አዲስ አበባ፡- አሜሪካ ኢትዮጵያ የጀ መረችውን የኢኮኖሚ ሪፎርም በተለያየ መልኩ ለመደገፍ እንቅስቃሴ መጀመሯ ታወቀ።የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለመደገፍ ዩኤስ ኤድ ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ለሦስት ዓመት የሚዘልቅ ፕሮጀክት ትናንት በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ይፋ አድርጓል።
ፕሮጀክቱ ይፋ ሲደረግ የአሜሪካን አምባሳደር በኢትዮጵያ ሚስተር ሚካዔል ሬይነር እንደገለፁት፣ በታዋቂው የሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ዶክተር ሪካርዶ ሁስማን የሚመራ የጥናት ቡድን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ በቀጣይ ሦስት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ይከውናል።ይህ የጥናት ቡድን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት በጥናትና ምርምር እንደሚያግዝ ታውቋል።የጥናት ቡድኑ በዋናነት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማምጣት ያላትን እምቅ አቅም መለየት አንዱ ሥራው ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ያለውን ተስፋና ስጋት የመለየት ሥራዎችን እንደሚያከናውን አምባሳደሩ ገልፀዋል።
አሜሪካ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጓን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ይህ ኢንቨስትመንት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ከማጠናከሩ ባሻገር በጤና፣ ትምህርትና ሌሎችም መስኮች ላይ ኢትዮጵያ ላሳየችው መሻሻል አስተዋፅኦ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።በቀጣይም አሜሪካ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም በተለያየ መልኩ ለመደገፍ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል የተናገሩት አምባሳደሩ ትናንት ይፋ የተደረገው የሦስት ዓመት ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ ፕሮጀክቱ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ የተለያዩ ሙያዊና ገንቢ አስተያየቶችን መስጠት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በዋናነት በታክስ ቁጥጥር ፖሊሲ፣ በሥራ ፈጠራና ድህነት ቅነሳ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አሥራ ስድስት ዓመታት ተጨባጭ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደቻለች ያስታወሱት ዶክተር ይናገር፣ በዚህ እድገት ውስጥ የማይክሮ ኢኮኖሚ አለመመጣጠን፣ ደካማ የኤክስፖርትና ገቢ አሰባሰብ ችግሮች መስተዋላቸውን ተናግረዋል። ይህም በቀጣይ ዓመታት በሚተገበረው የኢኮኖሚ ሪፎርም የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተሻሽሎ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር እንደ ሚቻል ዶክተር ይናገር እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።ለዚህ አሁን ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲና ዩኤስ ኤድ ጋር ይፋ የተደረገው የሦስት ዓመት ፕሮጀክት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011
ቦጋለ አበበ