አምና ይህን ጊዜ …

እንደመነሻ …

ዕለቱ አዲስ ዓመት ሊገባ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የዓውደ ዓመት ዋዜማ ነው። ሁሌም ዓመት በዓል ሲደርስ የሚኖረው ግርግርና ዝግጅት ዛሬም ቀጥሏል። አዎ! ዓውደ ዓመት ነው። ለዚያውም አዲስ ዓመት። ይህን ጊዜ ሙስሊም ክርስቲያኑ በእኩል ይጋረዋል። አዲስ ዓመት የእከሌ ብቻ አይባልም። ሁሉም በአንድ ያከብረዋል።

ዘመን መለወጫ ለብዙዎች የአዲስ ብስራት ምልክት፣ የመኖራቸው ብሩህ ተስፋ ነው። በርካቶች አሮጌውን ሸኝተው አዲሱን ሲቀበሉ ውስጣቸው ለሌላ ዕቅድ ይዘጋጃል። አዲስ ዓመት ሲመጣ ከፊት ከጀርባው መልካም ትርጉም ይዞ ነው። ይህ ጊዜ ከበዓላት ሁሉ ይለያል። ከዓውደ ዓመቶች ልቆ ደምቆ ይታያል።

ይህን እውነት በውስጤ ይዤ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሆነው ጉዳይ በሀሳብ ተመላለስኩ። አሁንም ድረስ የማልረሳው ነውና ጊዜው ጊዜ ላይ ሲያቆመኝ ሐቁ ትውስ ሊለኝ ግድ ሆነ። እናም በወቅቱ ያየሁትን እማኝነት ዛሬም ዳግም ላወሳው መዝገቤን ገላለጥኩ። እነሆ ትውስታዬን ተጋሩት።

አምና በአዲስ ዓመቱ ዋዜማ በዕለተ ‹‹በጎ ፈቃድ ቀን›› ከፊቴ የቆሙት ወገኖች የተስፋ ጭላጭል ውስጣቸው ያለ አይመስልም። በሁሉም ገጽታ ኃዘን ከጉስቁልና ይነበባል። አብዛኞቹ በትካዜ እንደተዋጡ ነው። ገሚሶቹ የውስጣቸውን እያወጉ ስለብሶታቸው ማልቀስ፣ ማንባት ይዘዋል።

ከወላጆቻቸው ጋር የመጡት ሕጻናት ይህ እውነት የገባቸው አይመስልም። የወላጆቻቸውን ጭንቀት እየተጋሩ አይደለም። እንደ ልጅነታቸው ከወዲያ ወዲህ ይቦርቃሉ፣ ይሮጣሉ። ነፍስ ያወቁት ደግሞ የእናቶቻቸው ስሜት ተጋብቶባቸዋል። ፊታቸው ላይ ፈገግታ አልባ ገጽታ ይነበባል።

ዕለቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታስቦ የሚውለው ‹‹የበጎ ፈቃድ ቀን›› ነው። በዚህ ቀን በርካቶች ሌሎችን በበጎነት ስሜት ይጎበኛሉ፣ የአቅማቸውን አካፍለው፣ የውስጥ ስሜትን ይጋራሉ። አሁን ላይ ይህ የአብሮነት ባሕል መለመድ ጀምሯል። በየቤቱ ዕንባን የሚያብሱ፣ ችግርን የሚጋሩ ወገኖች እየበረከቱ ነው።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የታደሙት ሴቶች ለቤቱ እንግዶች አይደሉም። ከዓመት በፊትም ይህን ጊዜ በዚህ ስፍራ ተገኝተው የቀኑን ትርጉም ተጋርተዋል። አሁን ደግሞ ለየት ባለ ዝግጅት የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ከዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ጋር በመቀናጀት ‹‹አለናችሁ›› ብለዋቸዋል።

ለዓውደ ዓመቱ ጓዳ ለእያንዳንዳቸው ሀምሳ ኪሎ ዱቄት፣ ማካሮኒና ፈሳሽ ዘይት ለስጦታ ተዘጋጅቷል። አብዛኞቹ ዓይናቸውን አላመኑትም። በአድናቆት የሚያስተውሉ፣ በሆነላቸው ሁሉ አብዝተው የሚያመሰግኑ ወገኖች ገጽታቸው ወገግ ብሏል።

ሕጻናት ልጆቻቸው ለእነሱ የሚበጁ የትምህርት ቁሳቁሶች በመኖራቸው ተደስተዋል። ሁሉም የዝግጅቱን መጀመር በጉጉት እየጠበቁ ነው። የበጎ ቀን ስጦታዎች ከመበርከታቸው በፊት በአዳራሹ የተገኙት ወገኖች የልባቸውን ይተነፍሱ ዘንድ ዕድል ተሰጣቸው። ሁሉም የውስጣቸውን ሚስጥር፣ የኑሯቸውን ገመና ለመተንፈስ ተሽቀዳደሙ።

በዝግጅቱ ከታደሙት መሐል የመጀመሪያዋ ተናጋሪ በፍጥነት ከነበረችበት ተነስታ ስትወጣ አየኋት። አወጣጧ ድንገቴ ነበር። አስቀድማ አምርራ እያለቀሰች መቆየቷን አስታውስኩ። ልክ እንደኔ ሁሉ ሌሎች ዓይኖች አተኮሩባት።

ወደ መሐል ቀርባ ንግግር ከመጀመሯ ፊቷ በአንዴ መለዋወጥ ያዘ። ኅዘን ያጠላው ገጽታዋ በዕንባ ሊታጠብ አልዘገየም። በምስጋና የታጀበው ቃል ደግሞ ብቻውን አልተገለጸም። የሕይወትን ምስጢራት፣ የኑሮ ፈተናዎችን አንድ በአንድ ሊያሳየን መዝገቡ ተገለጠ።

ወጣቷ ተናጋሪ የታዳሚው ውስጠት በኅዘን አስደፋች። ከአንደበቷ የሚፈልቁ እውነታዎች የእያንዳንዱን አድማጭ ስሜት ሊፈትኑት ግድ ሆነ። በዕንባ የታጀበ ሐቅ፣ በኅዘን የተሰበረ እውነታ እንዲህ መሰማት ጀመረ።

‹‹አንድ ወር ሙሉ የደከምኩበትን ገንዘብ ያገኘሁት ዛሬ ‹‹እማዬ! ዱቄቱ ላይ ተኝተን ፎቶ እንነሳ ››

ነበር። አንድ ሁለት ብዬ ሰባት መቶ ብር ቆጠርኩ። ይህ የላቤ ወዝ፣ የጉልበቴ ዋጋ ነው። አማራጭ የለኝም። ገንዘቡ ውሎ ካደረ ይጠፋብኛል። በዚህ ብር ላደርግ የምችለው ደግሞ ጤፍ መግዛት ብቻ ነው። ሰባት መቶ ብሩን ይዤ ከገበያ ሄድኩ። አምስት ኪሎ ጤፍ ተመዝኖልኝ ይዤው ወጣሁ። ወዲያው ምን እንደማደርገው ጨነቀኝ።

ጤፉን ማበጠር ፣ማነፈስ አልፈለኩም። ይህን ከሞከርኩ ብን ብሎ ሊያልቅብኝ ነው። አሁንም ጭንቅ ጥብብ አለኝ። ስጋት ቢይዘኝ ጤፉን ማበጠር ተውኩት። በዚህ ስሜት ሳለሁ በድንገት አንድ የስልክ ጥሪ ለጆሮዬ ደረሰ። ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወይዘሮ ብርሃኔ ደመቀ ነበረች።

የደወለችበትን ምክንያት ስትነግረኝ በእጅጉ ደነገጥኩ። ልክ እንደአምናው ርዳታ ሊሰጠኝ መሆኑን ስሰማ በእጅጉ ገረመኝ። ውስጥ ደርሼ ሃምሳ ኪሎ ዱቄቱን ስመለከት ደግሞ ሸርተት ያልኩ እስኪመስለኝ ውስጤ ካደኝ። ዓይኔን አላመንኩም።

‹‹ኧረ ጉድ ፈላ!›› ስል ጮህኩ አሁንም አላመንኩም። እውነት ይህ ሁሉ ዱቄት እኔ ቤት ሊገባ ነው? ስል ራሴን ጠየቅሁ። መለስ ብዬ ማኮሮኒውን፣ አምስት ሊትሩን ዘይት አየሁት። እሱም የኔ ነው። ስቅስቅ… ብዬ አለቀስኩ።

ከጎኔ የነበሩት እማማ ለምን ታለቅሻለሽ ሲሉ ተቆጡኝ። በእርግጥ ዛሬ ማልቀስ አልነበረኝም። ግን ምን ላድርግ እጅግ ደስ ብሎኝ ነው። አዎ! ዛሬ አለኝ፣ ሀብታም ነኝ። ወግ ደርሶኛል። ቡና አፍልቼ ጎረቤቶቼን እጠራለሁ። እኔ አስተዳደጌ በድርጅት ውስጥ ነው። ቤተሰብ የለኝም። ዘመዶቼን አላውቅም።

