አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር ያደረገው ስምምነት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞቹ ዓለም አቀፍ የቪዛ ካርዶች በስፋት መጠቀም እንዲችሉ የሚረዳ ስምምነት ከቪዛ ኢንተርናሽል ጋር ትናንትና ተፈራርሟል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እንደገለጹት፤ ንግድ ባንክ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር ለረጅም ዓመታት የዘለቀ አጋርነት አለው፤ የሚጠቀምባቸው ኤቲኤም ካርዶችም ከተቋሙ ጋር የተያያዙ ናቸው።
ስምምነቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን የያዘ መሆኑን አንስተው፤ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ የባንኩ ደንበኞች በተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን በስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠቀም እንዲችሉ የሚረዳ ስምምነት መደረጉን አንስተዋል።
በተጨማሪም የቪዛ ካርዶች በብዛት እንዲቀርቡና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችል ስምምነት መፈጠሩን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ለውጭ ተጓዦች ሲሰጥ የነበረውን የቪዛ ካርድ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪን ብቻ እንዲጠቀሙ የሚረዳ መሆኑን አስታውሰው፤ የአሁኑ ስምምነት ደንበኞች በሒሳብ ደብተራቸው ያለውን የውጭ ምንዛሪ በዓለም አቀፍ ምንዛሪ ያለገደብ እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለስምምነቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፤ መሰል ተቋማት በሀገሪቷ ለሚያደርጉት ተሳትፎ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርና ብዙ አማራጮች እንዲፈጠሩም ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ካለው የፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት ጋር ተያይዞ እንደ ቪዛ ካሉ ትልቅ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራት ፋይዳው ጉልህ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ባንኩ ከፋይናንስ ተቋሙ ጋር ዘለቄታዊ አጋርነቱን እያጠናከረ መምጣቱ በተሻለ ውጤታማ ለመሆን የሚረዳ ነው ብለዋል።
አጋርነቱ ለባንኩ ደንበኞች እንዲሁም በአጠቃላይ ለፋይናንሱ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ፤ ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የቪዛ ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዚዳንትና የምሥራቅ አፍሪካ ጀነራል ማናጀር ቻርድ ፖሎክ በበኩላቸው፤ ቪዛ ኢንተርናሽል በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ያለውን አቅም እየተጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ መሥራታቸው በልምድ ልውውጥ፣ በሰው ሀብት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብይትና መሰል ጉዳዮች የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያግዛቸው መሆኑን አመላክተዋል።
ስምምነቱ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፤ የጋራ ዓላማዎችን ለማሳካት ቪዛ ኢንተርናሽናል ለንግድ ባንክ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ተገልጿል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም