ለውጥ አስፈላጊና ተፈጥሮአዊ ሂደት ቢሆንም ቀላል ደግሞ አይደለም። ሁሉም ነገር በለውጥ ሂደት ላይ ነው። በተፈጥሮ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማህበራዊ ሕይወት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዕድሜ፣ በግንኙነት ወ.ዘ.ተ ለውጦች አሉ። ለውጥን ማስቀረት አይቻልም። በዚህ ክፍለ ዘመን በቴክኖሎጂና በሳይንስ ረገድ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጆች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወት ላይ ዘርፈ ብዙ፣ መጠነ ሰፊና እጅግ ፈጣን ለውጥ ከመካሄዱ የተነሳ ለውጥ ራሱ በሰዎች ዘንድ ምንነቱና ይዘቱ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠና ግድ ብሏል።
በ2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ በርካታ የተቋም ግንባታና የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል። እነዚህ ስራዎች ጅምር ቢሆኑም በአዲሱ 2017 ዓ.ም በስፋት አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡና የሪፎርም ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ ሲከናወኑ ነው ሀገራዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚቻለው። ለዚህ ደግሞ ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ ሁለንተናዊ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። ለውጥ ደግሞ ከራስ ነው የሚጀምረው። ግለሰብ ሲለወጥ ቤተሰብ ይለወጣል። ቤተሰብ ሲለወጥ አካባቢ ይለወጣል። አካባቢ ሲለወጥ ወረዳዎች ይለወጣሉ። ወረዳዎች ሲለወጡ ደግሞ ከተሞች ይለወጣሉ። ከተሞች ሲለወጡ ሀገር ትለወጣለች።
ስለዚህ ለውጥ ማለት ከተለመደው፣ ከታወቀው፣ ከኖረው ወዘተ አሰራርና ሁነት ወደ አዲስ፣ያልተለመደና እንግዳ ወደ ሆነ አሰራር፣ ሁነት ወዘተ የመቀየር ሂደት ነው። ለውጥ ሲታሰብ እና ተግባራዊ ሊደረግ ሲሞከር ሶስት አይነት አስተሳሰቦች ጎልተው ይወጣሉ። የመጀመሪያው አስተሳሰብ የለውጥ እንቅፋት በሆኑ የቀጣይ ሀገራዊና ከባቢያዊ ራዕይ በሌላቸው፤በነበሩ አሰራር ያለአግባብ ተጠቃሚ በሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚቀነቀን ለውጥ አያስፈልግም የሚል አስተሳሰብና አቋም (Reactionary force) ነው።
ሁለተኛው አስተሳሰብ ደግሞ በነባሩ ስርዓት አሰራሮችና የህጎች ማዕቀፎች እንዲሁም አጠቃላይ ሁለንተናዊ አካሄዶች ላይ ፍፁም ጥላቻ ባላቸው፣ ስልጣን የማግኘት ወይም የመጋራት እድል ካጋጠማቸውም ለበቀል በሚነሳሱ ኃይሎች በብዛት የሚቀነቀን አስተሳሰብ ሲሆን ለውጡ መሰረታዊና ስር-ነቃል (Revolutionary change) ሊሆን ይገባል የሚል ነው።
የዚህ አስተሳሰብ ዋነኛው ጉድለት ከነበሩ ስርዓት ምንም የሚጠቅም ነገር የለም ብሎ በጅምላና በጥላቻ እይታ ውሳኔ መስጠት ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው። ይህ አስተሳሰብ በአብዛኛው ገና ታዳጊ በሆኑ ሀገራት የሚዘወተር ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ስር-ነቀል ለውጥ (Revolutionary change) በ1966 እና 1983 በመካሄዱ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል።
ሶስተኛው አስተሳሰብ የበሰለና ያደገ አመለካከት ባላቸው የለውጥ ኃይሎች፣ሚዛናዊና አርቆ አሳቢ በሆኑ ዜጎች ፣ጥልቅ የፖለቲካ እውቀት ባላቸውና በተግባር በብዙ ነገር በተፈተኑ የለውጥ አራማጆች የሚቀነቀን አስተሳሰብ ነው። ለውጡ አስፈላጊና አይቀሬ መሆኑን የሚያምኑ ሲሆን ለውጡ ግን ስር- ነቀል (Revolutionary change) ሳይሆን ጥገናዊ (Reform) መሆን ይኖርበታል የሚሉ ናቸው።
እንደ ፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎች ለአንድ ሀገር አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ለውጥ ያስፈልጋል የሚለው አስተሳሰብ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ለውጡ ግን ሁሌ እንደ ጭቃ ቤት አፍርሶ በመስራት ሳይሆን በቡሎኬት እንደተገነባ ቤት በፅኑ መሰረት ላይ ተገንብቶ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ መሰረታዊ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል በሚል አስተሳሰብ አብዛኞቹ ይስማሙበታል።
ከዚህ አንፃር ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ የለውጥ መንግስት ከዚህ በፊት በነበረው የኢህአዴግ መንግስት የተከናወኑ ስራዎችን ወደማፈራረስ አልገባም። ጥገናዊ ለውጥ ነው ያደረገው። ቀደም ሲል የነበሩ ጠንካራ ስራዎችን ተቋማዊ በማድረግና በማሻሻል ማስቀጠል ችሏል። በተቃራኒው የሀገርን እድገት የሚጎትቱና ወደኋላ የሚያስቀሩ አሰራሮችን በማስወገድ የተሻሉና ሀገራዊ ብልፅግናና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያስቀጥሉ ሪፎርሞችን አካሂዷል። በዚህም የሚታዩ ሁለንተናዊ ለውጦች መጥተዋል።
ስለዚህ አሁንም ቢሆን የተጀመሩ ተቋማዊ ግንባታዎችንና የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠሉ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያ ለውጥ ያስፈልጋታል። ለውጥ ግን ከራስ ይጀምራል። መንግስት እንዲሁ በባዶ ሜዳ ተቋማዊ ግንባታና የሪፎርም ስራ ቢል ሰዎች በራሳቸው መለወጥ ካልቻሉ የታሰበው ሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ሰዎች እንዲለወጡ ደግሞ መንግስት የለውጥ አራማጅ ሆኖ ከፊት በመቅደም የለውጡን መንገድ ለዜጎች ማሳየት ይጠበቅበታል።
ለውጥ ሁሉም ነገር ባለበት እንደማይቀጥል ነገር ግን ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላው ደረጃ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው። “የማይለወጥ ነገር ቢኖር ለውጥ ራሱ ነው” እንደሚባለው፣ ከለውጥ በቀር ሁሉም ነገር የሚለወጥ ነው። ለውጥ ባይኖር ሕይወት ትርጉም አይኖረውም። ሕይወትን አጓጊና አስደሳች የሚያደርገው ለውጥ በመኖሩ ነው። ስለዚህ ለውጥ የመኖር ተስፋ ነው። የለውጥ መኖር ሊፋቅ የማይችል ተፈጥሮአዊ ሕግ ቢሆንም ለውጥ ሁሉ ደግሞ ጠቃሚ ነው ማለት አይደለም።
አዎንታዊ ለውጥ የለውጡ መምጣት በኑሮአችንና በወደፊታችን ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው። አሉታዊ ለውጥ ደግሞ በኑሮአችንና በወደፊታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያመጣል። ስለዚህ አንድ ጤናማ ማህበረሰብ የሚፈልገው ለውጥን ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ለውጥን ጭምር ነው። ከዚህ አንፃር መንግሥት አሉታዊውን ትቶ አወንታዊውን ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል። ሕዝብም ቢሆን አሉታዊ ለውጦችን በመንቀፍ መንግሥት የሚያደርጋቸውን አወንታዊ ለውጦችን መደገፍና ማበረታታት ይኖርበታል።
ሁሌም ቢሆን ለውጥ ውጤት አለው። ለውጥ ውጤት እንዲኖረው ግን መጀመር አለበት። ለውጥ ደግሞ የሚጀምረው ከራስ ነው። የተጀመረ ለውጥ ሂደት ውስጥ ይገባል። ውጤት ከጅማሬና ከሂደት በኋላ የሚመጣ ነው። ለውጥ በሚፈጠርበት ጊዜ ታዲያ ሦስት አይነት ቡድኖች ይኖራሉ። እነዚህም የለውጡ አራማጆች፣ የለውጡ ታዛቢዎችና የለውጡ ተቃዋሚዎች ናቸው። ማንኛውም ለውጥ እንዲህ ዓይነት ሦስት ቡድኖችን መፍጠሩ አይቀርም።
የለውጡ አራማጆች፤ ለውጡ ይመጣ ዘንድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሁሌም ቢሆን ለመለወጥ ዝግጁ የሆኑና አዳዲስ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። ስለዚህ የለውጥ አራማጆች ሁሌም ቢሆን መንግሥት የሚያከናውናቸውን የሪፎርም ስራዎች የሚደግፉ ናቸውና ብዙም ችግር የሚፈጥሩ አይደሉም።
የለውጡ ታዛቢዎች የለውጡ አዎንታዊነትና አሉታዊነት ጥርት ብሎ ያልታያቸው፣ አቋም ለመያዝ ተጨማሪ ጊዜ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው ስለለውጡ በቂ ግንዛቤ አግኝተው ከለውጡ ተራማጆች ጎን እንዲሰለፉ እያንዳንዱ የሪፎርምና የተቋም ግንባታ ስራ ግልፅና በተጠያቂነት መከናወን አለበት። የለውጡ ተቃዋሚዎች ደግሞ የለውጡ አሉታዊነት ያመዘነባቸው እንደመሆናቸው ሃሳባቸውን በመቀበል ከአሉታዊነት ወደ አወንታዊነት እንዲሸጋገሩ የለውጡን አሳማኝ ሃሳቦችን ማቅረብ ተገቢ ነው።
ህዝብ ምክንያታዊ ሲሆን ከለውጥ ደጋፊነት ወደ ለውጥ አራማጅነት ይሸጋገራል። ህዝቡ የለውጥ አራማጅ ሲሆን በለውጡ ውስጥ ያለውን ድርሻ በመለየት ራሱን በአዕምሮና በድርጊት አሳታፊ ያደርጋል። በርግጥ አሁንም ቢሆን ህዝቡ በቅድሚያ እንዲለወጥ የሚፈልገው ነገር ይኖራል። ነገር ግን በቅድሚያ ሕዝቡ በአስተሳሰብና በንቃተ ህሊና ራሱን መለወጥ እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል። ህዝቡ ሳይለወጥ የሚለወጡ ነገሮች እንደሌሉ ሊያስብ ይገባል። ስለዚህ የሚለወጥ ነገር መኖሩን የምንናፍቀውን ያክል ቢያንስ በአስተሳሰብ ልንለውጣቸው የሚገቡ ነገሮች ሊታዩን ይገባል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ የጋራ መግባባት እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ እርስ በእርስ መስማማት ባይቻል እንኳን እርስ በእርስ መግባባት ግን ይገባል። ከመስማት ይልቅ መናገር እየቀደመን ወደ መግባባት ልንመጣ አንችልም። መስማት የመግባባት መሠረት ነው። ከመስማት ይልቅ መናገር ከቀደመ፣ ማን ማንን ሊሰማ ነው? ስለዚህ እንደ ሀገር የመስማት ባህላችን ሊጎለብት ይገባል። ብዙ ጊዜ ከሌሎች ጋር የማንስማማው ሳይገባን ነው። ባንስማማ እንኳን ገብቶን አንስማማ።
ይህንን የለውጥ ጊዜ ራሳችንንና አስተሳሰባችንን እያየን ለመለወጥ እንጠቀምበት። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ እየተለወጠ ያለው ነገር ብዙም ዘላቂነት አይኖረውም። ‹‹ከሚሰማ ይልቅ የሚያዳምጥ ብፁዕ ነው›› እንደሚባለው መስማት ከመናገር ይበልጣል፤ ማዳመጥ ደግሞ ከመስማትም በላይ ነውና ከፍረጃና ለውጥን ከመኮነን በፊት አድማጭ መሆን ተገቢ ነው።
የፊዚክስና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቁ ኩርት ሌዊን የለውጥ ሞዴልን በተመለከተ እ.ኤ.አ በ1940 ማቅለጥ – መለወጥ – ማቀዝቀዝ በሚል ያስቀመጠው ጠቃሚ የለውጥ ሞዴል ይጠቀሳል። ይህን ሞዴል ለማብራራት አራት ማዕዘን በረዶን ወደ ሦስት ማዕዘን ለመለወጥ ያለውን ሂደት መመልከት ይቻላል። በመጀመሪያ አራት ማዕዘኑ በረዶ እንዲቀልጥ ይደረጋል። ቀጥሎ በረዶው በቅርፅ መለወጥ ይችላል። ከዛ አራት ማዕዘኑን በረዶ በሦስት ማዕዘን ቅርጽ ይደረጋል። በረዶው ሶስት ማዕዘን ሆኖ እንዲቀር ግን እንደገና ማቀዝቀዝ ያስፈልጋል።
ይህንን ሞዴል የማኔጅመንት ኤክስፐርቶች በአንድ የቢዝነስ ወይም የድርጅት መዋቅር ላይ ለውጥ ለማምጣት ይጠቀሙበታል። እንደ ሀገርም እንዲቀልጥ የተደረገ ብዙ ነገር አለ። የቀለጠው ነገር ለለውጥ አመቺ የሆነ ከባቢ ፈጥሯል። የሕዝብ ስሜት መነሳሳት፣ የነበረው ተቃውሞና እንቅስቃሴ የነበረው ነገር እንዲቀልጥ አድርጎታል። ይህ መቅለጥ ደግሞ በሀገሪቱ ላይ ባልተለመደ ሁኔታ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል። በዚህ የአመራር ለውጥ አብዛኛው ሕዝብ ደስተኛ ነው። ነገር ግን ይህ ለውጥ ውጤታማ፣ የጸናና ከዳር የሚደርስ እንዲሆን ማቀዝቀዝ ያስፈልጋል። በተለይ አሁን የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራ ወደኋላ እንዳይመለስ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት። ተቋም የመገንባት ሥራውም እንደዛው።
ምናልባት ጥያቄው የቀለጠውን ማን ያቀዝቅዘው? የሚል ይሆናል። ስናቀልጥ የነበርን ሰዎች ሁሉ በማቀዝቀዙ ላይ ድርሻ ሊኖረን ይገባል እንጂ ይህንን የማቀዝቀዝ ሂደት ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ አይገባም። ስለዚህ የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ከዳር እንዲደርስ የሕዝቡን ያልተቆጠበ ድጋፍ ይፈልጋል። ከመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ደግሞ ሌት ተቀን ሥራ ይጠይቃል። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሪፎርም ሥራውን ለማስቀጥል በየደረጃው ተሳትፏቸውን ማሳየት አለባቸው። ያኔ የሚታሰበውን ብልጽግና በኢትዮጵያ ማረጋገጥ ይቻላል!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም