ባለፈው ዓመት ነው። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አራት ኪሎ ያለ አንድ ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለን መጽሐፍ አዟሪ መጣ (መቼም የአራት ኪሎ መጽሐፍ አዟሪ የምታውቁት ነው)። አዟሪዎች ሁሌም እንደሚያደርጉት አዲስ የወጣ መጽሐፍ ካለ ለማስተዋወቅ ለብቻው ነው በእጃቸው የሚይዙት። ይሄም ወደ እኛ የመጣው አዟሪ አንድ መጽሐፍ በእጁ ይዟል።
መጽሐፉን እንድናይለት ወደ እኛ ሲሰነዝር ርዕሱ ቀልባችንን ያዘው። ከሰባት ወይም ስምንት ቀን አካባቢ በፊት በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተን አንድ ሁነት ርዕስ አድርጎ ወጥቷል። ግራ ተጋባን! ስለእንዲህ አይነት መጽሐፎች በተደጋጋሚ ይወራ ስለነበር ለመግዛትም ሳንጓጓ ተገርመን ተውነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ባለው ለውጥ በርካታ መጻሕፍት እየወጡ ነበር። አብዛኞቹም ከዶክተር አብይ በፊት የነበሩ ባለሥልጣናትን የሚያብጠለጥሉ ናቸው። ከዚህ አለፍ ያሉትም በዘውገኝነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ከዚህ በላይ ግን አስራሚ ነገራቸው በአንድ ጀንበር የሚጻፉ መሆናቸው ነው።
መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም በቤተ መንግሥት አካባቢ የሠራዊቱ እንቅስቃሴ ታይቶ ነበር። መንግሥት ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ የተነሳ ቅሬታ ነው ሲል አይ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ነው የሚሉም ነበሩ። ይሄ ክስተት በተከሰተ ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ የመፈንቅለ መንግሥቱን ሴራ የሚተነትን መጽሐፍ ገበያ ላይ ታየ! ይሄ መጽሐፍ እነዚህን ጥያቄዎች ያስነሳል።
እንኳን ትልቅ ምሥጢር ያለበት የመከላከያን ጉዳይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ስለአረንጓዴ ልማትስ መጻፍ ይቻላል ወይ? ወይስ ጸሐፊው ከክስተቱ በፊት ምሥጢሩን ያ ውቅ ነበር?
በዚህ ጉዳይ ላይ በአንዳንድ የህትመት ውጤቶችና በማህበራዊ ገፆች የተባለ ነገር ነበር። ሙሉ ታሪኩ ስለመስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ሳይሆን አጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ ስለነበሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ነው። እሱማ እኮ አንድ መጽሐፍ እነዚያን ታሪኮች ሳይጨምር የአንድ ቀን ክስተት ብቻ ገጽ አይሞላለትም። ግን ለምን በዚህኛው ሰሞን ሆነ? ወይም ደግሞ ርዕሱን ጠቅልሎ በአገሪቱ ውስጥ ስለተሞከሩት መፈንቅለ መንግሥት ማድረግ ነው።
ይሄ በጣም ቀላሉ ነው። ቢያንስ የመጽሐፍ ቅርጽ አለው። አጠቃላይ የአገሪቱን ፖለቲካም ይነካካል። ከዚህ የባሰ ደግሞ ልንገራችሁ! በነገራችን ላይ የሚጻፉት ለገንዘብ ስለሆነ ስማቸውን መጥራት ይቅርብን።
በአንድ ብሄርተኝነት ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ በጓደኞቹ ጋባዥነት እጄ ገባ። ስለይዘቱ አላወራችሁም፤ የመጽሐፍ ቅርጽ እንኳን የለውም። የመጽሐፍ ውበቱ መልኩና ቅርጹ አይደለም እንዳትሉኝ። በቃላት መካከል ክፍተት (space) ሳይኖር እንዴት ይነበባል? የተደራጀው የመጽሐፍ ቅርጽ ይቅር፤ አንቀጽ (paragraph) ሳይኖረው እንዴት ይነበባል? ርዕስ ሳይኖረው አንዱ ከአንዱ እንዴት ይለያል? ምዕራፍ ይቅር (የሌላቸው መጽሐፎችም ስላሉ) እንዴት የተጻፈበትን ቋንቋ ሆሄ አይለይም? ይሄን ሁሉ ጉድ ይዞ ዋጋው ከ100 ብር በላይ ነው።
እነዚህ መጽሐፎች ለምን የመጽሐፍ ቅርጽ እንኳን የላቸውም ካልን ነገሩ እንዲህ ነው። የሚገለበጡት ከኢንተርኔት ነው፤ ለዚያውም ጠለቅ ያለ ሀሳብ ካላቸው ድረ ገጾች ሳይሆን ከፌስቡክ! ከኢንተርኔት የሚገለበጥ ነገር ደግሞ ልብ ብላችሁ ከሆነ ይዘበራረቃል። ትክክለኛ አንቀጽና በቃላት መካከል ክፍተት አይኖረውም። በዚያ ላይ ፌስቡክ ላይ የሚጻፍ ጽሑፍ የሥርዓተ ነጥብና የአጻጻፍ ሥርዓት የማይታይበት ነው። በሥርዓት ቢጻፍ እንኳን ‹‹ኮፒ ፔስት›› ሲደረግ ይፈራርሳል፤ እንደገና ነው መስተካከል ያለበት። እንግዲህ እነዚህ የአንድ ጀንበር ጸሐፊዎች ይህን እንኳን ማስተካከል አልቻሉም ማለት ነው።
ለመሆኑ ግን የእነዚህ መጽሐፎች ፋይዳ ምን ይሆን?
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ጠየቅናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት መነሻው ድህነት ነው። ይህን የሚያደርጉት ገንዘብ ፍለጋ ነው። ይሄ ደግሞ በነፃ ገበያ ውስጥ ያለ ነው። እንደሚሸጥላቸው ካወቁ ለመጽሐፉ ጥራት አይጨነቁም። ጸሐፊው ስሜት ኮርኩሮት ሳይሆን ምን ብጽፍ ይሸጥልኛል ብሎ በማሰብ ነው።
የአበረ አዳሙን ሀሳብ የሚያጠናክረው ደግሞ ገበያ ላይ የምናየው ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ርዕሳቸው ስሜታዊ ይሆንና ከውስጡ ሲገባ የርዕሱ ሃሳብ ላይገኝ ይችላል፤ ወይም እንደተባለው አይሆንም። ብዙዎቹም በስስ ስሜት ላይ አተኩረው የሚጻፉ ናቸው። በተለይም የብሄር ጉዳይ ጥሩ መነገጃ እየሆነ ነው።
ደራሲ አበረ አዳሙ እንዲህ አይነት መጽሐፎችን መከልከልም እንደማይቻል ይናገራሉ። የአገሪቱ ህገ መንግሥትም አይፈቅድም፤ ማንም የመሰለውን የመጻፍ መብት አለው። እዚህ ላይ ግን አንድ ጥያቄ እናንሳና ራሳችን እናብሰልስለው!
የእነዚህ መጽሐፎች ችግር እኮ ምሥጢር ማውጣታቸው አይደለም! ግልብ መሆናቸው እንጂ! ውሸት መሆናቸው ነው እንጂ ችግሩ መንግሥትን መተቸታቸው እኮ አይደለም። እንዲያውም ምሥጢር የያዙና በጥልቅ ጥናት የተጻፉ ቢሆንማ ተፈልጎ የሚነበብ ነበር። መንግሥት የሚከለክለው ለምን ያጠፋሁት ጥፋት ታወቀብኝ ብሎ ነው። የእነዚህ መጽሐፎች ችግር ግን ያ አይደለም!
እርግጥ ነው በይዘትም ይሁን የመጽሐፍ ቅርጽ በማጣት የቱንም ያህል የተበላሹ ቢሆን አይታተሙ አይባልም፤ ዳሩ ግን እያስከተሉት ያለው ችግር ደግሞ ቀላል አይደለም። እስኪ ይሄን ችግር ልብ እንበለው!
በእነዚህ መጽሐፎች ምክንያት በጥልቅ ጥናትና ምርምር የተጻፉት ዋጋ እያጡ ነው። አንድ የመጽሐፍ አዟሪ ‹‹አዲስ መጽሐፍ›› እያለ ሲያስተዋውቅ ማንም ቀልቡ ድንግጥ አይልም። ‹‹ደግሞ በአንድ ጀንበር ለሚጻፍ መጽሐፍ›› እያለ ያልፈዋል። በእነዚያ መጽሐፎች የተሰላቸ ተደራሲ መጽሐፍ ሁሉ እንደዚያው ይመስለዋል ማለት ነው። በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አንድ መጽሐፍ ላይ በተደረገ ውይይት፤ አንድ አስተያየት ሰጪ ‹‹አሁን አሁን መጽሐፍ ወደ እኔ እስከሚመጣ እጠብቃለሁ እንጂ እኔ ወደ መጽሐፍ መሄዱን ትቼዋለሁ›› ብለው ታዳሚውን ፈገግ አድርገው ነበር። የንግግራቸው መልዕክት፤ ገንዘቤን አውጥቼ የማይረባ መጽሐፍ አልገዛም፤ ስለመጽሐፉ ጠቃሚነት ከሰማሁ በኋላ ነው የምገዛው እንደማለት ነው። ‹‹አሁን አሁን›› ሲሉ በፊት አዲስ መጽሐፍ ወጣ ከተባለ ከማንም አስተያየት ሳይሰሙ ይገዙ ነበር ማለት ነው። አሁን አሁን ነው የማይጠቅም መጽሐፍ እያጋጠማቸው ያለ ማለት ነው።
ይሄ የሚያሳየን የችግሩን አሳሳቢነት ነው እንጂ መጽሐፍ የሚገዛው ከሰው አስተያየት ሰምቶ መሆን አልነበረበትም። አንዱ የወደደውን ሌላው ላይወደው ይችላል፤ አንዱ ያልወደደውንም ሌላው ሊወደው ይችላል። ቢሆንም ግን በቃላት መካከል ክፍተትና አንቀጽ የሌለውን መጽሐፍ ከመግዛትስ መጽሐፍ ወደ እኛ እስከሚመጣ መጠበቅ ይሻላል!
እንግዲህ እነዚህ በአንድ ጀንበር የሚጻፉ መጽሐፎች በሌሎች መጽሐፎች ላይ ያሳደሩትን ጫና ልብ በሉ! እኝህ ‹‹መጽሐፍ ወደ እኔ ካልመጣ እኔ ወደ መጽፍ መሄዱን ትቼዋለሁ›› ያሉት ሰውየ አንድ መጽሐፍ መነጋገሪያ ካልሆነ አይገዙም ማለት ነው። ወይም ስለዚያ መጽሐፍ የቅርብ ጓደኛ ካልነገራቸው ላያውቁ ነው ማለት ነው። ብዙ የሚጮህላቸው ደግሞ በጥልቅ ጥናትና ምርምር የተጻፉት ሳይሆኑ በወቅታው ጫጫታ ላይ አሉቧልታ ይዘው የሚወጡት ናቸው።
ወደ ደራሲ አበረ አዳሙ አስተያየት ስንመለስ መፍትሔው የተደራሲው እንደሆነ ይናገራሉ። ለመጽሐፍ የደረጃ ምደባ አይደረግም፤ ማንም የመሰለውን ሀሳብ፣ በሚፈልገው ቅርጽ ማሳተም ይችላል። ይሄ ችግር የተከሰተው በተደራሲው ብስለት ማጣት ነው። ምን አይነት መጽሐፍ መግዛት እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። በፊልሞች ላይ የታየውን ለውጥ እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ። ተመልካቹ መምረጥ ስለጀመረ እንደበፊቱ ማንም እንቶፈንቶ ፊልም እየሰራ አይደለም። አሁን ላይ ፊልም የሚታየው ይዘቱ ከታወቀ በኋላ ነው እንጂ እንደበፊቱ ማንም እየተንጋጋ አይሄድም። በመጽሐፍም ይሄ ቢደገም እንዲህ አይነት የአንድ ጀንበር መጽሐፎች ይቆማሉ። በሳልና ጥልቅ ሥራ ያላቸው ሰዎች የሚያሳትሙት ለገንዘብ አይደለም፤ ለሥራው ነው። እንዲህ አይነት ሥራ ደግሞ በሂደት ጠቃሚነቱ እየታወቀ ይመጣል።
እንደ ደራሲ አበረ አስተያየት፤ የአንድ ጀንበር ሥራዎች ደራሲውን ብቻ ሳይሆን የተደራሲውንም ደረጃ ያወርዳሉ። ለዚህም ነው ሚዛናዊ ሆነው ከሚጻፉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ይልቅ የአንድ ወገን ይዘት ያላቸው ገበያው ላይ በስፋት የሚታዩት።
ለመሆኑ ግን መጽሐፍ ለመጻፍ ምን ያስፈልግ ይሆን?
መቼም ይሄ ጥያቄ ጥልቅ ጥናትና ምርምር የሚፈልግ አይሆንም። መጽሐፍ ለመጻፍ ደራሲው ለጻፈው ይዘት ቅርብ መሆን አለበት። ታሪክ ከሆነ ታሪክ የሚያነብ መሆን አለበት። ፖለቲካም ከሆነ ፖለቲካውን የሚከታተልና የሚያነብ መሆን አለበት። ይህ ግን እየሆነ አይደለም። ለምሳሌ የመንግሥትን ምስጢር አወጣን የሚሉ ጸሐፊዎች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አላይም ብለው የማሉ ናቸው። በመንግሥት በኩል ያሉትም የግል መገናኛ ብዙኃን ላያዩ የማሉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ታዲያ ምን አይነት መጽሐፍ ነው የሚጽፉት? ለመታዘብም እኮ የሚሉትን ነገር መከታተል ይገባ ነበር፤ እንዲያውም አዲስ ነገር የሚገነው ተቃራኒ ሀሳብ ካለው አካል ነው እንጂ ከተመሳሳዩ ጋር ከሆነማ ምን አዲስ ነገር አለው? ያው ራሱ የሚያስበው ማለት እኮ ነው።
ምንም እንኳን ዋናው ነገር አንባቢነት ቢሆንም መጽሐፍ ለመጻፍ ዕድሜም ወሳኝ ነው። እርግጥ ነው ወጣት ሆኖ ብዙ ዓመት ከኖረ በላይ መጻፍ ይቻላል! ከሁሉም ሳይሆኑ መጻፍ ግን እንዴት ይቻላል?
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
ዋለልኝ አየለ