አዲስ አበባ፦ የካፊቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ‘’ማሽቃሬ ባሮ’’ የብሔረሰቡን ባሕላዊና ታሪካዊ ትውፊት በጠበቀ መልኩ በተለያዩ ሁነቶች መስከረም 12 እና 13 ‘’በቦንጊ ሻምቤቶ’’ እንደሚከበር የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻው ከበደ ገለጹ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻው ከበደ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዓሉን አስመልክቶ የካፊቾን ብሔረሰብ የሚገልጹ ባሕላዊና ታሪካዊ ጨዋታዎችና ዘፈኖች ይቀርባሉ። ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የቋንቋና የባሕል ሲምፖዚየም የሚካሄድ ይሆናል።
ኮሚቴ ተዋቅሮ በዓሉ የሚከበርበት ስፍራ የደመቀ እንዲሆን የቦታ ዝግጅት፣ መንገድ የማመቻቸትና ለአካባቢው ተወላጆችና ወዳጆች ጥሪ የማድረግ ሥራ መሠራቱን የጠቆሙት አቶ እንዳሻው፤ “ማሽቃሬ ባሮ” የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ መጠን ዜጎች ሃይማኖት፣ ፆታ፣ እድሜ፣ ብሔርና በሌሎች መስኮች የሚታዩ ልዩነቶች ሳይገድቧቸው እንደሚያከብሩት ገልጸዋል።
እንደ አቶ እንዳሻው ገለጻ፤ ‘’ማሽቃሬ ባሮ’’ የዜጎች የአንድነትና አብሮነት መገለጫ በመሆኑ ከባሕላዊነቱ አልፎ የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ የበለጠ ማጠናከር የሚቻልበት ነው። እንዲሁም የአካባቢው ልማት ይበልጥ እንዲፋጠንና የካፊቾ ብሔረሰብ ባሕላዊና ታሪካዊ ትውፊት ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያግዝ ነው።
በቀድሞ ጊዜ ‘’ማሽቃሬ ባሮ’’ ሲከበር የቆየው ነገሥታቱ ያለፈውን ዓመት አጠቃላይ ተግባራትን ገምግመው የተሻለ ለሠሩት ሽልማት የሚሰጡበትና በአፈጻጸማቸው ጉድለት ያሳዩትን በመገሰጽ ሌሎችን በመሾም ነበር። እኛም ልምዶችን በመውሰድ በገጠርና በከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠልና የጎደሉትን ማሟላት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል።
የጥንት የካፋ ነገሥታት መናገሻ በሆነው ‘’በቦንጊ ሻምቤቶ’’ በዓሉ እንደሚከበር በመግለጽ፤ ስፍራው ታሪካዊ በመሆኑ ከልማት ጋር በማስተሳሰር ለአካባቢው እድገት አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉ የባሕል ማዕከላትን በመገንባት ገቢ የሚገኝበት ሁኔታ ለመፍጠር ጅምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አውስተዋል።
በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ዘመድ አዝማድ የሚገናኝበት፣ የአካባቢው ተወላጆች የጋራ ሥነልቦና ይዘው ዞኑን የበለጠ በልማት ማሻገር የሚቻልበት ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የጋራ ቁርጠኝነትና ኃላፊነት የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ የአካባቢው ባሕልና ቋንቋ የሚተዋወቅበት፣ ዜጎች እንዲቀራረቡና ልማትን የጋራ አጀንዳቸው በማድረግ በአንድ ላይ ሆነው እንዲነሱ የሚያስችል ነው። የአካባቢው ማኅበረሰብ የዞኑን ልማት ለማደናቀፍና ወደኋላ ለመመለስ ለሚፈልጉ አካላት ቦታ ሳይሰጥ በዓሉን በአንድነት ማክበር ይጠበቅበታል ነው ያሉት አቶ እንዳሻው።
‘’ማሽቃሬ ባሮ’’ ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ይህንን በማጠናከር በዩኔስኮ ላይ ለማስመዝገብ ባለፈው ዓመት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት አስተዳዳሪው፤ ለበዓሉ አከባበርም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአስተዳደርና ፖለቲካ መቀመጫ የሆነችው የቦንጋ ከተማ እንግዶቿን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
አካባቢው የቡና መገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም፣ የ18ቱ የከፋ ነገሥታት የቀብር ቦታ ‘’ሾሻ ሞጎ’’፣ የእግዜር ድልድይ፣ ታሪካዊ ገዳማትና መስጊዶች፣ ፏፏቴዎች፣ የጥንት የከፋ ነገሥታት መናገሻ፣ ጥቅጥቅ ደን እና ሌሎች ቅርሶች እንደሚገኙበት አመላክተው፤ አካባቢው ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ አልሚዎች ወደዞኑ በመምጣት በልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም