ባና ወይም ዝተትና በርኖስ የመንዝና የመንዞች ጥንታዊና ባህላዊ ልብስ ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን እና ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳደር በአማራ ብሔራዊ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ ለኢንደስትራላይዜሽን ምሳሌ የሆነውን የአርሶ አደሮችን በክላስተር /የኩታ ገጠም/ የተዘራ የስንዴ ሰብልን ለመጎብኘት በወረዳው ተገኝተው ነበር። የአካባቢው ህዝብ ጥንታዊና ባህላዊ ልብስ የሆነውን በርኖስ ሸልሞና አልብሶ ሲያከብራቸው ሳይ በእውነት እላችኋለሁ ተደስቻለሁ፡፡
ይህንኑ አለባበስ የረጅም ጊዜ ጓደኛዬና ወዳጄ የሆነው በመንዝ ላሎ ምድር አካባቢ የተወለደውና በአዲስ አበባ የሚኖረው አቶ ንጉሴ ጉቻለ በማህበራዊ ሚዲያ የለቀቀውን ፎቶግራፍና ሌሎች መረጃዎች አካፍያችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ጥንታዊና ባህላዊ ልብስ እንዴት እንደሚሰራ ከመነሻው መንዞች ለምንና እንዴት? ሊለብሱት እንደ ቻሉ ከጽሁፉ መረጃ ያገኘሁትን፣ ከዕድሜ ታላላቆቼና አባቶቼ ከተሰጠኝ መረጃ በማጠናከር ያልተሸራረፈ መረጃ ልሰጣችሁ ቅድሚያ አደረግሁኝ፡፡
መንዝ የሚባለው አካባቢ የቱ ነው? ለምንስ «ባና» ወይም «ዝተት» እንዲሁም «በርኖስ» መልበስ አስፈለጋቸው? «መንዝ» የሚባለውን አካባቢ ከማሳየቴ በፊት መንዝ ከሚለው ቃል እንነሳ፡፡
«መንዝ» የሚለው ቃል በትርጉም ረገድ የተጻፈ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት ባይቻልም አባቶች እንደሚሉት «መኑ-ዝ» ይሄ ማን ይባላል? በማለት ከሰሜን የመጡ ተጓዦች በግዕዝ ቋንቋ ጥያቄ አቅርበው ከተናገሯቸው ሁለት ቃላት ተወስዶ በጊዜ ብዛት ቃላቱ መንዝ የሚል የአማረኛ ስያሜ ሆኗል ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ «መንዝሃ» ትርጉሙም «ነዛ ነዛ ነዛ ረጨ ውሃ ዘ ፈሰሰ ውሃ ግስ የተነጻጸረ ስለሆነ ከክርስቶስ ደም እንደውሃ ያፈሰሰበት አገር ነው» ከሚል ነው የመጣው ይላሉ። ድርሳነ ዑራኤልን በመጥቀስ የሚገልጹት፡፡
መንዝ የቃሉ ትርጉም ምንም ይሁን ምን አሁን የአካባቢው መጠሪያ ስም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
መንዝ በንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘመን /1813-1847ዓ.ም ከዘጠኝ የሸዋ መንግስታት አሃዶች ማለትም ቡልጋ፣ ይፋት፣ ግድም፣ ተጉለት፣ ግሼ፣ ሞረት፣ ምንጃር፣ ሸዋ ሜዳ፣ መንዝ አንዱ ሆኖ ከጣርማ በር ወደ ሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ያለውን አካባቢ ወይም ከጣርማ በር በስተምዕራብ ባሶና ወረና ወረዳን፣ ሞጃናወደራ ወረዳን፣ ሞረትና ጅሩ ወረዳ (እነዚህ ወረዳዎች ተጉለት በሚባለው ውስጥ የሚካተቱ ናቸው) ወደ ግራ በመተው ወደ ቀኝ በኩል መንዝ ማማ ምድር፣ መንዝ ላሎ ምድር፣ ወደ ቀኝ የሚያካትተውና ከሞፈር ውሃ ወንዝ፣ ዝቅም ሲል አዳባይ ወንዝን እያካለለ በስተቀኝ በኩል ያለው አካባቢ መንዝ ነው፡፡
እንዲሁም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ዠማ ወንዝ፤ ወደ ምስራቅ መንዝ ወደ ምዕራብ ደግሞ መርሃቤቴ ወረዳን እየተዋሰነ፤ በሰሜን ምስራቅ በደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወርኢሉና አልብኮ ወረዳዎች ወደ ግራ እየተዋሰነ ወደ ቀኝ ግሼን ይዞ መንዝ ቀያ ገብርኤል ወረዳን በመያዝ መንዝ ይባላል፡፡ ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ መንዝና ግሼ አውራጃ በመባልም ይጠራ ነበር፡፡ ሲቀጥልም በምስራቅ አቅጣጫ ደግሞ ጓሳን እየተዋሰነ አንፆኪያና ገምዛ፣ ይፍራታና ግድምን፣ ቀወትና ጣርማ በር ወረዳን እየተዋሰነ ወደ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ያለው የመንዝ ጌራ ምድርና የመንዝ ማማ ምድር ወረዳዎች አካባቢዎች መንዝ ነው የሚባሉት፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ፣ የመንዝ ላሎ ወረዳ ፣የመንዝ ቀያና ገብርኤል ወረዳ፣ የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ፣ የግሼ ወረዳ፣ የመሐል ሜዳ ከተማ አስተዳደር የአሉበት አካባቢ መንዝ በሚል የተጠቃለለ መጠሪያ ይጠራሉ፡፡ በዘመነ-ሳህለ ስላሴ ከዘጠኙ የሸዋ መንግስታት አሃዶች አንዱ መንዝ ነበር ብለናል፡፡ አሁንም ከሰሜን ሸዋ ዞን 27 የገጠር ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች 6ቱ የመንዝ ወረዳዎች ይባላሉ፡፡
የእነዚህ አካባቢዎች የመሬት አቀማመጥ በአብዛኛው ሜዳማና ገደላማ ሲሆን የአየር ንብረቱም ሰፊው ደጋ ሲሆን ወይናደጋማ እና ቆላማ አለው፡፡ የአባይና የአዋሽ ተፋሰስ ወንዞችም በውስጡ ይገኛሉ፡፡ በእንስሳት እርባታና በእርሻ ስራም ህዝቡ ይተዳደራል፡፡ በአብዛኛው ደጋማው አካባቢም ከፍተኛ የሆነ ቅዝቃዜ ያለው በመሆኑ ሙቀት የሚሰጡ ልብሶችን መልበስ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ባህል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍቱን መድሀኒቱ በጎች በብዛት የሚረቡበት አካባቢ በመሆኑ የበጎችን ተዋጽኦ ለልብስነት መጠቀም ግድ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ተጉለት በሚባለው በተለይ ባሶና ወራና ወረዳ የበጎችን ደበሎ በመስፋት ደበሎውን እንደ ሀዘን ልብስ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡
መንዞችም የበጎቻቸውን ጸጉር በመቁረጥ ወይም በመሸለት የሚወጣውን ጸጉር በመፍተል «ባና» ወይም «ዝተት» እና በርኖስ በመስፋት ለተለያዩ አገልግሎቶች ማለትም ለብርድ መከላከያ፣ በበዓላት ቦታ፣ በሀዘንና በአደባባይ ቦታ ይለብሱታል፡፡ ወንዶች «ዝተት» ወይም «ባና» እንዲሁም በርኖስ ሲለብሱ ሴቶች ደግሞ ዝተቱን ወይም ባናውን በመሸንሸን ከወገብ በታች እንደ ቀሚስ ይለብሱታል፡፡ ይህም «መላወሻ» ይባላል፡፡
አካባቢው ቀዝቀዝ ስለሚል አብዛኛው ህዝብ ይህን ቅዝቃዜ ለመቋቋም ሲል «ባና» ወይም «ዝተት» የሚባለውን ከበጎች ፀጉር የሚሰራውን ይለብሳል፡፡ በተመሳሳይ ደግሞ በርኖስን የጥንት አባቶች መኳንቶች የክብር ልብስ፣ የሀዘን ልብስ በመሆኑ ታቦት ሲነግስ፣ በሰርግ ላይ እና ለየት ላለ ስነ-ስርዓት ይለበሳል፡፡ እነዚህ የመንዝ ጥንታዊና ባህላዊ ልብሶች እንዴት ይዘጋጃሉ? የሚለውን እንቃኝ።
ባና ወይም ዝተት በመጀመሪያ በጉ ይታጠ ባል፡፡ አንድ ቀን ከዋለ በኋላ በማግስቱ ይሸለ ታል፡፡ ከዚያም ፀጉሩ በግልም ሆነ በቡድን በመሆን በእጅ ይፋታል፡፡ የተፋታውም ፀጉር በደጋን፣ በቅል አንገትና መታፈሪያ ይነደፋል /ይባዘ ታል/፡፡ ደጋንና ቅል አንገት ስንል ምን ማለት እንደሆነ ግራ አንዳይገባዎት የበግ አንጀት ታልቦ ለሁለት ታጥፎ ይከረራል፡፡ ከዚያም ተወጥሮ ከታሰረ በኋላ እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ይህ በሶስት ወይም በሁለት ይደረባል፡፡ ከዚህ በኋላ ጅማት ይባላል፡፡ ይህ ጅማት በቆላፋ እንጨት ላይ ተወጥሮ ደጋን የሚባለውን ስም ያገኛል፡፡
ከቅል ተክል ከጫፍ ያለው እንቡቶ አይነት ቅርፅ ተቀርፍፎ ይወጣና «ቅል አንገት» የሚል ስያሜ ያገኛል፡፡ «መታረሪያ» የምንለው ደግሞ ቀጭንና ጠንካራ ከወይራ ወይም ከቀጨሞ እንጨት ግማሽ ሜትር ርዝመት ያለው ከእስክርቢቶ ትንሽ ወፈር ያለ ሲሆን አገልግሎቱም ጅማቱን እና ደጋኑን በማያያዝ በቅል አንገቱ በሚወጣው ንዝረት አማካኝነት የሚነደፈውን ፀጉር በአግባቡ እንዲበተንና እንዲለሰልስ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የተፋታው ፀጉር ይነደፋል፡፡ የተነደፈው ፀጉር በአመልማሎ መልክ እየተሸመለመለ ወይም እየተጠቀለለ በእንዝርት ይከረራል። ከዚያም ለዚህ በተዘጋጀው ከበድ ያለ እንዝርት አማካኝነት በወፍራሙ ይፈተልና ልቃቂት ይለቀቃል፡፡
በዚህ ሁኔታ ልቃቂቶች ከተጠራቀሙ በኋላ ሁለቱ በአንድ ላይ ይኮባሉ /ይጠቀለላሉ/፡፡ በተዘጋጀው እንዝርት አማካኝነት ወደ ቀኝ ተፈትሎ የነበረውን ወደ ግራ በተቃራኒዉ ይከረራል፡፡ እንደዚህ ከተከረረ በኋላ ልቃቂት ይሆናል የተከረረውም ልቃቂት ይኮባል /ይጠቀለላል/፡፡ በዚህ መንገድ የተደራው ይደራና ለሸማኔ ይሰጣል፡፡ የተዘጋጀው ፈትል በሸማኔ ከተሸመነ በኋላ ሲያልቅ ሽክሽክ የሚባል ስያሜ ያገኛል፡፡ ሸማኔውም ሲሸምን የተለያዩ ቀለማትን እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡ ለአብነት ከጥቁርና ከነጭ የበግ ፀጉር የተሰራው ሽክሽክ ጉሬዝማ ከሆነ አፍሪካ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡
ይህ ሽክሽክ ባለበት ሁኔታም በሶስት ወይም በአራት ፈርጅ በዶሮ ባላ ተሰፍቶ የሚለበስ ሲሆን በተጨማሪም ጥንካሬና ውበት እንዲያገኝ ደግሞ ከተፈጥሮ ጥንጫ በተሰራ ጉድጓድ/መርገጫ/ ውሃ ተሞልቶ ከአንድ ሙሉ ቀን በላይ ጠንካራ ጉልበት ባለው ጎረምሳ ከተረገጠና ከታሸ በኋላ አዳሩን በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲንጠፈጠፍ ይደረጋል። በዚህ ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን በጠፍር አልጋ ላይ ከቁርበት ስር ይነጠፍና ከአንድ ሳምንት በኋላ ወጥቶ ለልብስነት አገልግሎት ይውላል፡፡