በሕይወቴ ሁለት ጊዜ ‹‹ሰርፕራይዝ›› ሆኛለሁ። አንዱ ባደኩበት ድርጅት አብሮ አደጎቼ ‹‹ዛሬ ልደትሽ ነው›› ብለው ኬክ የቆረሱልኝ ቀን ነው። ዛሬ ደግሞ በእናንተ ፊት የተደረገልኝ ታላቅ ስጦታ ሁለተኛዬ ሆኗል። ከጎኔ ያለችው ልጄ በሆነው ሁሉ ተገርማለች። እሷም እንደኔ ዓይኗን አላመነችም። እናም ደጋግማ እንዲህ አለችኝ ‹‹እማዬ ዱቄቱ ላይ ተኝተን ፎቶ እንነሳ››

እኔም እውነትሽን ነው ልጄ ቤታችን ስንገባ ሁላችንም ተሰባስበን ፎቶ እንነሳበታለን›› አልኳት። የሁሉም ታዳሚ ስሜት እንደተረበሸ ቀጣይዋ እናት ከወንበሯ ተነሳች።

ይህቺ ሴት በአካል እራሷን ከምትመስል ልጅ ጋር አይቻታለሁ። አዎ! አልተሳሳትኩም ልጇ ነች። እናት ጎስቋላ ፊቷ ብዙ ይናገራል። ከንግግሯ በፊት ዕንባ እያነቃት ነው። ሆድ በባሰው አንደበቷ የውስጧን ለመተንፈስ ሞከረች። ሳግ የያዘው ድምፅ እንደምንም አሸንፎ ለብዙኃን መሰማት ጀመረ።

‹‹ልጄ ሊደፍሯት ባሉ ሰዎች በጩቤ ተወግታለች››

እኔ ቤተሰቦቼን አላውቅም። ያደኩት በሌሎች እጅ ነው። አስራ አንደኛ ክፍል ሳለሁ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቅሁ። አብረን መኖር ጀመርን። አረገዝኩ። ሴት ልጅም ወለድኩ። ይህን ያወቀው ባለቤቴ አብሮኝ መዝለቅ አልፈለገም። በድንገት ከነልጄ ትቶኝ ጠፋ። ከዚህ በኋላ የነበረው ሕይወት የፈተና ሆነ። እሷን ይዤ ጎዳና ለጎዳና መንከራተት ያዝኩ።

መኖሪያችን ጎዳና ቢሆንም ልጄ እንደምንም በውጣ ውረድ መሐል አደገች። የጎዳና ሕይወት ግን ብዙ ችግር አመጣብን። ልጄ ሊደፍሯት በሞክሩ ጎረምሶች በጩቤ ተወጋች። ይህን ችግር ያስተዋለው ወረዳ ዘጠኝ እንደ ቤተሰብ ሆነኝ።

በአሁኑ ግዜ የወረዳው ሴቶችና ሕጻናት በቀን የመደብ መኝታ እየከፈለልኝ በቤት ውስጥ አድራለሁ። እኔ እስካሁን ወገን ዘመድ እንደሌለኝ አስብ ነበር። አሁን ግን በእናንተ ሁሉን አግኝቻለሁ። ስላደረጋችሁልኝ በጎነት ሁሉ ምስጋናዬ ከልብ ነው።

‹‹ተጠልቼ የኖርኩ ሰው ነኝ››

ያለአባት የሚያድጉ የሁለት ልጆች እናት ነኝ። የአስራ ስድስት ዓመቱ ልጄ በድንገት ወድቆ የነርቭ ታማሚ ሆኗል። ከዚህ ቀድሞ በሰዎች እገዛ በዊልቸር ይሄድ ነበር። አሁን ግን በመጠኑ ተሽሎት በእግሩ እየተራመደ ነው። በኑሮዬ ችግረኛ ነኝ። የእኔ አቅም ጨው በርበሬ ከመግዛት አያልፍም። ጓዳዬን የምታውቅ አንዲት ሴት ግን ሙሉ የቤት ወጪዬን ትሸፍናለች።

ማንኛውንም ሥራ አልንቅም። ወንዶች የሚሠሩትን ሁሉ እየተሸከምኩ ልጆቼን አሳድጋለሁ። ዕውቀት የሚያስፈልገውን ግን ትምህርት ስለሚጠይቅ አልሞክረውም። እንዲያም ሆኖ ሰዎች ሊቀርቡኝ አይፈልጉም። ሕመሜ ስለሚታወቅ ተገልዬ፣ ተጠልቼ የኖርኩ ሰው ነኝ።

