መልካቸው አንድ አይነት ቢሆንም ባለቤቶቻቸው ግን በስም ሊጠሯቸው አይቸገሩም። ለዘመናት አገራቸውን ያገለገሉ ቢሆኑም አንድም ቀን እውቅና አግኝተው አያውቁም። አፋቸውን አውጥተው አይናገሩ ነገር ሆኖባቸው እንጂ ጀርባቸው የተላጠ፤ ሰውነታቸው የተጋጋጠ፣ አጥንታቸው ያገጠጠ በመሆኑ ስለጉዳታቸው አይቶ መፍረድ አይከብደውም። ከድካምና የሥራ ጫና የተነሳ ሰውነታቸው አልቆ በየበረንዳው ጥግ አንገታቸውን ደፍተው አንዳንዶቹም የዕንባቸው መስመር ከአይናቸው ወርዶ ይታያል። በርሃብ ብዛት ወደ ውስጥ የሰረጎደ ሆዳቸውን ለታዘበ እነዚህ እንስሳት ከአህያ ህልውና ወጥተው ሌላ ገፅ ሊላበሱ የዳዳቸው ሊመስለው ይችላል።
አንዳንዶቹ ደግሞ ሰውነታቸው እንደ ድልብ በሬ አለጥልጦ፣ በቅባት እንደወረዛች ልጃገረድ እያብለጨለጩ በደንዳና ሰውታቸው ለቱሪስት መስህብ የቀረቡ ይመስል ለእይታ የደስ ደስ አላቸው። ይህ ሁሉ ትዕይንት ለመርካቶና እህል በረንዳ አካባቢ ነዋሪዎች አዲስ ባይሆንም ከእነዚህ አካባቢዎች ራቅ ብለው ለሚገኙት ግን አጃዒብ የሚያስብል ሁነት አለው።
በመርካቶ ግርግር ላይ የአህዮች ግፊያን ተጨምሮ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ከሰው ብዛት ጋር ተዳምሮ መንገዱ ለአላፊ አግዳሚ አስቸጋሪ አድርጎታል። በኑሮ ጡዘት በሚናውዘው ማህበረሰብ ውስጥ የእንስሳት ግፊያ፤ የመንገድ ጥበት ላስቸገረው አሸከርካሪ ደግሞ የአህዮች መንገድ መዝጋት ሌላ ራስ ምታት ነው። የቆሻሻ ክምር በመሀል ከተማ እንደ ራስዳሽን ተራራ በተቆለለበት ከተማ ደግሞ የአህዮች ፋንድያ ተጨምሮበት አዲስ አበቤን መልከ ብዙ አድርጓታል።
ወዲህ ደግሞ የትራንስፖርት ታሪፍና የወዛደር የላብ ዋጋ ወደ ሰማይ ባሻቀበት አስቸጋሪ ወቅት አህዮች በርካሽ ዋጋ በከተማዋ አራቱም አቅጣጫ እየከነፉ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠታቸው ጥሩ ጉዳይ ሆኗል። ጠዋትና ማታ በትራፊክ አደጋ የሰው ሕይወት ሲቀሰፍ አህዮች የሰው ሕይወትን ቀጠፉ የሚል ዜና በሌለበት፣ የተሽከርካሪ ነዳጅ ለመግዛት በማደያዎች ረጃጅም ሰልፍ በሚስተዋልባት አዲስ አበባ ነዳጅ አልባ አህዮች ነዳጅ ማደያ ሄደው ቦታ ሳያጣብቡ እንደ አቅማቸው የትራንስፖርት ሥርዓቱን ማሳለጣቸው ደግሞ ተሞጋሽ ያደርጋቸዋል።
አቶ አሰፋ ከበደ ሁለት ልጆችና ሁለት አህዮች አላቸው። ከ18 ዓመታቸው ጀምሮ በውትድርና ሕይወት የአገራቸውን ዳር ድንበር ሲጠብቁ ቆይተዋል። ዳሩ ግን 1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ሲመጣ ከውትድርናቸው ተሰናበቱ። ደመወዝ ይሁን ጡረታ የሚባል አንዳች ነገር የለም። በቃ ለአገራቸው ብዙ እንዳልሆኑ፣ በዱር በገደሉ እንዳልተዋደቁ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ወደቀ። ከዚያም በአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው በቾ በምትባለው አካባቢ ወደ ቤተሰባቸው ዘንድ ሄደው ተጠለሉ።
ትንሽ ቆይተውም ነገሮች እየተለዋወጡ እርሳቸውም የአዕምሮ ታማሚ ሆኑ። ግን በቤተሰባቸው ዕርዳታ ወደ ጤናቸው መመለሳቸው አልቀረም። ትዳርም ይዘው ሁለት ልጆች ወለዱ። ገና የግብርና ሥራ እንዳይጀምሩ መሬት የላቸውም። በመሆኑም አንድ መላ ዘየዱ። ጥቂት ገንዘብ ቋጥረው አዲስ አበባ እህል በረንዳ ወደሚባለው አካባቢ መጥተው ቤት ተከራዩ፤ ከኪራይ በተረፋቸውም ገንዘብ ሁለት አህዮች ገዝተው ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ጭነት እያመላለሱ ኑሯቸውን ይገፉ ጀመር። በዚህ ሥራ ከ10 ዓመት በላይ ቆይተዋል።
አቶ አሰፋ ሁለት አህዮች እንዳሏቸው ሁሉ ልጆችም አሏቸው። ሁለት አህዮቻቸውን ግን ልክ እንደ ልጆቻቸው ነው የሚወዷቸው። የባለቤታቸውንና የሁለት ልጆቻቸው የኑሮ እጣ ፋንታ በሙሉ በእነዚህ ሁለት አህዮች ጀርባ ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ ነውና። እነዚህ አህዮች ከታመሙ የዚህ ቤተሰብም አባላትም ይታመማሉ። ከደከሙም እንደዚያው የቤተሰቡ ገቢም ይዳከማል። ሁለቱ አህዮች ለእነርሱ ሁሉ ነገር ናቸው። የቤተሰቡ አባላት ሲታመሙ ለህክምና፣ ሲራቡ የሚመገቡት፣ ሲታረዙ የሚለብሱት፣ ሲጠማቸው የሚጎነጩት፣ እግራቸው ባዶ ሲሆን ጫማ የሚጫሙት እነዚህ አህዮች ደፋ ቀና ብለው በሚያመጡት ገቢና በአሳዳሪያቸው ብርታት ነው።
አዛውንቱ በየወሩ 1ሺህ 200 ብር የቤት ኪራይ ከፍለው ይኖራሉ። በዚያ ላይ ሁለት ልጆቻቸውን እያስተማሩ ነው። አንደኛው ልጃቸው 10ኛ ክፍል ሲሆን፤ ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ 11ኛ ክፍል ለመግባት እየተጠባበቀ ነው። የቤተሰባቸው ሙሉ ቀለብ እና ወጪ የሚሸፈነው በእነዚህ አህዮች ጥረት በሚገኝ ገቢ ነው። አህዮቹን ለማሳደር ደግሞ በየወሩ 200 ብር ይከፍላሉ። ለሁለቱ አህዮች በየቀኑ ለቀለብ የሚሆን የእህል ንፋሽ እና ግርድ ለመግዛት በየቀኑ 40 ብር ያወጣሉ። ታዲያ እነዚህ አህዮች ራሳቸውንም ቤተሰባቸውን እየመገቡ የኑሯቸውን መሠረት በመሀል አዲስ አበባ እህል በረንዳ አድርገዋል።
አቶ ተሾመ ጣሰው ደግሞ የገዟቸውን ሁለት አህዮች እየነዱ ብር ማግኘትን ልክ እንደ ውርስ ከአባታቸው ተቀብለው ይሠራሉ። ቀደም ሲል ወፍጮ ቤት ይሰሩ ነበር። በአሁኑ ወቅት አባታቸው ደክሟቸው ቤት ውስጥ ቀርተዋል። እርሳቸው ደግሞ ከአዲስ አበባ ራቅ ብለው ዓለም ባንክ የሚባል አካባቢ ነው የሚኖሩት። በጥዋት ተነስተው ሁለት አህዮቻቸውን በአለንጋ ሾጥ! እያደረጉ ከዓለም ባንክ ወደ መርካቶ እህል በረንዳ ያቀናሉ። ከዚያም ሙሉ ቀን ሥራ እያሰሱ ወደ ተገኘው አካባቢ ይጭናሉ።
በቀን እስከ 200 ብር የሚሰሩት አህያ ነጂው፤ የእለት ጉርስ ለማግኘት አራቱን የአዲስ አበባ አቅጣጫ ማሰስ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ገቢ ለማግኘት ከእህል በረንዳ ወደ ቃሊቲ፣ ሸጎሌ፣ ላምበረት ብቻ በአራቱም አቅጣጫ ይከንፋሉ። ማታ ደግሞ ከመርካቶ አዲስ ዓለም ድረስ አህዮቻቸውን እየነዱ ይገባሉ። በቀን ቢያንስ ወደ ዓለም ባንክ ደርሶ መልስ ሲሄዱ አራት ሰዓት ይወስድባቸዋል። በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ በተገኘ ገቢ መላ ቤተሰባቸውን ደጉሙው ይኖራሉ።
ዕድርና ዕቁብም እንዲሁም ሌላ ማህበራዊ ሕይወትን በዚህ ይደጉማሉ። እነዚህ ሁለት አህዮችም በጀርባቸው ጭነት ተሸክመው፤ ለአሳዳሪዎቻቸው የጀርባ አጥንት ሆነዋል። አቶ ተሾመ <<ለዚህም ልክ እንደቤተሰባችን እንወዳቸዋለን፣ እንጨነቅላቸዋን>> ይላሉ። አቶ ከበደም ሆኑ አቶ ተሾመ ስለ አህዮቻቸው ጤና ይፀልያሉ፤ ይጨነቃሉ። አትሙቱብን ብለውም ይለምኗቸዋል።
አደራ አትሙቱብን!
ሁለቱም ሰዎች የአህዮቻቸው ጤንነት ያሳስባቸዋል። ምንም እንኳ እህል በረንዳ አካባቢ ለአህዮቹ ነፃ ህክምና የሚሰጥ ቢሆንም ሥራ ስለሚበዛባቸው ተደጋጋሚ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ህክምናውም እንደ ድሮው ብዙም የሚያረካ እንዳልሆነም ነው የሚናገሩት። ምናልባትም የአህዮች መበራከት ለችግሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው። በተጨማሪም ከአህዮቹ ሞት ጀርባ ብዙ የሚያሳስባቸው ጉዳይ አለ። የቤተሳባቸው የዕለት ጉርስ ማጣት ዋነኛው ጉዳይ ሲሆን፤ እንደ አጋጣሚ አህዮቹ መሀል ከተማ ከሞቱ ከአዲስ አበባ ውጭ ራቅ ብለው መጣል ስላባቸው ለሞቱ አህዮችን ለማስነሳት ክፍያ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።
አንዲት አህያ ለመግዛትም ከ3ሺህ እስከ 4ሺህ ብር ስለሚያስፈልም ቢሞቱባቸው ዳግም ለመግዛትም ይከብዳቸዋል። ለዚህም ሲሉ አትሙቱብን! ብለው ይፀልዩላቸዋል። ሳይንስ አህዮች እስከ 25 ዓመት እንደሚኖሩ ይናገራል። የእኛ አህዮች ግን ከሠባት ዓመት በላይ አይቆዩም። <<የእኛ ምኞት ግን እንዳይሞቱብንና ሳይንስ እንደሚለው 25 ዓመት እንዲኖሩልንም ነው>> ይላሉ።
ገጠመኞች
አህዮቹ በአራቱም አቅጣጫ ሲከንፉ ከፍተኛው ታሪፍ 50 ብር ሊሆን ይችላል። ግን አንዳንድ ሰዎች ከተነጋገሩት በእጥፍ የሚከፍሉ አሉ። ሌሎች ደግሞ ለመክፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ግጭት ፈጥረዋል። አህዮቹ ምንም እንኳን ስልጡን ቢሆኑም በርካታ ጊዜ ያልጠበቋቸው ገጠመኞችን ለማስተናገድ ይገደዳሉ። አህዮቹ ጭነት ሲበዛባቸው እየተንገዳገዱ ከተሽከርካሪ ጋር ይላተማሉ። አልፎ አልፎ የተሽከርካሪ ‹‹ፍሬቻ›› እና ‹‹ስፖኪዮ›› ይሰብራሉ፤ ሰዎችን ገፍተው ይጥላሉ፤ እቃ ይሰብራሉ። በመንገዱ ዳር ያገኙትን ስጥ ደፍተው አሊያም በአፋቸው አፍሰው ይሄዳሉ። ሲያሻቸው ህፃናትን ረግጠው ያልፋሉ፤ አልፎ አልፎም ተገጭተው ይሞታሉ። በዚህ ጊዜ ግን ያለውን ውጣ ውረድ ሲያስቡት ሥራቸው የሰቀቀን በመሆኑ እንደሚጠሉት ነው የሚያስረዱት ባለቤቶቹ።
በተለይም አህዮቹ ተገጭተው ሲሞቱ አሽከርካሪዎች ካሳ ለመከፈል ፈቃደኛ አይሆኑም። የተሽከርካሪ አካልም ሲሰበር ቀላል ክፍያ አይጠየቁም። አንዳንድ ሰዎችም እቃ ሲሰበርባቸው በእጥፍ ለመቀበል ስለሚጥሩ ለግጭት መዳረጋቸውንና እስከ መታሰር መድረሳቸውን ያብራራሉ። ከዚህም ውጭ ሌቦች አህዮቻቸው ሰርቀውባቸው ምርር ብለው ማልቀሳቸውን ያስታውሳሉ።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እቃውን የሚያራግፉበት ቤት ሲደርሱ ምራቅ የሚያስውጥና በጎበዝ ሴት ወይዘሮ የተከሸነ ምግብ ላይ ደርሰው ለመብላት እየጓጉ ምራቃቸውን ውጠው ተመልሰዋል። አልፎ አልፎ ደግሞ ገራገር ሰዎች ይገጥሟቸውና ምግቡን አብረው ሰልቅጠዋል። ብቻ ጥሩ እና መጥፎ በሚሉ ገጠመኞች የተከበበ ሕይወትን እየገፉ መሆኑን ይናገራሉ።
ተማፅኖ
እነዚህ አህዮች ለበርካታ ሰዎች ህልውና እንደመሆናቸው መጠን ለጤናቸው የሚበጅ ህክምና በየጊዜው ቢሰጥ ባለቤቶቹ ምኞታቸው ነው። ከዚህም በዘለለ ከተማዋ ውስጥ ያሉ አህዮች እየተበረካቱ በመሆናቸው መንግስት ሌሎች ዜጎችን አደራጅቶ እንደሚሰሩ ሁሉ እነርሱንም አደራጅቶና ችግር ሲደርስባቸው በሕግ የሚዳኙበትን ቋሚ አሠራር ቢፈጥር ይሻሉ። <<ከተቻለ ደግሞ ከዚህ ሥራ ወጥተን በሌላ ሥራ ላይም ብንደራጅ መልካም ነው። እኛም ተለውጠን፣ ቤተሰባችን ቢለወጥ ይላሉ።
እኛም አርፈን አህዮቹንም እናሳርፍ ነበር>> ይላሉ። በዚያም አለ በዚህ ግን ለጊዜውም ቢሆን አህዮች ሰውን እይደጎሙ ሰዎችም አህዮችን ተጠቅመው በአፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ ኑሯቸውን እየገፉ ነው። ለአየር ንብረት መለወጥም ሆነ ለድምጽ ብክለት በማይታሙ ሰው ሰራሽ ሳይሆን ነፍስ ያላቸው ባለአራት እግር ተሽከርካሪዎች አሁንም አገልግሎት ላይ ናቸው። የአቶ ተሾመም ሆነ የአቶ አሰፋ አህዮች የባለቤቶቻቸውን መላውን ቤተሰብ ቀጥ አድርገው እያስተዳደሩ በችግር የተበሳሳውን ኑሮ ቀዳዳ ለመሸፈን ዛሬም ነገም ስራ ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር