በወጣትነት ዘመናቸው ከበርካታ ሰዎች ጋር ከመጋጨት ጀምሮ እስከ እስር የደረሰ መራራ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። ከእናትና አባታቸው ጋር ተለይተው ማደጉን በከበዳቸው ወቅት ደግሞ ሰባትና ስምንት ቤቶችን ቀያይረው ወንድምና የቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር ተጠግተው ኖረዋል። ኑሮን ለማሸነፍ ዘመድ ጋር ሲኖሩ ሁሉም ለህይወታቸው መሻሻል የበኩላቸውን ቢያደርጉም እርሳቸው ግን ከቁብ ይቆጥሩት እንዳልነበር ያስታውሳሉ።
ከሁሉም በላይ ግን የእናታቸው ሞትና ትዳር ሲመጣ ባህሪያቸውን መቀየሩ ይገርማቸዋል። በአጋጣሚ በጸብና በመጠጥ ምክንያት ህይወታቸው ሊጠፋ የሚችልበት ዕድል እንደነበር የሚያስታውሱት የዛሬው እንግዳችን ከባለቤታቸው ጋር ያገናኛቸው የህይወት መንገድ ግን አሁን ላይ ጠንካራ ሠራተኛ እንዳደረጋቸው ይመሰክራሉ። በኮንስትራክሽን ዘርፉ ተሰማርተውም በርካታ ህንጻዎችን መገንባት ችለዋል።
የዛሬው እንግዳችን አቶ ኤፍሬም ሰሀሌ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ሲወለዱ ለቤተሰባቸው 13ኛ ልጅ ነበሩ። በሁለት ዓመታቸው ገና ዳዴ ብለው ሳይጨርሱና የወላጆቻቸውን ስም በቅጡ ጠርተው አፍ ሳይፈቱ፤ እናትና አባታቸው አብረው ላለመኖር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለያዩ። በ1970ዎቹ መጀመሪያ የተለያየው ቤተሰብ በየአቅጣጫው መበተን ጀመረ። እናታቸው ሦስት ልጆች ይዘው ወደ መርሐቤቴ አቀኑ።
በወቅቱ ደግሞ ከተጓዙት ልጆች መካከል የአሁኑ እንግዳችን አቶ ኤፍሬም አንዱ ናቸው። የተቀሩት ወንድምና እህቶች ከአባት ወገን ናቸው በሚል አዲስ አበባ ቀርተዋል። ህይወት በመርሐቤቴ ፈታኝ እንደነበረች ያስታውሳሉ። አደግ ሲሉም አጎታቸው ጋር በእርኝነቱና መጠነኛ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ያገለግሉ ጀመር።
ዕድሜያቸው ሲጨምር ቀስ በቀስ የገጠሩን ኑሮ ይለምዳሉ ተብሎ ቢታሰብም አልሆነም። 13 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ አንድም የቀለም ትምህርት እንዲያገኙ ያልተደረጉት አቶ ኤፍሬም ቀድሞ የነበሩበትን ከተማ ታሪክ ሰምተዋልና የሸገርን ኑሮ መናፈቃቸው አልቀረም።
የወጣትነት ዕድሜያቸው በእረኝነት ተግባር ብቻ ሊያበቃ መሆኑን በማሰብ ሁልጊዜም እናታቸውን ሲያገኙ መጠየቁ አይሰለቻቸውም ነበር። እናታቸውም በመርሐቤቴ ጓዛቸውን ጠቅልለው ተቀምጠው ነበርና የአቶ ኤፍሬምን ወደ አዲስ አበባ ልሂድ የሚል ጥያቄ መመለስ እንደማይችሉ በመንገር ደምድመውታል። አብረዋቸው ወደ መርሐቤቴ ካቀኑት የአቶ ኤፍሬም ወንድሞች መካከል ደግሞ ታላቃቸው ቀድሞም ወደ ገጠር ከተሞች እየተዘዋወሩ ሥራ ጀምረው ነበርና የከተማን ህይወት ለምደዋል። እናም ታላቃቸው የከተማ ኑሮ ይሻሻል በሚል ወደ አዲስ አበባ ሄደው ወንድምና እህቶቻቸው ጋር ይቀመጣሉ።
በዚህ ወቅት የተቀሩት የአቶ ኤፍሬም ቤተሰቦች ለምን አዲስ አበባ አይመጣም እያሉ ወንድማቸውን መወትወት በመጀመራቸው አቶ ኤፍሬም ወደሸገር እንዲመጡ ተደረገ። ህይወት በመዲናዋ ዳግም ስትቀጥል አቶ ኤፍሬም ያኔ የ15 ዓመት ወጣት ነበር።
በወቅቱ ልደታ አካባቢ ከሚገኝ ወንድማቸው ጋር አርፈው የቄስ ትምህርት ቤት መከታተል ጀመሩ። ከዚያም አንደኛ ደረጃን ባልቻ ትምህርት ቤት ገብተው መከታተሉን ቀጠሉበት። አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍልን ደብል መተው በሁለት ዓመት ውስጥ አራተኛ ክፍል መግባታቸውን አቶ ኤፍሬም ያስታውሳሉ።
5ተኛ ክፍልን አንደኛ ሆነው ከጨረሱ ደግሞ መርሐቤቴ የሚገኙትን እናታቸውን ለክረምት ጎብኝተው እንደሚመለሱ ቃል ገብቶላቸዋል። ይሁንና አምስተኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት በአንደኝነት ሲያጠናቅቁ ግን እናታቸው ጋር እንደማይሄዱና አዲስ አበባ እንደሚቆዩ ይነገራቸዋል።
በነገሩ የተበሳጩት አቶ ኤፍሬም ጠፍተው ከአዲስ አበባ መርሐቤቴ ድረስ እናታቸው ጋር በእግራቸው ለመሄድ ይነሳሉ። አንድ ብለው የጀመሩት እርምጃ እየጠያየቁ ሲኳትኑ ምሽት ላይ አዲሱ ገበያ አካባቢ ያደርሳቸዋል። እናም ለሰፈሩ እንግዳ መሆናቸውን የተረዱ ሰዎች ቤታቸው አሳድ ረው በጠዋት ቁርስ አብልተው በነጋታው ሸኟቸው።
ከስድስት ሰዓታት የእግር ጉዞ በኋላ ደግሞ ከቤት በጠፉ በሁለተኛው ቀን እንጦጦ ፍተሻ ኬላ ይደርሳሉ። በዚያም ፖሊሶችን እንዲሸኟቸው በመጠየቅ እስከ ዘጠኝ ሰዓት እንዲጠብቁ ተደርጎ መኪና በመገኘቱ ተጭነው ይላካሉ። ተሽከርካሪው ደግሞ መድሃኒት የጫነ የእርዳታ ድርጅት ንብረት ነበርና የእናት ናፍቆት ያንገበገባቸው አቶ ኤፍሬም ከመድሃኒቶቹ ጋር ከኋላ ተጭነው መርሐቤቴ ከተማ ምሽቱን ገቡ።
የእርሳቸው መኖሪያ ቀዬ ከከተማው ወጣ ያለ በመሆኑ ደግሞ ከወሰዳቸው ሹፌር ጋር አድረው በጠዋት ወደ እናታቸው መንደር ገሰገሱ። በኋላም አገር ቤት መሄዳቸው ሲሰማ በየከተማው የተለጠፈው የአፋልጉኝ ምስላቸው ወርዶ የአዲስ አበባው ቤተሰብ ስለእርሳቸው መጨነቁ ጋብ አለ።
እናታቸው ጋር ደርሰው ፍቅራቸውን ከተለዋወጡ በኋላ እዚያው ሁለት ዓመት ቆይተው በእረኝነቱ ስራ ተሰማርተው አገለገሉ። በኋላ ላይ ግን መዲናዋ ላይ የሚገኙት ታላቅ እህታቸው እኔ ጋር መኖር ትችላለህ በሚል ንፋስ ስልክ የተባለው አካባቢ አንዲመጡ አደረጉ። ዳግም በመዲናዋ ቆይታቸው እህታቸው ቤት እየኖሩ ግማሽ ቀን ደግሞ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀምረዋል።
ሥራው አነስተኛ ክፍያ ያለውና የጉልበት ስራ የሚበዛበት መሆኑን የተረዱት አጎታቸው ደግሞ እርሳቸው ጋር እየተማሩ መኖር እንደሚችሉ በማሳመን ወደቀጨኔ መኖሪያቸው ወሰዷቸው። የተቋረጠው ትምህርትም ቀጠለና ስምንተኛ ክፍል አጠናቀቁ። በወቅቱ ግን በጉርምስና ዕድሜ ላይ የነበሩት አቶ ኤፍሬም አልባሌ ጓደኞች በመያዛቸው ፀባያቸው አስቸጋሪ ወደመሆን መቀየሩን ያስታውሳሉ።
በየጊዜው ጸብ እና አምቧጓሮ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን በፖሊስ ጭምር ተፈላጊ ሰው ነበሩ። አጎታቸው ጋር ሲጋጩም አንድ ጊዜ ወንድማቸው ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ እህቶቻቸው ቤት እየኖሩ ከሰባትና ስምንት የዘመድ አዝማድ ቤቶች ውስጥ ለመኖር ተገደው ነበር።
ይባስ ብሎ ደግሞ በጸብ ተሳታፊ በመሆን ለሦስት ዓመታት እስር ተዳረጉ። ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ ደግሞ በ1984 ዓ.ም አንደኛዋ እህታቸው ቤት መኖር እንደጀመሩ እናታቸው በጠና በመታመማቸው ለሞት ይዳረጋሉ። በዚህ ወቅት ነበር አቶ ኤፍሬም ብቸኝነትና መረጋጋቱ እንዲሁም ጭምት ባህሪን መላበስ የጀመሩት።
ከዚያም ታላቅ ወንድማቸው ቤት ለረጅም ጊዜያት በመኖር የተረጋጋ ህይወትን መምራት ጀመሩ። በወቅቱ ቅቤ ሊሸጥ ካመጣ ነጋዴ ላይ ተቀብለው ለፈላጊዎች አትርፈው በመሸጥ 300 ብር ማትረፍም ቻሉ። በወቅቱ ደግሞ ሰዎችን ሲያማክሩ ከመርካቶ በጅምላ ገዝተው መዋቢያ ምርቶችን በየአካባቢው ቢያቀርቡ እንደሚያዋጣ ይነገራቸዋል።
እናም በዚህ ንግድ ውስጥ ተሰማርተው ገቢ መሰብሰቡን በአንድ ጊዜ ተካኑበት። ለአራት ዓመታት በንግዱ እንደሰሩ ደግሞ ትዳር መስረቱ፡፡ ትዳር ሲመጣ የፋብሪካ ስራ ተቀጥረው በትርፍ ሰዓታቸው ደግሞ ንግዱን ማከናወናቸውን ተያያዙት። በዚህ ወቅት ነበር በኮንስትራክሽን ስራ የተሰማራ አንድ የቅርብ ዘመዳቸው በፎርማንነት ሰራተኞችን እየተቆጣጠሩ አብረዋቸው እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡላቸው። ጥሪውንም ተቀብለው አቶ ኤፍሬም የተለያዩ ግንባታዎችን ቆመው እያሰሩ ህይወታቸውን መምራት ጀመሩ፡፡
የትዳር አጋራቸው ጥንካሬና ምክር በእጅጉ ያሻሻላቸው አቶ ኤፍሬም ግልፍተኛነቱንና የመጠጥ ሱሶችን እየቀነሱ ስራቸው ላይ ማተኮሩን ተያያዙት። እናም ለሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ከሰሩ በኋላ አንድ የግንባታ ስራ ላይ በግላቸው ለመሰማራት ወደ ዲላ ከተማ አመሩ። በዲላም ስራቸውን አጠናቀው ባገኙት ሙያዊ እውቀት በመታገዝ በእራሳቸው ኮንትራክተርነት የመጋዘን ግንባታ ይዘው መስራት ጀመሩ።
ታታሪነታቸውን የታዘበው የመጋዘኑ ባለቤት ደግሞ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ገንብቶ ነበርና እርሳቸውን በሥራ አስኪያጅነት ቀጥሮ ጥቂት ማሰራት ፈልጓል። አቶ ኤፍሬምም ባላሰቡት የመንገድ ስራ አስኪያጅ ሆነው ጥቂት ከሰሩ በኋላ ወደአዲስ አበባ ባለቤታቸው ጋር ከሁለት ዓመታት በኋላ ተመለሱ።
አሁን ሁለት ልጆችም ተወልደው ትዳራቸውም ሞቅ ሞቅ ብሏል። ከልምድ ባገኙት ዕውቀት የታገዙት አቶ ኤፍሬም በእራሳቸው ስም በሚንቀሳቀሱበት የኮንስትራክሽን ፈቃድ በርካታ ግንባታዎችን ማከናወናቸውን ቀጥለዋል። በተለይ አያት አካባቢ የተለያዩ መኖሪያ ቤቶችንና በተለያዩ አካባቢዎች ባለሶስትና አራት ወለል ህንጻዎችን እየገነቡ ለባለቤቶቹ በማስረከብ ይታወቃሉ። አንድ ህንጻ በሚገነቡበት ወቅት እስከ ሃያ የሚደርሱ ሰራተኞችን ቀጥረው እንደሚያሰሩ የሚናገሩት ኮንትራክተሩ ሚሊዮን ብር የፈሰሰባቸውን ህንጻዎች በጥራት ገንብተው በመጨረስ ከእርሳቸው አልፈው ለሌሎች ሰራተኞችም የስራ በር ከፍተዋል።
እንደየስፋታቸውና መጠናቸው ለተለያዩ የቤትና የህንጻ ግንባታዎች ከ300 ሺህ ብር ጀምሮ በሚሊዮኖች ክፍያ ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ይገልጻሉ። እርሳቸው ደግሞ በስራ ያገኙትን ብር በአግባቡ በማዋል በቀጣይ ጊዜያት የተለያዩ ዘመናዊ የግንባታ ማሽነሪዎችን ገዝተው ድርጅታቸውን ወደ ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ድርጅት ለማሳደግ ውጥን ይዘዋል።
በተለያዩ ዘመዶች ቤት የኖሩባቸውን ጊዜያት በማስታወስ አሁን ላይ የእራሳቸው ቤት ባለቤት መሆናቸውና ለሌሎች ስራ የፈጠረ ዘርፍ ውስጥ በመገኘታቸው ደስተኛ ናቸው። ድርጅታቸው አቅሙን ሲያጠናክር ደግሞ የገቢ መጠናቸውን በማሳደግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን የመቅጠር እድል እንደሚኖረው ተስፋ አድርገዋል።
ለአቶ ኤፍሬም ስራ ምንግዜም ጥረትና እድገትን ይጠይቃል። እድገቱ የሚገኘው ትርፍን በአግባቡ ተጠቅሞ ለሌላ ዓላማ የማዋል ጥረት ሲታከልበት ነው። ማንም ሰው ያተረፈውን ሀብት አልባሌ ቦታ ካዋለው የነገውን ተስፋ ማየት አይችልም።
በኮንስትራክሽን ዘርፉም ሆነ በተለያዩ ሙያዎች ላይ አትርፎ እራሱንም አገሩንም መጥቀም የሚፈልግ ዜጋ በቅድሚያ እጁ ላይ ያለውን ማንኛውንም ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ ነገን የተሻለ ስለማድረግ ማሰብ ይኖርበታል። ነግዶ ማትረፍ ሰርቶ ማግኘት ያለ ቢሆንም ያገኙትን በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ብልህነት መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
ጌትነት ተስፋማርያም