕዛዝ ) ጥበቃ ፣ ከለላ ያደርግለት ነበር ። ከደም መላሹ ፣ ተበቃዩ የሚሸሽበት፣ የሚማፀንበት ከተማ ነበረው። እንደ ዛሬው ፖሊስ ጣቢያ አልያም ማረሚያ ቤት ስላልነበር ስድስት ከተሞች ለመማፀኛነት ተለይተው ነበር። እነርሱም ኬብሮም ፣ ሴኬም ፣ ቃዴስ ፣ ቦሶር ፣ ራሞት እና ጎላን ናቸው ።
ሰውየው ከደም ንጹህ ሆኖ ሲገኝ እና በመማፀኛ ከተማው በዚያው ጊዜ የነበረው ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ መቆየት ነበረበት ፤ ታላቁ መፅሐፍ ዘኀልቁ ላይ 35 ÷ 9- 15 እንዲህ ይነበባል። “…እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው ። ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንተ ለዩ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ።
በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። …” በታላቁ መፅሐፍ ምዕራፍ እንደተመለከተው እነዚህ የመማፀኛ ከተሞች ነፍስ በስህተት በአደጋ ለጠፋባቸው ሰዎች መጠጊያ ነበሩ ። እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው ለእያሱም ከመናገሩ ባሻገር የመማፀኛ ከተሞችን በመፅሐፈ እያሱ 20 ÷ 1- 9 ላይ “… እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው ። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው ። ሳይወድድ ሳያውቅም ሰውን የገደለ ገዳይ እንዲሸሽባቸው በሙሴ እጅ የነገርኋችሁን መማፀኛ ከተሞችን ለዩ፤ ከደም ተበቃዩ መማፀኛ ይሆኑላችኋል።
ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ይሸሻል፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሞ በከተማይቱ ሽማግሌዎች ጆሮ ነገሩን ይናገራል፤ እነርሱም ወደ ከተማይቱ ይቀበሉታል፥ የሚቀመጥበትም ስፍራ ይሰጡታል። ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው፥ አስቀድሞ ሳይጠላው ባልንጀራውን በስሕተት ስለ ገደለው ነፍሰ ገዳዩን በእጁ አሳልፈው አይስጡት። በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ፥ በዚያም ወራት ያለው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቀመጥ፤ ከዚያም ወዲያ ነፍሰ ገዳዩ ይመለሳል፥ ወደ ከተማውም ወደ ቤቱም ሸሽቶ ወደ ወጣባትም ከተማ ይገባል።
በንፍታሌም ባለው በተራራማው አገር በገሊላ ቃዴስን፥ በኤፍሬምም ባለው በተራራማው አገር ሴኬምን፥ በይሁዳም ባለው በተራራማው አገር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያትአርባቅን ለዩ። በዮርዳኖስም ማዶ ከኢያሪኮ ወደ ምሥራቅ ከሮቤል ነገድ በምድረ በዳው በደልዳላው ስፍራ ቦሶርን፥ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ራሞትን፥ ከምናሴም ነገድ በባሳን ጎላንን ለዩ። በማኅበሩ ፊት እስኪቆም ድረስ በደም ተበቃዩ እጅ እንዳይሞት ሳያውቅ ሰውን የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ፥ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመካከላቸውም ለሚቀመጥ መጻተኛ የተለዩ ከተሞች እነዚህ ናቸው። ስለመማፀኛ ከተሞች በዘፅዓት፣ ዘኅልቁ ፣ ዘዳግምና በእያሱ መገለፁ ጉዳዩ በፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንደተሰጠው ያስረዳል ።
ሆኖም ነፍስ ሆን ብለው ላጠፉ ነፍሰ ገዳዮች ግን እነዚህ የመማፀኛ ከተሞች መጠጊያ እንደማይሆኑ ሽማግሌዎችም ካገኟቸው አሳልፈው እንደሚሰጧቸው በኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 19 ÷ 11 – 12 ላይ “… ሰው ግን ባልንጀራውን ቢጠላ፥ ቢሸምቅበትም፥ ተነሥቶም እስኪሞት ድረስ ቢመታው፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ የከተማው ሽማግሌዎች ይልካሉ ።
ከተማጠነበትም ከተማ ይነጥቁታል፥ እንዲሞትም በደም ተበቃዩ እጅ አሳልፈው ይሰጡታል። …” በኦሪት ፣ በሙሴአዊ ትዕዛዛት ዘመን እንኳ የሰውን ልጅ ህይወት ያጠፋ ተላልፎ በሚሰጥበት ወደ መማፀኛ ከተማ እንዳይገባ በሚከለከልበት ገብቶ ሲገኝም ተላልፎ በሚሰጥበት ዘመን ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በ2011 ዓ. ም ላይ የሶስቱ አብርሀማዊ እምነት የክርስትና ፣ የአይሁድና የእስልምና ዕምነቶች መገኛ በሆነችው ታላቋ ሀገራችን ብዙ ክልሎችና ከተሞች ለተጠርጣሪ ነፍሰ ገዳዮች፣ በሰው ልጅ ላይ ስቃይ በመፈፀም ፣ በዘረፋ፣ በግፍ ክስ ለተመሰረተባቸው ግፈኞች “ መማፀኛ “፣ መሸሸጊያ፣ መደበቂያ መሆናቸው እንደ ዜጋ የእግር እሳት ያህል ይለበልባል ።
ከዚህ ጋር በተገናኘ እንደ እናት ሞት ሁል ጊዜ የእግር እሳት ሆኖ የሚለበልበኝ ፣ የሚከነክነኝ ጉዳይ ቢሆንም ብዕሬን ለማንሳት መንስኤ የሆነኝ ግን ከሰሞኑን ሀገራችን 1 . 5 ትሪሊዮን ብር ዕዳ እንዳለባት የሚገልፀው መርዶ እንዲሁም በ1993ቱ ህንፍሽፍሽ በተጋዳላይ መለስ ከጓዶቻቸው ጋር ገሸሽ የተደረጉት የቀድሞዋ የህወሀት ከፍተኛ አመራርና ታጋይ አረጋሽ አዳነ በዚያ ሰሞን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የነሐሴ 4 ፣ 2011 ዓ. ም ዕትም ላይ” ወንጀል ሰርተው የተሸሸጉ ብቻ ሳይሆን ያልተሸሸጉትም መጠየቅ አለባቸው ብዬ አምናለሁ ።
“ ብለው ያስተላለፉት ከብሔር ፈለፈል የወጣ ጠንካራና ዘመኑን የዋጀ መልዕክት እና በዚሁ ጋዜጣ በነሐሴ 1 ፣ 2011 ዓ ም ዕትሙ የብረታ ብረት ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሀምዛ እንደ ዋዛ “… የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን 70 ቢሊየን ብር እዳ እንዳለበት የተወሰነ የፕሮጀክቱ ገንዘብ የት እንደገባ አይታወቅም ። 27 ቢሊዮን ብር እዳ መንግስት እንዲሰርዝለትና ወደ ካፒታል እንዲቀይርለት ጠይቋል። 17 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ለስድስት ዓመታት ጥቅም ሳይሰጡ የተከማቹ እቃዎች አሉት።
123 ቢሊዮን ብር ተመዝብሯል። ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኮንትራቱን እንደተዋዋለ 16 ቢሊዮን ብር ወሰደ። ይህ ብር ምን ላይ እንደዋለው መንግስት ሳያረጋግጥ ገንዘብ ሚኒስቴርን ዋስ አድርጎ 8 ቢሊዮን ብር ከንግድ ባንክ ወሰደ ።…” ይፋ ያደረጉት ዘገባ መገጣጠም ነው ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እንዲሁም የሰላም ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ አንዳንድ ክልሎች ለተጠርጣሪ ወንጀለኞች ከለላ በመሆን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንቅፋት መሆናቸውን ማስታወቃቸው በአናቱ ተጨምሮ ስለ “ መማፀኛ “ ክልሎች እና ከተሞች ከታላቁ መፅሐፍ አጣቅሼ ተንደርድሬአለሁ ።
የአራዳ ልጆች ትዕግስት ስለሌላቸው ይሁን ነገር ለማሳጠር “ ወደ ገደለው …!? “ እያሉኝ ስለሆነ ወደ ገደ ለው። ካለፉት 16 ወራት ወዲህ ለውጡን ተከትሎ በርከት ያሉ “ የመማፀኛ “ ከተሞች ተከትመዋል። ክልሎች ተከልለ ዋል። አሁንም እየተከተሙ ፣ እየተከለሉ ነው። መማፀኛዎቹ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ቢቆረቆሩም መሰረታቸው የተጣለው ከ27 ዓመታት በፊት በማንነት በተቦካው ሲሚንቶና አርማታ ነው። በእነዚያ የመከራ ፣ የጭንቅ ፣ የፈተና ዓመታት ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው በግፍ ተገድለዋል ፣ አካላቸው ጎሏል ፣ ዘር እንዳይተኩ ሆነዋል ፣ ያለጾታ ልዩነት ወሲባዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል፣ እግራቸውን አጥተዋል ፣ በተደጋጋሚ በተፈፀመባቸው ስቃይ ለአእምሮ ህመም ተዳርገዋል ፣ ጥፍራቸው ተነቅሏል ፣ ተሰቃይተዋል።
ቤተሰባቸው ተበትኗል። ለጅምላ እስር ስደት ተዳርገዋል። በአጠቃላይ ለመስማት ለማየት ለማድመጥ የሚከብድ ግፍ በገዛ ዜጎቻቸው እጅ ተፈፅሞባቸዋል። በሚከፍሉት ግብር ደመወዝተኛ በሆነ መርማሪ ፣ በተገዛ የማሰቃያ መሳሪያ ፣ በተገነባ ማጎሪያ ፤ በስማቸው እርዳታ ብድር በሚቀላውጥ መንግስት በተዘረጋ የአፈና መዋቅር ሹመኛ ቀጭን ትዕዛዝ ይህ ሁሉ አረመኔአዊ ድርጊት ተፈፅሞባ ቸዋል። ፍትሕ ተነፍገዋል። ሰብዓዊ ክብራቸው ተዋርዷል። ብዙ ብዙ አንገት የሚያስደፉ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ተፈፅሞባቸዋል።
ፈልገው ያገኙት ይመስል ማንነ ታቸው እየተጠቀሰ ለማሸማቀቅ ተሞክሯል። ከአንድ ወይ ከሌላ ብሔር መወለድ እንደ ስህተት ጥፋት ተቆጥሮ ተሰቃይተዋል። ከዚህ ሁሉ ህመም ስቃይ በላይ የሚያመው ይሄን ሁሉ ፋሽስታዊ ስቃይ ግፍ የፈፀሙባቸው ምንዝሮች ከእነ አለቆቻቸው ለፍርድ ቀርበው አለማየታቸው ነው። እነዚህ አረመኔዎች ለስልጣናቸው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የፈፀሙትን ግፍ ለብሔራቸው ያደረጉት ይመስል ያለአዛዥ ናዛዥ ሲዘርፉ ሲከብሩ ዞረው ያላዩትን የትወደቅህ ያላሉትን ብሔራቸውን ዛሬ መደበቂያ አድርገውታል። ከተሞቹን ፣ ክልሎቹን “ መማፀኛ “ አድርጓቸዋል ።
ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ታላቅ ሙስና Grand Corruption ተፈፅሟል። ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፣ ለስኳር ፋብሪካዎች፣ ለማዳበሪያ ፋብሪካ እና ለሌሎች ከፍተኛ ፕሮጀክቶች በብድርና በእርዳታ የተመደበ ሀብት ለታለመለት አላማ ባለመዋሉና በመባከኑ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል። ከለውጡ በፊት በጥቅም ትስስር ይካሄድ የነበር የኮንትሮባንድ ንግድ የሀገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ ከማድቀቅ ባሻገር የንግድ ውድድሩን በማዳከሙ ኢኮኖሚውን ወደለየለት ቀውስ ዘፍቆት ነበር። ሀገሪቱን ለ1 ነጥብ 5 ቲሪሊዮን ብር እዳ ብትዳረግም ዛሬም የስራ አጥነቱን መቀነስ፣ እንጀራን ከሌማቱ ማድረስ ፣ የኑሮ ውድነቱን ፣ የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ አልቻለም።
በሌለ አቅሟ በ10 ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ሀብት ወደውጭ ሸሽቷል። በአንድም በሌላ በኩል በእነዚህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች ፣ ሻጥሮች የሚጠረጠሩ ወንጀለኞች በ”መማፀኛ “ ከተሞች ክልሎች ተደብቅው ይገኛሉ። ይባስ ብለው በዘረፉት የሕዝብ ፣ የሀገር ሀብት ግጭትን ፣ ቀውስን ፣ የሴራ ፖለቲካን እየቀፈቀፉ ነው ። ከ”መማፀኛ” ከተሞች በሪሞት በመላ ሀገሪቱ በሚዘውሩት ደባ ሀገር እያተራመሱ ውዥንብር እየነዙ ይገኛል። ከለውጡ ወዲህ ከእነዚህ የጥፋት ኃይሎች እና እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል ባዮች በቀጥታ ተልኮ እየወሰዱ በመላው ሀገሪቱ ለዜጎች መሞት ፣ መቁሰል መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ተጠርጣሪዎች እንደ አስተማሪዎቻቸው፣ እንደ ጌቶቻቸው በየክልሉ በየከተማው “ የመማፀኛ “ ከተማ ከትመው ፣ ክልል ከልለው ተደብቀዋል።
ክልሎች ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ እነ እንቶኔ ያን ሁሉ ግፍ ፣ ዘረፋ ፈፅመው እንትና የሚባለው ክልል ደብቋቸው እያለ እኛ ምን እዳ አለብንና ነው አሳልፈን የምንሰጠው በማለት በእልህ የሕግ የበላይነቱን ለውጡን እየተገዳደሩት ነው ። አሁን አሁን “ የመማፀኛ “ ከተሞችም ክልሉም ወደ ሌሎች ክልሎችና ከተሞች ተዛምቷል ማለት ይቻላል። የሕግ አስከባሪው የፌዴራል አካል የሚፈልጋቸው ተጠርጣሪዎች በሁሉም ክልሎችና ከተሞች ስለመኖራቸው አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል ። ፍትሕ ፣ የሕግ የበላይነት ብሔር ፣ ማንነት እንደሌላቸው የተዘነጋበት ዘመን ላይ ደርሰናል ሳያስብል ይቀራል !?
እንደ መውጫ
ይህ በ”የመማፀኛ “ ከተሞች ፣ ክልሎች ተደብቆ ያለ ተጠርጣሪ የጥፋት ኃይል ቀን እስኪጥለው ተያዝሁ አልተያዝሁ በሚል ፍርሀት አርፎ ቢቀመጥ ፣ ቢፀፀት ያባት ነበር። እያደረገ ያለው ግን ሀገሪቱን ወደማያባራ የእርስ በእርስ ግጭትና ትርምስ መዝፈቅ ነው ። ባለፉት 16 ወራት ያደረገውም ይሄንኑ ነው ። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ እስከ በዜጎች መካከል በተቀሰቀሱ ግጭቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ የጅግጅጋው ግፍ እንዲሁም በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድና የገንዘብ ዝውውር ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ሀገሪቱን እየናጣት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም።
በዚህ ሳያበቃ ሺህዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች በማሰማራት በዜጎች መካከል መጠራጠርን ፣ ጥላቻን እየነዛ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲዎቻችን በተደጋጋሚ ለተከሰቱ ግጭቶችም ይሄው የጥፋት ኃይል እጁ እንዳለበት መወራት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የሴራ፣ የደባ ፖለቲካን በጓዳ በማስገባት በኢህአዴግ አባል ሆነ አጋር ድርጅቶች መካከል መተማመን እንዳይኖር ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ከሀገር ቤት አልፎም በጎረቤት ሀገርም መንግስት እስከመገልበጥ መንቀሳቀሱን በዚያ ሰሞን ሰምተናል ።
ስለሆነም መንግስት ከሕዝብ ጋር በመተባበር ይህን ክፉ ኃይል ለሕግ የማቅረብ ጥረቱን የበለጠ ሊያጠናክር ይገባል። ይህ ተግባር ከለውጡም ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ጎን ለጎን እኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ።
( ይቀጥላል…
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011