ዛሬ መንግሥት ቤት ሠርቶ አስረክቦኛል። ይህ ሲታወቅ ትናንት በሩቁ የሚሸሹኝ ሁሉ ለሰላምታ እጃቸውን ይዘረጋሉ። በሕይወቴ ብዙ ሰዎች ቤቴን አንኳኩተዋል። እናንተ ደግሞ በዛሬው ቀን ለበዓል የሚያስፈልገኝን አሟላችሁልኝ። እጅግ በጣም አመሰግናለሁ ።

‹‹ዘንድሮም አስታወሳችሁን ››

ይህች ሴት ተናግራ እንደገባች አንዲት ትልቅ እናት ወደ መድረኩ ብቅ አሉ። ከመምጣታቸው አስቀድሞ ከአንዲት ልጃቸው ጋር ተቀምጠው ይጫወቱ ነበር። የእናትና ልጅ ቀረቤታ ዓይን ይስባል። ልጅ በየምክንያቱ እያቀፈች ትስማቸዋለች። እሳቸውም በተለየ ስስትና ፍቅር ያስተውሏታል።

ወይዘሮዋ ሰውነታቸው ወፍራም በመሆኑ ችግር አይቷቸው የሚያውቅ አይመስልም። ገጽታቸው ፈገግ፣ ፈካ ያለ ነው። ያያቸው እንዲህ ይገምት እንጂ ንግግር ከመጀመራቸው የታዳሚውን አንገት በኃዘን አስደፉት ።

‹‹አንቆርጫ›› ከሚባለው ሰፈር ተከራይቼ እኖራለሁ። የስኳር ታማሚ ነኝ። በየቀኑ ለበሽታው መድኃኒት መውሰድ ግዴታዬ ነው። እኔ ግን አንዳች መተዳደሪያ የለኝም። ለነፍስ ያሉ አጉርሰው ያለብሱኛል። ልጆቼን የማልስ የማቀምሰው የለኝም። እነሱን ለማኖር ስል ግን ‹‹ቡሌ›› እየወሰድኩ አሳድጋቸዋለሁ።

ከዚህ በፊት ሠርቼ ለመብላት ጉልበቴ የበረታ፣ ውስጤ የጠነከረ ነበር። አሁን ሕመሙ አቅሜን አዳክሞታል። ከቀናት በፊት የምቀምሰ፣ የምልሰው አልነበረም።በቀደም በባዶ ሆዴ ከቤት ወጣሁ። ከመንገድ በድንገት ራሴን ብስት አንዲት ሴት ስኳር ሰጥታኝ ሕይወቴ ተረፈ።

ልጆቼን ይዤ በኪራይ እኖራለሁ። ለቤቱ ግን እምከፍለው የለም። ይህች ትንሽ ልጅ ግን ማስቲካ እየሸጠች የወር ኪራዩን ትሸፍናለች። አምና ይህን ጌዜ ለልጆቻችን ደብተር ሰጥታችሁን ነበር። አሁንም ጊዜው ትዝ ብሎኝ ሳስባችሁ ቆይቻለሁ። እናንተ ግን ፈጽሞ አልረሳችሁንም። ዘንድሮም አስታወሳችሁን። ከምስጋና ውጭ ምን ልል እችላለሁ? ብድሩ ይግባችሁ እንጂ።

‹‹የሃያ አምስት ዓመት ፀበልተኛ ነኝ››

ያመኛል። ለሕመሜ ፈውስ ለመሻት እንጦጦ ማርያም መጠመቅ ከጀመርኩ ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ሆኗል። አንዲት ልጅ አለችኝ። ይዣት ስመጣ የሦስት ዓመት ሕጻን ነበረች። የምኖረው በቤት ኪራይ ነው። አከራዮቹ እንዳሻቸው ‹‹ውጭ ፣ ግቢ›› ይሉኛል። እንዲያም ሆኖ ኪራይ የምከፍልበት ቋሚ ገቢ የለኝም። ዛሬ ይህ ድርጅት ድጋፉን ሲሰጠኝ ከልብ ተደሰትኩ። በሆነልኝ ሁሉ ከልብ አመሰግኛለሁ።

የሴና እናት ሌሊሴ

ፈገግታ ያበራው ገጽታ ጆሮን ከሚስብ አንደበት ሲዳመር የሌሊሴ ውበት ይበልጥ ይጎላል። ሌሊሴን የማያውቅ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኛ የለም። እሷ የፕሬስ የቅርብ ቤተሰብ ሆናለች። ደስተኛ ልጇ ሴና በሠራተኛው ዕቅፍ ያደገች እንቦቃቅላ ናት። እንደ እናቷ ፍልቅልቅ የሆነች ሳቂታ ሕጻን ።

ሌሊሴ ከዓመታት በፊት ከድርጅቱ አጥር በአጭር ርቀት ተቀምጣ ትውል ነበር። የእሷ መቀመጥ የሚለውጥ ሥራ አልነበረም። አላፊ አግዳሚው ያለውን እንዲጥልላት ለመለመን እንጂ። ደግነቱ በርካታው መንገደኛ አይቶ አያልፋትም። ቆንጅዬዋን ሕፃን ያየ ሁሉ በኃዘኔታ የእጁን ይጥልላታል።

የሌሊሴ ሕይወት ግን በዚህ መስመር አልቀጠለም። ከቀናት በአንዱ በአንዲት መልካም ሴት ዓይኖች ተጎበኘች። ይህች ሴት ቀረብ ብላ ስለሥራ፣ ስለራስን መቻል አዋየቻት። ይህ እውነት የሌሊሴም ነበርና ዓይኗን አላሸችም። ከቀናት በኋላ የድንች መጥበሻና አስፈላጊ ቁሶች ከእጇ ደረሱ። ይህ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቅርብ አጋሯ ሆነ። ሌሊሴ ልመናን ተጠይፋ ወደ ሥራ ፈጥና ገባች።፡

ትናንት ለምፅዋት እጃቸውን የዘረጉላት ዛሬም ገንዘብ ይዘው የላቧን ዋጋ ገዟት፣ ቀመሱላት። ደንበኞቿ በረከቱ። ስለሆነው ሁሉ ‹‹አድናቂዎቿ ቃል አጠራቸው። ትንሽዬዋ ሴና ከድርጅቱ የሠራተኛ ልጆች አንደኛዋ ሆና በሕጻናት ማቆያ መዋል ጀመረች። ሌሊሴ ታሪኳ ፍጹም ተቀየረ። በየጊዜው ጥሩ ትርፍ ማግኘት ያዘች። ዕቁብ ገባች። ገንዘብ ቆጠበች ።

ዛሬ ሌሊሴ ከእንግዶቹ መሐል አንደኛዋ ሴት ሆናለች። እሷ ግን እንደሌሎቹ የከፋ ችግሯን እያወራች አይደለም። በጣፋጭ አንደበቷ ደግማ ደጋግማ ‹‹አመሰግናለሁ›› እያለች ነው።

አዎ! ዘንድሮ የትናንትናዋ ሴና ተማሪ ልትሆን ወግ ደርሷታል። ለዚህ ሕጋዊነት አስፈላጊውን ሁሉ ያሟላላት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው።

ፕሬስ እንደ እናት በሚጦራቸው እማማ ግምጃ ዋስትና የሴናን ሕጋዊ የትምህርት መታወቂያ ለማውጣት ችሏል። ወደፊት በትምህርት ዓለም ለሚኖረው ማንኛውም ድጋፍም ከጎኗ አይርቅም።

ይህ ብቻ አይደለም። ሌሊሴ አሁን እየሠራችበት ከሚገኘው የፕሬስ ድርጅት አካባቢ ያለአንዳች ችግር በሥራው እንድትቀጥል በሰነድ የተደገፈ ሕጋዊ ማረጋገጫ አግኝታለች። ዛሬ የሌሊሴ ድምፅ ከሌሎች ሁሉ ይለያል። የትናንት ታሪኳ ከዛሬው ፍጹም ተቀይሯል። ስለነገው አሁን ላይ ቆማ በብሩህ ተስፋ ትሮጣለች ።

ዘንድሮ…

ዘንድሮ ሌላ አዲስ ዓመት ነው። አምና ይህን ግዜ እነዚህን ድምፆች ያሠሙን ወገኖች ሕይወት ምን እንደሚመስል አይታወቅም። ዘንድሮ ጊዜ ወስዶ የጎበኘ፣ የጠየቃቸው የለም። የኑሮ ውድነቱ ጫንቃቸውን ያገበጣቸው፣ ወላጆች በትምህርት አምሮት የሚሰቃዩ ሕጻናት የወገኖችን ድጋፍ ይሻሉ። ልክ እንደዓምናው በረከት። መልካም ዓዲስ ዓመት።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You