በሀገራችን ያለውን የሠው ኃይል በተቀናጀ መልክ ወደ ሥራ የሚያስገባ እውቀትም ሆነ አሠራር ባለመኖሩ የሥራ አጡ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል:: በአሁኑ ወቅት ብዛቱ ከአስር ሚሊየን በላይ እንደደረሰ መንግስት አስታውቋል:: ይህንን ኃይል ወደ ሥራ ለማስገባት በተያዘው ቁርጥ አቋም በ2012 ዓ.ም ሦስት ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧል:: በዚህም መሰረት የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞችን በመለየት የሥራ ዕድሉን በሁለት መርሀ ግብሮች ለወጣቱ ተደራሽ የማ ድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል::
ይህ ምልከታም ትኩረት ያደረገው በገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ወጣቱን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል? ምን ዓይነት የሥራ ዘርፎች ተለዩ ? ለምን ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፈጠር ታሰበ? ምን ምን ተግዳሮቶች አሉ? ምን መፍትሄ ተሰጣቸው? የሚሉትን ለማየት የሞከረ ነው:: በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማነጋገር የተገኘውን መረጃ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል::
አቶ ስለሺ በቀለ በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክተር እንዳስረዱት መንግስት በ2012 ዓ.ም ሦስት ሚሊየን ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ባቀደው መሠረት በ2012 ዓ.ም በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል:: የገጠር ሥራ እድል ፈጠራን ተግባራዊ ለማድረግ ከፌዴራልና ከክልል በብድር ይቀርባል ተብሎ የተዘጋጀው ስድስት ቢሊየን ብር ሲሆን የብድር አሰጣጡን በተመለከተም ተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦትን የተከተለ ነው ተብሏል:: በብድር አሰጣጡ ሂደት ያሉ አሰልቺ አሰራሮችንም ለማስቀረት መሞከሩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::
ግብርና ሚኒስቴር በዋናነት በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ተቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ ከግብርና ሥራዎች ውጭ ሌሎች ሴክተሮችን የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ከዚህ በመነሳትም ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ዕቅድ ማቀድ የመጀመሪያ ተግባሩ እንደነበር አቶ ስለሺ አስረድተዋል:: ከክልሎች የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ዕቅድ ከተዘጋጀ በኋላም ከክልል አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዕቅዱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት መደረጉንና ዕቅዱን የማናበብ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል:: የእያንዳንዱን ክልል ልምድና ተሞክሮ መነሻ በማድረግም ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተፈትሸዋል:: በመቀጠልም በፌዴራልና በክልል ደረጃ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ተለይተዋል::
ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊትም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራት እንዳለበትና ይህም የፌዴራል መንግስት ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አመራሩና ባለድርሻ አካላት ተስማምተዋል:: አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ የሥራ ዘርፎችንም እንደ አመቺነታቸው ለመለየት ተሞክሯል:: ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እንዴት መተግበር እንደሚችሉ ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል:: አፈጻጸሙን በተመለከተም ለእያንዳንዱ ሥራ የጊዜ ሰሌዳ በማስቀመጥ ወደ ሥራ መገባቱን አቶ ስለሺ አስረድተዋል::
ግብርናው ዘርፍ
