የሙዚቃ ጥበብ ለወሎ ማህበረሰብ ልዩ መገለጫው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወሎ በአዝማሪዎቿና የሙዚቃ ቅኝቶች መገኛነት ትታወቃለች። ከአራቱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅኝቶች መካከል አምባሰልና ባቲ ወሎ በሚገኙ ቦታዎች ስም የተሰየሙ ናቸው፡፡ ትዝታ ቅኝት የቀድሞ ስሙ ወሎ ቅኝት ይባል እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለወሎ ማህበረሰብ ሙዚቃ አንድ ማህበራዊ ተግባር ነው፡፡ ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ይከውኑታል፡፡ አንዱ በድምፅ ሲያንጎራጉር ሌላው ይወዛወዛል፤ የተቀረው ሌላው ደግሞ ያጨበጭባል፤ የዘፈኑንን ግጥሙን እየተቀበለ ያጅባል፡፡ በሌላው ማህበረሰብ ዘንድ ሳይቀር በበዓል ወቅት ከሚዘፈኑ መካከል አማሮ፣ መጋሌ ሰመረ፣ ኧረባቲ ባቲ፣ እሪኩም፣ የመሳሰሉት የአማርኛ እና የኦሮምኛ ቃላት ያሏቸው ዜማዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
«አርሂቡ አብዶዬ ነው ቡና እንጠጣ
ለጀግንነቱማ ብቅ ብሎ ማዬት ላስታ እና ሰቆጣ
ቃሉ ወረድ ብዬ ቀጠልኩኝ ባቲ
አቤት ደስ ማለቱ ናትራ እና አሽኩቲ
ቦርከናን አልፌ ስቃኝ ጦሳ ዳውዶ
ደሴ ሰውን እንጅ አያበቅልም ሰርዶ
የተማረ ሁሉ እጁን ቢዘረጋ
ስህን ታብባለች ሠላምን ፈልጋ
ማሪቱ ትጫዎት ጠላውም ይቀዳ
ፈረስ ለመጋለብ አዬ ቦሩ ሜዳ» በማለት አዝማሪው በሰርግ በድግሱ ድምጹን ያንቆረቁራል።
ስለ ወሎ የሙዚቃ ሁነቶች ከተነሳ ደግሞ የአዝማሪ ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም። አዝማሪ ሲባል ማሲንቆ ይዞ የሚጫወተውን ሙዚቀኛ ነው። በዚህ ረገድ በወሎ ከልጅነታቸው ጀምሮ አዝማሪነትን ተክነው ኋላም በኢትዮጵያ ገናና የሆኑ ሙዚቀኞችን እናገኛለን። እነማሪቱ ለገሰ፣ አሰፋ አባተ እና ሀብተሚካኤል ደምሴን መጥቀስ ይቻላል። የነገስታት ፖለቲካ ተንታኝ የሚባሉት ማየት የተሳናቸው ሐሰን አማኑም የወሎን አነጋገር ዘዬ ተከትለው ቅኔያቸውን የሚደረድሩ አዝማሪ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል።
የአዝማሪ አመጣጥ በርካቶች ከመጽሃፍ ቅዱሱ እዝራ ታሪክ ጋር ያያይዙታል። እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና ዝማሬያቸውን ለአምላክ የሚያቀርቡ መሆናቸው ሐይማኖታዊው ታሪክ ያስረዳናል። ኢትዮጵያውያንም የበርካታ ጨዋታ አሳማሪና መልዕክት አስተላላፊ አዝማሪዎች መፍለቂያ ናት።
ጸጋዬ ደባልቄ የተባሉ ጸሃፊ የጥንት አዝማሪ እንደዘፋኝ መሰንቆና ክራር ተጫዋች፤ እንደ ፖለቲካዊ ሁናቴ አስተያየት ሰጪ፤ እንደ ታሪክ ደግሞ ተራኪ ነበሩ ይሏቸዋል። ሲያሻቸውም እንደታዛቢ ቅሬታ ተናጋሪ እና እንደ ፍቅር መላክተኛ በመሆን ስላገለገሉ ቀደም ባሉ ጊዜያት የአዝማሪ ተፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ።
ደስታ ተክለ ወልድም አዝማሪን የሚለው ቃል «የሚያዘምር፣ ያዘመረ፣ ባለማሲንቆ፣ ዘፋኝ፣ አርኾ፣ ጯሂ» የሚለውን ቃላት የሚተካ በሚል በይነውታል። የኢትዮጵያ ቋንቋና ጥናት ምርምር ማዕከል መዝገበ ቃላት ደግሞ አዝማሪን የሙያውን ባህርይና የማህበረሰቡን ግንዛቤ መሰረት በማድረግ «በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እየታጀበ በመዝፈን የሚተዳደር ሰው» ይለዋል። በተጨማሪም «ምላሰኛ፣ ተሳዳቢ» ሲል አዝማሪን በመፈረጅ ሁለት የተለያየ ብያኔ ይሰጠዋል።
በወሎ የአዝማሪው ህይወት ከባላባት እና ከድግስ መድረኮች ጋር የተቆራኘ ነበር። አዝማሪ በጥንት ጊዜ የባላባት አጫዋች በመሆን አገልግሏል። አዝማሪም ከጭሰኛው መደብ ቢሆን እንጂ የእራሱ ሰፋፊ መሬት ይዞ የሚተዳደር አልነበረም። ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ በታወጀው መሬት ላራሹ አዋጅ መሰረት ጭሰኞችና ገባሮች የራሳቸው መሬት እንዲኖራቸው እድል አግኝተዋል፡፡
አዋጁ አዝማሪዎችን ከባላባላቱ ጋር እየተዘዋወሩ ማጫወታቸው ግዴታ ሳይሆን በውዴታ ስር እንዲወድቅ ፍቃድ የሰጠ አጋጣሚ ነበር። ምክንያቱም አንድ ባላባት በሄደበት አካባቢ ሁሉ የሚያጫውተው አዝማሪ ይዞ ይዞር ነበርና በውድም በግድም አዝማሪው የባላባቱ ታዛዥ ነበር ማለት ይቻላል። በወሎ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ አዝማሪዎች ይገኛሉ። አዝማሪዎቹ ታዲያ የሰው ሰርግ ማድመቅ ብቻ ሳይሆን የእራሳቸውንም በተለየ ሁኔታ መከወን ይችሉበታል።
ይህን ሁሉ ማንሳቴ የወሎ አዝማሪዎችን ጋብቻ የሚያከናውኑበትን ለየት ያለ ስርዓት ለማውሳት ነው። የአዝማሪዎቹ የጋብቻ ስርዓቱ እንደተለመደው በቤተሰብ አማካኝነት ሽማግሌ ተልኮ በሚደረግ ‹‹ልጅህን ለልጄ›› ጥያቄ ይጀመራል፡፡ ለጋብቻው ጥያቄው የሚቀርበው ከወንዱ ቤተሰብ ነው። ዶክተር አስቴር ሙሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ስነ-ፅሁፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል የምረቃ ማሟያ ጥናታቸውን «ተከታታይነትና ለውጥ በወሎ አዝማሪዎች የኑሮና የዘፈን ልምድ» በሚል ርዕስ አቅርበዋል። በጥናቱ መሰረት በአዝማሪዎቹ ዘንድ ሴቷ ለሚስትነት እንድትመረጥ የሚያደርጋት ምክንያት በዋነኛነት ጥሩ ድምፅ ያላት እና ዘፍና ለማደር ፍላጎት ያላት ከሆነች ብቻ ነው።
የሴቷ ቤተሰብ የጋብቻ ጥያቄ ሲቀርብለት የጠያቂውን ቤተሰብ ማንነት ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። የጠያቂው ቤተሰብ የዘር ሐረግና ባለ ጥሩ ድምጽ አዝማሪ መሆን አለመሆን ይጣራል። ካመኑበት ደግሞ ፈቃድ ይሰጥና የጋብቻው ቀን ይቆረጣል። ድግሱና መሞሸሩ በሴቷ ቤተሰብ አማካኝነት የሚካሄድ በመሆኑ የሴቷ ቤት ልዩ ዝግጅት ይደረጋል። በጥናቱ የተካተቱት የአቶ አሰፋ ለገሰ ሃሳብ እንደሚያስረዳው፤ የአዝማሪ ዋናው ሰርግ እስከ ሶስት ቀን ይቆያል፡፡
ሙሽራው የሚሞሸረው ደግሞ ሴቷ ቤት ነው፡፡ ከባህል መበረዝ ጋር ተያይዞ አሁን አሁን እየቀረ የመጣ ቢሆንም ሙሽራው ሴቷ ቤት ተቀምጦ እስከ አስራ አምስት ቀን ድረስ ብሉልኝ ጠጡልኝ ይባላል። የድግሱን ሙሉ ወጪ የሚሸፍኑት ደግሞ ደጋሾች ናቸው። ጠላ ይጠጣል፤ ድፎ ዳቦ (ሙጌራ) ይመጣል፤ ጨጨብሳ ይበላል፤ ዶሮ ይቀርባል። ዘመዱ ሁሉ ያለውን ሊያመጣም ይችላል። እስከ ዋናው ሰርግ ማለትም ሶስት ቀን ድረስ ቤተዘመድ በድግሱ ይቆያል። ከዚያ በኋላ ግን ዘመድ ወደመኖሪያው ይመለሳል። ዘመድ ቢወጣም ሙሽራው ከነሚዜዎቹ እስከ ሁለት ሳምንት ይቆያል።
በአዝማሪዎች ቤት ድግሱ ይህንን ያህል ቀን መርዘሙ የራሱ የሆነ ምክንያት አለው፡፡ አዝማሪዎች ጋብቻቸውን የሚፈፅሙት በአካባቢያቸው ከሚገኝ አዝማሪ ጋር ላይሆን ይችላል። ይህ ምክንያት ከአካባቢያቸው ርቀው ወደሚገኝ የወሎ ክፍል ሊወስዳቸው ይችላል። የቦታው ርቀት እስከ ሶስት ቀናትና ከዚያ በላይ ሊያስጉዝ የሚችል ከሆነ ያንን ያህል ርቀት ተጉዞ የመጣ ሰርገኛ የግድ ማረፍ ይኖርበታል፡፡ እረፍቱም በጥሩ መብልና መጠጥ የታጀበ እንዲሆን ጥረት ስለሚደረግ ቀኑ ይራዘማል፡፡
በጥናቱ መሰረት ለአብነት «በማርዬ፣ ጠጠር አምባ» በሚደረግ ሰርግ ላይ ሰርገኛው ከኮምቦልቻ፣ ከወልድያ፤ ከወረኢሉ ሊመጣ እንደሚመጣ ያስረዳናል፡፡ አብዛኛው ቤተዘመድ አድሮ ሂያጅ ስለማይሆን ከርመው ዋናውን ጠላ እየተቃመሱ ጭፈራቸው ላይ ያተኩራሉ።
በሰርጉ የመጀመሪያ ቀን የአዝማሪዎች ሰርገኛ ሙሽራውን ይዞ ሴቷ ቤት የሚሄድው መሸትሸት ሲል ነው፡፡ ሚዜዎቹንና ሰርገኛውን ይዞ በተጣለው ዳስ ይቆማል፡፡ ከዚያም «ምነው ቆማችሁ» ሲባሉ «አባት ትሆኑንን ብለን ቁመናል» የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ «ልጅ ከሆናችሁን አባት እንሆናችኋለን» ሲባሉ ደግሞ «ምን ቅርብ ቢሆን ሽንታችን ሲመጣ የሚያሳየን አንድ ሰው ይሰጠን» ይላሉ፡፡ ከዚያም ሰርገኛው የሴቷን ቤተሰቦች ጠይቆ ለሚያስፈልገው ጉዳይ ሁሉ የሴቷን ቤተሰብ ወክሎ መልስ የሚሰጥ አንድ ሰው ይመደብለታል፡፡ አሳላፊ ተመድቦ ካለቀ ቀጣዩ ስራ ግብር ማውጣት ይሆናል፡፡ እየተበላ ጨዋታ ይጀመራል። ይህ ሁሉ ሲሆን ሙሽራዋ ከጫጉላ ሆና በነጠላ ተሸፋፍና ነው የምትጠብቀው፡፡ ሙሽራም ይሄድና ወጣ ገባ… ወጣ ገባ እያለ በቀስታ ይገርፋታል፡፡ በኋላ የማሲንቆ ጨዋታው ከሴት ወገን ይጀመራል።
አንድ አዝማሪ ሴት ልጁን ሲድር ሚዜውና ሰርገኛው መሰንቆ ይዘው ቦታቸው ላይ ይቀመጣሉ። ከሴቷ ወገን በዕድሜ ገፋ ያለው ተነስቶ በመዲናና ዘለሰኛ ጨዋታውን ይጀምረዋል፡፡ ከዚያ ወዲያ በዕድሜ ተዋረድ ከታላቅ ወደ ታናሽ መሰንቆ የያዘው ሰው ሁሉ እየተነሳ ታዳሚውን ያዝናናል፡፡ መከባበሩ አለ። በኋላ ላይ ግን ታዳሚው ጥሩ አዝማሪ መርጦ እከሌ ያጫውተን ይላል፡፡ በሰርጉ ወቅት ግን ሙሾ መሰል ግጥሞችም ይቀርባሉ። ለአብነት የሙሽራዋ አባት በህይወት ከሌሉ ስማቸውን እያነሱ «ዛሬን እንኳን ብቅ ብለህ ልጅህን ዳር» እያሉ ያዜማሉ፡፡
ከሁሉ የሚያስገርመው ግን ሙሽራው ማሲንቆ ይዞ ታዳሚውን የሚያዝናናበት ትርኢት መኖሩ ነው። አዝማሪ ነውና ማሲንቆ መግረፉን በደንብ ያውቅበታል። ለባለቤቱ የሚሆን ግጥም እየፈለገ በሰርጉ ቀን እንዲህ እያለ ያወድሳታል።
«ከተረከዞቿ ውሃ ጠብ ሚለው፣
እልፍ ብሎ ባቷ ቡችል ቡችል ያለው፣
ሽንጥና ዳሌዋ የተደላደለው፣
አንገቷ እንደ ጠርሙስ አፈፍ ለቀቅ ያለው፣
ግንባሯ መስታይት የሚያጥበረብረው፣
ጠጉሯ ሃር ነዶ ግንፍል ግንፍል ያለው፣
ዋ በግድ ይለዩ ይዣት መሄዴ ነው።»
እንዲህ እንዲህ እያለ እስከ ሁለት ሳምንት በሴቷ ቤት ከቆየ በኋላ ወደ ራሱ ቤት ይዟት ይሄዳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
ጌትነት ተስፋማርያም