አገልጋይነት ክብር ነው!

አገልጋይነት ክብርን፣ ሞገስን፣ የራስ ፍላጎትንና ጥቅምን ወደ ጎን ትቶ ለሌሎች መስራት ነው። አገልጋይነት ከአንገት በላይ ሳይሆን ከልብ በመነጨ መልኩ ሌሎችን ማገዝ ነው። አገልጋይነት ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ከፍ ማድረግ ነው። አገልጋይነት በራስ ሳይሆን በሌሎች ደስታ መርካት ነው። በበጎ ፍቃደኝነት ሌሎችን ለመርዳት ራስን ማዘጋጀት ነው። የሰዎችን ችግር መረዳትና መጋራት ብሎም መፍትሄ መፈለግ ነው። አገልጋይነት ክብር ነው!

አገልጋይነት ሲባል ታዲያ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ተገድቦ የሚቆይ ሳይሆን ከቤተሰብ አንስቶ እስከ ሀገር የሚዘልቅ ነው። በቤተሰብ ውስጥ አገልግሎት አለ። አንዱ አካባቢ ሌላውን አካባቢ ያገለግላል። ወረዳዎች ሕዝብን በልዩ ልዩ መልኩ ያገለግላሉ። ከተሞችም እንደዛው። ሀገርም ሕዝቧን በሕዝቧ ታገለግላለች። አዲሱ 2017 ዓ.ም የአገልጋይነት ዓመት እንዲሆን ተሰይሟል።

አገልጋይነት የሚለው ፅንሰ ሀሳብ መልከ ብዙ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን ስጋዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሕሊናዊና ስብዕናዊ እርካታዎችን የሚያጎናጽፍ እሴት ወይም የማንነት መገለጫ እንደሆነ በሰዎች ዘንድ ሲነገር ይሰማል። በአሁኑ ዘመን ደግሞ የአገልጋይነት ትርጉም ለአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ተቀጥሮ መስራትና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት የሚል ጥቅል ትርጉም ተሰጥቶታል። ይሁን እንጂ አገልጋይነት በውልና በስምምነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ሳይሆን ከራስ በጎ የማድረግ ሀሳብ የሚመነጭ በመሆኑ ገደብ የሌለው ጽንሰ ሀሳብ መሆኑን የሚገልጹም አልጠፉም።

ሕዝብ የሰጠው አደራና ኃላፊነት ላለበት መንግስት ደግሞ አገልጋይነት ዋንኛ እና መሰረታዊ አልፎም ዘላቂነቱን ማረጋገጫ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም። ምክንያቱም መንግስት ወደ ስልጣን የሚመጣው በሕዝብ ይሁንታ ነውና። በሕዝብ ይሁንታ ማለትም በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት ደግሞ ቃል በገባው መሰረት ሕዝብ የማገልገል ትልቅ ኃላፊነት አለበት። የአገልጋይነት ምሳሌ ሆኖ መታየትም ይጠበቅበታል።

ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሰረት መንግስት ሲቪል ሰርቪስ እያለ በሚጠራው የስራ አወቃቀር ውስጥ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰራተኞች እንዳሉ ይነገራል። እነዚህ በመንግስት የስራ መዋቅር ውስጥ ያሉና ሕዝብን ለማገልገል የተሾሙ አልያም የተቀጠሩ ናቸው። ስለዚህ የነዚህ ሰራተኞች ተቀዳሚና ዋነኛ ተግባራቸው በቅንነትና ታማኝነት ሌላ ነገር ሳይጠብቁ ሕዝባቸውን ማገልገል ነው።

‹‹ሲቪል ሰርቪስ›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ወደ አማርኛ ተወስዶ ሲተረጎም የመንግስት ስራ/አገልግሎት የሚለውን ትርጉም ይሰጣል። በ1940ዎቹ መጀመሪያ የእንግሊዝ ቢሮክራሲ የሆኑ አንዳንድ አሰራሮች በሕንዶች ተለምደው ከዛም በሂደት እነዚሁ አሰራሮች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ‹‹ሲቪል ሰርቪስ›› የሚለው ቃል የመንግስት ስራንና ሰራተኛን እየተካ የሄደበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በጥቅሉ ሲታይ ‹‹ሲቪል ሰርቪስ›› በጥሬ ትርጉሙ የመንግስት ፖሊሲን መፈፀም ወይም መንግስትን ማገልገል ትርጉም እንዳለው ‹‹ዲፈረንስ ቢትዊን ኔት›› የተሰኘ ድረ ገጽ “Difference Between Civil Service and Public Service” በሚል ርዕስ ያሰፈረው ጽሁፍ ያትታል። ‹‹ሲቪል ሰርቫንት›› ደግሞ የመንግስትን ፖሊሲዎች የሚፈጽም ሰራተኛ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በመዝገበ ቃላት ትርጉሙም ቢሆን ሲቪል የሆነ ሰራተኛ ማለት ሰላማዊ የሆነና ስራን የሚሰራ ከጦር ሰራዊት ወይም የመከላከያ ኃይሎች ስራ የተለየ ባህሪ ያለው መሆኑን የሚያመለክት ነው።

ሲቪል ሰርቪስ ሲነሳ አብረው የሚነሱ ሁለት ምሰሶዎች አሉ። አንደኛው ከገንዘብና ሀብት ጋር የሚያያዝ ሲሆን ሁለተኛው የሰው ሀብትን፤ ፖሊሲንና ተቋምን የሚያመልከት ነው። በመሆኑም በሁለንተናዊ የአገር ዕድገት ላይ እነዚህ ምሰሶዎች የሚጫወቱት ሚና ሁሉ ከሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ የሚጠበቅ እንደሆነ ይታመናል።

አንድ አገር ሚዛናዊ የሆነ የሕዝብ አስተዳደር ስርዓት አለው ለመባል ከፖለቲካዊ የአገረ መንግስት ምስረታ ጎን ለጎን ለገንዘብና ለሰው ሃብት እንዲሁም ለፖሊሲና ለተቋም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። ይህ ከሆነ ሲቪል ሰርቪስ በእርግጥም ለመንግስትና ዜጎች ጤናማ የሆነ ግንኙነት ብሎም ለአገር ዕድገት መሰረታዊ ሚና የሚጫወት ዘርፍ መሆኑ ይረጋገጣል።

ሲቪል ሰርቪስ ለዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር የማይተካ ሚና እንዳለው ይነገራል። በሕዝብ የተመረጠን መንግስት ገለልተኛ የአስተዳደር መዋቅር የሚሸከመው ሲቪል ሰርቪስ በመሆኑ የዴሞክራሲ ሁነኛ አካል እንደሆነ ይቆጠራል። በዚህ ሚናውም ሲቪል ሰርቪስ ከፍ ያለ የሙያዊና የስነ ምግባር ደረጃዎች ሊኖረው እንደሚገባ ይመከራል። እናም ሲቪል ሰርቪሱ ፖሊሲውን፣ ሕጎችን፣ አሰራር ሂደቶችን፣ ስርዓቶችን፣ ድርጅታዊ አወቃቅርንና ሰዎችን ያካትታል።

ሲቪል ሰርቫንት በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተቀጠረ ሰው ማለት ነው። ይህ ሰው አስተዳደራዊ መሳሪያዎችን የሚያንቀሳቅስ፣ መንግስታዊ ውሳኔዎችን የሚያስፈጽም በመሆኑ ሲቪል ሰረቫንቱ የማይተካ ሚና አለው። ይህ ሚናውን ጥግ ድረስ እንዲወጣ ከተፈለገ ደግሞ የአገልጋይነት ባህሪ መላበስ ይኖርበታል።

ዓለም የሄደበትና ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የገነባበት መንገድ ዓለም አቀፋዊ እሳቤን የያዘ ነው። ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የሚገነባው አቅምን፣ ችሎታን፣ ቁርጠኝነትን፣ ለሕዝብ ተቆርቋሪነትን መሰረት አድርጐ ሲዋቀር ነው። ሲቪል ሰርቫንቱ ወይም የመንግስት ሰራተኛው በአቅሙና በችሎታው እንዲወዳደርና እንዲመደብ ይጠበቃል። ሲቪል ሰርቪስ ከፖለቲካና ከዳኝነት ስራዎች ውጭ የሲቪል ተግባራትን ለመከወን የተቀጠሩ መንግስት አካላትን ያጠቃልላል የሚባለውም ለዚሁ ነው።

ወደ አገልጋይነት ሀሳብ ስንመለስ ፅንሰ-ሀሳቡ በዘመናት በብዙ ባህሎችና ሃይማኖቶችም ተቀባይነት ያለው ነው። በመሰረቱ፣ አገልጋይነት የሌሎችን ፍላጎት ከራስ ማስቀደምና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ በትህትና ማገልገል መሆኑ ይገለጻል። ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ላይ ያተኮረና በማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ባህሪይ ነው አገልጋይነት።

የአገልጋይነት አላባውያን ተብለው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ትህትና ነው። አገልጋይ ለስራው ትኩረትን ወይም እውቅናን ሳይፈልግ ማገልገልን ብቻ ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገ ነው። ትህትና የአገልጋይነት አስፈላጊ አካል በመሆኑ ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደምና በምላሹ ምንም ሳይጠብቁ ማገልገልን ይጠይቃል።

ሌላኛው የአገልጋይነት ገጽታ ራስን መስጠት ነው። ይህ ማለት ሌላ ሰውን ለመርዳት ጊዜን፣ ሃብትን ወይም የራስን ምቾት መተውን ያካትታል። ከራስ በላይ ሌሎችን ለማስቀደም ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። አገልጋይነት ርህራሄና መተሳሰብ ነው። እውነተኛ አገልጋይ የሌሎችን ፍላጎት የሚረዳና ችግራቸውን ለማቃለል የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ነው።

በዘመናዊው ሕብረተሰብ ውስጥ አገልጋይነት በተለያየ መልኩ ይታያል። ሌሎችን ለመርዳት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በሚሰጡ በጎ ፈቃደኞች፣ የታመሙትን ለመንከባከብ ራሳቸውን ለአደጋ በሚያጋልጡ የጤና ባለሙያዎች፣ የሀገር ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ የፀጥታ ባለሙያዎች እና ነገን በቀጣይ ትውልድ ላይ የሚሰሩ መምህራኖች እንዲሁም በየደረጃው ባለው የመንግስት ሰራተኛ ውስጥ ሊገኝ ይችላል።

በስራ ቦታ ያለ ሁሉም ሰው በአገልጋይነት መንፈስ ከሰራ ከሌሎች ጋር የተሻለ ግንኙነትና ትብብር ለመፍጠር አይቸገርም። ይህ ደግሞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ዕድል ይሰጣል። ምርታማነትና የደንበኞችን እርካታ እንዲጨምር ያደርጋል። አገልጋይነት የአንድነት ስሜትና የቡድን ስራን ያጎለብታል። ሁሉም ሰው ሌሎችን ለማገልገል የጋራ ግብ ላይ እንዲሰራ ያደርጋል። የአገልጋይነት ባህል ለሁሉም ሰው የተሻለና ፍትሐዊ የሆነ አገር ለመፍጠር ይረዳል።

የዜጎች ግልጋሎት ጉዳይ ታዲያ ዘመናዊነትን እንዲላበስ ይጠበቃል። ወጥ በሆነ መንገድ ደረጃውን ጠብቆ በስራ መዋቅር ውስጥ ሊዘረጋ ይገባዋል። እዚህ ጋር የመንግሥት አገልግሎት ጉዳይ የመንግሥት አቋምን የማገልገል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይልቁኑም የሕዝብና የአገር አገልግሎት ነው። ስኬታማ ልማት የሚመጣውና አገር የሚገነባው በስኬታማ ሲቪል ሰርቪስ ስርዓት ነውና።

አሁን ላይ መንግሥት የጀመረውን ሲቪል ሰርቪሱን በሙያተኛ የማደራጀት ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ጅምሮቹ ተጠናክረው ከቀጠሉ ጥሩ የሲቪል ሰርቪስ መገንባት ይቻላል። የሲቪል ሰርቪስ ዘመን ተሻጋሪና በመንግስት መለዋወጥ የማይዛባ መዋቅር እንዲሆን ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።

በ2013 ዓ.ም የተዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ፍኖተ-ካርታ (2013) እንደሚጠቁመው አዲስ የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲ ከሚገዛባቸው መርሆዎች ዋናው ከስትራቴጂዎችና ከአደረጃጀት፣ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና መሳሪያዎች በላይ ለሰዎች ዕውቀትና የአስተሳሰብ ልህቀት አብልጦ ትኩረት አድርጓል።

ከሰው ሀብት ልማት መስኮች መካከልም በመንግሥት ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲ ለሰዎች የፈጠራ ችሎታ፣ ምጡቅ አስተሳሰብና ሐሳብ የማመንጨት ችሎታ ከእውቀትና ክህሎት በላይ ዋጋ የሚሰጠው “ቅድሚያ ችሎታ ላላቸው” የሚል መርህ አንዱ ነው።

ለሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛነት የሚመለመሉ ሰዎች ‘ምሉዕ ስብእና’ን ተላብሰው ዘርፉን እንዲቀላቀሉ፣ ለዜጎች የላቀ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ፣ ፈጠራን የሚያመነጭ ብሩህ አዕምሮ፣ ምጡቅ አስተሳሰብና የአዳዲስ ሀሳብ ባለቤቶች ሊሆኑ ይገባል።

ስለሆነም የቅጥር ሂደቱን በጥንቃቄ መምራት፤ ጥፋትን ፈጥኖ ማረም፣ ሰንሰለትን ማሳጠር፣ አሰራርን ማቅለል ተገቢ ነው። በተጨማሪም ችግር-ፈቺዎች፣ ለሰራተኞች ግልጽ እቅድ የሚሰጡ፣ አዳዲስ የስራ ሂደቶችን የሚቀርጹና በተግባር ደግፈው ለሰራተኛው የሚያስተዋውቁ ብቁ የስራ መሪዎችን ማፍራት ያስፈልጋል።

ማገልገል ክብር የሆነበት ስርዓት መገንባት በተለይም የመንግሥት ሰራተኞች አገልግሎታቸው በገንዘብና በንብረት ጥቅም የሚለካ ሳይሆን ዜጎችን አክብሮ ከሚሰጥ የላቀ አገልግሎትና ከተገልጋይ ዜጎች እርካታ በሚመነጭ አንጸባራቂ ክብር መሆኑን በተግባር እንዲያረጋግጡ ማድረግ ያሻል።

የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ፍኖተ-ካርታ ላይ በግልጽ እንደተመላከተው ነጻ፣ ገለልተኛና ሙያዊ ብቃት ያለው የመንግስትና የሕዝብ አገልጋይነትን እውን ለማድረግ የአደረጃጀቶችን ምክንያታዊነት ማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ ለውጤት ተኮር አፈጻጸም ትኩረት መስጠት፣ ግልጽነት፣ ተደራሽነትንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት ይሰራል።

የመንግስት ዘርፍ የሰው ሀብት ልማቱ በተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ለውጦች የሚያልፍ በመሆኑ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል። በዚህም ምክንያት ከዘመን ዘመን የሚለዋወጥ ቁመናውን የሚወስኑ “ዕሴቶችን” ዜጎች/ተገልጋዮች ከሚፈልጉት ውጤት ጋር የሚጣጣሙ አድርጎ መላበስና ለየዘመኑ ጥያቄ ምላሽ ሰጪ የሆኑ አሰራሮችንም ቀርጾ መተግበርንም እንዲሁ ይጠይቃል።

በእርግጥም በማንኛውም የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ የሚሰማራ የሰው ኃይል በብቃትና ችሎታው ተመልምሎና ተመርጦ ከተሰማራ፣ አገልጋይነት አስተሳሰብና እምነት በሕዝብ ውስጥ ከሰረጸ፣ ንቃተ ሕሊና ካደገና በአዲስ እውቀት ከበለጸገ የአገልግሎት ዘርፉ ችግር ይቀረፋል። ስርዓቱ በማይናወጥ ማዕዘን ላይ ከተሰራ ደግሞ ‘መንግስት በተቀያየረ ቁጥር የሚቀያየር ሲቪል ሰርቫንት ይዘን እስከመቼ ነው የምንዘልቀው’ የሚለው ጥያቄ ገቢራዊ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።

በአጠቃላይ አገልጋይነት ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት በማስቀደም በዓለም ላይ ለውጥ ማምጣት ነው። ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ላይ ያተኮረ የአኗኗር ዘይቤ ነው፤ እና በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችልም ባህሪ ነው።

ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብን ወይም በአጠቃላይ ዓለምን በማገለግል የአገልጋይነት ጽንሰ ሃሳብን መቀበል በሌሎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣና ዘላቂ የሆነ የርህራሄና ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ትሩፋት ያስገኛል። ይህ ጥንካሬን፣ ድፍረትንና የኃላፊነት ስሜትን ይጠይቃል።

የተሻለ አገር ለመፍጠር የአገልጋይነት ባሕል አስፈላጊ ነው፤ ስለዚህ በመላው አገሪቱ በሚገኙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ከፌዴራል እስከ ወረዳ ተቀጥረው የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች እና የሕዝብ አገልጋዮች በየተሠማሩበት የሥራ መስክ አገልግሎት በሚሠጡበት ወቅት በትህትና፣ በደግነትና በስራ ወዳድነትና በአገልጋይነት መንፈስ በማገልገል ለአገር እድገትና ብልፅግና የራስን ድርሻ መወጣት ይገባል።

አገልጋይነት በተገልጋይ እርካታ የሚገኝ ሐሴት ነው። ለሀገር ክብር ነው! ታላቅ ስብእናም ነው! ዝቅ ብለን አገልግለን፤ ታላቅ ሃገር ለመገንባት ኢትዮጵያን እናገልግል! አገልግሎት ሰጪነት ግን ከራስ እንደሚጀምር ልብ ይለዋል። አገልጋይነት ከራስ ሲጀምር ግልጋሎቱ ሌሎችም ይተርፋል!!

አስቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You