ኢትዮጵያ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ከመቶ ዓመት በላይ ታሪክ ያላት አገር ናት። በኢትዮጵያ የባቡሩ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት በ18ኛው ክፍለ ዘመን በጅቡቲ ወደብ በኩል ለውጭ ገበያ በየዓመቱ 12 ሺህ ቶን የሚሆን ሸቀጥ ታቀርብ ነበር። ሸቀጡን ወደ ወደብ ለማድረስም 50 ሺህ ግመሎችን ትጠቀም እንደነበርና ጉዞውም ከሰባት ወራት በላይ ይፈጅ እንደነበር መዛግብት ያሳያሉ።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ በወቅቱ አገሪቱን ይመሩ የነበሩት አፄ ምኒልክ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከሌሎች አገራት ጋር በመደራደር ስራውን አስጀምረዋል። የመጀመሪያው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ከአዲስ አበባ ጅቡቲ 784 ኪሎ ሜትር ርዝመት የነበረው ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሐረር፤ ድሬዳዋን አቋርጦ ጅቡቲ የሚዘልቅ ነበር።
የባቡር መንገዱ ግንባታ 20 ዓመታት የፈጀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የባቡር ቴክኖሎጂም በኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ብቻ ተወስኖ ለዘመናት መቆየቱ ይታወቃል። ነባሩ ባቡርም ለሁለቱ አገራት የኢኮኖሚና የንግድ ትስስር ማደግ አስተዋፅኦ ሲያበረክት የቆየ ቢሆንም አገልግሎት መስጠት ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ምንም እንኳን ነባሩ የባቡር መስመር አስፈላጊውን ጥገና ተደርጎለት ወደ ስራ ባይገባም፤ ኢትዮጵያ አዲስ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ የባቡር መስመር ወደ ጅቡቲ በመዘርጋት በጅቡቲ ወደብ የሚከማቹ እቃዎችን ወደ መሀል አገር የማስገባትና ምርቶቿን ለዓለም ገበያ የመላክ ስራ በ2009 ዓ.ም ጀምራለች።
ነገር ግን የአገሪቱ የወጪና ገቢ እቃዎች ከተገመተው በላይ በየዓመቱ እያደገ በመምጣቱ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው እቃዎች በጅቡቲ ወደብ እየተከማቹ ስለሚቆዩ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በወቅቱ ማድረስ ካለመቻሉ ባሻገር፤ አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪና ኪሳራ እየዳረጋት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡
በተለይ እንደማዳበሪያና መድኃኒት የመሳሰሉ በወቅቱ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚገባቸው ምርቶች በማጓጓዣ እጥረት ሰበብ በወደብ ተከማችተው በመቆየታቸው አገርን ለኪሳራ እየዳረጉ መሆኑ ይሰማል፡፡ ለዚህ ችግር ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የመጓጓዥያ እጥረት መሆኑም ይጠቀሳል፡፡
ይሄንን የመጓጓዥያ ችግር ለማቃለል 400 ያህል ፉርጎዎች ያሉትን የቀድሞው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅትን ወደ ስራ በማስገባት፤ በወደብ ላይ የሚከማቹትን እቃዎች በማጓጓዝ ለአገር የበኩሉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማበረከት ይቻላል ሲሉ የድርጅቱ የህግና የሰራተኛ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት መኮንን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
እርሳቸውም እንደገለጹት፤ ነባሩ የባቡር ኩባንያ እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ቀጥታ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን፤ በ1999 ዓ.ም ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የእርዳታ ገንዘብ የመተሃራን ሃይቅ የሚያቋርጠውን የባቡር ሃዲድ ለመጠገን አንድ የውጪ አገር ኮንትራክተር ኃላፊነቱን ወስዶ በዚያው ዓመት ወደ ስራ በመግባቱ፤ በዚህ ምክንያት ከጂቡቲ ቀጥታ አዲስ አበባ አገልግሎቱ ሊቋረጥ ችሏል።
ነገር ግን እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ የቀድሞው ባቡር ከድሬዳዋ እስከ ጅቡቲ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አስራት፤ በ2006 ዓ.ም አዲሱ የባቡር መስመር ዝርጋታ ግንባታ ሲከናወን የቀድሞውን የባቡር መስመር ሁለት ቦታ ላይ በማቋረጡ ምክንያት ከጂቡቲ እስከ ድሬዳዋ ይሰጥ የነበረው የማጓጓዝ አገልግሎት ሊቋረጥ ችሏል። ያም ሆኖ፤ እስካሁንም ከድሬዳዋ እስከ ደወሌ (እስከ ጅቡቲ ድንበር) ድረስ 112 ኪሎ ሜትር በመሸፈን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“አዲሱ የባቡር መስመር ሲዘረጋ ነባሩን የባቡር መስመር ያላገናዘበ፤ ግልጽነት የጎደለው፤ ከነባሩ የባቡር ድርጅት ጋር ተወያይቶና ተቀናጅቶ ወደ ስራ ያልተገባ ነው” የሚሉት አቶ አስራት፤ “ስራው ነባሩን የባቡር መስመር ታሳቢ ያላደረገበት ምክንያት ይሄነው ብሎ ለመናገር አይቻልም። ነገርግን ሁለቱ ድርጅቶች ተናብበው ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ግንባታ መስራት ነበረባቸው። በአዲሱ የባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት ነባሩ ባቡር አገልግሎቱን ሳያቆም ተመጋግበው የሚሰሩበትን የቴክኖሎጂ አማራጭ መጠቀም እየተቻለ ነባሩ ባቡር እንዲቆም ተደርጓል” ብለዋል።
በመሆኑም፤ በ2008 ዓ.ም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከቀድሞው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር እና ከድርጅቱ የተውጣጡ ባለሙያዎች በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሰብሳቢነት በቀድሞው የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ላይ ጥናት አካሂደው ነበር። በጥናቱም፤ ድርጅቱ ባለው ሀብትና ንብረት በመንግስት ድጋፍና እገዛ እየተደረገለት እስከ 20 ዓመት ድረስ ዳግም ወደ ስራ ገብቶ ስራውን መቀጠል እንደሚችል ሪፖርት ቀርቦ እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን፤ ጥናቱ ተግባራዊ ሳይደረግ በ2009 ዓ.ም እንደ አገር በመጣው ለውጥ ሳቢያ ሚኒስትሮችና አመራሮች በመቀያየራቸው ጥናቱ ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል። ከለውጡ በኋላ በ2011 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ዳግም በትራንስፖርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች በድርጅቱ ላይ ሌላ ጥናት የተደረገ ሲሆን፤ ጥናቱም በአገሪቱ ያሉ ሶስት የባቡር ድርጅቶች በምን አይነት መልኩ ተመጋግበው በመስራት የሚጠበቅባቸውን ጥቅም ማበርከት ይችላሉ? አደረጃጀታቸውስ ምን መሆን አለበት? የሚል ጥናት በትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠንቷል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ የጥናቱ ውጤት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይፋ ሆኖ ገና ውሳኔ እንዳላገኝ ገልጸዋል።
ትናንት ላይ ኃላፊነቱን ወስዶ የሰራው የመንግስት አካል ጥፋት እንዳለ ሆኖ አሁን በመላ አገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የቀድሞውን ባቡር ወደ ስራ ለማስገባት በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተጠናው ጥናት በሂደት ላይ እንዳለ የጠቆሙት እኝሁ ኃላፊ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያና ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ብዙ ንብረትና ሀብት ያለው ነው። የባቡር ሃዲዱም መቶ ዓመታት ያለዝገት የተሻገረ ነው። ለወደፊትም መለስተኛ ጥገና ተደርጎለት ለረጅም ዓመታት አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው። እንዲሁም ድርጅቱ ከ400 በላይ የመጓጓዣ ጋሪዎች (ፍርጎዎች) ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያና በጅቡቲም ጎታች ማሽኖችም አሉት።
ስለዚህ በየቦታው የተበታተነውን የድርጅቱን ንብረት በማሰባሰብና ከአውሮፓ ህብረት ለጥገና ተለግሶት ከነበረው ገንዘብ በእንጥልጥል ላይ ያለ ከ20 ሚሊዮን ዮሮ በላይ ገንዘብ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ እንዲለቀቅ ግፊት ቢያደርግ፤ በትንሽ ወጪ በአዲሱ የባቡር መስመር ዝርጋታ የተቋረጠውን ነባሩን የባቡር መስመር መልሶ በማገናኘት የቀድሞውን የባቡር ሃዲድ መለስተኛ ጥገና አድርጎ ወደ ስራ በማስገባት ከጂቡቲ ወደብ እስከ መተሃራ ሃይቅ ድረስ 560 ኪሎ ሜትር የትራንስፖርትና የእቃ ማጓጓዣ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፤ ብለዋል።
እርሳቸው እንዳብራሩት፤ 560 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የቀድሞውን የባቡር መስመር መለስተኛ ጥገና በማድረግ ወደ ስራ ለማስገባት ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቅና ከአዲሱ የባቡር መስመር ጋር እንደማይጋጭ በጥናት የተረጋገጠ ነው። በመሆኑም አዲሱ የባቡር መስመር ሲገነባ የአገሪቱ የካርጎ መጠን ሲጠና በዓመት አራት ሚሊዮን ቶን የገቢና የወጪ እቃ ነበር። አሁን ግን በዓመት 12 ሚሊዮን ቶን እቃ ደርሷል።
ይሄ የካርጎ መጠን ከአዲሱ ባቡሩና ከሌሎች የማጓጓዣ አማራጮች አቅም በላይ በመሆኑ፤ በተለይ ከወደብ በወቅቱ ተጓጉዘው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚገባቸው እቃዎች ለብልሽት ይዳረጋሉ። እንዲሁም፤ ከፍተኛ መጠን ያለው እቃ በወደብ ላይ ስለሚከማች መንግስት ለመጋዘን ኪራይ ከፍተኛ ወጪ ይዳረጋል። ስለዚህ፤ የቀድሞው ባቡር እንደ አማራጭ ወደ ስራ ቢገባ በወደብ አካባቢ የሚከማቹ እቃዎችን በወቅቱ በማጓጓዝ በጅቡቲ ለመጋዘን ኪራይ የሚከፈለውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽፆ ያበረክታል።
የቀድሞው ባቡር ፋብሪካዎች የሚጠቀሙትን የድንጋይ ከሰል እና በወደብ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ የሚከማች የእርዳታ እህል፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት የመሳሰሉ እቃዎችን በተለይ ለምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ፍጆታ የሚውለውን ቁሳቁስ በቀላሉ በማጓጓዝ በትራንስፖርት ዘርፉ ያለውን መጨናነቅ ማቃለል ይችላል። እንዲሁም ወደ ምስራቁ የአገሪቱ ክፍል የሚጓጓዝ ማንኛውንም እቃ በቀድሞው ባቡር በመጠቀም በማጓጓዝ በሌላው የትራንስፖርት ዘርፍ የሚፈጠርን ጫና ማቃለል ይችላል።
በጥናቱ መሰረት የቀድሞውን ባቡር ወደ ስራ ለማስገባት ድርጅቱ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስራት፤ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ አካባቢ አንድ የባቡር መስመር ድልድይ በጎርፍ ተወስዶ በአገር ውስጥ ኩባንያ ተሰርቶ ነበር። ነገር ግን ይሄ ድልድይ እንደገና በጎርፍ በመወሰዱ ይሄን ድልድይ መልሶ ለማሰራት እና በአዲሱ የባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት የተቋረጡ የቀድሞው የባቡር መስመሮችን መልሶ ለማያያዝ፤ እንዲሁም ነባሩን የባቡር ሃዲድ መለስተኛ ጥገና አድርጎ በአጭር ጊዜ በጥራት እና በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ ስራ ለማስገባት ድርጅቱ ከቻይና ኩባንያ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሄንን ታሪካዊ የባቡር ድርጅት ወደ ስራ ማስገባት ዘርፈ ቡዙ ጠቀሜታ አለው የሚሉት አቶ አስራት፤ ድርጅቱ ትኩረት ስለተነፈገው ነው እንጂ በቀላሉ ወደ ስራ በማስገባት ኢኮኖሚውን ከመደገፍ ባሻገር ከመቶ ዓመት በላይ የቆየ ታሪካዊ ባቡር መስመር ስለሆነ በቱሪስት መስህብነትም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
እንዲሁም አዲሱ ባቡር ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ስድስት የባቡር ጣቢያ ብቻ እና በአማካኝ የባቡር መስመሩ ከከተሞች ከ12 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው በመሆኑ፤ መንገደኞች ከባቡሩ ወርደው ለተጨማሪ የትራንስፖርት እንግልትና ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ከመሆኑ በተጨማሪ ለከተሞች የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ፋይዳ ዝቅተኛ ነው።
የቀድሞው ባቡር ግን ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ 34 የባቡር ጣቢያ የነበረው ሲሆን፤ ወደ ስራ ቢገባ ከጅቡቲ ወደብ እስከ መተሃራ ኃይቅ ድረስ ብቻ የባቡሩን መስመር ተንተርሰው የተመሰረቱ ከተሞች ተቀዛቅዞና ተዳክሞ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴያቸው ዳግም የሚያንሰራራበትና ማህበረሰቡም የስራ እድል የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል።
እንዲሁም እንደ ድሬደዋና ሐረር የመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞችን የንግድ እንቅስቃሴ ከማሳደግ ባሻገር፤ እንደ ሁረሶ፣ ኤረር፣ አፍደም፣ ሙሉ፣ ፒኬ፣ አሰቦት፣ አርባ፣ ቦርደዴ፣ ኮራ፣ የመሳሰሉ ትንንሽ ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል አቶ አስራት።
በሌላ በኩል፤ አባታቸው በቀድሞው ምድር ባቡር ድርጅት ተቀጥረው እየሰሩ በደረሰባቸው የባቡር አደጋ ህይወታቸው ማለፉን የሚናገሩት በድሬዳዋ ከተማ 03 ቀበሌ ገነቲቱ ምድር ባቡር ለገሃር ዙሪያ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እማዋይሽ ሞላ፤ የአባታቸው ህይዎት ማለፉን ተከትሎ ሮጠው ባልጠገቡበት እድሜያቸው የቤተሰብ ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ በመውደቁ ከጂቡቲ ድሬዳዋ ሸቀጦች በመነገድ በሚያገኙት ገቢ ስድስት ወንድሞቻቸውን እና አንድ እህታቸውን አስተምረው ለቁም ነገር እንዳበቁ ያስረዳሉ።
የቀድሞው ባቡር ስራ ሲያቆም ድሬዳዋ ከተማ የሞተች ሲሆን የከተማዋ ነዋሪም አብሮ ግባተ መሬቱ ተፈጽሟል የሚሉት ወይዘሮ እማዋይሽ፤ ድሬዳዋ ብቻ አይደለችም የተጎዳችው ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከጅቡቲ ድረስ ያሉ የቀድሞውን የባቡር መስመር ተከትለው የተመሰረቱ ከተሞች በኢኮኖሚ ደቅቀው እንዳልነበር ሆነዋል። አብዛኞቹ ኗሪዎች ድሮ ባቡሩ በስራ ላይ በነበረ ጊዜ ተሯሩጠው ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ያለ አንዳች ችግር ልጆቻቸውን ያስተምሩና ቤተሰብ ያስተዳድሩ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ ግን የሚሰሩት ስራ ባለመኖሩ የቤት ኪራይ ከፍለው ለማደር እንኳን እንደተቸገሩ ያስረዳሉ።
“ስለዚህ መንግስት የቀድሞው የባቡር መስመር ተመልሶ ወደ ስራ የሚገባበትን መንገድ ቢያመቻች፤ በከተማዋ የሚስተዋለውን ሰፊ የስራ አጥ ቁጥር የሚቀርፍና አዳዲስ የስራ እድል የሚፈጥር፤ በድርጅቱ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ዛሬ ላይ ያለስራ ሜዳ ላይ የተበተኑ የማህበረሰብ ክፍል ወደ ስራቸው የሚመለሱበት እንዲሁም የምስራቋ ጮራ ድሬዳዋ ከተማ ወደ ቀደመ የነቃ የንግድ እንቅስቀሴዋና አቃፊነቷ ትመለሳለች፤” ሲሉ ወይዘሮ እማዋይሽ ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011
ሶሎሞን በየነ