ዜና ሐተታ
የምገባ መርሐ ግብር የተማሪዎችን የትምህርት ማቋረጥ መጠን ከመቀነስ ባለፈ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ። መርሐ-ግብሩ የተማሪዎች ተሳትፎ፣ የመማር ምጣኔን ከማሻሻል፣ አካታችነትና ከሥርዓተ ምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍተት የጎላ ሚና እንዳለው ይገለጻል።
ከምግብ ችግር ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህም በሰብዓዊ ሀብት ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳረፉም በላይ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሚዛን አዛብተዋል።
ይህንንም መነሻ በማድረግ መፍትሔ ለመሻትም በአሁኑ ወቅት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመተግበር ላይ የሚገኘው የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሽ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለማቃለል በ2012 ዓ.ም የምገባ ኤጀንሲ በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቷል።
በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ በመሆናቸው በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ይገልጻሉ።
በፕሮግራሙ የሚካተቱ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ኤጀንሲው በ2017 በጀት ዓመት የምገባ አገልግሎቱን በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አንድ ሺ 106 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 800 ሺ 34 ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የቁርስና የምሳ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዷልም ይላሉ።
በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መበጀቱን አውስተው፤ ኤጀንሲው ለፕሮግራሙ የሚያስፈልጉ የግብዓትና የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቆ መስከረም ስድስት ቀን ፕሮግራሙን በይፋ አስጀምሯል ብለዋል።
ተማሪዎች አካላዊና አዕምራዊ እድገታቸው የተሻለ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የምገባ ፕሮግራሙ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉና ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው የሚገልጹት ም/ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከምገባ ፕሮግራሙ መጀመር በኋላ በተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱንም ያክላሉ።
በተጨማሪም ተማሪዎች ደስተኛ ሆነው ተመግበው ትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድርገው እንዲማሩና ወላጆች ምግብ ለመቋጠር የሚያወጡትን ድካምና ወጪ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በምገባ ፕሮግራሙ የተካተቱ ተማሪዎች ጤናማና በትምህርታቸው ውጤታማ ስለሚሆኑ ይህም ትምህርት የሚያቋርጡና ክፍል ደጋሚ ተማሪዎችን ለመቀነስ በእጅጉ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
የተማሪ ቁጥር ከመጨመር ባሻገር አገልግሎቱን ጥራት ባለው መንገድ ለማከናወን በበጀት ዓመቱ አዳዲስ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋቱን አውስተው፤ ለዚህም ምግቦች በሥርዓተ ምግብ ጥናት ላይ የተመሠረተ እንዲሆኑ የምግብ አበሳሰል የመቆጣጠሪያ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን ለልጆች አካላዊና አዕምሯዊ እድገት የሚጠቅሙ እንደ እንቁላል፣ ጥቁር ጤፍ፣ ጨጨብሳ፣ ገብስ፣ ቅንጬ ያሉ ምግቦች በመዘርዝሮች የማካተት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በዘንድሮ የምገባ ፕሮግራም የአዕምሮ ውስንነትና መሰል ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ለብቻቸው የምግብ መዘርዝር መዘጋጀቱን ጠቁመው በተጨማሪም ለ16ሺ እናቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ይናገራሉ።
የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በሁለቱም ፆታ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻሉን አመላክተዋል። ፕሮግራሙ ትውልድ ላይ የሚሠራ ሥራ በመሆኑ ጥራት ባለው ሁኔታ ለማስቀጠል ወላጆች፣ መምህራንና የትምህርት ማኅበረሰብ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም ምክረ-ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም