ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን፤ እንደምን ከረማችሁልኝ? ደግ እንግዲህ ሰላምታዬን አሳጥሬ ወደ አብይ ነገሬ ልግባና፤ ኪነ ጥበብ የአንድን ማህበረሰብ ባህል፣ እሴት፣ ታሪክና ሌሎች ዕሴቶች ባማረና በተዋቡ ቃላት በመከሸን ታዳሚ ሳይሰለቸው ሀሳብ የሚጋራበት ዕፁብ ኢ-ቁሳዊ ሀብት ሲሆን በውስጡም አያሌ ዘርፎችን ያቀፈ ነው። ታዲያ ለዛሬ ከአያሌ ከያኒያን መካከል ደራሲያንን፤ ከኪነ-ጥበብም መስኮች ድርሰትና ስነ- ጽሑፍን መዝዤ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ እነሆ ብዕሬን አንስቻለውና አብሮነታችሁ እንዳይለየኝ እያልኩኝ ወደመሰናዶዬ ላዝግም።
በእርግጥ የሀገሩ ኪነ-ጥበብ ጉዳይ የሚገደው ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲወያይ ጠቆም ለማድረግ ካልሆነ በቀር ነገሩ እንኳንስ ቀለም ለቀመሰ ቀርቶ እንደኔ ላለ ጨዋ ኢትዮጵያዊም ድብቅ እንዳይደለ አይጠፋኝም። ምክኒያቱም በየዕለቱ እንደሚምገው አየር ከኪነ-ጥበብ ጋር ተወልዶ ላደገ ኢትዮጵያዊ ስለ ሥነ-ጽሑፍም ሆነ ድርሰት መሰረታዊ ሀሳብ ለማወቅ ቀለም መቁጠር አልያም ኮሌጅ መበጠስን አይጠይቅም። እዚህ ላይ ታዋቂውን ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞን።
ደራሲ የሚለውንም መጠሪያ መዘን ስናየው “ደረሰ” ከሚለው ስርወ-ቃል የተገኘ ሲሆን ስያሜውም በምጡቅ ጥበባዊ ዕይታ በተመራ ኪናዊ ጉዞ ከማህበረሰቡ ውስጠ- ልቦና፣ ከአካባቢ፣ ሀገር አለፍ ሲልም ዓለም አቀፍ ኩነታዊ ዋሻ ደጃፍ ለሚደርስ፤ ደርሶም የቀሰመውን ማርም ይሁን እሬት ያለስስት ለሚያካፍል (ለሚያደርስ) ልባም፣ ቸርና
ደግ ሙያተኛ የተሰጠ ስያሜ ነው። ደራሲ እይታው፣ ቃላት አጠቃቀሙ እንዲሁም ሀሳብ አገላለፁ ከአዘቦታዊነት ወጣ ያለና ምጡቅ ነው። በመሆኑም ኪነ-ጥበብ የዕለት ተዕለት ኑሮ አካል በሆነባት ምድረ ቀደምት በደራሲነት ነጥሮ ለመውጣትም ሆነ ስያሜውን ለማግኘት ልዩ አስተውሎና ምጡቅ አሳቢነት ይጠይቃል። ታዲያ ሲፈጥረውም ነገር አዋቂና መርማሪ መሆኑን በምናውቀው ሀበሻ ፊት ልዩ ነገር ይዘን መቅረብ እንደምንችል እርግጠኛ ሳንሆን ብዕራችንን ለማንሳት ስለምን ደፈርን? በትክክልም ደራሲ ለሆነ ሰውኮ ህዝብ እጅግ የተከበረ ንጉሥ ነው። እጅ መንሻዬ ንጉሡ ዘንድ ቀርቦ ሞገስ ያገኝ ይሆን ብሎ የማይጨነቅ ሰው ታዲያ ደራሲ ቀርቶ ተደራሲ ለመሆንስ ብቁ ነውን?
መልካም ለሰራኮ ኢትዮጵያውያን ሙገሳንም ሆነ ክብርን አይነፍግም። ሌላው ቢቀር ለሙዚቃ ከዋሉ ግጥሞች፣ ከሥነ-ጽሑፍ ስንኞች፣ ከፊልምና ሌላም ኪናዊ ሥራዎች ላይ የልቡን ለመግለፅ ምቹ የሆኑ ቃላት ሲኖሩ እያሞካሸን ከተቀባበልናቸው ቃላት እስቲ ላንሳላችሁ። ይሞታል ወይ፣ ያስተሰርያል፣ ዓለም ዘጠኝ ነው፣ ማን እንደናት ለጊዜው ያስታወስኳቸው ናቸው። እንግዲህ ለኔ ደራሲ ማለት እንዲህ ነው። የልባችን መግለጫ አጥተን እንዳንጨነቅ አዲስ ብሂል አቀብሎ ዘመን የሚሻገር።
ታዲያ ስለምን የቀደምት ገጣሚንና ሙዚቀኞችን ርዕስና ቃላት ብቻ እየመዘዝን የፊልምና የመጽሐፋችን ርዕስ ከማድረግ ተሻግረን ኪናዊ ዕይታና ለዛቸውን የተላበሰ ይዘት ያለው ሥራ መሥራት አቃተን? ለዚሁ እኮ ነው ጀርባው ላይ ዋጋው 200.00 የተደነቀርንበት መጽሐፍ በሳምንቱ መንገድ ላይ ሃያ አምስት! ሃያ አምስት! ሰላሳ! ሰላሳ! ሲባል የምናየው። ለዚሁ እኮ ነው ፊልሞቻችን ለወረት በሲኒማ ቤት ከመታየት አልፈው ለአቅመ ሲዲ ለመሸጥ የማይበቁት።
ስሜታዊ ሰው የነፈሰው ነፋስ ሁሉ ይዞት የሚሄድ ገለባ ነው። የራሱ እውነት፣ የራሱ መንገድ፣ የራሱ ዕይታ የሚባል ነገር የለውም። ደራሲነት ግን ከዚህ በፀዳ መልኩ ከቶ የማይናወጥ መሰረት ያለው ሺዎች ወደግራ ሲሄዱ ትክክለኛው መንገድ ወደቀኝ ከሆነ ወደ ግራ በሚሄደው ሰው ብዛት ሳይሸበር በያዘው እምነት ውስጥ የሚጓዝ የእውነት ምሰሶ ነው። ስለዚህም የሚያዘጋጀው መጽሐፍ በረባዳ መሬት በቀስታ እንደሚጓዝ፣ የማይፈናጠርና የማያበሰብስ ወንዝ፤ ባለሙያ እንደጠመቀው ወይን ቀስ እያለ ሰውነትን እያሞቀ ሄዶ በስተመጨረሻ ከማናውቀው ዓለም ጋር አስተዋውቆን ከደስታና ግርምት ማዕበል እንደሚያስዋኝም የጨዋ ሰው ስካር ነው። ለዚህም ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ አንብቤቸው ለዓመታት ከህሊናዬ ጓዳ ያልወጡት “ሰመመን”፣ “እሳት ወይአበባ”፣ “ኦሮማይ”ና ያጋፋሪ እንዳሻው ታሪክ የዚህ ስሜት ህያው ማስረገጫ ስካሮቼ ናቸው።
በአንፃሩ ዛሬ በየቀኑ እየተፃፉ ይሁን እየተፈበረኩ ግራ በሚገባ መልኩ አብይ ሥልጣን በያዘ ሁለት ወር ውስጥ፣ ህወሓት መግለጫ በሰጠ አንድ ወር ውስጥ፣ የሆነ ነገር በተከሰተ ሳምንታት ውስጥ ታትመው የሚወጡ ጋዜጣ ይሁኑ መጽሐፍ በማይለይ የሳምንታት ስሜት የታጨቁ ጥራዞች ቢያታክቱንም ዝምታን መርጠናል። ወገኖቼ በዕለቱ ተነቦ የሚያልፍ ዘገባ የሚታተመው ጋዜጣና መጽሔት ላይ እንጂ መጽሐፍ ላይ አለመሆኑን ዘንግተናል እንዴ? መጽሐፍኮ እኮ ሲሆን ለልጅ ልጅ የሚወረስ ቅርስ ነው። ይህ የገባው፣ መጽሐፍንና ጸሐፊነትንም የሚያከብር ሰው ደግሞ ወሬው በተሟሟቀ ሰሞን ላፍታ ተነቦ የሚወረወር፣ በሳምንቱ ቢሊሊቆና ቆራልዮ ተራ የሚገንኝ መጽሐፍ አያሳትምም። ሲጀመር መጽሐፍ ሙያዊ ትንተናው፣ የምዕራፍና ሀሳብ ፍሰቱ፣ የቃላቱ ኪናዊ ለዛው፣ አመክኗዊ መስተጋብሩ፣ ፈጠነ ቢባል ለአንድ ዓመት ተብላልቶ፣ ይሻላል በሚባል ሰው ተይቶ፣ በስሎና ጎልብቶ ነው መውጣት ያለበት የሚል እምነት አለኝ። ወገኔ እንጀራምኮ ዕለት በዕለት አቡኩተው ቢጋግሩት አፍለኝነቱ አያስበላም። እናም ደራሲ ተብዬዎች ሆይ ወሬው ሳይቀንስ፣ ገበያው እንደደራ ልጠቀም በሚል መንቶ የሆዳም ሰው እሳቤ ፌስቡክ ላይ ስትፖስቱ ብዙ ላይክ ያገኛችሁበትን የአንድ ሳምንት ስሜትና ግርድፍ ማብራሪያ አጭቃችሁ ያሳተማችሁት መጽሐፍ ተብዬ ነገር በወጉ እንዳልተበጠበጠ በሶ በየገፁ የጓጎለ ሀሳብ ሞልቶት አልዋጥ እያለን ነውና ምድሪቱን በተራ ወረቀት እየሞላችሁ ደህናዎቹን መጽሐፍ ለመግዛት ስንሄድ በፍለጋ እንድንደክም አታድርጉን።እባካችሁ!! እባካችሁ!!። ቸር እንሰንብት
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
በአንዳርጋቸው ምንዳ