የተፈጥሮ ማዳበሪያ፤ በእጅ ያለ ወርቅ

ባሕር ዳር፡- አርሶ አደር አስፋው ታደሰ በደቡብ ወሎ ዞን የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው። አርሶ አደሩ ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ይልቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም እንዳለው እንደሚረዱ ይናገራሉ።

የማዳበሪያ እጥረት ብዙ ጊዜ ሲገጥም ይስተዋላል ያሉት አርሶ አደሩ “መፍትሔን በቀዬ” እንዲሉ በራስ አቅም ይህን ችግር ለመሸፈን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የአካባቢያቸውን ሁኔታ በማንሳት ነግረውናል።

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት በቀያቸው ለሌሎች ምሳሌ ለመኾን እየሠሩ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት።

ባለፈው ዓመት ግማሽ በግማሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀማቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ ወደፊት ሙሉ ለሙሉ የመሬታቸውን ደኅንነት በሚጠብቀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመጠቀም ተግተው እንደሚሠሩ ነው የገለጹት።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ብዙ ጊዜ ብዛት እንጂ ጥራት ላይ ትኩረት ሳይደረግ በመቆየቱ በሚገባ እንዳልተጠቀሙበት ነው የተናገሩት።

አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት ከብዛትም በተጨማሪ ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው ለመሥራት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ከግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ በመውሰድ ለመሥራት እየተዘጋጁ እንደሆነም ተናግረዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ልክ እንደ አርሶ አደር አስፋው ታደሰ ሁሉ ሌሎች አርሶ አደሮችም የእርጥበቱ ጊዜ ሳያልፍባቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚያዘጋጁበት ግብዓት እያሠባሠቡ ነው።

8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት የእርጥበት ወቅቱ ሳይጠናቀቅ ለመሠብሠብ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነ ነው ዞኑ ያስታወቀው።

እስካሁንም 300 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ግብዓት ስለመቀበሩም የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ይመር ሰዒድ ተናግረዋል።

ለዚህ ተግባር ብቻ ዞኑ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለሙያ መድቦ ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት የሰብል ልማት ቡድን መሪው፤ ይህ ወር ዋናው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጃ ወር በመሆኑ ክትትል እየተደረገ እየተሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

አቶ ይመር በዞኑ የተወሰኑ አካባቢዎች ባለው ወቅታዊ የሠላም እጦት ችግር መድረስ ያልተቻለባቸው ስድስት ወረዳዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ከእነዚህ ውጭ ሁሉም ወረዳዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ሙያዊ እገዛ እየተሰጠ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት።

በዞኑ ውስጥ 462 ሺህ አባወራዎች እንደሚገኙ የተናገሩት ባለሙያው በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራው ላይ ሁሉም አባወራዎች እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሠራ ነው ተብሏል። የግብርና ባለሙያዎች መድረስ በቻሉባቸው አካባቢዎችም ጥሩ እንቅስቃሴ እንደሚታይ ነው የነገሩን።

በዝግጅት ደረጃ በመጠን ቢለያይም ሁሉም አርሶ አደር እንዲያዘጋጅ ግን መግባባቱ እና የተግባር እንቅስቃሴው መጀመሩን ነው ያስረዱት።

የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሊሸፍን እንደሚችልም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች በየዓመቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ያዘጋጁ ስለነበር የነበሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መቅበሪያ ጉድጓዶችን የመጥረግ እና የሌላቸው ደግሞ አዲስ የማዘጋጀት ሥራ እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት የሚሆኑ አስፈላጊ ግብዓቶችን የአረንጓዴው ወቅት ሳያልፍ የማሠባሠብ ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም አስገንዝበል።

በዘንድሮው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ ከብዛት ባለፈ ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ነው የነገሩን።

በተለይ በያዝነው ሳምንት መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዞኑ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት በመስጠት “በአንድ ቀን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት” በሚል አንድ ቀበሌ ተመርጦ የመሥራት ዘመቻ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትን ልምድ ለማድረግ እና ሌሎች ተሞክሮ የሚወስዱበት እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ በ2017 የምርት ዘመን ከ66 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ መደበኛ ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ በመሠራት ላይ ነው። እስካሁን ባለው መረጃ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መደበኛ ኮምፖስት ተዘጋጅቷል።

በተጨማሪ 9 ሺህ 96 ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት እና 10 ሺህ 471 ሜትር ኩዩብ ባዮሳላሪ ኮምፖስት ተዘጋጅቷል። አርሶ አደሮች ከባለሙያዎች ባገኙት ሙያዊ ድጋፍ መሠረት በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ሥራው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን አሚኮ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You