ከተለዩት የሥራ ዓይነቶች ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ግብርና እንደመሆኑ በእጽዋትና በእንስሳቱ ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በርካታ የሰው ኃይል መሸከም እንዲችል ለማድረግ ተሞክሯል:: ስለሆነም ግብርናው ዘርፍ በአጠቃላይ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል 60 በመቶውን እንዲሸፍን መደረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል:: ከግብርናው በመቀጠል የተሻለ የማስተናገድ አቅም ይኖራቸዋል ተብለው የተለዩትም እንደ ማኑፈክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ንግድ፣ ኮንስትራክሽን፣ አገልግሎት ዘርፎች የመሳሰሉት ናቸው:: ከእነዚህም በተጨማሪ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በገጠር አካባቢ አመቺ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ሁሉ ወጣቱን ለማሰማራት ታስቧል::
መንግስት ትኩረት ከሰጠውና በርካታ የሰው ኃይልን መሸከም ይችላል ተብሎ ከታሰበው አንዱ ቱሪዝም ነው:: ቱሪዝም በአገልግሎት ዘርፍ ሥር እንደተጠቃለለም ዳይሬክተሩ የገለጹ ሲሆን በገጠሩ ነባራዊ ሁኔታ ዘርፉን አንድ የሥራ መፍጠሪያ በማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት በዕቅድ እንደተያዘ ጠቅሰዋል:: ይሁንና ቱሪዝም በዋናነት የመሰረተ ልማት መሟላትን የሚጠይቅ በመሆኑ በመዳረሻ ቦታዎች ያሉ የቱሪስት መስዕቦችን ማልማት እንደሚያስፈልግም አቶ ስለሺ ተናግረዋል:: በተለያዩ የገጠሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ የቱሪዝም ጸጋዎች ያሉ በመሆኑ ሁሉንም እንደአስፈላጊነታቸው ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ መታሰቡንም ገልጸዋል::
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ምን ይመስላል በሚል በተደረገው ጥናት ላይም ውይይት መደረጉንና ችግሮች መለየታቸው ተገልጿል:: በነበረው ተሞክሮ በሥራ ዕድል ፈጠራው እንደ ችግር ከተጠቀሱት ውስጥ የማስፈጸም አቅም ውሱንነት አንዱ ነው፣ ይህ ማለትም በአመራሩ፣ በባለሙያውም ይሁን በሥራ ፈላጊው ዘንድ ለሥራው የሚመጥን ዕውቀትና ክህሎት ያለመያዝ ነው:: በሥራ እድል ፈጠራ እውቀትና ክህሎት ወደ ገንዘብ የሚመነዘሩ ሀብቶች እንደመሆናቸው ይህን ለማድረግ የሚያስችል አሠራር እንዳልነበረም ተወስቷል::
ሌላው ችግር የመዋቅር ሲሆን ስለገጠር የሥራ እድል ሲታሰብ በቀበሌ ደረጃ ይህንን ጉዳይ በባለቤትነት የሚመራና የሚያስፈጽም አካል ያለመኖር ችግር ነው:: እስከዛሬ በነበረው ተሞክሮ ሥራው በውክልና የሚሠራ በመሆኑ የተለያዩ ክፍተቶች ተፈጥረዋል:: ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ሥራው በቀበሌ ደረጃ እራሱን የቻለ ባለቤት እንዲኖረው ተመክሯል::
ሌላው ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ ተቀናጅቶና ተናቦ ያለመሥራት ችግር ሲሆን በአንድ አካል ብቻ የሚተገበር ባለመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ተቀራርቦ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑ ተነስቷል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ እያንዳንዱን አስፈላጊ መረጃ በአግባቡ ያለመያዝና ሙሉ ጊዜን ሥራ ላይ ያለማዋል ችግሮች እንዳለ በመረዳት አሁን በተያዘው ዕቅድም እነዚህን ችግሮች ለማረም የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱ ተገልጿል::
ከዚህ በተጨማሪም እንደ ዶሮ እርባታ፣ የወተት ልማት፣ የመስኖ ልማትን የመሳሰሉ አዋጭ የሥራ ዘርፎችን በመለየት በእነዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የታለመው ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻል ውይይት መደረጉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል::
በቱሪዝም ዘርፍ
በሌላ በኩል የቱሪዝም ኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍጹም ካሳሁን እንደገለጹት መንግስት እንደሀገር ትኩረት ከሰጣቸው የሥራ ዘርፎች ውስጥ ቱሪዝም አንዱ መሆኑን በመግለጽ በ2012 ዓ.ም የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የተያዘውን ሀገራዊ ንቅናቄ ለመተግበር ተቋሙ በቱሪዝም ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንዳለ ተናግረዋል::
በዚህም መሰረት በቋሚነት ለ74 ሺ ዜጎች በጊዜያዊነትም ወደ 100 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል:: ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት የሚሠራ እንደሆነና ባለሀብቶች የሚሰሩባቸው ሰባት የቱሪዝም መዳረሻዎች ተለይተው መቀመጣቸውን አስረድተዋል:: በይበልጥ በእነዚህ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ወጣቶች ተያያዥ ሥራዎችን በመስራት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር እንደሚዘረጋ አስረድተዋል::
ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ትኩረት ተደርገው የተለዩ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች እንዳሉም ገልጸዋል:: እነዚህም የመጀመሪያው የማርኬቲንግና የፕሮሞሽን ሥራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቱሪስት መዳረሻዎች የማልማት ሥራዎችን መሥራት ነው:: በሆቴል ኢንቨስትመንትም ይሁን በሌላ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን በማበረታታት በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል:: ከዚህም ጎን ለጎን 22 የቱሪስት መዳረሻዎችን በመለየት የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ፣ የመረጃ ማዕከላትን የማደራጀትና የተለያዩ ለውጦችን በማድረግ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቧል::
አብዛኛዎቹ የቱሪስት መዳረሻዎች መገኛቸው ገጠር አካባቢ እንደመሆኑ በዛ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ተናግረዋል:: ለምሳሌም ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያጸደቃቸውን እንደ ባሌ ተራራ፣ ሰሜን ተራሮች፣ ወንጪ፣ ገራንታን የመሳሰሉት የቱሪስት መዳረሻዎች በገጠር አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆኑ ለማሳያነት ተጠቅሰዋል:: በእነዚህ ቦታዎች ኮሚኒቲ ሎጆች ቢገነቡ ለሥራ ዕድል ፈጠራው አንድ አቅም እንደሆኑ አስረድተዋል::
ቱሪዝም ህዝቡ ማንነቱንና ባህሉን እያስተዋወቀ ገቢ የሚያገኝበት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ፍጹም ዘርፉ ለስራ ዕድል ፈጠራ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ትልቅ ዋጋ እንዳለው የሚያጠራጥር አለመሆኑን ተናግረዋል::
በማዕድን ዘርፍ
የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል መንገሻ በበኩላቸው በ2012 ዓ.ም የማዕድን ዘርፉ በሥራ እድል ፈጣሪነቱ የተመረጠ ሲሆን ከ500 ሺ በላይ ዜጎችን ተሳታፊ ያደርጋል ተብሎ እንደተገመተ ተናግረዋል:: በዚህ ውስጥ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑም ተመልክቷል::
የክልሎችን እና የባለሀብቱን አቅም መገንባት፤ የአሠራሮች፤ የአደረጃጀቶች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማሻሻል፤ አቅም እና ልምድ ያላቸውን ልማታዊ ባለሀብቶች መምረጥ፤ ማሳመን እና መሳብ፤ በዕቅድ የተያዘ እንደሆነ ገልጸዋል:: ጥራት ያለው መረጃ በማቅረብ ኢንቨስትመንቱን ማስፋፋት፤ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እና ለገበያ የሚቀርቡ ማዕድናትን ምርት በመጠንም ሆነ በዓይነት እንዲጨምር ማድረግ እና ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ አስረድተዋል::
በአማራጭ ኢነርጂ ኢታኖል በማምረት 8 ሚሊዮን ዶላር ማዳን የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ኢንተርፕራይዞች በማዕድን ዘርፍ በግልም ሆነ በሽርክና እንዲሠሩ አገር አቀፍ የፕሮሞሽን መድረኮችን በመፍጠር ወጣቱን ያማከለ ቢያንስ 1,124 አዲስ ኢንተርፕራይዞች በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲፈጠሩ ይደረጋል ተብሏል:: በሀገሪቱ የተለያዩ ማዕድናት በባህላዊና በፋብሪካ ደረጃ እንዲመረቱ በማድረግም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል:: ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ልዩ ልዩ የኮንስትራክሽን ማዕድናትን፡- አሸዋ፣ ጥቁር/ቀይ/ነጭ ድንጋይ፣ የሸክላ አፈር፣ ሰሌክትድ ማቴሪያል/ገረጋንቲ/፣ ስኮሪያ፣ ጠጠር፣ ኢግኒምብራይት፣ ሳንድስቶን እና ሌሎችም እንዲመረቱ ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል::
በአጠቃላይ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራው ይሸከማል ተብሎ የታሰበውን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን የሰው ኃይል እውን ለማድረግ ግብርና ሚኒስትር ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ያለ ሲሆን የተለያዩ ሴክተሮችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የማስተባበር ስራን እያከናወነ ይገኛል:: በዚህም መሰረት እንደ ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፍ የመሳሰሉት በአመዛኙ የመገኛ ቦታቸውም ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ ለገጠር ወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ከግብርናው ዘርፍ በመቀጠል ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በመሆናቸው ሊበረታታ ይገባል::
አዲስ ዘመን ነሀሴ 16/2011
ኢያሱ መሰለ