አንድን ዜጋ በሥነምግባርም ሆነ በአዕምሮ ማጎልበትና ለቤተሰቡ፣ ለማሕበረሰቡ ብሎም ለአገር አምራችና ጠቃሚ እንዲሆን በሚደረገው የግንባታ ሒደት ቤተዕምነቶች ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ የተለያዩ የማሕበራዊ ሣይንስ ምሁራን ያስቀምጣሉ:: ሆኖም ግን ይህ መሆን የሚችለው ተቋማቱ ተምሳሌት መሆን ሲችሉ እንደሆነ እሙን ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የቤተክርስቲያን ሀብት ምዝበራ እንዳለ በመግለጽ፤ የተጠያቂነት ሥርዓቱ የላላ መሆን በችግሩ ተሳታፊዎች ላይ የሚወሰድ የእርምት እርምጃ እንዳይኖር በማድረጉ ቅሬታ የፈጠረባቸው አባቶች ለተቋማችን አቤቱታቸውን አቅርበዋል:: እኛም ከእነርሱ አንደበት ያደመጥነውን፣ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን በማገላበጥና የሚመለከተው አካልስ በጉዳዩ ላይ ምን ይላል? በሚል ያጠናቀርነውን ዘገባ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል::
ከአንደበታቸው
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር መኖሩን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የየካ አባዶ ጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መለአከ ገነት አባ ሀብተማርያም ቦጋለ ይጠቁማሉ:: ችግሩ ስር የሰደደና ከአቅም በላይ በመሆኑም ሲኖዶሱንና ፓትርያርኩን የተፈታተነ ነው ይላሉ:: ጉዳዩ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት በመድረሱም ቤተክርስቲያናቱ ምሳሌ እንዲሆኑ ቢጠበቅም ዕውነታው ግን በተቃራኒው በመሆኑ ገጽታውንም እያበላሸ ይገኛል ባይ ናቸው::
በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋሉትን ችግሮች በማሳያ ሲያቀርቡም፤ ቤተክርስቲያኒቱ ተራራማ ስፍራ ላይ የምትገኝ በመሆኗ በተለይም ለአረጋውያንና ለሕፃናት መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ስለሚያዳግት አቶ ከፍያለው ደርቤና ወይዘሮ ሮማን ኪዳነማርያም ከተባሉ ግለሰቦች በ85 ሺህ ብር ይዞታን ትገዛለች:: በቦታውም የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን ለመትከል አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ሕጋዊ ሆኖ ለመሥራት ትጠይቃለች::
በ2009 ዓ.ም የቤተክርስቲያኒቱ ጥያቄ ፈቃድ በማግኘቱ ጽላት እንዲዘጋጅና በሕጋዊ መንገድ እንድትቋቋም በመንበረ ፓትርያርክ ታምኖበት ተቋቁሞ ለአንድ ዓመት አገልግሎት ይሰጣል:: ነገር ግን በወቅቱ የነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ ያለምንም ምክንያት ሕገ ቤተክርስቲያንን ሥርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ ሌላ ሠራተኛ በማዋቀር ቤተክርስቲያኑን እንደገነጠለ ያስታውሳሉ::
በፍርድ ቤትም ቦታው የቤተክርስቲያኒቱ እንደሆነ መረጋገጡን የሚያመላክቱና ሌሎች ማስረጃዎችን በማቅረብ ሀገረ ስብከቱ የፈፀመውን ችግር በመዘርዘር ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን ይገልፃሉ:: ለዚህም እንደ አንድ ማረጋገጫ የሚሆነው ቤተክርስቲያኒቱ በተቋቋመችበት ወቅት ሕገወጥ ይዞታ (የጨረቃ ቦታ ነው) በሚል ከአስተዳደሩ ጋር በነበረ አለመግባባት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቤተክርስቲያኒቱ ባለቤት እንደሆነች ያረጋገጠበት ሰነድ ነው ይላሉ::
በቤተክርስቲያኒቷ ሀብት ንብረት ላይ ግለሰቡ በጉልበት ይህን መሰል ድርጊት መፈፀሙ ተገቢ ባለመሆኑ በሕግ አግባብም ስለማያስኬድ በአስቸኳይ እንዲያስተካክል ድርጊቱ በተፈፀመበት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ደብዳቤ ይጽፋሉ:: ነገር ግን ምላሽ የሰጣቸው እንዳልነበረ ነው አባ ሃብተማርያም የሚናገሩት:: በሒደትም ችግሩን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ያቀርባሉ:: ሲኖዶሱም ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱን ሕግና ስርዓት የጣሰ ድርጊት መሆኑን በመግለጽ፤ በአስቸኳይ ወደነበረበት እንዲመለስ የሚል ውሳኔውን ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ያስተላልፋል::
የተፈጠረው ችግር እንዲስተካከል የተደረገውም ሥራ አስኪያጁና የድርጊቱ ተባባሪ ሠራተኞች ከሥራ ታግደው ነው:: ሐምሌ 16 ቀን የተወሰነው ውሳኔ ባለመፈፀሙም ለአዲሱ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ነገ ዛሬ በሚል ያልተጨበጠ ምላሽ ለእንግልት ተዳርገዋል:: ፈጣንና ተገቢው የመፍትሔ እርምጃ ባለመወሰዱም ችግሩ ሊቃለል አለመቻሉን ያብራራሉ:: ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የተጠያቂነት ሥርዓቱ የላላ መሆኑ የችግሩ ምንጭ አድርገው ያቀርባሉ::
ውሳኔው ሲያርፍ የቤተክርስቲያኒቱን ጉዳይ ጨምሮ ሌሎች በርካታ በሀገረ ስብከቱ የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም በጋራ ታይተው ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ተደርጓል የሚሉት አስተዳዳሪው፤ ቅሬታዎች እየተበራከቱ በመሄዳቸው የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመመርመር አጣሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ መቋቋሙን ያስታውሳሉ:: ኮሚቴውም በማጥራቱ የደረሰባቸውን ግኝቶች አቅርቦ ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔውን ያሳርፋል:: ሆኖም ግን የሲኖዶስ ውሳኔ ስለማይከበር ተፈፃሚ ያላደረገ አካልም ተጠያቂ ስለማይደረግ ውሳኔው ከወረቀት በዘለለ ተፈፃሚ እንደማይሆንና እንደማይከበር ነው አስተዳዳሪው የሚጠቁሙት::
ጥፋት በማስረጃ ከተረጋገጠ ተገቢውን ቅጣት ማሳረፍ ይገባል:: ይሁን እንጂ ይህን መሠል ሌሎች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ሊያደርግ የሚችል አስተማሪ ተመጣጣኝ እርምጃ አይወሰድም:: ይልቁንም ጥፋተኛ ነው የተባለ አካል ከሥራ ወደ ሥራ ጥቅማ ጥቅሞቹ ተከብረውለት ስለሚዘዋወር አዲስ ተተኪውም ተጠያቂነት እንደሌለ ስለሚያውቅ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ እንዲሯሯጥ ሲያደርገው ይታያል::
ጥፋተኞች ከቦታ ቦታ እየተቀያየሩ በዝምታ ስለሚታለፉ አዲስ በቦታው ላይ የሚቀመጠውም ተደራጅቶ ተመሳሳይ ጥፋት ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደርገዋል:: የቀድሞ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ ተጠያቂነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉት አስተዳዳሪው፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔው ባለመፈፀሙ ዳግም 350 የሚደርስ ከየቤተክርስቲያናቱ የተሰባሰበው ኃይል ‹‹አዲስ የተቀየረው ሀገረ ስብከትም እየሠራ፤ የሲኖዶሱን ውሳኔም በትክክል ተግባራዊ እያደረገ አይደለም›› በሚል ቅሬታ ማቅረቡን ይገልፃሉ:: በዚህ ምክንያትም አዲሱ የሀገረ ስብከቱ አመራር በስድስት ወሩ በድጋሚ በ2011 ዓ.ም ታሕሳስ ወር ላይ እንዲባረር ተደርጎ አዲስ አመራር እንዲመደብ ተደርጓል::
ሲኖዶስ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳርፎ እንደነበር በመግለጽ፤ ተፈፃሚነታቸው ላይ ግን ችግር ስላለ ምን ይደረግ? በሚል ጥያቄ ሲቀርብ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በመሆኑ በዚህ አፈፃፀም ላይ ገብተው ምንም የሚሉት ነገር እንደሌለ ነው የሚናገሩት:: ለዚህም በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ፈጽሙ የሚል ትዕዛዝ እስካልመጣ የእርሳቸው ሀገረ ስብከት ስለሆነ የራሱ የሆነ አሠራርና ሒደት አለው:: ስለሆነም በጠቅላይ ቤተክህነቱ በኩል ቀጥታ የሚደረግ ነገር እንደማይኖርም እንደተገለፀላቸው ያስታውሳሉ::
ምላሹን በመቀበል ለቅዱስ ፓትርያርኩ በሲኖዶሱ ያሳረፉት ውሳኔ ሊፈፀም ባለመቻሉ ሕዝቡ እየተሰቃየ፣ ንብረት እየተዘረፈ መሆኑን በመግለጽ፤ ተረኛ መደበኛ ሠራተኞችን በመውሰድ የቤተክርስቲያኒቱን ቁልፍ በሌሊት ተገንጥሎ ዘረፋ በመከናወኑ ሕዝቡ ከሰበካ ጉባዔ አባላት ጋር በመሆን ያመለክታል:: ቅዱስ ፓትርያርኩም በአስቸኳይ የሲኖዶሱ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ መመሪያ ያስተላልፋሉ:: ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ምላሽ መስጠት ሳይቻል ቀርቶ ችግሩ እንደቀጠለ ነው::
በሥልጣን እርከን መሠረት የቤተክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ወይንም የበላይ ሆኖ ሕግ፣ መመሪያ ቃለአዋዲውን ደንግጎ የሚያወጣ፣ አይደለም በሥራ በኃይማኖት ህፀፅ እንኳ አንድን ሠው ክርስቲያን አይደለም ብሎ ሥመ ክርስትናውን፣ ሥልጣነ ክህነትን የመግፈፍ ብሎም ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በታች በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ማንኛውንም ነገር የማድረግ የበላይ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ ውሳኔውም የመንፈስ ቅዱስ ውሳኔ ተደርጎ ነው የሚወሰደው:: የቤተክርስቲያኒቱ መጋቢ የሆነውን የሲኖዶሱን ትዕዛዝ መቃወምም ሆነ ያሳረፈውን ውሳኔ አለመፈፀምም ቤተክርስቲያንንና ኃይማኖትን እንደመቃወም ይቆጠራል:: ይህም ተግባራዊ ባለመሆኑ ከፍተኛ ችግሮች እንዲፈጠሩ በር እየከፈተ እንደሆነ ነው አባ ሀብተማርያም የሚጠቁሙት::
የሲኖዶሱን ውሳኔ ተፈፃሚ ያላደረጉ የሀገረ ስብከቱ አመራሮችና የድርጊት ተባባሪ ሆነው የተገኙ ሠራተኞች በአንድ ዓመት ብቻ ለሁለት ጊዜ እንዲሰናበቱ ተደርጓል:: ችግሩ ግን በጽሁፍና በቀላል ውሳኔዎች ብቻ ሊቃለል የሚችል ባለመሆኑ ቀጥሎ ይታያል ሲሉ ጠንካራ ውሳኔዎች እንደሚያስፈልጉ አስተዳዳሪው ይናገራሉ:: በቦታው ላይ የሚቀመጡ አዲስ አመራርና ሠራተኞች ቀድሞ የነበሩት ባለመኖሪያ ቤት፣ ባለመኪና ሲሆኑና ሀብት ሲያካብቱ ስለሚመለከቱ ከዚህ አልፎም ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂነት እንዳሌለ ስለሚያውቁ ኑሯቸውንና የራሳቸውን ሕይወት በቶሎ የማስተካከል አስተሳሰብን ይዘው ስለሚቀመጡ ተቀዳሚ ሥራቸው ራሳቸውን ማዕከል ያደረገ ነው::
አባ ሃብተማርያም፤ የቀድሞ ሀገረ ስብከት በርካቶችን ለእንግልት የዳረገና ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር የነበረበት በመሆኑ ታግዶ ቢባረርም ቀጥሎ የተቀመጠውም ከችግር የወጣ ስላልነበር ዓመት ሳይቆይ ሊለወጥ ችሏል:: ለዚህም መነሻ ምክንያቱ በጥፋታቸው ልክ ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ አለመወሰዱና ሲኖዶሱም የማስገደድ አሠራሩ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ነውና በትኩረት ሊታይ ይገባል ይላሉ::
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የእርቱ ሞጆ ቅድስት ክርስቶስ ሣምራ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቤ ኃይማኖት መንግስቱ ድረስ፤ መንግስት በቤተክርስቲያኒቱ ሥራ ውስጥ ዳኝነት አለመስጠቱ ጥፋተኞች በሕግ ተጠያቂ እንዳይደረጉ ማስቻሉን ይናገራሉ:: በሌሎች ዕምነቶች ከመንፈሳዊ ዳኝነቱ ባሻገር በዓለማዊው የዳኝነት ሥርዓት መብትን ማስከበር እንደሚቻል በማንሳት የሸሪያ ፍርድ ቤትን ለማሳያነት ያቀርባሉ:: በዚህ ግን በችግር ውስጥ ተሣታፊ የሚሆኑ አካላት በሕግ ተጠያቂ ስለማይደረጉ የሲኖዶሱም ይሁን የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ተፈፃሚ አይሆኑም::
ለአራት ዓመታት ያለ ሥራ እንደተቀመጡ የሚናገሩት መጋቤ ኃይማኖት መንግስቱ፤ ሀገረ ስብከቱ ጥበቃ በር እንደሚዘጋባቸው ነው የሚናገሩት:: በዚህም የሚመለከተውን አካል አግኝተው ማነጋገር አይችሉም:: ሲኖዶስ ያስተላለፈውን ውሳኔ ከማስፈፀም ይልቅ ብዙዎች የራሳቸውን ሕይወት መለወጥ ላይ ትኩረት መስጠታቸውና የዘረፉትንም የቤተክርስቲያናት ሀብት እንዲመልሱ አለመደረጋቸው አሠራሩ ምን ያክል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍጠር ምቹ መሆኑን ያመላክታል ባይ ናቸው::
ፓትርያርኩም የሚጽፉት ደብዳቤ ለምን ተፈፃሚ እንዳልሆነና ባልፈፀመው አካል ላይ እርምጃ አይወሰዱም:: ይልቁንም ከበላ በኋላ ተነስቶ ሌላ የሚመቸው ቦታ ላይ እንዲቀመጥ ይደረጋል:: ይህ ስለሆነም በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ከመቃለል ይልቅ የሚሰበሰበው ብር በሌላ መንገድ ግለሰቦች ሲከብሩበት ይታያል በማለት መጋቤ ኃይማኖት መንግስቱ ችግሩን ያብራራሉ::
የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚወሰድ እርምጃ ባለመኖሩ ረጅም ዓመታትን ያለ ሥራ የተቀመጡ እንዳሉና ተጎጂዎችም ቢጮሁ የሚሰማቸው እንዳሌለም ነው መጋቤ ኃይማኖት የሚያስረዱት:: በሩን አልፈው እንኳ አቤቱታቸውን ለማቅረብ በጥበቃ ስለሚከለከሉ ይቸገራሉ:: በሌላ በኩል ደግሞ በሲኖዶስ የሚያርፉ ውሳኔዎችም ተፈፃሚ ስለማይሆኑ ትርጉም አልባ ሆነዋል::
በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ መሐል የፍትሕ መጓደሎች በሚፈጥሯቸው ችግሮች ቤተሰብን የሚጎዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይፈጠራሉ:: ይህም የሚሆነው አንዳንድ አባቶች አለአግባብ ሥራቸውን ተቀምተው በባዶ ሜዳ ለሌላ ሠው ስለሚሰጥባቸው ነው:: ሌላ ሥራ ለመሥራትና ቤተሰብ ለማስተዳደር ደግሞ በኃይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ ያገለግል የነበረን አባት ቀጥሮ ከማሠራት በገንዘብ መደገፍን ምርጫቸው የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው:: የተማሩም ቢሆኑ እንኳ ‹‹ቆብ ደፍቶ ቀሚስ ለብሶ ወደ ቢሮ ሥራ የሚገባን ቄስ ለመቅጠር ፍላጎት የለም››:: በዚህም ልጆች ትምህርት ለማቋረጥ ይገደዳሉ:: ለዚህም ደግሞ መጠየቅ የሚገባው ሲኖዶሱ በተለይም ደግሞ ፓትርያርኩ ናቸው ይላሉ:: የተወሰነ ውሳኔ ሳይፈፀም ሲቀር ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ባለመኖሩ የችግሩን አስከፊነት እየጨመረው ነው በማለት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን መጋቤ ኃይማኖት ይጠቁማሉ::
ሰነዶች
ቤተክርስቲያኒቱን አስመልክቶ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል በቀን 08/12/2003 ዓ.ም የታሰረው የመኖሪያ ሽጭ ውል ስምምነት ሰነድ ይገኛበታል:: በሰነዱ ላይ ሰፍሮ እንደሚታየው፤ ውል ሰጭዎች አቶ ከፍያለው ደርቤና ወይዘሮ ሮማን ኪዳነማርያም ሲሆኑ፤ ውል ተቀባይ ደግሞ የካ አባዶ ጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ናት:: በዚህም ውል ሰጪዎች ወይንም ሻጮች በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘውን አዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ልዩ ሥሙ አዳማ ቁጥር አንድ ውስጥ የሚገኘውን የቦታው ስፋት 230 ሜትር ካሬ 20 ቆርቆሮ አንድ ክፍል ቤት ያረፈበት ቤትና ቦታ ለውል ተቀባይ በ85 ሺህ ብር መሸጣቸውንና ገዢዎችም ክፍያውን ሙሉ በሙሉ ከፍለው መግዛታቸውን ያሳያል::
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት በቀን 23/05/2009 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 277/35/09 ወጪ ተደርጎ የተላከው ደብዳቤ ቤተክርስቲያኒቱን አስመልክቶ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል አንዱ ነው:: ደብዳቤው የጽላት ፈቃድን አስመልክቶ የተፃፈ ነው:: በዚህም ቤተክርስቲያኒቷ ሰበካ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት በቁጥር 10/385/09 በቀን 22/03/2009 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ቤተክርስቲያኗ ተራራ ላይ በመሆኗ ሕዝበ ክርስቲያኑን አገልግሎት ለመስጠት በተለይም አረጋውያንና ሕፃናት በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ቀደም ሲል በስጦታ ካገኙትና በፀበል ቤትነት ሲጠቀሙበት በነበር ቦታ የቅዱስ ገብርኤልን ጽላት አስገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ጽላቱ እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ያወሳል::
ጉዳዩንም ክፍለ ከተማው በቅርበት አይቶ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን እንዳመነበትና ጽላቱ እንዲፈቀድላቸውና እንዲሰጣቸው ማሳሰቡን ደብዳቤው ያሳያል:: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤትም ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በቀን 24/05/2009 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 1069/718/09 ወጪ የተደረገው ደብዳቤ ሌላኛው ሰነድ ነው:: በዚህ ደብዳቤ እንደሰፈረው፤ ቦታውን በቅርበት የሚከታተለው የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አምኖ ሀገረ ስብከቱን መጠየቁን በመግለጽ፤ በደብሩ ሥም የቅዱስ ገብርኤል ጽላት ተዘጋጅቶ በደብሩ አስተዳዳሪ አማካኝነት እንዲረከቡ ሲል ያስቀምጣል::
የፍርድ ሒደት
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ28/03/2010 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር የኮ/መ/196033 ወጪ የሆነው የመዝገብ ግልባጭ እንደሚያመላክተው፤ ይግባኝ ባይ የካ አባዶ ጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እንዲሁም መልስ ሰጭ የካ ክፍለ ከተማ /ወ/አ/12/ማ/ጽሕፈት ቤት ሲሆን፤ አለመቅረቡንና መዝገቡን መርምሮ ፍርድ እንደሰጠ ያሳያል:: በመዝገቡ የቀረበው ይግባኝ አቤቱታ መነሻ የሆነው ጉዳይ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 247271 በቀን 25/07/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት መሆኑንም በፍርድ ሒደቱ ያብራራል::
ይግባኝ ባይ በስር ፍርድ ቤት ከሳሽ መልስ ሰጭ ደግሞ ተከሳሽ በመሆን ለአቤቱታ መነሻ የሆነውን ቤተክርስቲያኗ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 28 ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሚገኘው ከአቶ ከፍያለውና ከወይዘሮ ሮማን ከአቶ ደበሌ አያኖ እና አስካለ ጅማ ጥቅምት 27 ቀን 1991 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ
ውል የተላለፈውን 230 ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት የካቲት 21 ቀን 1996 ዓ.ም በተደረገ የስጦታ ውል ተቀብላ በእጇ አድርጋ እየተጠቀመችበት እንደምትገኝ መዝገቡ አስፍሯል:: ተከሳሽም ቤተክርስቲያኒቱ በንብረቷ ላይ ያላትን ሙሉ መብት እንዳትጠቀም የተለያዩ ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱ ይነበባል:: በተደጋጋሚ በተከሳሽ የሚፈፀመውን ሕገወጥ ተግባር እንዲቆም በየደረጃው ለሚገኙ የበላይ አካላት ከሳሽ ቤተክርስትያኒቷ ብታሳውቅም መፍትሔ ግን ሳታገኝ ቆይታለች:: ተከሳሽም ከድርጊቱ ባለመታቀብ ከሳሽ በእጇ አድርጋ እየተጠቀመችበት የሚገኘውን እና በስጦታ ያገኘችውን ሕጋዊ ቤት እንድታፈርስ የአራት ቀን ገደብ በማስቀመጥ ሕዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም የፃፈው ማስጠንቀቂያ በከሳሽ ላይ የፈፀመው ሁከት ድርጊት በመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሁከቱ እንዲወገድ መጠየቃቸውን በስር ፍርድ ቤት ላይ መቅረቡን መዝገብ ግልባጩ ያብራራል::
በችሎቱም መልስ ሰጭ የነበረው ተከሳሽ ይዞታው ከቀድሞ ሻጮች ሕጋዊ ይዞታ ስለመሆኑና ገዥዎች ናቸው ወደተባሉት ግለሰቦች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ስለመተላለፉ የቀረበ ማስረጃ የለም፤ የስጦታ ውሉም በሚመለከተው አካል የፀደቀ አይደለም፤ ቤቱም በአየር ካርታ ላይም ሆነ በጂ አይ ኤስ የሚታይ አይደለም ሲል ይከራከራል:: ይህ ደግሞ በመንግስት ባዶ ቦታ ላይ የተገነባ ሕገወጥ ግንባታ ነው:: ሕገወጥ ግንባታን መቆጣጠር እንዲያፈርሱ ማስጠንቀቂያ መስጠትና ካላፈረሱ በግብረ ኃይል እንዲፈርስ ማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ጥሰትን ለመከላከል ለመቆጣጠርና የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት እና አሰራር ለመወሰን የወጣን ደንብ ቁጥር 54/2005 መሠረት ለተከሳሽ የተሰጠ የሥራ ኃላፊነት በመሆኑ ኃላፊነቱን ከመወጣት ውጭ የፈፀመው የሁከት ተግባር የለም እንዲባል በማለት ማቅረቡን መዝገቡ አስፍሯል::
የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ ከሳሽ ይህንን ለክርክር መነሻ የሆነ ቦታና ቤት ባልተጭበረበረ ወይም በሕጋዊ መንገድ የያዘው ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ አለማቅረቧንና በይዞታው ላይ አለ የሚባለው ቤትም በ2003 ዓ.ም የመስመር ካርታ ላይ እንደማይታይ በተቋሙ ምላሽ ማረጋገጡን መዝገቡ ያሳያል:: ይህም የሚያስገነዝበው የይዞታው አመጣጥ በሕጋዊ መልኩ የተገኘ አለመሆኑን ነው:: ስለሆነም ተከሳሽ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ተገቢ የሆነና አስተዳደራዊ እርምጃ በመሆኑ ለከሳሽ የሰጠው ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር ስላልሆነ የከሳሽን ክስ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም በማለት ውሳኔውን ይሰጣል::
ይግባኝ ባይም በውሳኔ ቅር በመሰኘት በስር ፍርድ ቤት የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዘው ያቀረቡ ሲሆን፤ ያቀረቧቸው የሰነድ ማስረጃዎችም የገጠር መሬት መጠቀሚያ የግብር መክፈያ ሰነዶች ማቅረባቸውን ያትታል:: ይህም የሚያሳየው ይዞታውና ቤቱ ላይ ተከሳሽ በሚያውቀውና ይዞታውን በሕጉ መሠረት ለመንግስት ግብር ሲከፍሉ እና ሲገለገሉ ከቆዩ ባለይዞታዎች በስጦታ ውል መሠረት ይዘው እየተጠቀሙበት መሆኑን በበቂ ሁኔታ አስረድተው ፍርድ ቤቱ ይዞታው የተላለፈው በሕጉ መሠረት መሆኑን አላስረዱም በማለት የሰጠው ውሳኔ ሊሻር ይገባል በማለት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን መዝገብ ግልባጩ ያብራራል::
ፍርድ ቤቱም በመዝገብ ቁጥር 247271 በቀን 25/07/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ካቀረበው ቅሬታ ጋር በመመርመር የስር ፍርድ ቤት ይግባኝ ባይ ለክርክር መነሻ የሆነውን ቦታና ቤት በሕጋዊ መንገድ የያዘው ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ አላቀረበም በማለት የሰጠው ውሳኔ አግባብነትና ሌሎችንም ነጥብ ለማጣራት መስል ሰጭን ያስቀርባል በማለት መልስ እንዲሰጥበት ያዛል:: ሆኖም ግን መልስ ሰጭ መጥሪያ ደርሷቸው በቀጥሮ ቀን ባለመቅረባቸው መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል::
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን አቤቱታ ከቀረበው ውሳኔ ጋር አገናዝቦ መመርመሩን ያስነብባል:: የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ ከሳሽ ለክርክር መነሻ የሆነ ቦታና ቤት ባልተጭበረበረ ወይም በሕጋዊ መንገድ የያዘው ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ አላቀረበም በይዞታው ላይ አሉ የሚለው ቤትም በ2003 ዓ.ም በመስመር ካርታ ላይ እንደማይታይ በተቋሙ ምላሽ ተረጋግጧል:: ይህም የሚያስገነዝበው የይዞታው አመጣጥ በሕጋዊ መልኩ የተገኘ አለመሆኑን ነው:: ስለሆነም ተከሳሽ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ተገቢ የሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ በመሆኑ ለከሳሽ የሰጠው ውሳኔ ማስረጃን መሠረት ያደረገ አይደለም በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንደተቸው መዝገቡ ያሳያል::
ለክርክር መንስኤ የሆነው ይዞታ ይግባኝ ባይ በስጦታ ያገኘችውና ስጦታ ሰጪዎቹም ከአቶ ደበሌ አያኖና አስካለ ጅማ ጥቅምት 27 ቀን 1991 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ውል የተላለፈላቸውን 230 ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት የካቲት 21 ቀን 1996 ዓ.ም በተደረገ የስጦታ ውል ይዞታው ከቀድሞ ሻጮች ሕጋዊ ይዞታ ስለመሆኑና ገዢዎች በስማቸው ግብር ሲገብሩና የልማት መዋጮ የከፈሉ መሆናቸውን በማስረጃ አያይዘው ማቅረባቸውን አስፍሯል:: በተጨማሪም ሕጋዊ በሆነ መንድ ስጦታ ስለመተላለፉ በበቂ ሁኔታ ያረጋገጡ በመሆኑ የኢፌዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 40/7/ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ መሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ሙሉ መብት አለው እንደሚል አጣቅሶ ያቀርባል::
ይህም መብት የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስና ባለቤትነቱን የማዛወር መብት ሰጥቶት እያለ ከሳሽ በሕጋዊ መንገድ በስጦታ ያገኘችውን ቤት እንድታፈርስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ሁከት ሆኖ ቢሆንም የስር ፍርድ ቤት ግን ሁከት የለም በማለት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ማለቱ በመዝገብ ግልባጩ ይነበባል:: የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 247271 በቀን 25/07/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሻሩንና መልስ ሰጭ በይግባኝ ባይ ላይ የፈጠረው ሁከት ይወገድ በማለት ውሳኔ ማሳረፉን ያትታል::
ይዞታው የቤተክርስቲያኒቷ መሆኑን ፍርድ ቤት በደረሰ ክርክር እንደረታች ከተመለከትን በኋላም ቤተክርስቲያኒቱ በሀገረ ስብከቱ ያጋጠማትን ችግርና ሌሎች ተያያዥ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በስብሰባው የያዘውን ቃለ ጉባዔ መመልከታችንን ቀጠልን::
የሲኖዶሱ ቃለ ጉባዔ
ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የያዘው ቃለ ጉባዔ ይገኛል:: በሰነዱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሰብሳቢ ሆነው መገኘታቸውንና እርሳቸውን ጨምሮ ሰባት አባላት እንደተሳተፉበት ያሳያል:: የስብሰባው ምክንያትም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተፈጠሩ የተባሉትን የአስተዳደርና የሙስና ችግሮች እንዲያጣራ የተሰየመው ልዑክ የማጣራቱን ሥራ በማጠናቀቅ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ያቀረበው 105 ገጽ የያዘ ጥራዝ ሪፖርት ላይ በመነጋገር ውሳኔ ለማሳረፍ የተያዘ መሆኑን ያመለክታል:: ቋሚ ሲኖዶስ የቀረበውን ሪፖርት በመመርመርና ከልዑካኑ በተሰጡ ማብራሪያዎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል::
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተከስቶ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና ችግር ገዝፎ ለበርካታ ሠራተኞች መፈናቀልና ከነቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲጋለጡ ከማድረጉም በላይ እሮሮው በከፍተኛ መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶች ድረስ ደርሶ የቤተክርስቲያንን መልካም ገጽታ ጤናማ ሆኖ እንዳይታይ ያደረገ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል:: ይህም በተደረጉ የመንግስት ስብሰባ መድረኮች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ፍትሕ አልባ ሆና እንድትታይ ያደረገ እንደነበር በውይይቱ ተወስቷል:: እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርክ ቅጥር ግቢ ከየአድባራቱ የተፈናቀሉ ሠራተኞች በየጊዜው በሚያደርጉት ሠላማዊ ሰልፍ እየተጨናነቀ አባቶችን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ እንደነበርም ያወሳል::
የአጣሪ ልዕካኑ ሪፖርት እንደሚያመለክተውና በማጣራቱ ሥራ የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሲታይ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦትና የሥራ ኃላፊዎቹ የመልካም አስተዳደር እጦት በእጅጉ የገነነ ስለነበር በቋሚ ሲኖዶስ የሚወሰኑ ውሳኔዎች፣ በመንፈሳዊም ሆነ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ውሳኔዎች ብሎም ከበላይ አካል የሚሰጡ መመሪያዎች ተግባራዊ አለመደረጋቸው እንደታወቀ ቃለ ጉባዔው ያሳያል::
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በነበሩት ችግሮች ሳቢያም ቃለ ዓዋዲውንና ሌሎች ሕጎችና መመሪያዎችን ያላገናዘበ ቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገት፣ የደመወዝ ጭማሪና ዕግድ መፈፀሙ፣ ሥራ አስኪያጁ ከተሰጣቸው ሥልጣን በዘለለና ከቃለ አዋዲው ሕግ ውጭ ጥብቅ አስተዳዳሪ በሚል መደበኛ አስተዳዳሪዎችን በማፈናቀል በሕገወጥ መንገድ አለቆችን መሾማቸው፣ ከየአጥብያ አብያተ ቤተክርስቲያናቱ ካለበደላቸው በርካታ ሠራተኞች እንዲባረሩና ከነቤተሰቦቻቸው ለረሀብ እንዲጋለጡ መደረጉ፤ ይህም በነበሩት ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ ግለሰባዊ አመራር የተፈፀመና ለሙስናም በር ከፋች እንደነበር ሪፖርቱ እንደሚገልጽ በቃለ ጉባዔው ሰፍሮ ይገኛል::
በሥራ አስኪያጁ ከመመሪያና ከሕግ ውጭ ለተከናወኑ ሥራዎች በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ የዋና ክፍል ሠራተኞች አስተዋፅዖ እንደነበረበት ጉባዔው መገንዘቡንም ያስነብባል:: በዚህም ቋሚ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ተነጋግሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በነበረው የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ያለአግባብ ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ተፈናቅለው ያለሥራና ደመወዝ የቆዩ ሠራተኞች አጣሪ ልዑኩ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ቋሚ ሲኖዶስ ሙሉ በሙሉ እንዳፀደቀው ያስረዳል:: ስለሆነም ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ከሥራቸው የተባረሩ ሠራተኞች አጣሪ ልዑኩ ባቀረበው ዝርዝር መሠረት ከሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ደመወዛቸው ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ተከፍሏቸው በአዲስ አበባ በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ደረጃቸው ተጠብቆ ቦታ ተፈልጎ በሥራ እንዲመደቡ ሲል ውሳኔ ማሳለፉን ቃለ ጉባዔው ያሳያል::
የሀገረ ስብከቱ የመልካም አስተዳደር እጦትና ለሙስና በር ከፋች በሆኑ አሠራሮች በዋናነት የችግሩ ባለቤትና ተጠያቂ የሆኑት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት መምህር ጎይቶኦም እንዲሁም በሥራቸው የሚገኙ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሌሎች የችግሩ ተጋሪዎች በሚመለከታቸው አካላት ልዩ የማጣራት ሥራ ተካሂዶባቸው ውሳኔ ሊያገኙ ስለሚገባ በቀጣይ ስብሰባ ጉዳዩ በአጀንዳ ተይዞ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶስ እንዲነጋገርበትም ይወስናል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሕገወጥ አሠራር ምክንያት በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ፊርማ ጥብቅ አስተዳዳሪ ተብለው የተመደቡት ጉዳያቸው በቋሚ ሲኖዶስ ተጠንቶ ውሳኔ እስኪያገኙ ባሉበት ሥራ እንዲቀጥሉም መወሰኑን ቃለ ጉባዔው ያስነብባል::
ከአጣሪ ልዑኩ የቀረበው ሪፖርት ተግባራዊ እንዲሆን ቋሚ ሲኖዶስ ያፀደቀው ስለሆነ ሪፖርቱ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት እንዲተላለፍና ሀገረ ስብከቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግና አፈፃፀሙን እንዲያሳውቅ ቋሚ ሲኖዶስ መወሰኑን ያሳያል::
የየካ አባዶ ጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስመልክቶም፤ ነባሯ ቤተክርስቲያን ተራራ ላይ ስለሆነች አቅመ ደካሞችና ሕፃናት መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማሰብ ከወይዘሮ ሮማንና ከአቶ ከፍያለው ላይ 230 ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ ይዞታ በ85 ሺህ ብር ገዝተው ከቤተክርስቲያኒቷ ስር ሆኖ የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጽላት በማስገባት ከነባሯ ጋር እንዲሠራ ተወስኖ የተሠራ ነው:: ሆኖም ግን ሙዳየ ምፅዋቱ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ አባላትና አስተዳደር ሠራተኞች በሌሉበት ተገንጥሎ ገንዘቡ ተዘርፏል:: በተመሳሳይ ሌሎች ንብረቶችም ተዘርፈዋል:: ቤተክርስቲያኑ የተገነጠለውም በሕገ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት አይደለም በማለት ቤተክርስቲያኒቷ አንጡራ ሀብቷን አውጥታ ያቋቋመችው ስለሆነ እንዲመለስላት ሲሉ መጠየቃቸውን ይገልፃል:: ስለሆነም ግንጠላው የሕግ ጥሰት ወንጀልም በመሆኑ ወደነበረበት ተመልሶ በአንድ ሰበካ ጉባዔና አስተዳደር እንዲመራ ቢደረግ ሲልም መወሰኑ በቃለ ጉባዔው ላይ ይገኛል::
ዳግም አቤቱታ
በመዝገብ ቁጥር 10/558/11 በቀን 11/01/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየካ አባዶ ጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የፃፉት ደብዳቤ ከሰነዶቹ መካከል ይገኛል:: በጽሁፉ፤ ያለ ሕግ አግባብ የተገነጠለውን የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንዲመለስ አባታዊ መመሪያ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ያሳያል::
ቤተክርስቲያኒቷ የተመሰረተችው ከፍተኛ ተራራ ላይ በመሆኗና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንደልባቸው ለመሳለምና ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት በመቸገራቸው በምዕመናን ጥያቄ መነሻነት ሕዝበ ክርስቲያኑን በቅርበት ለማገልገልና የላይኛዋን ቤተክርስቲያን በገቢ እንዲያግዝ ታስቦ አንጡራ ሃብቷን አውጥታ ቦታ መግዛቷን ያስነብባል:: የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤትም ከቦታው ድረስ ሄዶ በማጥናትና ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን በማመን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ጽፏል:: ሀገረ ስብከቱም ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት በደብሩ ስር በአንድ አስተዳደር እንዲተዳደር የቅዱስ ገብርኤል ጽላት እንዲፈቀድ በጻፈው መሠረት በሕጋዊ መንገድ ጽላቱን ተረክበው በደብሩ ስር በተዘጋጀው ቦታ አስገብተው በማገልገል ላይ እንደነበሩም ያወሳል::
ስለሆነም የላይኛዋን ቤተክርስቲያን በገቢ የሚያግዝ፣ ለምዕመናኑም በቅርበት ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥና በአንድ ሰበካ ጉባዔ የሚተዳደር ሆኖ የቅዱስ ገብርኤል ጽላት ይፈቀድላቸው በሚል የጻፉት ማሕተም ገና ሳይደርቅ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሳያውቁትና መመሪያ ሳይሰጡበት፣ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሳያውቅና ሳይጠየቅ፣ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ሳይፈልግና ሳይፈቅድ እንዲሁም ቀን ከሌት ለፍተው ገንዘባቸውን አውጥተው ቤተክርስቲያኒቱን ያቋቋሙት የደብሩ መንበረ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ሳይካተቱበትና ፍላጎታቸው ሳይጠየቅ ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም ቀደም ሲል የነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር የቤተክርስቲያኒቱንና የሕዝቡን ችግር ይፈታል ተብሎ በቤተክርስቲያኗ ሥም የተቋቋመውን የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን በመገንጠል በሥራውም ሆነ በቦታው ላይ ላልነበሩ ሰዎች እንደሰጠባቸው ያትታል::
በሀገረ ስብከቱ በተፈጠረው የአሰራር ችግር ምክንያት ለተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የተፈፀመውን በደል ከነማስረጃው በማቅረብ ኮሚቴው አጣርቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረበው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ጉባዔ በደብሩ ላይ ሀገረ ስብከቱ ብልሹ አሰራር እንደፈፀመ ገልፆ፤ እንዲስተካክል ሲል መወሰኑን ያስታውሳል:: ይሁን እንጂ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ባለመፈፀሙ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ጽሕፈት ቤትና ማህበረ ካህናት እንዲሁም የአጥቢያው ምዕመናን በከፍተኛ ችግርና እንግልት ላይ ስለሚገኙ ቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ እንዲሰጡላቸውና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተከብሮ በሀገረ ስብከቱ በኩል የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ወደነበረበት ተመልሶ የአፈፃፀም ደብዳቤ እንዲፃፍላቸው ዳግም መጠየቃቸውን ያሳያል::
በመዝገብ ቁጥር 10/8/2011 ዓ.ም በቀን 20/08/2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአባዶ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ለአንድ አገልጋይ የፃፈው የሥራ ዕግድ ደብዳቤ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈው ውሳኔ ተፈፃሚ ባለመደረጉ ችግሩ እንደቀጠለ የሚያሳይ ነው:: ደብዳቤው፤ ግለሰቡ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በጥብቅ አስተዳዳሪነት እንዲሠሩ የአዲስ አበባ ሀገር ስብከት ጽሕፈት ቤት መድቧቸው እንደነበር ያወሳል::
በደብሩ ሰበካ ጉባዔ ባለመኖሩ የቤተክርስቲያኑን የሒሳብ ደብተር በስማቸው አድርገው በማንቀሳቀስ ያለውሳኔና ያለማዘዣ የደብሩን ገንዘብ እያወጡ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው፣ ሦስት መቶ ቲሸርት ያለውሳኔ በደብሩ ሥም አሳትመው በአውደ ምህረት ሽጠው ከ30 ሺህ ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ በ17/1/2011 ዓ.ም በአምባገነንነት የእህታቸውን ልጅ ሙዳየ ምፅዋት ዋስ ሆነው ሰጥተው በማዘረፍ የሰውየውን አድራሻ እያወቁ ሲጠየቁ አባሪ ተባባሪ ሆነው አላውቅም በማለታቸው፣ለጽላት ማስፈቀጃ ብለው 14 ሺህ ብርና ለደብሩ ድምፅ ማጉያ (ሞንታርቮ) መግዣ በሚል ሰበብ ትኬት አሳትመው ቁጥሩ ያልታወቀ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ ለመስራች አገልጋዮች ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በስብሰባ ላይ ለደብሩ መሬት መግዣ ያዋጡት 240 ሺህ ብር ከእርሳቸው እንዳለ ከገለጹ በኋላ በመካዳቸው ዕግዱ እንደተደረገባቸው ያስቀምጣል::
የተፈፀሙት ችግሮችም ከአንድ አባት ነኝ ባይ የማይጠበቅ፣ የሚያሳፍርና የቃለ አዋዲውን መመሪያ ያልተከተለ በመሆኑ በ19/07/2011 ዓ.ም በአውደ ምህረት የደብሩ ገንዘብ ተዘርፏል ብለው ስለተናገሩ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤትም ሆነ ክፍለ ከተማው አጣርቶ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ይህ ደብዳቤ ከደረሳቸው ቀንና ሰዓት ጀምሮ የባንኩን ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ ከሥራቸው የታገዱ መሆኑን ያስነብባል::
እኛም የተወሰኑ ውሳኔዎች ስለምን ተፈፃሚ አይሆኑም? ለምንስ ተፈፃሚ ያላደረገ አካል ተጠያቂ አይደረግም? በሚል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ሊቀ ጳጳስን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም::
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011
ፍዮሪ ተወልደ