ጀሜ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ውስጥ ካሉት ጥቂት ስፍራዎች አንዱ ወደ ሆነው የጃኪ ባህላዊ ማዕከል ለመዝናናት ትሄዳለች፡፡ በባህል ማዕከሉ የሚስቁና በቡድን ሆነው የሚያወሩ ወጣቶች አይታጡበትም፡፡ ለከተማዋ እንግዳ የሆነ ሰውም እንዲዝናና የሚጠቆመውም ወደዚሁ ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን 500 ሺ ያህሉ ሰዎች ከወደብ ዳርቻማው ከተማ የፈለሱበት ምክንያት የውይይት ርዕስ ሆኖ ሲመጣ ሁሉም ሰዎች ፀጥ ማለት ይጀምራሉ፡፡
«ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ ዓይኖቻችንን እንከፍታለን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር ጥቁር መጥፎ መሆኑን እናውቃለን» በማለት ጀሜ ለአልጀዚራ ትገልፃለች፡፡ በአቅራቢያ ያሉ አንዳንድ ወጣት ሴቶች ስለዚህ ጉዳይ በግልፅም ይሁን በድብቅ አያወሩም፡፡ ስለሚያደርጉት ነገርም አሳፋሪነት ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ይናራሉ፡፡ ቆዳን ማስነጣት ልማድ የተደረገ ሲሆን፣ ከግብፅ የተመለሰችው ጀሜን ጨምሮ በባህል ማዕከል ውስጥ የሚያዘወትሩት ሰዎች ያምኑበታል፡፡ ጀሜ «አሁን እኔ አገሬ ውስጥ ስለሆንኩ ማንም ሰው እኔ አስቀያሚ እንደሆንኩ አይመለከተኝም» ትላለች፡፡
በአብዛኛዎቹ የዓለም ክፍሎች ከአፍሪካ እስከ እስያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ወደ ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ቆዳን ማስነጣት የውበት መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ሥራ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ገበያው ዋጋ በየዓመቱ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ደቡብ ሱዳንም ቅርብ ጊዜ የተመሰረተች አገርና ብዛት ያላቸው ጥቁር ህዝቦች የሚኖሩባት ስፍራ በመሆኗ ቆዳን ማስነጣት እንደ ክብር ይታይባታል፡፡ በተጨማሪም ጥቁር መልክ ያላቸውን ሰዎች ማግለል በታሪካቸው ውስጥ ረጅም ጊዜ ተከስቷል፡፡ ደቡብ ሱዳን ለብዙ መቶ ዓመታት ወደ ኋላ በመመለስ የቅኝ ገዥዎች ዘመን፣ አንድ አገር ለመመስረት በብጥብጥ እና መፈናቀል፣ ከሰሜን ሱዳን ነጻ ለመሆን ለአሥርት ዓመታት የዘለቀ ትግል እንዲሁም ነፃ ከሆነች በኋላ የእርስ በርስ ጦርነት አስተናግዳለች ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች
አብዛኞቹ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች የአፍሪካ ተወላጆች ሲሆኑ ብዛት ያላቸው ደግሞ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ሰሜን ሱዳኖች ግን አመጣጣቸው ከአረብ በመሆኑ የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከማግኘቷ በፊት ቆዳቸው ፈካ ያሉትና የአረብ ዝርያ ያላቸው ሰሜን ሱዳኖች ካርቱምን ዋና ከተማ አድርገው አገሪቱን በበላይነት ይመሩ ነበር፡፡ እ.አ.አ በ1987 የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሳድቅ አል-መሀዲ እንዲህ ብለው ነበር «የአገራችን ዋነኛው ገጽታ ኢስላማዊ አረብ ነው:: እናም ይህች ሀገር ማንነቷ ከአረብ ተለይቶ አይታይም፡፡ ህዝቦቿም በታላቅ ክብር በእስልምና ስር የተጠበቁ ናቸው»።
የደቡባዊ አፍሪካ ማንነት ያላቸው ዜጎች በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እና በቆዳ ቀለም ምክንያት መድልዎ ደርሶባቸዋል፡፡ ክልሉ የዝሆን ጥርስና ባሪያዎች ንግድ ለረጅም ጊዜ የቆየ ሲሆን ከባርነት ጋር ያለው ግንኙነትም ከፍተኛ ነበር፡፡ መድልዎ እና የዘር ትችቶች የተለመዱ ሆነዋል፡፡ ዛሬ በሱዳን እና በአጎራባች ሀገሮች እንደ «ሰማያዊ ጥቁር» ወይም «አረንጓዴ ጥቁር» የመሳሰሉ የተለመዱ መከፋፈሎች በሰዎች ጥቁር ቆዳ ላይ ያለውን ልዩነት መገለጫ ተደርጎ እየተቆጠረ ይገኛል፡፡
በደቡብ ሱዳን መንገዶችና ድልድዮች ግንባታ ሚኒስትርና የቆዳ ማስነጣት ተቃዋሚ የሆኑት ሬቤካ ጆሻ ኦክዋይቺ እንደሚሉት፤ ሱዳን አንድ አገር በነበረችበት ወቅት ደቡብ ሱዳኖች እንደ ሁለተኛ ዜጎች ይታዩ ነበር፡፡ «አፍሪካዎች ከባሪያ ዘሮች የመጡና ባርነት ሁልጊዜ ከጥቁር ቀለም ጋር የተያያዘ ነው» የሚለው አስተሳሰብ ትልቅ ሚና መጫወቱን ይናገራሉ፡፡
ሚኒስትሯ ባላት ጥቁር ቀለም ይኮራሉ፡፡ ጆሻ እንደሚሉት «ሱዳን» የሚለው አገላለጽ የሕዝቦችን የቆዳ ቀለም መሰረት ተደርጎ የተሰጠ ስም ነው፡፡ «ሱዳን ወይም ደቡብ ሱዳን የመጣው ሱድ ከሚል ቃል ነው»፡፡ «ሱድ» በአረብኛ «አሽዋድ» ሲሆን የቃሉ ትርጉም ደግሞ ጥቁር ማለት ነው፡፡ «እኛ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳኖች ቢላድ አልሱድ ወይም የጥቁር አገር ተብለን እንጠራለን፡፡ ምክንያቱም የቆዳችን ቀለምና ታሪካችን ስለሆነ ነው» ይላሉ ሚኒስትሯ፡፡
የእርስ በርስ ግጭትና የማንነት ትግል
ሱዳኖች እ.አ.አ ከ1955 እስከ 1972 እና እ.አ.አ ከ1983 እስከ 2005 ድረስ ሁለት የእርስ በርስ ጦርነቶች አስተናግደዋል፡፡ እነዚህም እ.አ.አ በ 2011 ለተደረገው መገንጠል ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ሁለቱም ግጭቶች በደቡብ እና ሰሜኑ መካከል የተደረጉ ነበሩ፡፡ በሁለተኛው የእርስ በርስ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገሮች ሸሽተዋል፡፡ ብዙ የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች እንደ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ኬንያ ወይም ኡጋንዳ ውስጥ የፈካ ቆዳ ካላቸው ሰዎች መካከል ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡
ዴፊሄትኖ የተባለ ፀረ-ጥላቻ ንግግር ድርጅት አስተባባሪ የሆኑት ሱዛን ኪም ኦቶር ያንን ሁኔታ አልፈውበታል፡፡ «ያደግሁት በኬንያ ሲሆን ኬንያኖች ከደቡብ ሱዳናውያን ቆዳቸው ነጣ ያለ በመሆኑ ችግር ፈጥሮብኛል» በማለት ኦቶር ተናግረዋል፡፡ ቆዳን የሚያነጣ ኬሚካሎች ተጠቅመው እንደማ ያውቁና ወደፊትም ለመጠቀም እንደማይሞክሩም ጠቅሰዋል፡፡
ጆሻ በግብፅ እና በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሚኖሩበት ጊዜ በቆዳ ቀለም ምክንያት ችግሮች ደርሶባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ወላጆች ከደቡብ ሱዳን ከሚመጡት ልጆች ተጠንቀቁ ሲሉ ይነግሯቸው እንደነበር ጆሻ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሰዎች በስነልቦና ይሸነፋሉ፤ በዚህም የመኖር አማራጫቸውን ለመፍጠር መንገድ ይጀምራሉ፤ በዚህም የተነሳ ቆዳቸውን በኬሚካል እንደሚያስነጡ ይናገራሉ፡፡
እ.አ.አ በ 2011 ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ የነበረውን የእርስ በርስ ግጭት በመሸሽ ወደ ውጭ አገር የተጓዙ ደቡብ ሱዳናውያን ቀስ በቀስ ወደተረጋጋ ችው አገራቸው ለመመለስ ወስነዋል፡፡ አንዳንዶች የዘር መድልዎ ሰለባ ስለነበሩ ጥሩ ሆነው ለመታየት ቆዳ ማስነጣትን እንደ ባህል ይዘውታል፡፡
ግጭት ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሴቶችና ቆዳቸውን ባስነጡ ሴቶች መካከል
አሁንም ኦቶር «በጥቁር ሰዎች ላይ ጥላቻ እና መድልዎ አለ፡፡ በተለይ ደግሞ የቆዳ ማንጫ የማይጠቀሙት ላይ ይብሳል» ይላሉ፡፡ በተለይም በሠርግ ወቅት ሴቶች የቆዳ ማንጫ እንዲጠቀሙ ማህበራዊ ግፊት ይደረጋል፡፡ አንድ ሙሽሪት ለማግባት ስትቃረብ ቆዳዋ እንዲነጣ ይጠበቃል፡፡ምክንያቱም ነጣ ያለ ቆዳ የውበት ምልክት ስለሆነ ነው፡፡ማንኛውም ሰው ቆዳው ነጣ ያለ ካልሆነ ወይም ማንጫ ኬሚካል የማይጠቀም ከሆነ በአቅራቢያው ያሉ ሰዎች ያገሉታል፡፡ በዚህም የዛ ሰው የቤተሰብ አባላት ቆዳን እንዲያስነጣ ግፊት እንደሚያደርጉ ኦቶር ይናገራሉ፡፡
የሴቶች ፍራቻ ባሎቻቸው የቆዳውን ቀለም ምክንያት በማድረግ እንዳይፈቷቸው ሲሆን፣ ሴቶቹ ግን ካገቡ በኋላ የተፈጥሮ ቀለማቸውን ማስነጣት እንደማይፈልጉ ለባሎቻቸው ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ባሎቻቸው በኬሚካል ቆዳቸውን ያስነጡ ሴቶችን መደረብ አላቆሙም፡፡
ኦቶር «እና አሁን ቆዳቸው ጥቁር የሆኑ ሴቶችና በኬሚካል ቆዳቸውን ያስነጡ ሴቶች መካከል ግጭት ተነስቷል» ይላሉ፡፡ ግን እሳቸው አልተቀላቀሉም፡፡ «በኔ ቀለም ችግር ያለበት ሰው በዙሪያዬ መሆን የለበትም» ይላሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን የአፍሪካውያን ዝርያ ያላቸውና ጥቁሮች መሆናቸውንም ይገልፃሉ፡፡
የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድኖች ለበርካታ አሥርት ዓመታት ባደረጉት የነፃነት ትግል፣ አገራቸውን አዲሲቷ አፍሪካዊት አገር ሆና እንድትመዘገብ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ከሰሜን ሱዳን ያገኙትን የግዛት ነፃነት ከአንድ ዓመት በላይ አላጣጣሙትም፡፡ ከሰሜኑ የሱዳን ክፍል በይደር የቆየው የድንበርና የሀብት ክፍፍል ሌላ ጦርነት ቢቀሰቅስም፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በውስጣቸው የተከሰተውን የእርስ በርስ ግጭት ያህል ቀውስ ያስከተለ አልነበረም፡፡ በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁ ሙት የእርስ በርስ ጦርነቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ወደ አጎራባች አገሮች ተሰዷል፡፡ ኢትዮጵያ ከ700 ሺህ በላይ የሚሆኑትን አስጠልላለች፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8.2011
መርድ ክፍሉ