ይህ ልብስ አሁን ባለንበት ጊዜም በአገልግሎት ላይ ነው፡፡ ከልብስም አልፎ እየተቆረጠ ለቤት ወለል በተለይ ወለላቸው ጣውላና ሸክላ የሆኑ ቤቶች ለመወልወያነት ያገለግላል፡፡ ይህ ምርት የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከመቋረጡ በፊት ወደ አስመራ እየተጫነ ሰፊ ገበያ ነበረው፡፡ አሁን ደግሞ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በመሻሻሉ የነበረው ገበያ እንደሚሻሻል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በርኖስ የሚሰራው መጀመሪያ ከጥቁር ሪዝ በግ በመጀመሪያ የበቀለው ፀጉር ብቻ ተመርጦ ከላይ እንዳየነው የዝተት ወይም ባና አሰራር ከተጋጀ በኋላ ለበርኖስነት በሚያመች መንገድ ተቆርጦ በባህር አርብና የተለያዩ ቀለማት ባሉት ሀር ይሰፋና ለአንገት ማስገቢያ በሚያመች መልኩ ተሰፍቶ ለአደባባይ፣ ለሀዘንና ለደስታና ሙግት ጊዜ ይለበሳል፡፡ በሀዘን ጊዜ ባህር አርቡ ወደ ላይ ተገልብጦ ሲለበስ በግራ ትክሻ ላይ እንደሻኛ ቆሞ የሚታየው ቅርፅ ወደ ፊት እንዲተኛ ይደረጋል፡፡
በደስታ፣ በአደባባይና በሙግት የአለባበስ ጊዜ ወደ ፊት ተኝቶ የነበረው የበርኖስ ሾጣጣ ክፍል በትክሻ ቅርፅ እንዲቆም ይደረጋል፡፡ ከዚህ ጋር ከነጭ አቡጀዴ እጅ ጠባብ እና ጠባብ ሱሪና ጭራ ጋር አብሮ የሚለበስበት ስርዓት አለው፡፡
ማጠቃለያ እነዚህ የመንዝ ባህላዊ ትሩፋቶች በመሆናቸው እንዳይጠፋ ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡ በግሌ እንደምታዘበው ለሆነ ሁነት ጊዜ ብቻ ሲፈልጉ እንጂ እንደ ቅርስነታቸው ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የማድረግ ትኩረት በእጅጉ ሲያንስ እየታዘብሁ በመሆኔ ነው፡፡ ለጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ጉዳይ ባልመለስበትም አገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች በታሪክ ማስታወሻነት የሸዋ መንዝ ጥንታዊ የባህል ልብስ መሰጠቱ አልፎ አልፎ በቅርስነት ከያዙ ወገኖች የሚገኝ መሆኑን በእግጠኝነት ለመናገር እደፍራለሁ፡፡ ስለዚህ የአባቶቻችንን በጎ ልምድና ባህል የማቆየት አደራ በእኛ ላይ ያለ ያለመሆኑ ሁላችንም ትኩረት ለባህላችንና ባህላዊ ቅርሶቻችን እንስጥ እላለሁ፡፡
በመጨረሻም የእኔን ጊዜ ለሚመለከተኝ ተግባር ብቻ እንዳውል የራሳቸውን ጊዜ በመሰዋት የጽሁፉን ስራ ለአገዙኝ ለወይዘሪት ሙሉነሽ ፀጋዬ እና ወይዘሪት ብርቱካን ታለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!
(ዘሪሁን ተፈራ ከሰሜን ሸዋ ዞን መሃል ሜዳ ከተማ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011